Monday, September 2, 2019

የኦሮምያ ቤተ ክህነት፡- ለትክክለኛ ጥያቄ የተሳሳተ መልስ


ከሰሞኑ የኦሮምያን ቤተ ክህነት የመቋቋም ነገር ገፋ ብሎ እየመጣ ነው፡፡ ነገሩን ያነሡት አባቶችና ምእመናን መነሻቸው ቅንዐተ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በኦሮምያ አካባቢ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እየተዳከመ መምጣቱ አሳስቧቸው፣ ‹እኛ ልጆቿ እያለንማ እንዲህ አይደረግም› ብለው የተነሡ ቆራጥ ምእመናንና አባቶች ናቸው፡፡ ያነሷቸው ችግሮችም በአካባቢው የሚታዩ ችግሮች ናቸው፡፡ መፍትሔም የግድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በአንድ በኩል የምእመናኑ ተገቢ ጥያቄ አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተገቢውን ጥያቄ ለፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም የሚፈልግ ኃይል አለ፡፡ለዚህ ማሳያዎቹ የሚሰጡ መግለጫዎች ናቸው፡፡
ከሰሞኑ የሚሰጡት መግለጫዎች ሦስት መሠረታዊ ስሕተቶች ይታዩባቸዋል፡፡
1.      የመጀመሪያው በቤተ ክርስቲያን ላይ የተጋረጡትን ፈተናዎች ሁሉ ሰብስበው ለአንድ አካባቢ መስጠታቸው፤
2.     ከዚህ በፊት ለነበሩ ጥረቶች ምንም ዕውቅና ባለመስጠት ችግሩን ይሁነኝ ተብሎ የተተወ ማስመሰላቸው፤
3.     ሦስተኛም ለችግሩ የሰጡት መፍትሔ ችግሩን የማይፈታ መሆኑ ነው፡፡
በኦሮምያ አካባቢ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ተዳክሟል፣ የካህናት እጥረት አለ፤ በኦሮምኛ ቋንቋ የሚቀድስና የሚያስተምር አገልጋይ በበቂ ሁኔታ አይገኝም፤ የአስተዳደር ችግር አለ በሚል የሚነሣው ቅሬታ ትክክለኛ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ችግር በኦሮምያ አካባቢ ብቻ የሚስተዋል አይደለም፡፡ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሠተ ችግር ነው፡፡ የሚለያየው የችግሩ መጠን ብቻ ነው፡፡ በአማራውና በትግራይ ክልልም በገጠሩ የአገልጋዮች እጥረት አለ፡፡ በተለይም ሕዝቡ በሚገባው ቋንቋ የሚያገለግል ካህን እጥረት አለ፡፡ ያ ባሆን ኖሮ የተሻለ አገልጋይ አለ ከሚባልበት አካባቢ ወደነዚህ ቦታዎች ሰባክያን እየተጋበዙ መሄድ ባላስፈለጋቸው ነበር፡፡ እንዲያውም በአዲስ አበባና በዋና ዋና ከተሞች የሚገኙ ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችን ስለሚስቡ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በድንኳን ሰፊ አገልጋዮች ነው የሚገለገሉት (የራሳቸውን መሬት እያረሱ በሚያገለግሉ)፡፡ በአማርኛና በትግርኛ ቋንቋ የሚቀደስባቸው የትግራይና የአማራ ክልል አጥቢያዎች ከ25 በመቶ አይበልጡም፡፡ ቅዳሴያቸው ቋንቋ ግእዝ ነው፡፡ የቤተ ክህነት አስተዳደራዊ ችግርም በእነዚህ አካባቢዎች ቢብስ እንጂ የሚሻል አይደለም፡፡ ለዚህም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የሚያታብቡትን የቅሬታ ፋይሎች መመልከቱ ብቻ በቂ ነው፡፡

Tuesday, June 11, 2019

ስም ከመቃብር በላይ ነው


አዲሷን የብራዚል ዋና ከተማ ትናንት ጎበኘናት፡፡ ገና 59 ዓመቷ ነው፡፡ አሠራሯ ግን የሚያስደንቅ ነው፡፡ ጽድት ያለች ከተማ፡፡ ወደ ታች እንጂ ወደ ላይ ፎቅ መደርደር የማይፈቀድባት፡፡ በዛፎች የተሞላች የጫካ ውስጥ ከተማ፡፡ እንደ ሰላሌ መስክ የተንጣለሉ፣ እንደ ቶራ መስክ የሚያማልሉ፣ እንደ ደንቢያ መስክ የማዕበል ቅርጽ ያላቸው ፓርኮች የሞሉባት ከተማ፡፡ 

ከተማዋን ለመሥራት የታሰበው እኤአ በ1960 ነበር፡፡ ከተማዋን የሠሩት ግን የብራዚል 21ኛው የብራዚል ፕሬዚዳንት ጄ.ኬ.ዲ. ኦሊቬራ(Juscelino Kubitschek de Oliveira)ናቸው፡፡ ሰውዬው የብራዚል የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ አባት እየተባሉ የሚጠሩ ናቸው፡፡ ብራዚል በእርሳቸው ዘመን እጅግ የተረጋጋ የዴሞክራሲ ግንባታ አካሂዳለች፡፡ ዛሬ ሀገሪቱን በሁለት እግሮቿ ያቆሟት ኢንዱስትሪዎችም የእርሳቸው ውጤቶች ናቸው፡፡ ሰውዬው ሠርተው የማይጠግቡ፣ ዐቅደው የማይቀሩ ነበሩ፡፡ 

Monday, March 11, 2019

የምንችለውን ወይስ የሚገባንን?


የሚቻለውን መሥራት የዐቅም ጉዳይ ነው፡፡ የሚገባውን መሥራት ግን የሕግና የሞራል ጉዳይ ነው፡፡ ኃይልን ለመጠቀም የሚያስችል ትምህርት ለሚማሩ ሰዎች በጥብቅ የሚነገራቸው ነገር ቢኖር የተገቢነት ጉዳይ ነው፡፡ ካራቴ፣ ጂዶ፣ ቦክስ፣ ውትድርና፣ ፖሊስነት የተማሩ ሰዎች ኃይልን ለመጠቀም ቅርብ ናቸው፡፡ በእጃቸው ማጠናፈር፣ በእግራቸው መዘረር፣ በጉልበታቸው ማርገፍ፣ በመሣሪያቸው ማንጠፍ፣ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በባረቀባቸው፣ በፈላባቸውና በነደዳቸው ቁጥር ኃይል እንዳይጠቀሙ የተገቢነትን ጉዳይ እንዲያስቡበት ይመከራሉ፤ ይሠለጥናሉ፡፡ ይቻላል ሳይሆን ይገባል ወይ? ብለው እንዲጠይቁ፡፡
አሁን ባለቺው ኢትዮጵያ ‹ይቻላል› እንጂ ‹ይገባል› ተገቢውን ቦታ አላገኘም፡፡ ሁሉም የሚችለውን ለማድረግ ነው የተነሣው፡፡ ‹ይህንን ማድረግኮ ይቻላል፤ እነ እንትናን መቀስቀስኮ ይቻላል፤ እንዲህ አድርገን ልናሳያቸውኮ እንችላለን፤ እንዲህ ብሎ መከራከርኮ ይቻላል፤ እንዲህ አድርጎ ምላሽ መስጠት ይቻላል፤ እንዲህ ሠርቶ መበሻሸቅ ይቻላል› የሚሉ ነገሮችን ነው የምንሰማው፡፡ ባለ ሥልጣኑም፣ ፖለቲከኛውም፣ አክቲቪስቱም፣ ጸሐፊውም፣ ጋዜጠኛውም ምን ማድረግ እንደሚችል እየነገረን ነው፡፡ ሁሉም የጉልበቱን ልክ እያሳየን ነው፡፡ ‹ይህንን ማድረግ ተገቢ ነው?› ብሎ የሚጠይቅ ግን ብዙም የለም፡፡

Friday, March 8, 2019

የዚህን ሕዝብ ትዕግሥት አትፈታተኑት


ማንኛውም ያልተስተካከለ ውሳኔና ተግባር የተስተካከለ ውሳኔና ተግባርን ያስከትላል፡፡ ለእያንዳንዱ ተግባር ተመጣጣኝና ተቃራኒ የሆነ ግብረ መልስ አለውና፡፡ ያልተገባ ውሳኔና ተግባር በፈጸምን ቁጥር የተገባ ውሳኔና ተግባር የያዘ ኃይል በተቃራኒያችን እንዲመጣ መንገድ እናመቻችለታለን፡፡ ይህንን ኃይል ማሸነፍ ግን አይቻልም፡፡ ትክክለኛ ምክንያት ከሌለው ትልቅ ኃይል ይልቅ፣ ትክክለኛ ምክንያት ያለው ትንሽ ኃይል የማሸነፍ ዐቅም አለውና፡፡ ማሸነፍ ከብረትና ከጉልበት ይልቅ ከምክንያትና ከዓላማ ትክክለኛነት ይመነጫል፡፡ በሥልጣኑ ወንበር ላይ ሆነው በስሜት እየተነዱ፣ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ብለው፣ እንደ ጓያ ነቃይ የፊት የፊቱን ብቻ እያዩ፣ የምርቃና መግለጫ የሚያወጡ አካላት ምላሹንም አብረው ሊያስቡበት ይገባል፡፡

Monday, February 25, 2019

‹ድንች ኃይል ይሰጣል›


ድሮ ከልጆች ጋር ስንጫወት ተመትተን ከመጣን ወላጆቻችን ይቆጣሉ፡፡ ‹ለምን ታለቃቅሳለህ› የሚለው የመጀመሪያ ቁጣቸው ነው፡፡ ወይ እዚያው ታግለህ አሸንፈህ መምጣት ነው፤ አለያም ደግሞ መሸነፍህን አምነህ በቀጣይ እንዴት እንደምታሸንፍ ማሰብ ነው፡፡ ማለቃቀስ መፍትሔ አይሆንም፡፡
ሦስተኛ ክፍል እያለሁ ሙሉጌታ የሚባል ልጅ እኛ ክፍል ነበረ(ስሙ ተለውጧል)፡፡ ሙሉጌታ እንደ ጸጋዬ የሚፈራው አልነበረም፡፡ ልጆቹም ተንኮለኞች ናቸው መሳቅ ሲፈልጉ ሙሉጌታና ጸጋዬን ማጋጠም ይወዳሉ፡፡ ጸጋዬ ወፍራም ነው፡፡ ሙሉጌታን ከመሬት ጋር ይሰፋዋል፡፡ ሙሉጌታ ሦስት ጊዜ ይቀጣል፡፡ ጸጋዬ ያደባየዋል፡፡ ልጆቹ ይስቁበታል፡፡ እናቱ ደግሞ ‹እያለቃቀስክ አትምጣ፣ የአንተ እጅስ ሙቅ ይዟል ወይ!› ብለው ይገርፉታል፡፡
አንድ ቀን የሳይንስ አስተማሪያችን ስለ ኃይል ሰጭ ምግቦች አስተማረን፡፡ ድንች ኃይል እንደሚሰጥ ከነ ሥዕሉ አሳየን፡፡ የሙሉጌታ ዓይኖች በሩ፡፡ ልቡ ሞቀ፣ አዲስ ሐሳብ የተገለጠለት መሰለው፡፡ እናቱ የድንች ነጋዴ ናቸው፡፡ ቤቱ የቅዳሜ ገበያ ፊት ለፊት ነበር፡፡
ቤቱ እንደገባ ድስት ሙሉ የድንች ቅቅል በሚጥሚጣ አስቀርቦ ራቱን በላ፡፡ ጠዋትም ቁርሱ እርሱ ነበር፡፡ ከዳንቴል በተሠራው ቦርሳው አንድ አምስት ድንች ይዞ መምጣቱ ትዝ ይለኛል፡፡

Friday, February 15, 2019

ተዋጽዖ


ለብሔር ብሔረሰቦች በዓል የመጡ ሰዎች በጀልባ እንዲንሸራሸሩ ተባለ፡፡ ከየብሔረሰቡ ሰው ወደ ጀልባዋ ገባ፡፡ ጀልባዋም ቀስ እያለች መንሳፈፍ ጀመረች፡፡ ተንሸራሻሪዎቹም ብሔር ብሔረሰቦችን እያመሰገኑ በስማቸው መንሸራሸር ቀጠሉ፡፡ የሽርሽሩ ዳርቻ ደርሰው ሲመለሱ ግን ከባድ ማዕበል ተነሣ፡፡ ጀልባዋም የግልንቢጥ ትደንስ ጀመር፡፡ ግማሹ ይጸልያል፣ ግማሹ ይሳላል፣ ግማሹ ይዘላል፤ ሌላው ጥግ ይፈልጋል..
የጀልባዋ ነጅ ያሰማውን የድረሱልኝ ጩኸት ሰምተው የመጡት የከተማው ሰዎች ሐይቁ ዳር ቆመው ይጨቃጨቃሉ፡፡
‹እንዴት አድገን እንርዳቸው?› አለ አንዱ፡፡
‹ሁሉንም ብሔር በሚያመጣጥን መንገድ ነው መርዳት ያለብን› አለ ሌላው
‹ሞት ደግሞ ምን ተዋጽዖ አለው› አሉ አንድ አዛውንት
‹ኖ ኖ ስናወጣቸው ከአንድ ብሔረሰብ እንዳይበዛ፤ ከሁሉም እኩል እኩል ሰው ነው ማዳን ያለብን›
‹ቆይ ከየብሔረሰቡ ስንት ስንት ሰው ነው የገባው›
‹አናውቅም፤ ብቻ አወጣጣችን ፍታዊ መሆን አለበት›
‹አሁን እኛ ቶሎ ደረስን ተረባርበን ማውጣት እንጂ፣ ከየብሔረሰቡ ሁለት ሁለት ሰው ኑ፤ ልንል ነው? አሁን በነፍስ የተያዘ ሰው መዳኑን እንጂ ብሔረሰቡን ያስብልሃል? ለመሆኑ ሲሰጥሙ ከየብሔረሰቡ ተመጣጥነው ነው የሚሰጥሙት?› አሉ አዛውንቱ ገርሟቸው፡፡

Wednesday, February 6, 2019

ታሪክን ትጥቅ ማስፈታት


ትውስታና ተስፋ ያለው ምድራ ፍጡር ሰው ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ታሪክና ዕቅድ አለው፡፡ የሰው ልጅ ጥንታዊ ጥያቄ የሚባለው ‹ከየት መጣሁ› የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ሰዎች ስለ ትናንት ለማወቅ ጉጉታቸው የጨመረውና ትናንታቸውን መፈልፈል የፈለጉት ይሄንን ጥያቄ ለመመለስ ነበር፡፡ ታሪክ ያለው የሰው ልጅ ብቻ ስለሆነ፡፡

የታሪክ አንዱ ጠባዩ ድርጊቱ የተጠናቀቀ፣ ጣጣው ያላለቀ መሆኑ ነው፡፡ የታሪክ ሂደት ከጊዜ ጋር የተሠናሰለ በመሆኑ ድጊቱ ተከናውኖ ይጠናቀቃል፡፡ የድርጊቱ ተጽዕኖ ግን ሺ ዓመታትን እስከመሻገር ይደርሳል፡፡ ተጽዕኖው እንዳይቋረጥ የሚያደርጉት ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው አዳዲስ መረጃዎችና ማስረጃዎች ስለሚገኙ የነበረውን ትረካ ይቀይሩታል፤ ሁለተኛ ደግሞ ቀድሞ ለተደረገ ድርጊት አዳዲስ ምልከታዎችና ትርጉሞች ይሰጡታል፡፡ ‹ለምን እንዲህ ሆነ? እንዲህ መሆን አልነበረበትም፤ እንዲህ ቢሆን ጥሩ ነበር› የሚሉ አእላፍ ጥያቄዎች ይነሣሉ፡፡

Thursday, January 31, 2019

አሁን የማድረግ አንገብጋቢነት


"The fierce urgency of now” በ1963 በአሜሪካ የሰብአዊ መብቶችን መከበር በተመለከተ ማርቲን ሉተር ኪንግ ያነሣው ሐሳብ ነበር፡፡ ነገሮችን ይዋሉ ይደሩ ሳይሉ አሁን የማደረግ አንገብጋቢነት፡፡ ይቆይ ይሰንብት አንበል፤ የመሥሪያ ቀን ዛሬ ነው፡፡ እኛ የዛሬ እንጂ የነገ አይደለንም፡፡ እኛ ‹ነገ› ስንል የምናስረዝመው የብዙዎችን ስቃይና መከራ ነው፡፡ ዛሬ መሥራት ያለብንን ባለመሥራታችን የሚጎዱት አያሌ ናቸው፡፡ ስለዚህም ‹አሁኑኑ እንሥራ›፡፡ ነገሮችን አሁን የማድረግ አንገብጋቢነት፡፡
‹ምነው ተንቀዠቀዥክ›፣ ‹አትቸኩል ይደርሳል›፣ ‹ምን ያጣድፍሃል›፣ ‹ተረጋጋ ጎበዝ›፣ የሚሉ ምላሾች በየቢሮ እንሰማለን፡፡ ‹እየተመላለስክ ጠይቅ›፣ ‹ከጥቂት ቀናት በኋላ ብቅ በል› እንባላለን፡፡ ዛሬን ለመቅጠሪያ እንጂ ለመሥሪያ የማይጠቀሙ ሰዎች አሉ፡፡ ሥራን ወደ ነገ ማሸሽ ማለት ወርቅን ጥልቀቱን በማታውቀው ጉድጓድ ውስጥ እንደ ማስቀመጥ ነው፡፡

Friday, January 25, 2019

አእምሮን ከተዋጊነት ማፋታት


ሰሞኑን Demilitarizing the Mind የተሰኘ መጽሐፍ እያነበብኩ ነበር፡፡ ሰባት የተለያዩ መጣጥፎች የቀረቡበትና አሌክስ ዲ. ዋል (Alex de Waal) የተባለ አርታዒ ያሰናዳው ነው፡፡ አእምሮን ከተዋጊነት ማፋታት ነው ሐሳቡ፡፡ ብዙ ጊዜ ተዋጊ ኃይሎችን ትጥቅ ስለማስፈታትና ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ የሆነ ቀጣና(DMZ) ስለመመሥረት ሲነገርና ቡድኖች ሲስማሙ እንሰማለን፡፡ በሀገራችንም አዲሱን ለውጥ ተከትሎ አያሌ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ቡድኖች ትጥቅ ፈትተዋል፡፡
አእምሮስ?

Friday, December 7, 2018

ሚዛኑ


አንድ ቅቤ አምራች ገበሬና ዳቦ አምራች ነጋዴ እንደ አጋጣሚ ድግስ ላይ ተገናኝተው ያወራሉ፡፡ በጨዋታቸው በጣም ስለተግባቡ ከዚህ በኋላ አጋጣሚ ፈጥረው ለመገናኘት ይስማማሉ፡፡ ነጋዴው ጠዋት ጠዋት 300 ግራም ዳቦ ሲልክለት ገበሬው ደግሞ ማታ ማታ 300 ግራም ቅቤ ሊልክለት ተስማሙ፡፡

በዚህ መልኩ ብዙ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ነጋዴ የቅቤ መጠን እየቀነሰ መሄዱን አየ፡፡ በመጨረሻም ሚዛን ላይ ሲያስቀምጠው 150 ግራም ሆኖ አገኘው፡፡ በዚህም በጣም አዘነ፤ ተበሳጨም፡፡ ገበሬውንም አስጠራው፡፡ ሌሎች ሰዎች እንዲያዳምጡት አድርጎ ‹ከተስማማነው ውጭ የቅቤውን መጠን ለምን ቀነስከው?› ሲል ጠየቀው፡፡ ገበሬውም ‹እኔ ፈጽሞ አልቀነስኩትም› ሲል በአግራሞት መለሰ፡፡ ነጋዴውም ቅቤውን በሚዛን ለክቶ አሳየው፡፡ 150 ግራም ነው፡፡ ገበሬውም አዘነ፡፡ ‹እኔ ቤት ውስጥ የ300 ግራም መለኪያ የለኝም፡፡ አንተ ጠዋት ዳቦውን ስትልክልኝ በእጅ ሚዛኑ አንደኛው ሰሐን ላይ አደርገዋለሁ፤ ከዚያም ቅቤውን በሌላኛው ሚዛን አስቀምጠዋለሁ፡፡ ልክ ከዳቦው ጋር እኩል ሲመዝኑ በዕቃ አዘጋጅቼ እልክልሃለሁ› አለው፡፡ ወዲያውም ጠዋት የላከለትን ዳቦ አውጥቶ ሚዛኑ ላይ አስቀመጠው፡፡ ዳቦው 150 ግራም ነበር የሚመዝነው፡፡ ነጋዴው አፈረ፡፡

‹የምታገኘው ለሌላው ባደረግከው ልክ ነው፡፡ 150 ሰጥተህ 300 ልታገኝ አትችልም፤ እባብ ሰጥተህ ርግብ፣ ድንጋይ ሰጥተህ ዳቦ፣ እሬት ሰጥተህ ማር ልታገኝ አትችልም፤ አንተ ብቻ ብልጥ ልትሆን አትችልም፤ ማሾውን አጥፍተህ ብርሃን ልታገኝ አትችልም፤ ሌላው ገድለህ አንተ በሰላም ልትኖር አትችልም› አለው ገበሬው፡፡

ማንኛውም ድርጊት ተመሳሳይና ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ አለው፡፡ አንተ እዚህ ለብቻህ ቤትህ ውስጥ ሆነህ ክፉ ስታደርግ ሌላውም በቤቱ ብቻውን ሆኖ ክፉውን ይመልስሃል፡፡ ‹እዛም ቤት እሳት አለ› እንዳሉት ነው አለቃ ገብረ ሐና፡፡ አንተ ጎመድ ይዘህ ከወጣህ ሌላውም አያቅተውም፤ አንተ ገጀራህን ከሳልክ ሌላውም ይስላል፤ አንተ የሌላውን ወገን ስታፈናቅል፣ ያኛውም ያንተን ወገን ያፈናቅላል፡፡ ዛፍ ቆርጠህ ዝናብ፣ በካይ ጋዝ እየለቀቅክ የተስተካከለ የአየር ንብረት አትጠብቅ፡፡ ተፈጥሮም በሰጠሃት መጠን ነው የምትመልስህ፡፡ በዓለም ላይ ሚዛኑ አንድ ነው፤ ተመዛኞቹ ግን ይለያያሉ፡፡ እዚህ ካጎደልክ፣ እዚያም ያጎድሉብሃል፡፡ እዚህኛው ዩኒቨርሲቲ የዚያኛው ልጅ አለ፤ እዚያኛው ዩኒቨርሲቲም የአንተ ልጅ ይገኛል፡፡ እዚህ የአንተ ወገን ብዙኃኑን ይዟል፣ እዚያ ግን አናሳ ነው፡፡ እዚህ አናሳ የሆነው ደግሞ እዚያ ብዙ ይሆናል፡፡ የብዙኃን ወገን በሆንክበት ቦታ አናሳው ካሰቃየህ፣ አናሳ በሆንክበት ቦታ ደግሞ ብዙኃን ያሰቃዩሃል፡፡ እዚህ ባለ ሥልጣን እንደሆንከው እዚያ ተራ ትሆናልህ፡፡ የሚያዋጣው በሚዛኑ ልክ ትክክለኛውን ማድረግ ብቻ ነው፡፡   

Wednesday, November 21, 2018

ኢትዮጵያ - ቦይንግ



ቦይንግ 747-8፣ ለመገጣጠም ብቻ 4 ወር የፈጀ አውሮፕላን ነው፡፡ ስድስት ሚሊዮን የሚገጣጠሙ ክፍሎች አሉት፡፡ በተለያየ የዓለም ክፍሎች ሆነው ከጥቃቅን እስከ ግዙፍ፣ ከመካኒካል እስከ ኤሌክትሪካል የሚያመርቱ ከ30 ሺ በላይ ሠራተኞች ይሳተፉበታል፡፡ ከእነዚህ መካከል የሚተዋወቁት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ የአንዱን መኖር ሌላው አያውቀውም፡፡ በእድሜ፣ በዜግነት፣ በጾታ፣ በእምነት፣ በመልክና በዘር ይለያያሉ፡፡ የሚከፈላቸው ክፍያ ይለያያል፡፡ የሚያመርቱትም የአውሮፕላኑን አንድ ክፍል እንጂ ጠቅላላውን አውሮፕላን አይደለም፡፡
ሁሉንም አንድ የሚያደርጓቸው ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ የሚሠሩት ለአንድ ኩባንያ መሆኑና የሚሠሩበት ዓላማ አንድ መሆኑ፡፡ እነዚህን ሁሉ ስድስት ሚሊዮን ተገጣጣሚ አካላት የሚያመርቱት ባለሞያዎች ቦይንግ ለሚባል ኩባንያ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ንኡስ ኮንትራት ወስደው የሚሠሩት እንኳን ለዚሁ ኩባንያ እንደሚሠሩ ያውቃሉ፡፡ ሁለተኛው ነገር ደግሞ የሁሉም ዓላማ አውሮፕላን መሥራት መሆኑ ነው፡፡ በዓይን ለማየት አስቸጋሪ የሆነቺው ብሎን ከሚሠራ ጀምሮ ትልልቁን አካል እስከሚያመርተው ድረስ ዓላማቸው ብሎን፣ ክንፍ፣ በር፣ ሞተር፣ ጎማ፣ ወንበር፣ መሥራት አይደለም፡፡ አውሮፕላን መሥራት ነው፡፡ ያ በሰማይ ሲበር የሚያዩት አውሮፕላን እንደየዐቅማቸው ተሳትፈው እነርሱ የሠሩት አንድ አውሮፕላን ነው፡፡

Thursday, November 8, 2018

አንድ ነን ብዙዎች፤ አንዶችም ብዙ ነን


የተፈጥሮ ሳይንስ ሊቃውንት ‹ዓለም በብዙ መልኩ የምትገለጥ ዉሑድ ዓለም ናት› ይላሉ፡፡ የተለያዩ የዓለም ከዊኖች ልዩ ልዩ ይምሰሉ እንጂ የአንዱ ዓለም ክፍሎች ናቸው፡፡ ከአንዱ ዓለም ጋር ተዋሕደውም የሚኖሩ ናቸው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ለብቻው ህልው ሆኖ ለመኖር የሚቻለው ማንም የለም፡፡ ሁሉም ፍጡራን ባለማቋረጥ እርስ በርሳቸው የሚገናኙ የተሣሠሩና የሚገነዛዘቡ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በየራሳቸው ከዊናዊ ህልውና ቢኖራቸውም፤ የአንድ ዓለም ክፍሎች ሆነው እንጂ ከዓለም ተገንጥለው ግን ለመኖር አይቻላቸውም፡፡ ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ሕይወት ከሌላቸው፣ ሕይወት የሌላቸው ፍጡራንም ሕይወት ካላቸው ጋር ፈጽመው የተወዳጁ ናቸው፡፡ ዕጽዋትና እንስሳት ያለ አፈር፣ አየርና ውኃ እንደማይኖሩት ማለት ነው፡፡
አንድነት መኖሪያ ብዝኅነት ደግሞ መገለጫ ነው፡፡ አንዱ ዓለም በብዙ ኅብር ይገለጣል፡፡ ጥበብ አንድ ነው መገለጫው ግን ብዙ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለው መስተጋብር አንድ ነው፤ የመስተጋብሩ መገለጫ ግን ልዩ ልዩ ነው፡፡ የባሕልና ቋንቋ ልዩነትም በዚህ ምክንያት የመጣ ነው፡፡ አንዱ የሰው ዘር ከተለያዩ የዓለም ክፍሎችና ሁኔታዎች ጋር በፈጠረው የተለያየ ዓይነት መስተጋብር ምክንያት የተለያዩ ባሕሎችና ቋንቋዎች ፈጠረ፡፡ ብርሃን አንድ ነው መገለጫው ግን ልዩ ልዩ ነው፡፡ ፀሐይም እንበል ጨረቃ፣ ወይም ከዋክብት የአንዱ ብርሃን መገለጫዎች ናቸው፡፡

Monday, November 5, 2018

እንደ ኖኅ ወይም እንደ ዮናስ


ከሚያብዱት ጋር ከማበድ ይልቅ ከአጥሩ ዘለቅ ብለው አይተው ትውልድን የሚያስጠነቅቁ ሰዎች፣ ሁለት ዓይነት ዕጣ ፈንታ አላቸው፡፡ ወይ እንደ ኖኅ አልያም እንደ ዮናስ፡፡
ኖኅ በምድር ላይ ሊመጣ ያለውን የጥፋት ውኃ ዐውቆ ትውልዱን ለ120 ዓመታት ያህል አስጠነቀቀ፡፡ የዚያ ዘመን ሰዎች (ሰብአ ትካት) ግን ‹ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ እንጂ ሌላው ነገር ሁሉ ምን አገባኝ› ብለው ሲላቸው እርስ በርሳቸው መዋጋት፣ ፋታ ሲያገኙም መብላትና መጠጣት ሆነ ሥራቸው፡፡ የአባታቸው የአዳም ትዝታው ሳይጠፋ ከሁለትና ከሦስት አባቶች ተወልደው አንዱ ሌላውን ለማየት ተጠየፈ፡፡ ከፊሎቹ ጦር ሰብቀው ዘገር ነቅንቀው ነጋ ጠባ ውጊያ ሆነ ኑሯቸው፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ የሚሆነውን ሁሉ እንዳላየና እንዳልሰማ አልፈው አሥረሽ ምቺው ሆነ ተግባራቸው፡፡ የሚዋጉትን ላየ በሀገር ጤና ያለው ያለ አይመስልም፤ የሚጨፍሩትን ላየ በሀገር ችግር ያለ አይመስልም ነበር፡፡
ኖኅ በዚህ መካከል ተነሥቶ ሁለቱንም ሲያስጠነቅቅ የሚሰማው አላገኘም፡፡ እየመጣ ያለው መዓት ሊፈስ የተዘጋጀው ቁጣ አስቀድሞ ታይቶት ነበር፡፡ የመንገዳቸው መጨረሻ ገደል፣ የጉዟቸው መዳረሻ እልቂት መሆኑን ተረድቶት ነበር፡፡ ሰሚ ግን አላገኘም፡፡
የሮምን ታሪክ የጻፉ ሊቃውንት ሮም ከመውደቋ ዐሠርት ዓመታት ቀድመው የነበሩ ሮማውያን ሀገራቸው ታላቋ ሮም እየወደቀች መሆኑን ለአፍታም ጠርጥረው አያውቁም ነበር ይላሉ፡፡ የባቢሎን ታላላቆችና ታናናሾች የነቢዩ ዳንኤልን ማስጠንቀቂያ ለመስማትና ከጉዟቸው ገታ ብለው ለማስተዋል ፈቃድ አልነበራቸውም፡፡ ታላቋ ባቢሎን ትወድቃለች ብለው ለአፍታም ጠርጥረው አያውቁም፡፡ ድንገት ግን በ539 (ቅልክ) በአንድ ሌሊት፣ ያውም ባቢሎናውያን ቅልጥ ባለ ድግሥ ላይ እያሉ፤ የፋርሱ ቂሮስ ከተማቸውን በእጁ አስገባት፡፡ የታላቋ ባቢሎንም ክብር በዚያው ሌሊት ተጠናቀቀ፡፡

Friday, October 19, 2018

መተው፤ ነገሬን ላይከተው



ታዋቂው የሥነ ልቡና ምሁር ሮልፍ ዶብሊ ‹አጥርቶ የማሰብ ጥበብ› በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ይላሉ፡፡ እንበልና አንተ የመድኃኒት አስተዳደር ኃላፊ ነህ፡፡ ለረዥም ግዜ ታምሞ የአልጋ ቁራኛ ለሆነ ሰው የሚሰጥን መድኃኒት በተመለከተ እንድትወስን ቀረበልህ፡፡ መድኃኒቱ ከባድ የሆነ የጎንዮሽ ችግር አለው፡፡ ከሚወስዱት መካከል 20 በመቶዎቹ ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ 80 በመቶዎቹን ደግሞ የማዳን ዕድል አለው፡፡ ይህን መድኃኒት ሰውዬው ይውሰድ ወይስ አይውሰድ? የሚለውን ጉዳይ እንድትወስንበት ፊትህ ላይ ቀረበ፡፡
ብዙዎች ይላሉ ሊቁ ከአምስት ሰዎች አንዱን የሚነጥቀውን ይህንን መድኃኒት ሰውዬው ይውሰድ ብለው ለመፈረምን ይፈራሉ፡፡ በሰው ሞት ላይ መፈረም ወይም በሰው ሕይወት ላይ መፍረድ አድርገው ይቆጥሩታልና፡፡ በቶሎ የሚታያቸውም 20 በመቶ ሰዎችን ይጎዳል የሚለው እንጂ 80 መቶ ሰዎችን ይጠቅማል የሚለው አይደለም፡፡ ምናልባትም ከመድኃኒቱ በኋላ ሰውዬው ቢሞት ሚዲያውም ሆነ ሰዎች የሚያወሩት ወሬ የሚገድል መድኃኒት ወስዶ መሞቱን የሚገልጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም ባንተ ውሳኔ መድኃኒቱን የወሰዱ ተከታታይ ሦስት ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ በአንተም፣ በሆስፒታሉም፣ በታካሚዎቹም ሆነ በኅብረተሰቡ ዘንድ ‹ለምን ወሰነ? ለምን አይተወዉም ነበር? ለምን አይቀርበትም?› የሚሉ ጥያቄዎችን ሊያስነሣ ይችላል፡፡ እነዚያ በተከታታይ ሞትን የቀመሱት ወገኖች ከጠቅላላው ውጤት 20 በመቶው ውስጥ መሆናቸውን የሚመለከት አይኖርም፡፡
ይህ ነው ሰዎችን ከዝምታ ይልቅ ተግባርን እንዲፈሩ የሚያደርጋቸው፡፡ ሮልፍ ዶብሊ ይህን ሁኔታ በኛ ብሂል ‹መተው ነገሬን ከተተው›  ወይም በእርሳቸው ቋንቋ ‹the omission bias› ይሉታል፡፡ የማይወስንና የማይሠራ ከሚወስንና ከሚሠራ ሰው ይልቅ የተሻለ ነገር እንዳደረገ የሚቆጠርበት አዝማሚያ ነው፡፡ ከሚመጡ ሚሊዮን መልካም ውጤቶች ይልቅ የሚከሠቱ አንድ ሺ ስሕተቶችንና ጥፋቶችን አጉልቶ በመመልከት ‹ቢቀርስ› የሚል ውሳኔ፡፡ 

Friday, October 12, 2018

መስተጋብር፡- አማራጭ አይደለም ሕልውና ነው


እጅግ ተቀራራቢ የሆነ ዘረመል ያላቸው(የቅርብ አያት ካላቸው) ወገኖች በሚመሠርቱት ግንኙነት ዝርያ የሚፈጠርበት ሂደት ኢንብሪዲንግ(Inbreeding) ይባላል፡፡ በዚህ መልኩ የሚፈጠሩ ዝርያዎች ተፈጥሯዊ ጥንካሬያቸውን ማጣት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ውስብስብ ችግሮችም ይገጥሟቸዋል፡፡ ይህ የተፈጥሮ አቅም ማጣትም ቀስ በቀስ የዝርያውን የመባዛት ዕድል እየቀነሰው ይመጣና ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ቀደምቶቻችን የቅርብ ዘመዳሞች እንዳይጋቡ የከለከሉት ይህ ችግር በሰው ዘር ላይ እንዳይከሠት በማሰብ ነው፡፡ ለዚህ ሁነኛ መፍትሔው ከሚራራቁ ወገኖች ጋር የሚመሠረት ግንኙነት ነው፡፡ 
በማኅበራዊ ግንኙነትም ሰው በዕውቀት፣ በአመለካከት፣ በሐሳብ፣ በመረጃ ምንጭና በአካሄድ ተመሳሳይ ከሆነ ማኅበረሰብ ጋር የሚኖር ከሆነ ውጤታማነቱ እየቀነሰ ይመጣል፡፡ የሐሳብ ኢምብሪዲንግ ይገጥመዋል፡፡ በዕውቀትና በሐሳብ ጠንካራ አይሆንም፡፡ በአመለካከትና በአካሄድ አይሰላም፡፡ አንድ ቋንቋ ብቻ እየሰማ፣ በአንድ መንገድ ብቻ እያሰበ፣ ከአንድ ምንጭ ብቻ እየሰበሰበ፣ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ እያየ ስለሚኖር የእርሱ ሐሳብ ከሌሎቹ ጋር ተወዳድሮ የማሸነፍ ዕድሉ ይጠብባል፡፡ ቀስ በቀስም እየጠፋ ይሄዳል፡፡ 

Tuesday, October 2, 2018

ሸዋ፡- የጥንትና ዛሬ መገናኛ


ዛሬ በተለምዶ ‹ሸዋ› እየተባለ የሚጠራውና ወደ ስድስት በሚጠጉ ዞኖች የተከፋፈለው የመሐል ኢትዮጵያ ክፍልን ታሪክ መረዳት የኢትዮጵያን ሕዝብ የውሕደት ታሪክ ለመረዳት ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ በሰሜን በዓባይ ወንዝና በበሽሎ፣ በመሐል ‹ሸዋ ሜዳ› እየተባለ በሚጠራው ሰፊ ሜዳ፣ በምሥራቅ በአዋሽ ወንዝ፣ በምዕራብ በወንጭት፣ በዠማና በሙገር ወንዞች፣ የተከበበ ነበር፡፡

ሴዋ (ሸዋ) የሚለውን ስም መጀመሪያ ለግዛታቸው የተጠቀሙት በይ(ኢ)ፋት አካባቢ ያለው ጥንታዊውን ግዛት የመሠረቱት ሙስሊም ሡልጣኖች ናቸው፡፡ ከ896/7-1285 በሸዋ ጠንካራ የሆነና እስከ ዘይላ ወደብ ድረስ ግዛቱንና ተጽዕኖውን ያስፋፋ የሙስሊም ሡልጣን ነበር፡፡ ኤንሪኮ ቼሩሊ እኤአ በ1936 በሐረር ከተማ አግኝቶ የቀዳው በ1863 የተጻፈው የዐረብኛ የእጅ ጽሑፍ ስለዚህ ጥንታዊ የሡልጣን ታሪክ የሚነግረን ብቸኛ ምንጫችን ነው፡፡ ይህንን ግዛት የመሠረተው ማሕዙሚ የተባለ ጎሳ ቤተሰብ ነበር፡፡ የዚህን ሡልጣናዊ ግዛት ድንበሮች በርግጠኝነት ለማመልከት አልተቻለም፡፡ እንደ ቼሩሊ ያሉ ባለሞያዎች ግን በደቡብ ከጣርማ በር ተራሮች፣ አንሥቶ እስከ እንጦጦ ተራራ ይደርስ እንደነበር፣ በምዕራብ የሙገር ሸለቆ፣ በምሥራቅም ይፋትና ፈጠጋር ድረስ እንደተዘረጋ ገልጠዋል፡፡ 

Wednesday, September 19, 2018

የድኅረ ወሊድ ጭንቀት

የድኅረ ወሊድ ጭንቀት(postnatal depression) እናቶች ከወለዱ በኋላ የሚያጋጥማቸው፣ ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት ሊዘልቅ የሚችል የጭንቀት ዓይነት ነው፡፡ ልጅ መውለድ የሚያስከትለውን አዲስ ሁኔታ፣ ጠባይ፣ የሰውነትና የስሜት ለውጥ ለማስተናገድ በሚደረገው እናታዊ ትግል ምክንያት በመጀመሪያዎቹ ቀናት የጠባይ ልውጠት(baby blues) ይከሠታል፡፡ ይህ ግን ለሁለትና ለሦስት ቀናት የሚቆይ ነው፡፡ ነገሩ ከእነዚህ ቀናት በላይ ከዘለቀ ወደ ጭንቀት ያድጋል፡፡ እርሱም የድኅረ ወሊድ ጭንቀት(postnatal depression) ይባላል፡፡ በዚህ ዓይነት ጭንቀት ውስጥ የሚገኙ እናቶች ‹ሙዳቸው› ይጠፋል፤ የተሸናፊነት ስሜት ይሰማቸዋል፤ ተስፋ ቢስነት ይነግሥባቸዋል፤ ስለ ተወለደው ሕጻን አብዝተው ይጨነቃሉ፤ አንዳች የሆነ ነገር ልጃቸውን የሚነጥቃቸውና የሚገድልባቸው ወይም የሚያሳምምባቸው ይመስላቸዋል፡፡ ይህ ፈልገው የሚያመጡት ጠባይ ሳይሆን ወሊድ የሚያመጣባቸው ክስተት ነው፡፡

Wednesday, September 12, 2018

‹ግቡ የአጥቂው፣ ድሉ የቡድኑ ነው›


ሰውዬው አንበሳ ሊያድን ጫካ ይገባል፡፡ እየተሽሎከለከ ዛፍ ለዛፍ ሲያነጣጥር፣ የአንበሳውንም ዱካ እያዳመጠ ሲከተል፣ ቆየና አንድ የአንበሳ ደቦል በቀስቱ አነጣጥሮ ጣለ፡፡ ገና ደስታውን ሳያጣጥም የሰውነት ክፍሎቹ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፡፡ እጁ አንበሳውን አነጣጥሮ የጣለው እርሱ መሆኑን በማስረዳት የተለየ ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ ተናገረ፡፡ ይህንን የሰማው እግሩም ‹መጀመሪያውኑ ማን ተሸክሞህ መጥተህ ነው ወጋሁት፣ መታሁት የምትለው› ብሎ ክብሩ የእርሱ መሆኑን ገለጠ፡፡ ነገሩን የታዘበው ዓይንም ‹በምን ዓይተህ ነው ያነጣጠርከው› አለና ክብሩ የእርሱ መሆኑን በኩራት ደሰኮረ፡፡ ጆሮም የአንበሳውን ዱካ እኔ በጽሞና ባልከተል የት ታገኙት ነበር? ሲል ቀዳሚው ባለ ድል እርሱ መሆኑን ደነፋ፡፡ አፍና ሆድም ‹ባልተበላ ምግብ በባዶ ሆድ እንኳን ማደን መታደን አይቻልም› ሲሉ ተከራከሩ፡፡ 

እንዲህ የሰውነት ክፍሎች ሁሉ እየተነሡ ‹ተኳሹ፣ መራዡ፣ አነጣጣሪው፣ እኔ ነኝ› እያሉ ሲከራከሩ ሰውዬው ወደ ግዳዩ ሳይሄድ ዘገየ፡፡ በዚህ መካከል ዓይን ቀና ቢል አንበሳው ሲሞት ያሰማውን ድምጽ የሰሙ ሌሎች አንበሶች ዙሪያቸውን ከበዋቸዋል፡፡ ዓይን በድንጋጤ ሲፈጥ ያስተዋለው እጅም ለሌሎች አካላት መከባባቸውን ጠቆመ፡፡ ይህን የተመለከተው እግር እሮጣለሁ ብሎ ሲያስብ እንኳን መሮጫ መሹለኪያ ቀዳዳ አላገኘም፡፡ ቅድም እኔ ነኝ እኔ ነኝ እሉ ሲፎክሩ የነበሩት ሁሉ ለየብቻ ሮጠው ማምለጥ አልተቻላቸውም፡፡ አንበሶቹ ግን የግዳይ ቀለበታቸውን እያጠበቡ እያጠበቡ ተጠጉ፡፡ ፍጻሜውም መበላት ሆነ፡፡

Thursday, September 6, 2018

የማይሰለቹት አባት፤ ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ


ንግግራቸው ምንጊዜም ፈዋሽ ነው፡፡ የትኛውም ቦታ ላይ ሆነው ቢሰሙት ለራስ የተላከ ደብዳቤ ይመስላል፡፡ ሃይማኖታቸውን ከንግግራቸው ማወቅ ከባድ ነው፡፡በቅርብ ለሚያውቋቸው ወይም ልብሳቸውን ለተመለከተ ካልሆነ በቀር፡፡ የሚናገሩት ሁሉንም እምነት የሚመለከት ነውና፡፡ የሁለቱን ሲኖዶሶች ዕርቅ ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የሚሊኒየም አዳራሽ ጉባኤ ላይ ያስተላለፉትን መልእክት ሊቃነ ጳጳሳቱ ከልባቸው ካዳመጡት ‹ሲታረቁ ከሆድ፣ ሲታጠቡ ከክንድ› የሚያደርግ ነው፡፡  
እሑድ ዕለት የበጎ ሰው ሽልማት ፕሮግራም ላይ ለክቡር አቶ ለማ መገርሳ ሽልማቱን ያበረከቱት እርሳቸው ነበሩ፡፡ ቢሮክራሲ የሚባል ነገር የማያውቃቸው፤ ነገርን በጉዳዩ ልክ ብቻ የሚመዝኑ¶ የተጠሩበትን ጉዳይ እንጂ የጠራቸውን ሰው ማንነት ከቁም ነገር የማይቆጥሩ፣ የአለቃ ሳይሆን የአባት ጠባይ ያላቸው ናቸው፡- ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ፡፡

Monday, September 3, 2018

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (1832 – 1911 ዓ.ም.)

አበባው አያሌው እንደ ጻፈው


እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ታሪክ የጎላ ሥፍራ ካላቸው እጅግ ጥቂት አንስት በግምባር ቀደምትነት የሚጠሩ ናቸው፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት ንጉሥ ምኒልክን (በኋላ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያን) በሕግ ጋብቻ ካገቡ በኋላ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ አስተዳደርና ሥልጣኔ ያበረከቱት አስተዋጽዖ ነው፡፡ ከበርካታ አስተዋጽዖዎቻቸው ጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው፡