Tuesday, June 11, 2019

ስም ከመቃብር በላይ ነው


አዲሷን የብራዚል ዋና ከተማ ትናንት ጎበኘናት፡፡ ገና 59 ዓመቷ ነው፡፡ አሠራሯ ግን የሚያስደንቅ ነው፡፡ ጽድት ያለች ከተማ፡፡ ወደ ታች እንጂ ወደ ላይ ፎቅ መደርደር የማይፈቀድባት፡፡ በዛፎች የተሞላች የጫካ ውስጥ ከተማ፡፡ እንደ ሰላሌ መስክ የተንጣለሉ፣ እንደ ቶራ መስክ የሚያማልሉ፣ እንደ ደንቢያ መስክ የማዕበል ቅርጽ ያላቸው ፓርኮች የሞሉባት ከተማ፡፡ 

ከተማዋን ለመሥራት የታሰበው እኤአ በ1960 ነበር፡፡ ከተማዋን የሠሩት ግን የብራዚል 21ኛው የብራዚል ፕሬዚዳንት ጄ.ኬ.ዲ. ኦሊቬራ(Juscelino Kubitschek de Oliveira)ናቸው፡፡ ሰውዬው የብራዚል የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ አባት እየተባሉ የሚጠሩ ናቸው፡፡ ብራዚል በእርሳቸው ዘመን እጅግ የተረጋጋ የዴሞክራሲ ግንባታ አካሂዳለች፡፡ ዛሬ ሀገሪቱን በሁለት እግሮቿ ያቆሟት ኢንዱስትሪዎችም የእርሳቸው ውጤቶች ናቸው፡፡ ሰውዬው ሠርተው የማይጠግቡ፣ ዐቅደው የማይቀሩ ነበሩ፡፡ እርሳቸው ወደ ሥልጣን ሲመጡ ትኩረት ከሰጧቸው ነገሮች አንዱ አዲሱን የብራዚል ዋና ከተማ መገንባት ነበር፡፡ ከተለያዩ ከተሞችና ክልሎች ጫና ነበረባቸው፡፡ በግልጽ ግንባታውን የተቃወሟቸውም ነበሩ፡፡ እርሳቸው ግን የሚደግፏቸውን ሠላሳ ሺ ብራዚላውያንን ለሥራው አሰለፉ፡፡ በሞያቸውና በዕውቀታቸው የሚደግፏቸውን በአንድ ላይ አቀናጁ፡፡ በአንድ በኩል የሀገሪቱን ዴሞክራሲ፣ በሌላ በኩል የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ አብዮት እያካሄዱ፣ ጎን ለጎን ደግሞ አዲሱን ዋና ከተማ መገንባትን ተያያዙት፡፡ 

ፍራቻቸው ሁለት ነበር፡፡ ሪዮ ዲ ጄኔሮ የብራዚል ታሪካዊት ከተማ ብትሆንም ለሰፊው የብራዚል ሕዝብ ግን ሩቅ ነበረች፡፡ በዚያ ላይ በራሷ ታሪካዊ ሂደት ተጨናንቃለች፡፡ የተገነባችው በፖርቹጋሎች መንገድ በመሆኑ እርሷን እያፈረሱ መገንባት ዘወትር ቀዶ ጥገና ሲያደርጉ እንደመኖር ነው፡፡ ስለዚህም የሀገሪቱን ዋና ከተማ ወደ መካከለኛው የብራዚል ክፍል ማምጣት ያስፈልጋል ተብሎ ከአንድም ሦስት ጊዜ የተወሰነውን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ቆረጡ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ይህችን አዲሲቷን ዋና ከተማ ይሁነኝ ብለው ካልሠሯት በራሳቸው ጊዜ በሚበቅሉ ግንባታዎች ምክንያት መልክና ቅርጽ አጥታ የቀድሞ ከተሞች በሽታ ሊጋባባት ነው፡፡ ዕቅድ ከሥራ በኋላ እየመጣ ብዙ ከተሞችን ገድሏቸዋል፡፡ ጄ.ኬ አንዱ ያሳሰባቸው ይሄ ነው፡፡ ሮቤርቶ በርል ማክስ የተባለ አርክቴክት የከተማዋን መልክዐ ምድር አዘጋጀ፡፡ ከተማዋ የሚበር አውሮፕላን እንድትመስል ነበር የታቀደችው፡፡ ግንባታዋም የተከናወነው በዚያ መንገድ ነው፡፡ የአውሮፕላኑ ዋና ክፍል (የተሣፋሪዎቹ መያዣ) ከተማዋን ለሁለት የከፈለው ዋናው አውራ ጎዳና ነው፡፡ በዚህ ጎዳና ግራና ቀኝ ጎዳናውን ተከትለው፣ በአውሮፕላን ውስጥ በግራና በቀኝ እንደሚቀመጡት ተሳፋሪዎች ግንባታዎች ተካሂደዋል፡፡ ክንፎቿን ግራና ቀኝ ዘርግታቸዋለች፡፡ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉት ግንባታዎች እነዚህን ክንፎች ተከትለው ተሠርተዋል፡፡ 

ብራዚልያ ውስጥ በፈለጉት አካባቢ ዘው ብሎ መገንባት አይቻልም፡፡ ሠፈራዎቹ በብሎክና በይዘት የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ የባንክ ሠፈር፣የሆቴል ሠፈር፣ የኤምባሲዎች ሠፈር፣ የንግድ ሠፈር፣ የመኖሪያ ሠፈር፣ የመዝናኛ ሠፈር፣ እየተባሉ ሁሉም በየሠፈራቸው ከትመዋል፡፡ አንድን ነገር ፍለጋ አሥር ቦታ መዞር የለም፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም በአንድ ሠፈር ብቻ ተሠድረዋል፡፡ የከተማዋ እምብርት የሦስቱ ሥልጣኖች መገናኛ ነው፡፡ ፓርላማው፣ የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤትና ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሦስት ማዕዘን ትይዩ ተገንብተው አንዱ ሌላውን እየተቆጣጠሩ ይታያሉ፡፡ በመካከላቸው ያለው ሠፊ መስክ ‹የሦስቱ ሥልጣናት አደባባይ› እየተባለ ይጠራል፡፡ የብራዚል ሠልፎች ሁሉ እዚያ ነው በዋናነት የሚካሄዱት፡፡

 የከተማዋ ሕንጻዎች ከፓርላማው ሕንጻ በላይ እንዲገነቡ ስለማይፈቀድላቸው ግንባታቸው እንደ ፍልፈል ወደ ታች ነው፡፡ ሰባትና ዐሥር ፎቆችን ከምድር በታች ማግኘት የተለመደ ነው፡፡ ከተማዋ ሦስት ወንዞች ይንፏለሉባታል፡፡ የዚያ ዘመን ቀያሾች ሦስቱ ወንዞች ተገናኝተው ሰው ሰራሽ ሐይቅ እንዲፈጥሩ አግባብተዋቸዋል፡፡ በከተማዋ ጥግ በተራሮች መካከል ከዝዋይ ሐይቅ የማይተናነስ ሐይቅ ተፈጥሯል፡፡ በከተማዋ መካከል በየሕንጻዎቹ ግራና ቀኝ የሚፈስ ውኃ ማየት ብርቅ አይደለም፡፡ 

ፕሬዚዳንት ጄ.ኬ በሥልጣን በሚቆዩባቸው አምስት ዓመታት ውስጥ ከተማዋን ገንብተው ለማጠናቀቅ ወሰኑ፡፡ ነገ የእርሳቸው አይደለም፡፡ ከግራ ከቀኝ የትችት ናዳ ይወርድባቸዋል፡፡ ቴሌቭዥኖችና ሬዲዮዎች፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች በጉዳዩ ላይ የተፈጠሩ ክርክሮችን ያሥስናግዳሉ፡፡ በተለይ ሪዮና ሌሎች ከተሞች አምርረው ጉዳዩን ይነቅፋሉ፡፡ ጄ.ኬ. ግን ይሠራሉ፡፡ 30 ሺ ሰዎችን፣ 200 ማሽኖችን አሠለፉ፡፡ ባለማቋረጥ ሌሊትና ቀን መሥራት ጀመሩ፡፡ እርሳቸው ራሳቸው ነበሩ ሥራውን የሚከታተሉት፡፡ ሉሲዮ ኮስታ የከተማውን የከተሜ ዕቅድ ሠራ፣ ኦስካር ኔይማር የከተማውን የግንባታ ንድፍ አዘጋጀ፣ ሮቤርቶ በርል ማክስ ደግሞ የከተማዋን የመልክዐ ምድር ንድፍ አወጣ፡፡ 

በመጋቢት 1960 እኤአ ከተማዋ በአስደናቂ ፍጥነትና ጥራት ተገንብታ ተጠናቀቀች፡፡ ሰፊውን የብራዚል ምድር በማቀራረብ፣ ተረስቶና ከኢኮኖሚ ዕድገት ርቆ ለነበረው የመካከለኛው የብራዚል ሕዝብ ዕድገትን በማምጣት፣ የብራዚልን የተንጣለለ መሬት በመሠረተ ልማት በማገናኘት ከተማዋ የብራዚል ዓይን ሆነች፡፡ ጥንት በደቡብ ምሥራቅ ከምትገኘው ሪዮ በሰሜን ምሥራቅ ብራዚል ወደምትገኘው ቤለም ለመሄድ የሚቻለው በአትላንቲክ ውቅያኖስ በኩል ብቻ ነበር፡፡ በብራዚሊያ መገንባት የተነሣ መንገዱ ተገናኘና ተቀራረቡ፡፡

ዩኔስኮ በ2017 የዓለም ቅርስ መዝገብ ውስጥ አስገብቷታል፡፡ ‹የዲዛይን ከተማ› ሲል ነበር ዩኔስኮ የገለጣት፡፡ 

‹የምንችለውን በተሰጠን ጊዜ ውስጥ እንሥራ፡፡ ዕድለኞች ከሆንን አሁን የሚያግዘን እናገኛለን፤ ዕድለኞች ካልሆንን ሳይቃወም ስንሠራ ዝም ብሎ የሚያየን እናገኛለን፡፡ ርግጠኛ መሆን ያለብን ግን ይህንን ሥራችንን የሚያደንቅ ትውልድ ወይ ዛሬ ወይ ነገ ማግኘታችን የማይቀር መሆኑን ነው› ይል ነበር ጄ.ኬ.፡፡ የሆነው የተናገረው ነው፡፡ ምንም እንኳን ኢኮኖሚው ቢሻሻልም፤ ፖለቲካው ቢሠለጥንም፣ የሕክምና ድግፉ ለድኻው እንዲደርስ ሆኖ ቢዘረጋም፣ ዝቅተኛው የክፍያ ወለል ቢጨምርም ሌሎች የሀገሪቱ ፈተናዎች ግን አንቀው ያዙት፡፡ በተለይም የዋጋ ግሽበቱ ሊያንቀሳቅሰው አልቻለም፡፡ የሀገሪቱ የብድር ጫና ጨመረ፡፡ ተቃውሞው በረታበት፡፡ በመጨረሻም እኤአ በ1961 በሌላ ፕሬዚዳንት ተተካ፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ ግን ወታደራዊ ጁንታ መጣ፡፡ በጁንታው ዘመን ልዩ ልዩ ክሶች ተመሥርተውበት ለ10 ዓመታት ፖለቲካዊ መብቱ ተገደበ፡፡ በዚህም ምክንያት ከሀገሩ ወጥቶ በአሜሪካና በአውሮፓ ከተሞች ተንከራተተ፡፡


ሕዝቡ የጄ.ኬን ጉዳይ እንደገና ማንሣት የጀመረው በወታደራዊው ጁንታ ዘመን ነው፡፡ ቂጣው ጠፍቶ ሽሉም ገፍቶ የጄኪ ሥራ እንደገና በሕዝቡ ልቡና ውስጥ መታወስ ጀመረ፡፡ ዘመኑ እየከፋ በሄደ ቁጥር ሕዝቡ ወደፊት መጓዝ ትቶ ወደ ኋላ መቃኘት ጀመረ፡፡ ጄ.ኬ. እኤአ በ1967 ወደ ሀገሩ ተመልሶ መጣ፡፡ ለዘጠኝ ዓመታት በሀገሩ ቆይቶ በገጠመው የመኪና አደጋ በ1976 እኤአ ሕይወቱ አለፈች፡፡ ዛሬም ያንን የመኪና አደጋ ‹አደጋ› ብቻ ነው ብለው የማይቀበሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በተደጋጋሚ አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ አደጋው የመኪና ነው ቢልም ሕዝቡ ግን ከነ ሐሜቱ አለ፡፡ በቀብሩ ላይ ከ350ሺ በላይ ሕዝብ ተገኝቶ ነበር፡፡ በብዙዎቹ የብራዚል ከተሞች በስሙ የተሰየሙ አደባባዮች፣ ሆቴሎች፣ ፓርኮችና ትምህርት ቤቶች አይጠፉም፡፡ ከአምስት ዓመታት በኋለ በገነባት ከተማ በብራዚልያ የመታሰቢያ ሙዝየም ተከፈተለት፡፡ አስከሬኑም በዚሁ ሙዝየም ውስጥ ዐረፈ፡፡ ፎቶዎቹ፣ ልብሶቹ፣ ማስታወሻዎቹ፣ ከ3000 በላይ መጻሕፍቱ፣ የቤት ዕቃዎቹ፣ ሽልማቶቹና ስጦታዎቹ ዛሬም ይታያሉ፡፡ ብራዚላውያን በአስከሬኑ ፊት ለፊት ሲያልፉ ጎንበስ ብለው እጅ እየነሡ ‹የዘመናዊቷ ብራዚል አባት› ይሉታል፡፡ ስም ከመቃብር በላይ ነውና፡፡  
ብራዚልያ፣ ብራዚል


No comments:

Post a Comment