Tuesday, June 11, 2019

ስም ከመቃብር በላይ ነው


አዲሷን የብራዚል ዋና ከተማ ትናንት ጎበኘናት፡፡ ገና 59 ዓመቷ ነው፡፡ አሠራሯ ግን የሚያስደንቅ ነው፡፡ ጽድት ያለች ከተማ፡፡ ወደ ታች እንጂ ወደ ላይ ፎቅ መደርደር የማይፈቀድባት፡፡ በዛፎች የተሞላች የጫካ ውስጥ ከተማ፡፡ እንደ ሰላሌ መስክ የተንጣለሉ፣ እንደ ቶራ መስክ የሚያማልሉ፣ እንደ ደንቢያ መስክ የማዕበል ቅርጽ ያላቸው ፓርኮች የሞሉባት ከተማ፡፡ 

ከተማዋን ለመሥራት የታሰበው እኤአ በ1960 ነበር፡፡ ከተማዋን የሠሩት ግን የብራዚል 21ኛው የብራዚል ፕሬዚዳንት ጄ.ኬ.ዲ. ኦሊቬራ(Juscelino Kubitschek de Oliveira)ናቸው፡፡ ሰውዬው የብራዚል የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ አባት እየተባሉ የሚጠሩ ናቸው፡፡ ብራዚል በእርሳቸው ዘመን እጅግ የተረጋጋ የዴሞክራሲ ግንባታ አካሂዳለች፡፡ ዛሬ ሀገሪቱን በሁለት እግሮቿ ያቆሟት ኢንዱስትሪዎችም የእርሳቸው ውጤቶች ናቸው፡፡ ሰውዬው ሠርተው የማይጠግቡ፣ ዐቅደው የማይቀሩ ነበሩ፡፡