የሚቻለውን መሥራት የዐቅም ጉዳይ ነው፡፡ የሚገባውን መሥራት ግን የሕግና የሞራል ጉዳይ
ነው፡፡ ኃይልን ለመጠቀም የሚያስችል ትምህርት ለሚማሩ ሰዎች በጥብቅ የሚነገራቸው ነገር ቢኖር የተገቢነት ጉዳይ ነው፡፡ ካራቴ፣
ጂዶ፣ ቦክስ፣ ውትድርና፣ ፖሊስነት የተማሩ ሰዎች ኃይልን ለመጠቀም ቅርብ ናቸው፡፡ በእጃቸው ማጠናፈር፣ በእግራቸው መዘረር፣ በጉልበታቸው
ማርገፍ፣ በመሣሪያቸው ማንጠፍ፣ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በባረቀባቸው፣ በፈላባቸውና በነደዳቸው ቁጥር ኃይል እንዳይጠቀሙ የተገቢነትን
ጉዳይ እንዲያስቡበት ይመከራሉ፤ ይሠለጥናሉ፡፡ ይቻላል ሳይሆን ይገባል ወይ? ብለው እንዲጠይቁ፡፡
አሁን ባለቺው ኢትዮጵያ ‹ይቻላል› እንጂ ‹ይገባል› ተገቢውን ቦታ አላገኘም፡፡ ሁሉም
የሚችለውን ለማድረግ ነው የተነሣው፡፡ ‹ይህንን ማድረግኮ ይቻላል፤ እነ እንትናን መቀስቀስኮ ይቻላል፤ እንዲህ አድርገን ልናሳያቸውኮ
እንችላለን፤ እንዲህ ብሎ መከራከርኮ ይቻላል፤ እንዲህ አድርጎ ምላሽ መስጠት ይቻላል፤ እንዲህ ሠርቶ መበሻሸቅ ይቻላል› የሚሉ ነገሮችን
ነው የምንሰማው፡፡ ባለ ሥልጣኑም፣ ፖለቲከኛውም፣ አክቲቪስቱም፣ ጸሐፊውም፣ ጋዜጠኛውም ምን ማድረግ እንደሚችል እየነገረን ነው፡፡
ሁሉም የጉልበቱን ልክ እያሳየን ነው፡፡ ‹ይህንን ማድረግ ተገቢ ነው?› ብሎ የሚጠይቅ ግን ብዙም የለም፡፡