Monday, February 25, 2019

‹ድንች ኃይል ይሰጣል›


ድሮ ከልጆች ጋር ስንጫወት ተመትተን ከመጣን ወላጆቻችን ይቆጣሉ፡፡ ‹ለምን ታለቃቅሳለህ› የሚለው የመጀመሪያ ቁጣቸው ነው፡፡ ወይ እዚያው ታግለህ አሸንፈህ መምጣት ነው፤ አለያም ደግሞ መሸነፍህን አምነህ በቀጣይ እንዴት እንደምታሸንፍ ማሰብ ነው፡፡ ማለቃቀስ መፍትሔ አይሆንም፡፡
ሦስተኛ ክፍል እያለሁ ሙሉጌታ የሚባል ልጅ እኛ ክፍል ነበረ(ስሙ ተለውጧል)፡፡ ሙሉጌታ እንደ ጸጋዬ የሚፈራው አልነበረም፡፡ ልጆቹም ተንኮለኞች ናቸው መሳቅ ሲፈልጉ ሙሉጌታና ጸጋዬን ማጋጠም ይወዳሉ፡፡ ጸጋዬ ወፍራም ነው፡፡ ሙሉጌታን ከመሬት ጋር ይሰፋዋል፡፡ ሙሉጌታ ሦስት ጊዜ ይቀጣል፡፡ ጸጋዬ ያደባየዋል፡፡ ልጆቹ ይስቁበታል፡፡ እናቱ ደግሞ ‹እያለቃቀስክ አትምጣ፣ የአንተ እጅስ ሙቅ ይዟል ወይ!› ብለው ይገርፉታል፡፡
አንድ ቀን የሳይንስ አስተማሪያችን ስለ ኃይል ሰጭ ምግቦች አስተማረን፡፡ ድንች ኃይል እንደሚሰጥ ከነ ሥዕሉ አሳየን፡፡ የሙሉጌታ ዓይኖች በሩ፡፡ ልቡ ሞቀ፣ አዲስ ሐሳብ የተገለጠለት መሰለው፡፡ እናቱ የድንች ነጋዴ ናቸው፡፡ ቤቱ የቅዳሜ ገበያ ፊት ለፊት ነበር፡፡
ቤቱ እንደገባ ድስት ሙሉ የድንች ቅቅል በሚጥሚጣ አስቀርቦ ራቱን በላ፡፡ ጠዋትም ቁርሱ እርሱ ነበር፡፡ ከዳንቴል በተሠራው ቦርሳው አንድ አምስት ድንች ይዞ መምጣቱ ትዝ ይለኛል፡፡

Friday, February 15, 2019

ተዋጽዖ


ለብሔር ብሔረሰቦች በዓል የመጡ ሰዎች በጀልባ እንዲንሸራሸሩ ተባለ፡፡ ከየብሔረሰቡ ሰው ወደ ጀልባዋ ገባ፡፡ ጀልባዋም ቀስ እያለች መንሳፈፍ ጀመረች፡፡ ተንሸራሻሪዎቹም ብሔር ብሔረሰቦችን እያመሰገኑ በስማቸው መንሸራሸር ቀጠሉ፡፡ የሽርሽሩ ዳርቻ ደርሰው ሲመለሱ ግን ከባድ ማዕበል ተነሣ፡፡ ጀልባዋም የግልንቢጥ ትደንስ ጀመር፡፡ ግማሹ ይጸልያል፣ ግማሹ ይሳላል፣ ግማሹ ይዘላል፤ ሌላው ጥግ ይፈልጋል..
የጀልባዋ ነጅ ያሰማውን የድረሱልኝ ጩኸት ሰምተው የመጡት የከተማው ሰዎች ሐይቁ ዳር ቆመው ይጨቃጨቃሉ፡፡
‹እንዴት አድገን እንርዳቸው?› አለ አንዱ፡፡
‹ሁሉንም ብሔር በሚያመጣጥን መንገድ ነው መርዳት ያለብን› አለ ሌላው
‹ሞት ደግሞ ምን ተዋጽዖ አለው› አሉ አንድ አዛውንት
‹ኖ ኖ ስናወጣቸው ከአንድ ብሔረሰብ እንዳይበዛ፤ ከሁሉም እኩል እኩል ሰው ነው ማዳን ያለብን›
‹ቆይ ከየብሔረሰቡ ስንት ስንት ሰው ነው የገባው›
‹አናውቅም፤ ብቻ አወጣጣችን ፍታዊ መሆን አለበት›
‹አሁን እኛ ቶሎ ደረስን ተረባርበን ማውጣት እንጂ፣ ከየብሔረሰቡ ሁለት ሁለት ሰው ኑ፤ ልንል ነው? አሁን በነፍስ የተያዘ ሰው መዳኑን እንጂ ብሔረሰቡን ያስብልሃል? ለመሆኑ ሲሰጥሙ ከየብሔረሰቡ ተመጣጥነው ነው የሚሰጥሙት?› አሉ አዛውንቱ ገርሟቸው፡፡

Wednesday, February 6, 2019

ታሪክን ትጥቅ ማስፈታት


ትውስታና ተስፋ ያለው ምድራ ፍጡር ሰው ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ታሪክና ዕቅድ አለው፡፡ የሰው ልጅ ጥንታዊ ጥያቄ የሚባለው ‹ከየት መጣሁ› የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ሰዎች ስለ ትናንት ለማወቅ ጉጉታቸው የጨመረውና ትናንታቸውን መፈልፈል የፈለጉት ይሄንን ጥያቄ ለመመለስ ነበር፡፡ ታሪክ ያለው የሰው ልጅ ብቻ ስለሆነ፡፡

የታሪክ አንዱ ጠባዩ ድርጊቱ የተጠናቀቀ፣ ጣጣው ያላለቀ መሆኑ ነው፡፡ የታሪክ ሂደት ከጊዜ ጋር የተሠናሰለ በመሆኑ ድጊቱ ተከናውኖ ይጠናቀቃል፡፡ የድርጊቱ ተጽዕኖ ግን ሺ ዓመታትን እስከመሻገር ይደርሳል፡፡ ተጽዕኖው እንዳይቋረጥ የሚያደርጉት ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው አዳዲስ መረጃዎችና ማስረጃዎች ስለሚገኙ የነበረውን ትረካ ይቀይሩታል፤ ሁለተኛ ደግሞ ቀድሞ ለተደረገ ድርጊት አዳዲስ ምልከታዎችና ትርጉሞች ይሰጡታል፡፡ ‹ለምን እንዲህ ሆነ? እንዲህ መሆን አልነበረበትም፤ እንዲህ ቢሆን ጥሩ ነበር› የሚሉ አእላፍ ጥያቄዎች ይነሣሉ፡፡