Friday, January 25, 2019

አእምሮን ከተዋጊነት ማፋታት


ሰሞኑን Demilitarizing the Mind የተሰኘ መጽሐፍ እያነበብኩ ነበር፡፡ ሰባት የተለያዩ መጣጥፎች የቀረቡበትና አሌክስ ዲ. ዋል (Alex de Waal) የተባለ አርታዒ ያሰናዳው ነው፡፡ አእምሮን ከተዋጊነት ማፋታት ነው ሐሳቡ፡፡ ብዙ ጊዜ ተዋጊ ኃይሎችን ትጥቅ ስለማስፈታትና ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ የሆነ ቀጣና(DMZ) ስለመመሥረት ሲነገርና ቡድኖች ሲስማሙ እንሰማለን፡፡ በሀገራችንም አዲሱን ለውጥ ተከትሎ አያሌ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ቡድኖች ትጥቅ ፈትተዋል፡፡
አእምሮስ?

የታጠቀ አእምሮ እስካለ ድረስ ያልታጠቁ ቡድኖች መኖር ሀገርን ሰላም አያደርጋትም፡፡ በማናቸውም ጊዜ መሣሪያ ከየትኛውም ቦታ በሕጋዊም ሆነ በሕገ ወጥ መንገድ ለማግኘት ይችላልና፡፡ ከስዊዘርላንዳውያን ብዙዎቹ ወታደራዊ ሥልጠና የወሰዱ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹም የመሣሪያ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ሀገራቸው በዓለም ላይ በግለሰብ መሣሪያ ብዛት ሦስተኛ ናት፡፡ ነገር ግን በመሣሪያ የሚፈጸሙ ጥፋቶች ካለው የመሣሪያ ቁጥር አንጻር ሲታዩ ኢምንት ናቸው ይባላል፡፡ ከስዊዘርላንዳውያን ያነሰ መሣሪያ ያላቸው ሀገሮች በመሣሪያ የታገዘ ጥፋት ይፈጸምባቸዋል፡፡ ጉዳዩን የሚተነትኑ ሰዎች አእምሮን ከመሣሪያ ጋር ከማፋፋት አንጻር ያዩታል፡፡ መሣሪያ ከታጠቀ ሰውነት በላይ መሣሪያ የታጠቀ አእምሮ አደገኛ ነው፡፡
የታጠቀ አእምሮ ነገሮችን ሁሉ በጠብ፣ በግጭት፣ በቁጣ፣ በግንፍልተኝነት፣ በትዕቢት፣ በኃይል፣ በጡንቻና በአስደንጋጭ ቃላት ለመፍታት ይሮጣል፡፡ ለሁሉም ነገር መፍትሔው መደቆስ፣ መደምሰስ፣ ማፍረስ፣ መዘረር፣ መምታት፣ መድፈቅ፣ ማንጠፍ፣ መስሎ ይታየዋል፡፡ ለውይይትና ለክርክር፣ ለምክክርና ለድርድር ቦታ የለውም፡፡ የታጠቀ አእምሮ ምንጊዜም በውስጡ የተሳለ ቢለዋ፣ የሾለ ጩቤ፣ የተቀባበለ ሽጉጥ፣ የጎረሰ ጠመንጃ፣ የተነቀለ ቦምብ፣ የተሞላ ፈንጂ አለ፡፡ ያንን በቃላት መዓት፣ በዓይን ግርፋት፣ በእጅ ማናፋት፣ በፊት ቅላት፣ በአንገት ሥግራት ያወጣዋል፡፡ ማናቸውም ድርጊቶቹ መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ፣ ነጎድጓድ የቀላቀለ ካፊያ ናቸው፡፡
የታጠቀ አእምሮ በውስጡ በቀል ይንተገተጋል፡፡ ምሕረትና ይቅርታ ከታጠቀው መሣሪያ ጋር ስለማይስማሙ ተሰድደዋል፡፡ ይድፋው፣ ይቀንጥሰው፣ ይስበረው፣ ምርቃቶቹ ናቸው፡፡ ዘፈኖቹ ሁሉ አዝማቾቻቸው ውቃው፣ በለው፣ አንክተውና ቅበረው ነው፡፡ ለእርሱ ነገር ሁሉ በሁለት ይከፈላል፡፡ ወዳጅና ጠላት፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ታጣቂ ቡድኖችን ትጥቅ ከማስፈታት እኩልና በላይ የሚያስፈልገን ነገር ቢኖር መሣሪያ የታጠቁ አእምሮዎችን ትጥቅ እንዲፈቱና ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ ማድረግ ነው፡፡ ታጣቂ ቡድኖች ትጥቃቸውን አውርደውና አስረክበው ብዕርና ወረቀት፣ ሐሳብና ርእይ፣ መርሕና ርእዮት እንደሚያነግቡት ሁሉ መሣሪያ የታጠቁ አእምሮዎችም ትጥቅ አውርደው ዕውቀት፣ ሐሳብ፣ ጥበብና ክሂሎት ማንሣት አለባቸው፡፡ ከዐውደ ውጊያ ወደ ዐውደ ክርክርና ወደ ዐውደ ውይይት፣ ወደ ዐውደ ድርድርና ወደ ዐውደ ንግግር መመለስ አለባቸው፡፡
ያን ጊዜ ሀገር ሰላም ትሆናለች፡፡ ትጥቅ የፈታ አእምሮ ሰውነቱ ቢታጠቅ እንኳን ከባሕልና ወግ ያለፈ ነገር አይኖረውም፡፡ ትጥቅ ያልፈታ አእምሮ ግን መሣሪያ ባያገኝ እንኳን ያገኘውን ነገር ሁሉ ወደ ጦር መሣሪያነት መቀየሩ አይቀርም፡፡
የታጠቁ አእምሮዎች ትጥቅ ይፍቱ
8 comments:

 1. Great article, every one need to learn from this article.And it is current issue of our country.

  ReplyDelete
 2. የታጠቁ አእምሮዎች ትጥቅ ይፍቱ

  ReplyDelete
 3. ጥሩ መልእክት ነው፡፡ ግን ውንድማችን በሰላም ነው ጠፋህብን እኮ እነደ በፊቱ ቶሎቶሎ ፃፍልን

  ReplyDelete
 4. cultural revolution, is it easy to bring such a change in a country war and bravery is a culture! Aggression is a norm. humility is an insult

  ReplyDelete
 5. Thanks Dani great read.Negereyeww endeww yaw mekemett neew belowall Pmachin.

  ReplyDelete
 6. እግዚአብሔር ይርዳን እንጂ ለዘመናት የታጠቀ አእምሮ እንዲህ በቀላሉ ይፈታል ብለህ ነው ውዱ? አንተ ግን ምትክ የማላገኝልህ የኢትዮጵያ ኩራት ነህ!!!

  ReplyDelete