Friday, February 15, 2019

ተዋጽዖ


ለብሔር ብሔረሰቦች በዓል የመጡ ሰዎች በጀልባ እንዲንሸራሸሩ ተባለ፡፡ ከየብሔረሰቡ ሰው ወደ ጀልባዋ ገባ፡፡ ጀልባዋም ቀስ እያለች መንሳፈፍ ጀመረች፡፡ ተንሸራሻሪዎቹም ብሔር ብሔረሰቦችን እያመሰገኑ በስማቸው መንሸራሸር ቀጠሉ፡፡ የሽርሽሩ ዳርቻ ደርሰው ሲመለሱ ግን ከባድ ማዕበል ተነሣ፡፡ ጀልባዋም የግልንቢጥ ትደንስ ጀመር፡፡ ግማሹ ይጸልያል፣ ግማሹ ይሳላል፣ ግማሹ ይዘላል፤ ሌላው ጥግ ይፈልጋል..
የጀልባዋ ነጅ ያሰማውን የድረሱልኝ ጩኸት ሰምተው የመጡት የከተማው ሰዎች ሐይቁ ዳር ቆመው ይጨቃጨቃሉ፡፡
‹እንዴት አድገን እንርዳቸው?› አለ አንዱ፡፡
‹ሁሉንም ብሔር በሚያመጣጥን መንገድ ነው መርዳት ያለብን› አለ ሌላው
‹ሞት ደግሞ ምን ተዋጽዖ አለው› አሉ አንድ አዛውንት
‹ኖ ኖ ስናወጣቸው ከአንድ ብሔረሰብ እንዳይበዛ፤ ከሁሉም እኩል እኩል ሰው ነው ማዳን ያለብን›
‹ቆይ ከየብሔረሰቡ ስንት ስንት ሰው ነው የገባው›
‹አናውቅም፤ ብቻ አወጣጣችን ፍታዊ መሆን አለበት›
‹አሁን እኛ ቶሎ ደረስን ተረባርበን ማውጣት እንጂ፣ ከየብሔረሰቡ ሁለት ሁለት ሰው ኑ፤ ልንል ነው? አሁን በነፍስ የተያዘ ሰው መዳኑን እንጂ ብሔረሰቡን ያስብልሃል? ለመሆኑ ሲሰጥሙ ከየብሔረሰቡ ተመጣጥነው ነው የሚሰጥሙት?› አሉ አዛውንቱ ገርሟቸው፡፡

Wednesday, February 6, 2019

ታሪክን ትጥቅ ማስፈታት


ትውስታና ተስፋ ያለው ምድራ ፍጡር ሰው ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ታሪክና ዕቅድ አለው፡፡ የሰው ልጅ ጥንታዊ ጥያቄ የሚባለው ‹ከየት መጣሁ› የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ሰዎች ስለ ትናንት ለማወቅ ጉጉታቸው የጨመረውና ትናንታቸውን መፈልፈል የፈለጉት ይሄንን ጥያቄ ለመመለስ ነበር፡፡ ታሪክ ያለው የሰው ልጅ ብቻ ስለሆነ፡፡

የታሪክ አንዱ ጠባዩ ድርጊቱ የተጠናቀቀ፣ ጣጣው ያላለቀ መሆኑ ነው፡፡ የታሪክ ሂደት ከጊዜ ጋር የተሠናሰለ በመሆኑ ድጊቱ ተከናውኖ ይጠናቀቃል፡፡ የድርጊቱ ተጽዕኖ ግን ሺ ዓመታትን እስከመሻገር ይደርሳል፡፡ ተጽዕኖው እንዳይቋረጥ የሚያደርጉት ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው አዳዲስ መረጃዎችና ማስረጃዎች ስለሚገኙ የነበረውን ትረካ ይቀይሩታል፤ ሁለተኛ ደግሞ ቀድሞ ለተደረገ ድርጊት አዳዲስ ምልከታዎችና ትርጉሞች ይሰጡታል፡፡ ‹ለምን እንዲህ ሆነ? እንዲህ መሆን አልነበረበትም፤ እንዲህ ቢሆን ጥሩ ነበር› የሚሉ አእላፍ ጥያቄዎች ይነሣሉ፡፡

Thursday, January 31, 2019

አሁን የማድረግ አንገብጋቢነት


"The fierce urgency of now” በ1963 በአሜሪካ የሰብአዊ መብቶችን መከበር በተመለከተ ማርቲን ሉተር ኪንግ ያነሣው ሐሳብ ነበር፡፡ ነገሮችን ይዋሉ ይደሩ ሳይሉ አሁን የማደረግ አንገብጋቢነት፡፡ ይቆይ ይሰንብት አንበል፤ የመሥሪያ ቀን ዛሬ ነው፡፡ እኛ የዛሬ እንጂ የነገ አይደለንም፡፡ እኛ ‹ነገ› ስንል የምናስረዝመው የብዙዎችን ስቃይና መከራ ነው፡፡ ዛሬ መሥራት ያለብንን ባለመሥራታችን የሚጎዱት አያሌ ናቸው፡፡ ስለዚህም ‹አሁኑኑ እንሥራ›፡፡ ነገሮችን አሁን የማድረግ አንገብጋቢነት፡፡
‹ምነው ተንቀዠቀዥክ›፣ ‹አትቸኩል ይደርሳል›፣ ‹ምን ያጣድፍሃል›፣ ‹ተረጋጋ ጎበዝ›፣ የሚሉ ምላሾች በየቢሮ እንሰማለን፡፡ ‹እየተመላለስክ ጠይቅ›፣ ‹ከጥቂት ቀናት በኋላ ብቅ በል› እንባላለን፡፡ ዛሬን ለመቅጠሪያ እንጂ ለመሥሪያ የማይጠቀሙ ሰዎች አሉ፡፡ ሥራን ወደ ነገ ማሸሽ ማለት ወርቅን ጥልቀቱን በማታውቀው ጉድጓድ ውስጥ እንደ ማስቀመጥ ነው፡፡

Friday, January 25, 2019

አእምሮን ከተዋጊነት ማፋታት


ሰሞኑን Demilitarizing the Mind የተሰኘ መጽሐፍ እያነበብኩ ነበር፡፡ ሰባት የተለያዩ መጣጥፎች የቀረቡበትና አሌክስ ዲ. ዋል (Alex de Waal) የተባለ አርታዒ ያሰናዳው ነው፡፡ አእምሮን ከተዋጊነት ማፋታት ነው ሐሳቡ፡፡ ብዙ ጊዜ ተዋጊ ኃይሎችን ትጥቅ ስለማስፈታትና ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ የሆነ ቀጣና(DMZ) ስለመመሥረት ሲነገርና ቡድኖች ሲስማሙ እንሰማለን፡፡ በሀገራችንም አዲሱን ለውጥ ተከትሎ አያሌ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ቡድኖች ትጥቅ ፈትተዋል፡፡
አእምሮስ?