Thursday, November 8, 2018

አንድ ነን ብዙዎች፤ አንዶችም ብዙ ነን


የተፈጥሮ ሳይንስ ሊቃውንት ‹ዓለም በብዙ መልኩ የምትገለጥ ዉሑድ ዓለም ናት› ይላሉ፡፡ የተለያዩ የዓለም ከዊኖች ልዩ ልዩ ይምሰሉ እንጂ የአንዱ ዓለም ክፍሎች ናቸው፡፡ ከአንዱ ዓለም ጋር ተዋሕደውም የሚኖሩ ናቸው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ለብቻው ህልው ሆኖ ለመኖር የሚቻለው ማንም የለም፡፡ ሁሉም ፍጡራን ባለማቋረጥ እርስ በርሳቸው የሚገናኙ የተሣሠሩና የሚገነዛዘቡ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በየራሳቸው ከዊናዊ ህልውና ቢኖራቸውም፤ የአንድ ዓለም ክፍሎች ሆነው እንጂ ከዓለም ተገንጥለው ግን ለመኖር አይቻላቸውም፡፡ ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ሕይወት ከሌላቸው፣ ሕይወት የሌላቸው ፍጡራንም ሕይወት ካላቸው ጋር ፈጽመው የተወዳጁ ናቸው፡፡ ዕጽዋትና እንስሳት ያለ አፈር፣ አየርና ውኃ እንደማይኖሩት ማለት ነው፡፡
አንድነት መኖሪያ ብዝኅነት ደግሞ መገለጫ ነው፡፡ አንዱ ዓለም በብዙ ኅብር ይገለጣል፡፡ ጥበብ አንድ ነው መገለጫው ግን ብዙ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለው መስተጋብር አንድ ነው፤ የመስተጋብሩ መገለጫ ግን ልዩ ልዩ ነው፡፡ የባሕልና ቋንቋ ልዩነትም በዚህ ምክንያት የመጣ ነው፡፡ አንዱ የሰው ዘር ከተለያዩ የዓለም ክፍሎችና ሁኔታዎች ጋር በፈጠረው የተለያየ ዓይነት መስተጋብር ምክንያት የተለያዩ ባሕሎችና ቋንቋዎች ፈጠረ፡፡ ብርሃን አንድ ነው መገለጫው ግን ልዩ ልዩ ነው፡፡ ፀሐይም እንበል ጨረቃ፣ ወይም ከዋክብት የአንዱ ብርሃን መገለጫዎች ናቸው፡፡


ሁላችንም ተደጋፊዎች ነን፤ ደጋፊዎች ነን፤ ተደጋጋፊዎችም ነን፡፡ ልጅ ሆነን ምንም ስለማናውቅ በሌሎች ላይ እንደገፋለን (dependent)፡፡ ከፍ ስንል ራሳችንን ችለናል ብለን ስለምናስብ በራሳችን ቆመን ሌሎችን ለመደገፍ (Independent) እንታገላለን፡፡ በጉልምስና እድሜ ስንበስል ደግሞ የተሻለውን የኑሮ መንገድ ተረድተን ከሌሎች ጋር እንደጋገፋለን(Interdependent)፡፡ በፍጡራን የሕይወት ጉዞ በሌሎች ብቻ የሚደገፍም ሆነ እርሱ ብቻውን ሌሎችን የሚደግፍ የለም፡፡ ሁላችንም ተደጋጋፊዎች ነን፡፡ አንዱ ሌላውን እልፈልግህም ብሎ የሚያስቀረው አይደለም፡፡ ይሄው ሰሞኑን በዓለም ላይ የትንንሽ ነፍሳት እየጠፉ መምጣት የዓለማችንን የሕይወት ዑደት እያዛባው መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
ብዙኅነት የአንድነት መገለጫዎች መሆናቸውን፤ አንድነትም የውጥንቅጥ ፍጡራን የህልውና ጉዞ መሆኑን አለማወቅ እውትን አለማወቅ ነው፡፡ አንድነትና ብዙኅነት ለምርጫ የሚቀርቡ ነገሮች አይደሉም፡፡ አብረው የሚጓዙ የዓለም ህላዌ መገለጫዎች ናቸው እንጂ፡፡ ጣቶችን ትተን ስለ እጅ፣ እጅንም ትተን ስለ ጣቶች ልናወራ አንችልም፡፡ ቅንጣቶች ሳይኖሩ እህል ህልው አይሆንምና፡፡ እህልነት ሳይኖር ቅንጣቶችም ትርጉም አልባ ናቸው፡፡ ዳቦ የቅንጣት ስንዴዎች መገለጫ ነው፡፡ ቅንጣት ስንዴዎችም የዳቦ ህልውና ምንጮች ናቸው፡፡
አንድ ሊቅ እንዲህ ይላል፡- ከአንድ ውቅያኖስ ፊት ቆመህ ውቅያኖሱን ስትመለከት በመቶዎች ብሎም በሺዎች የሚቆጠሩ ማዕበሎች ሲያናውጹት ትመለከታለህ፡፡ እያንዳንዱ ማዕበል የራሱ ጠባይና ህልውና አለው፡፡ በተመሳሳይ የሚነሡ ማዕበሎችም የጋራ ጠባይ አላቸው፡፡ ሁሉን የተሸከመው ውቅያኖስ ደግሞ ከዓለም የውኃ አካል ጋር የተሣሠረ ህልውና አለው፡፡ አንድ ውቅያኖስ ላይ ብዙ ማዕበሎች፣ በአንድ የዓለም የውኃ አካል ላይ ብዙ ውቅያኖሶች፡፡ አንድና ብዙ የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ ሁሉም ነገር አንድና ብዙ ነው፡፡
ኅብር ያስፈልገናል፡፡ እያንዳንዳችን የየራሳችን መገለጫ ማንነትና ፍላጎት አለንና፡፡ ቅንጣቶችን ማክበር መውደድና ማድነቅ አለብን፡፡ ሁሉም የየራሱ የተለየ ውበት፣ ጣዕም፣ አስተዋጽዖ አለው፡፡ የዓለም ውበቷ ቅንጣቶቿ ናቸው፡፡ ወደ ጠፈር ስናይ፣ ሰማዩን ሁሉ የሚሸፍን አንድ ወጥ ኮከብ ብናይ ኖሮ ምንኛ ባስጠላን ነበር? ከዋክብቱ ግን ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን በአንድ ሥርዓት ይጓዛሉ፡፡ ግን ደግሞ እነዚህ ሁሉ ኅቡራን ብቻቸውን ሊቀጥሉ አይችሉም፡፡ የተዛመደ፣ የተጋመደና የተዋሐደ አንድነትም አላቸው፡፡ ይገናኛሉ፣ ይዋረሳሉ፣ ይረዳዳሉ፣ ይተባበራሉ፣ አንዱ ለሌላው ያስፈልጋሉ፣ አንዱ በሌላውና ለሌላው ይኖራሉ፡፡ አንዱ እርሱ ብዙ ነው፡፡ እርሱ አንዱም ሊገለጥ የሚችለው በብዙ ኅብርና መልክ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ከብዙዎች የተነጠለ ህልውና የለውም (The One is the many. The one is manifested only in and through the Many. It has no separate existence apart from the Many.)
እንደዚሁም ሁሉ ብዙ መስለው የሚታዩት ቅንጣቶች እነርሱ አንድ ናቸው፡፡ መለያየታቸው ጊዜያዊ ነው፡፡ የቅንጣቱ ህልውና ሲያከትም ተመልሰው ከትልቁ አንድነት ውስጥ ይጠቃለላሉ፡፡ ስንሞት ሁላችንም አፈር እንደምንሆነው፡፡ ልዩ ልዩዎች ከሌሎች ጋር የተሣሠሩና የተዋሐዱ ናቸው፡፡ ሁላችንም ብቻችንን ሳንሆን የትልቁ አንድነት ክፍሎች ነን፡፡ ብቻችንን እየጸጓዝን ይመስናል እንጂ አብረውን የሚጓዙ ሚሊዮኖች አሉ፡፡
ሁለቱን የማይነጣጠሉትን፣ አንድነትንና ልዩ ልዩነትን ወደ ግራና ቀኝ እንነጣጥላለንና ለየብቻቸው እናቆማቸዋለን ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይሳካ አድክም ሥራ መሥራት ነው፡፡ የሚሻለው መኖራቸውን ዐውቆ ለየህልውናቸው መተዉ ነው፡፡ እኔ ብቻ ነው ያለሁት ወይም እኔ ብቻዬን መኖር እችላለሁ ማለትም ውሸት ነው፡፡ አንተ መኖር አትችልም ማለትም ክህደት ነው፡፡ ሌላውን መከባከብ መጠበቅና መፈለግ ያለብን ለእርሱ ብለን ሳይሆን ለራሳችን ስንል ነው፡፡ እርሱ ለእኛ የግድ ያስፈልጋልና፡፡ እንኳንስ ሌላውን የሰው ዘር፣ ዕጽዋትና እንስሳትን፣ ነፍሳትና ተሐዋስያንን ሳይቀር መጠበቅና መከባከብ አለብን፡፡ የዓለም ህልውና የተመሠረተው አብሮ በመኖር ነው፡፡ ሁላችንም ተደጋፊዎች ወይም ደጋፊዎች ብቻ አይደለንም ተደጋጋፊዎች ነን፡፡ ሰው ዓለምን ፈተናት የሚባለው እኔ ብቻዬን ካልኖርኩ ብሎ ተዋሕዶ የሚኖርባትን ዓለም በየምክንያቱ እያጠፋ መምጣቱ ነው፡፡ የአካባቢ ጉዳይ አንገብጋቢ አጀንዳው እስከመሆን የደረሰውም ስንቱን ለህልውናው አስፈላጊ ነገር ዐውቆም ሆነ ሳያውቅ በሥልጣኔ ጉዞው ውስጥ እያጠፋው በመምጣቱ ነው፡፡ የሥነ ምኅዳር(ecology)ና ሥርዓተ ምኅዳር (ecosystem) ጉዳይ ማለትም ቅንጣቶች በውሕደት የሚኖሩበትን ዓለም መስተጋብሩንና መስተሣሥሩን ማስጠበቅ ማለት ነው፡፡    
  

8 comments:

 1. "He who has ears, Let them hear" Matthew 11:15
  God bless you, Daniel

  ReplyDelete
 2. እጅግ በጣም ጥሩ እይታ ነው፡፡ ነገር ግን የእኛ የሰዎች አዕምሮ እንደገና መሰራት አለበት፡፡ ማስተዋል ጎሎናል፡፡ በይበልጥ ደግሞ የተማረ የምንባለው ብሶብናል፡፡ ስለዚህ እባካችሁ ሰው ለመሆን እንሰራ ሰውንም እንስራ፡፡

  ReplyDelete
 3. ኅብር ያስፈልገናል፡፡ እያንዳንዳችን የየራሳችን መገለጫ ማንነትና ፍላጎት አለንና፡፡ ቅንጣቶችን ማክበር መውደድና ማድነቅ አለብን፡፡ ሁሉም የየራሱ የተለየ ውበት፣ ጣዕም፣ አስተዋጽዖ አለው፡፡ የዓለም ውበቷ ቅንጣቶቿ ናቸው፡፡ ወደ ጠፈር ስናይ፣ ሰማዩን ሁሉ የሚሸፍን አንድ ወጥ ኮከብ ብናይ ኖሮ ምንኛ ባስጠላን ነበር? ከዋክብቱ ግን ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን በአንድ ሥርዓት ይጓዛሉ፡፡ ግን ደግሞ እነዚህ ሁሉ ኅቡራን ብቻቸውን ሊቀጥሉ አይችሉም፡፡ የተዛመደ፣ የተጋመደና የተዋሐደ አንድነትም አላቸው፡፡ ይገናኛሉ፣ ይዋረሳሉ፣ ይረዳዳሉ፣ ይተባበራሉ፣ አንዱ ለሌላው ያስፈልጋሉ፣ አንዱ በሌላውና ለሌላው ይኖራሉ፡፡ አንዱ እርሱ ብዙ ነው፡፡ እርሱ አንዱም ሊገለጥ የሚችለው በብዙ ኅብርና መልክ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ከብዙዎች የተነጠለ ህልውና የለውም.

  ReplyDelete
 4. ዳቦ የቅንጣት
  ስንዴዎች መገለጫ ነው፡፡ ቅንጣት ስንዴዎችም የዳቦ
  ህልውና ምንጮች ናቸው፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፡፡

   Delete
 5. it is a good point of view......kibir yigebahal dani....long live for you.

  ReplyDelete