Wednesday, November 21, 2018

ኢትዮጵያ - ቦይንግቦይንግ 747-8፣ ለመገጣጠም ብቻ 4 ወር የፈጀ አውሮፕላን ነው፡፡ ስድስት ሚሊዮን የሚገጣጠሙ ክፍሎች አሉት፡፡ በተለያየ የዓለም ክፍሎች ሆነው ከጥቃቅን እስከ ግዙፍ፣ ከመካኒካል እስከ ኤሌክትሪካል የሚያመርቱ ከ30 ሺ በላይ ሠራተኞች ይሳተፉበታል፡፡ ከእነዚህ መካከል የሚተዋወቁት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ የአንዱን መኖር ሌላው አያውቀውም፡፡ በእድሜ፣ በዜግነት፣ በጾታ፣ በእምነት፣ በመልክና በዘር ይለያያሉ፡፡ የሚከፈላቸው ክፍያ ይለያያል፡፡ የሚያመርቱትም የአውሮፕላኑን አንድ ክፍል እንጂ ጠቅላላውን አውሮፕላን አይደለም፡፡
ሁሉንም አንድ የሚያደርጓቸው ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ የሚሠሩት ለአንድ ኩባንያ መሆኑና የሚሠሩበት ዓላማ አንድ መሆኑ፡፡ እነዚህን ሁሉ ስድስት ሚሊዮን ተገጣጣሚ አካላት የሚያመርቱት ባለሞያዎች ቦይንግ ለሚባል ኩባንያ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ንኡስ ኮንትራት ወስደው የሚሠሩት እንኳን ለዚሁ ኩባንያ እንደሚሠሩ ያውቃሉ፡፡ ሁለተኛው ነገር ደግሞ የሁሉም ዓላማ አውሮፕላን መሥራት መሆኑ ነው፡፡ በዓይን ለማየት አስቸጋሪ የሆነቺው ብሎን ከሚሠራ ጀምሮ ትልልቁን አካል እስከሚያመርተው ድረስ ዓላማቸው ብሎን፣ ክንፍ፣ በር፣ ሞተር፣ ጎማ፣ ወንበር፣ መሥራት አይደለም፡፡ አውሮፕላን መሥራት ነው፡፡ ያ በሰማይ ሲበር የሚያዩት አውሮፕላን እንደየዐቅማቸው ተሳትፈው እነርሱ የሠሩት አንድ አውሮፕላን ነው፡፡


ምናልባትም የመጨረሻውን ቅርጽ ሲይዝ ብዙዎቹ ላይገኙ ይችላሉ፡፡ ይህ የሚፈጸመው ሲያትል ፓይነ በተባለው ሜዳ በሚገኘው የቦይንግ ኤቨረት ፋብሪካ ነው፡፡ 13.4 ሚሊዮን ኪውቢክ ሜትር የሚጠጋው ይህ መገጣጠሚያ በፕላኔታችን ላይ ለአውሮፕላን ከተሠሩ መገጣጠሚያዎች ሁሉ መሰል የሌለው ነው፡፡ እዚህ ቦታ አውሮፕላኑ ተገጣጥሞ የመጨረሻውን ቅርጽ ሲይዝ ብዙዎቹ ሠራተኞቹ የሉም፡፡ በአንድ ነገር ግን ርግጠኞች ናቸው፡፡ እነርሱ ያመረቱት አካል ተገጣጥሞ አስደናቂውን የቦይንግ አውሮፕላን እንደሚፈጥረው፡፡
ሀገር የምትገነባው እንደዚህ ነው፡፡ በየዘመናቱ፣ በተለያየ ድርሻ፣ ሞያና አስተዋጽዖ የሚችሉትን በሚያበረክቱ ዜጎች፡፡ በአሜሪካም ይሁኑ በጃፓን፣ በአውስትራልያም ይሁኑ በካናዳ፣ በአውሮፓም ይሁኑ በእስያ፣ በአፍሪካም ይሁኑ በዐረቡ ዓለም ለአንዲት ኢትዮጵያ በሚሠሩ ዜጎች፡፡ የሚሠሩት ሥራ እጅግ አነስተኛ መስሎ ይታይ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ገዝፎ የሚታይ ጉልሕ ይመስላል፡፡ ግን ኢትዮጵያ ለምትባል አንዲት ዓላማ፣ ኢትዮጵያዊነት በሚባል አንድ ኩባንያ ውስጥ ሆነው የሚያመርቱ ዜጎች ናቸው ኢትዮጵያን የሚገነቧት፡፡ ምናልባትም አንዳንዶች የእነርሱ አስተዋጽዖ የመጨረሻው ሥዕል ምን እንደሆነ አላዩም፣ ወደፊት አያዩ ይሆናል፡፡ ግን በአንድ ነገር ርግጠኞች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በሁሉም አስተዋጽዖ ትገነባለች፡፡  
የእያንዳንዱ ቅንጣት በጥራትና በብቃት መመረት ለአውሮፕላኑ ጥራትና ብቃት ወሳኝ ነው፡፡ እያንዳንዳችን በተሠማራንበት ቦታ የምንሠራው፣ የምናስበው፣ የምንጽፈው፣ የምንወስነው፣ የምናካሂደው ነገር ጥራትና ብቃት እንዲኖረው ከተደረገ ሀገራችን የጠራችና የበቃች ትሆናለች፡፡ እያንዳንዱ የቦይንግ አውሮፕላን ቅንጣቶችን አምራች ባለሞያ የሚሠራው ነገር ከሌሎች ጋር ተጋጥሞ፣ ተስማምቶና ተዋድዶ አንድ አውሮፕላን ካልፈጠረ ሥራው ዋጋ የለውም፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በየቦታውና በየዘመናቱ የሚሠራው ሥራ ከሌላው ጋር ተጋጥሞ፣ ተስማምቶና ተዋድዶ አንዲት ኢትዮጵያን ካልፈጠረ ትርፉ ድካም ነው፡፡
ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ሁላችንም መተዋወቅ የለብንም፡፡ ለአንድ ዓላማ እስከሠራን ድረስ የትም ሆነን፣ ማንም ሆነን በግንባታው ላይ መሳተፍ እንችላለን፡፡ አንድ ዓይነት መሆንም የለብንም፡፡ የተለያየ እምነት፣ ዘርና ፖለቲካ ይዘን፣ በተለያየ ዘመንና ቦታ ሆነን መገንባት እንችላለን፡፡ ብቻ ለአንድ ዓላማ እንሰለፍ፡፡ ለማፍረስ ያይደለ፣ ለመገንባት፡፡
ማንም ብቻውን አውሮፕላኑን አያመርተውም፡፡ እያንዳንዱ ባለሞያ ለአንድ ዓላማ ተሠማርቶ በሚቻለውና በተሰጠው መጠን ይገነባል እንጂ፡፡ ኢትዮጵያም እንዲሁ ናት፡፡ ማንም ብቻውን አይገነባትም፡፡ ሁላችንም በተሰጠን መጠንና በቻልነው ያህል አሻራችንን እያሳረፍን እንገነባታለን፡፡
ኑ፣ በጋራ አገር እንገንባ፣ አኮብኩባ ስትበርም እንያት፡፡  

13 comments:

 1. ብቻ ለአንድ ዓላማ እንሰለፍ፡፡ ለማፍረስ ያይደለ፣ ለመገንባት፡፡

  ReplyDelete
 2. እጅግ በጣም ጥሩ አስተማሪ፣ አገናዛቢና አመላካች መልእክት ነው፡፡ ሰው ሆኖ እራሱን፣ ህዝብን፣ ወገኑን፣ ሀገሩንና ሌላውን በሙሉ ያለአድልዎና ነቀዝ ከሆነው ዘረኝነት በጸዳ መንገድ መሰራት፣ ማሰራት፣ መመራት፣ መምራት፣ ማመን፣ መታመን፣ መኖር፣ ማኖር ሲቻል የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነች ሀገራችን ታድጋለች፣ ትለመልማለች፣ ትሰፋለች፣ ትመራለች፣ ቀዳሚ ሆና ለዓለም ሁሉ መዳኛ መርከብ ትሆናለች፡፡

  ReplyDelete
 3. እያንዳንዳችን በተሠማራንበት ቦታ የምንሠራው፣ የምናስበው፣ የምንጽፈው፣ የምንወስነው፣ የምናካሂደው ነገር ጥራትና ብቃት እንዲኖረው ከተደረገ ሀገራችን የጠራችና የበቃች ትሆናለች፡፡ Amazing View

  ReplyDelete
 4. እያንዳንዳችን በተሠማራንበት ቦታ የምንሠራው፣ የምናስበው፣ የምንጽፈው፣ የምንወስነው፣ የምናካሂደው ነገር ጥራትና ብቃት እንዲኖረው ከተደረገ ሀገራችን የጠራችና የበቃች ትሆናለች፡፡ Amazing View

  ReplyDelete
 5. እያንዳንዳችን በተሠማራንበት ቦታ የምንሠራው፣ የምናስበው፣ የምንጽፈው፣ የምንወስነው፣ የምናካሂደው ነገር ጥራትና ብቃት እንዲኖረው ከተደረገ ሀገራችን የጠራችና የበቃች ትሆናለች፡፡ Amazing View

  ReplyDelete
 6. ማንም ብቻውን አውሮፕላኑን አያመርተውም፡፡ እያንዳንዱ ባለሞያ ለአንድ ዓላማ ተሠማርቶ በሚቻለውና በተሰጠው መጠን ይገነባል እንጂ፡፡ ኢትዮጵያም እንዲሁ ናት፡፡
  thank u

  ReplyDelete
 7. ewunet new ......ሀገር የምትገነባው እንደዚህ እንደ አውሮፕላን ነው፡፡

  ReplyDelete
 8. Your article reminded me this quote below.All those airplane parts go through these stages and work in unison to call it a functioning airplane.
  "Coming together is the beginning.Keeping together is progress.Working together is the Success."
  Henry Ford

  ReplyDelete
 9. እግዚአብሄር ጸጋውን ያብዛልህ።
  መድረሻውን ሳያውቅ የሚራመድ/ የሚጓዝ እንደተጓዘ ይኖራል እንጅ መድረሻ የለውም። አውሮፕላኑን ሰርተው እንደሚበር ሁሉም ያውቁና ያልሙ ነበር። ህልማቸው ግልጽ ስለሆነ ቢኖሩም ባይኖሩም ይሳካል። እኛም ለሃገራችን መሪዎች የምንለው ሁላችንም የምናየው ግልፅና ቀላል ግብ/መድረሻ አሳዩንና ተባብረን እናሳካው ነው።

  ReplyDelete
 10. ሀገር የምትገነባው እንደዚህ ነው፡፡

  ReplyDelete
 11. እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ . . . አምላክ ሀገራችንን በምህረት ይጎብኝ! አንተ መልካም ድንቅ ሰው በምን ቃል ልግለጽህ?

  ReplyDelete