ቦይንግ 747-8፣ ለመገጣጠም ብቻ 4 ወር የፈጀ አውሮፕላን ነው፡፡ ስድስት ሚሊዮን የሚገጣጠሙ ክፍሎች አሉት፡፡ በተለያየ የዓለም ክፍሎች ሆነው ከጥቃቅን እስከ ግዙፍ፣ ከመካኒካል እስከ ኤሌክትሪካል የሚያመርቱ ከ30 ሺ በላይ ሠራተኞች ይሳተፉበታል፡፡ ከእነዚህ መካከል የሚተዋወቁት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ የአንዱን መኖር ሌላው አያውቀውም፡፡ በእድሜ፣ በዜግነት፣ በጾታ፣ በእምነት፣ በመልክና በዘር ይለያያሉ፡፡ የሚከፈላቸው ክፍያ ይለያያል፡፡ የሚያመርቱትም የአውሮፕላኑን አንድ ክፍል እንጂ ጠቅላላውን አውሮፕላን አይደለም፡፡
ሁሉንም አንድ የሚያደርጓቸው ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ የሚሠሩት ለአንድ ኩባንያ መሆኑና
የሚሠሩበት ዓላማ አንድ መሆኑ፡፡ እነዚህን ሁሉ ስድስት ሚሊዮን ተገጣጣሚ አካላት የሚያመርቱት ባለሞያዎች ቦይንግ ለሚባል ኩባንያ
የሚሠሩ ናቸው፡፡ ንኡስ ኮንትራት ወስደው የሚሠሩት እንኳን ለዚሁ ኩባንያ እንደሚሠሩ ያውቃሉ፡፡ ሁለተኛው ነገር ደግሞ የሁሉም ዓላማ
አውሮፕላን መሥራት መሆኑ ነው፡፡ በዓይን ለማየት አስቸጋሪ የሆነቺው ብሎን ከሚሠራ ጀምሮ ትልልቁን አካል እስከሚያመርተው ድረስ
ዓላማቸው ብሎን፣ ክንፍ፣ በር፣ ሞተር፣ ጎማ፣ ወንበር፣ መሥራት አይደለም፡፡ አውሮፕላን መሥራት ነው፡፡ ያ በሰማይ ሲበር የሚያዩት
አውሮፕላን እንደየዐቅማቸው ተሳትፈው እነርሱ የሠሩት አንድ አውሮፕላን ነው፡፡