ታዋቂው የሥነ ልቡና ምሁር ሮልፍ ዶብሊ ‹አጥርቶ የማሰብ ጥበብ› በተሰኘው መጽሐፋቸው
ላይ እንዲህ ይላሉ፡፡ እንበልና አንተ የመድኃኒት አስተዳደር ኃላፊ ነህ፡፡ ለረዥም ግዜ ታምሞ የአልጋ ቁራኛ ለሆነ ሰው የሚሰጥን
መድኃኒት በተመለከተ እንድትወስን ቀረበልህ፡፡ መድኃኒቱ ከባድ የሆነ የጎንዮሽ ችግር አለው፡፡ ከሚወስዱት መካከል 20 በመቶዎቹ
ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ 80 በመቶዎቹን ደግሞ የማዳን ዕድል አለው፡፡ ይህን መድኃኒት ሰውዬው ይውሰድ ወይስ አይውሰድ? የሚለውን ጉዳይ
እንድትወስንበት ፊትህ ላይ ቀረበ፡፡
ብዙዎች ይላሉ ሊቁ ከአምስት ሰዎች አንዱን የሚነጥቀውን ይህንን መድኃኒት ሰውዬው ይውሰድ
ብለው ለመፈረምን ይፈራሉ፡፡ በሰው ሞት ላይ መፈረም ወይም በሰው ሕይወት ላይ መፍረድ አድርገው ይቆጥሩታልና፡፡ በቶሎ የሚታያቸውም
20 በመቶ ሰዎችን ይጎዳል የሚለው እንጂ 80 መቶ ሰዎችን ይጠቅማል የሚለው አይደለም፡፡ ምናልባትም ከመድኃኒቱ በኋላ ሰውዬው ቢሞት
ሚዲያውም ሆነ ሰዎች የሚያወሩት ወሬ የሚገድል መድኃኒት ወስዶ መሞቱን የሚገልጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም ባንተ ውሳኔ መድኃኒቱን
የወሰዱ ተከታታይ ሦስት ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ በአንተም፣ በሆስፒታሉም፣ በታካሚዎቹም ሆነ በኅብረተሰቡ ዘንድ ‹ለምን
ወሰነ? ለምን አይተወዉም ነበር? ለምን አይቀርበትም?› የሚሉ ጥያቄዎችን ሊያስነሣ ይችላል፡፡ እነዚያ በተከታታይ ሞትን የቀመሱት
ወገኖች ከጠቅላላው ውጤት 20 በመቶው ውስጥ መሆናቸውን የሚመለከት አይኖርም፡፡
ይህ ነው ሰዎችን ከዝምታ ይልቅ ተግባርን እንዲፈሩ የሚያደርጋቸው፡፡ ሮልፍ ዶብሊ ይህን
ሁኔታ በኛ ብሂል ‹መተው ነገሬን ከተተው› ወይም በእርሳቸው ቋንቋ
‹the omission bias› ይሉታል፡፡ የማይወስንና የማይሠራ ከሚወስንና ከሚሠራ ሰው ይልቅ የተሻለ ነገር እንዳደረገ የሚቆጠርበት
አዝማሚያ ነው፡፡ ከሚመጡ ሚሊዮን መልካም ውጤቶች ይልቅ የሚከሠቱ አንድ ሺ ስሕተቶችንና ጥፋቶችን አጉልቶ በመመልከት ‹ቢቀርስ›
የሚል ውሳኔ፡፡