Wednesday, September 12, 2018

‹ግቡ የአጥቂው፣ ድሉ የቡድኑ ነው›


ሰውዬው አንበሳ ሊያድን ጫካ ይገባል፡፡ እየተሽሎከለከ ዛፍ ለዛፍ ሲያነጣጥር፣ የአንበሳውንም ዱካ እያዳመጠ ሲከተል፣ ቆየና አንድ የአንበሳ ደቦል በቀስቱ አነጣጥሮ ጣለ፡፡ ገና ደስታውን ሳያጣጥም የሰውነት ክፍሎቹ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፡፡ እጁ አንበሳውን አነጣጥሮ የጣለው እርሱ መሆኑን በማስረዳት የተለየ ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ ተናገረ፡፡ ይህንን የሰማው እግሩም ‹መጀመሪያውኑ ማን ተሸክሞህ መጥተህ ነው ወጋሁት፣ መታሁት የምትለው› ብሎ ክብሩ የእርሱ መሆኑን ገለጠ፡፡ ነገሩን የታዘበው ዓይንም ‹በምን ዓይተህ ነው ያነጣጠርከው› አለና ክብሩ የእርሱ መሆኑን በኩራት ደሰኮረ፡፡ ጆሮም የአንበሳውን ዱካ እኔ በጽሞና ባልከተል የት ታገኙት ነበር? ሲል ቀዳሚው ባለ ድል እርሱ መሆኑን ደነፋ፡፡ አፍና ሆድም ‹ባልተበላ ምግብ በባዶ ሆድ እንኳን ማደን መታደን አይቻልም› ሲሉ ተከራከሩ፡፡ 

እንዲህ የሰውነት ክፍሎች ሁሉ እየተነሡ ‹ተኳሹ፣ መራዡ፣ አነጣጣሪው፣ እኔ ነኝ› እያሉ ሲከራከሩ ሰውዬው ወደ ግዳዩ ሳይሄድ ዘገየ፡፡ በዚህ መካከል ዓይን ቀና ቢል አንበሳው ሲሞት ያሰማውን ድምጽ የሰሙ ሌሎች አንበሶች ዙሪያቸውን ከበዋቸዋል፡፡ ዓይን በድንጋጤ ሲፈጥ ያስተዋለው እጅም ለሌሎች አካላት መከባባቸውን ጠቆመ፡፡ ይህን የተመለከተው እግር እሮጣለሁ ብሎ ሲያስብ እንኳን መሮጫ መሹለኪያ ቀዳዳ አላገኘም፡፡ ቅድም እኔ ነኝ እኔ ነኝ እሉ ሲፎክሩ የነበሩት ሁሉ ለየብቻ ሮጠው ማምለጥ አልተቻላቸውም፡፡ አንበሶቹ ግን የግዳይ ቀለበታቸውን እያጠበቡ እያጠበቡ ተጠጉ፡፡ ፍጻሜውም መበላት ሆነ፡፡


ዛሬም በኢትዮጵያ የሚታየው ይሄ ነው፡፡ ባለ ድሉ እኔ ነኝ፣ ታጋዩ እኔ ነኝ፣ ለውጡን ያመጣሁት እኔ ነኝ፣ የዚህ ሁሉ ፊታውራሪ እኔ ብቻ ነኝ፣ ሠሪ ፈጣሪው፣ ያዡ ገናዡ እኔ ነኝ፤ የቅድምና ሩጫ የክብር እሽድድም፡፡ ከአንባሰው ሞት በኋላ ምን እናድርግ? ብለው ከመወያት ይልቅ አንበሳውን የገደለው ማነው? በሚል ውዝግብ ውስጥ እንደገቡት የሰውነት ክፍሎች፣ዛሬም ከተፈጠረው ለውጥ በኋላ ምን እናድርግ? ችግሩ ተመልሶ እንዳይመጣ፣ የተሻለ ቀንም እንዲፈጠር ምን እናድርግ? ከማለት ይልቅ ‹የዚህ ሁሉ ጫጩት አውራው እኔ ነኝ› የሚል በሽታ ውስጥ ገብተናል፡፡ የአንድ ሰውነት አካላት መሆናችን ረስተናል፡፡ የሚና ልዩነት የአስተዋጽዖ ተዋረድ ፈጥሮብናል፡፡ አሁንም ከትናንት ሳንወጣ በትናንት አዙሪት ውስጥ እየገባን ነው፡፡ አንድ ሯጭ ምን ያህል ኪሎ ሜትር እንደሮጠ ከማሰብ ይልቅ ምን ያህል ከፊቱ እንደሚቀረው ማሰቡ ነው የሚጠቅመው፡፡ የሮጠው ያለቀ ጉዳይ ነው፡፡ የሚሮጠው ግን ገና የሚቀርና የሚፎካከርበት መድረክ ነው፡፡ ምንም ያህል እየመራ ቢሆን ገመዱን በጥሶ እስካልፈጸመ ድሉ ተጠናቅቋል ማለት አይቻልም፡፡ አንደኛ ሆኖ መቅደም አንደኛ ሆኖ ለመውጣት ብቸኛው ዋስትና አይደለም፡፡ ድሉን እስከ መጨረሻው ካላስጠበቀ በቀር፡፡ 

በአንድ ሀገር ታሪክ ውስጥ አንድ ሰው፣ ቡድን፣ ፓርቲ፣ ማኅበረሰብ ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ለውጥ የሂደት ውጤት ነውና፡፡ ነገር ግን የሚታዩና የማይታዩ ለውጥ አምጭዎች አሉ፡፡ መቼም የሰው መታወቂያ ላይ የሆድ ዕቃው ፎቶ አይወጣም፡፡ የፊቱ ጉርድ ፎቶ እንጂ፡፡ ያ ማለት ግን ሰውዬው ፊቱ ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ ለውጥና ትግልም እንደዚያው ነው፡፡ ከፊት የሚታዩት ፊታውራሪዎች የማይታዩት ውጤቶች መሆናቸውን ከረሱ አንገትን የዘነጋ ጭንቅላት ይሆናሉ፡፡ ዝናብ እንዲመጣ የተፈጥሮ ኃይሎች ሁሉ የተባበረ አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ ሁሉ ለውጥ እንዲመጣም ማኅበራዊ ኃይሎች ሁሉ የሚታይና የማይታይ አስተዋጽዖ አላቸው፡፡ 

የተሻለውና የሚጠቅመው ነገር ‹እኔ ብቻ ነኝ‹ ና ‹ለእኔ ብቻ ነው› የሚለውን ስሜት አጥፍቶ ‹እኛ ነንና ለእኛ ለሁላችን ነው› የሚለውን እውነታ መቀበልና ማስፈን ነው፡፡ ድልን ማስጠበቅ ድል ከማድረግ በላይ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ለአንድ የእግር ኳስ ቡድን ግብ ከማስቆጠር በላይ የማሸነፊያ ነጥቡን አስጠብቆ መውጣቱ እጅግ አድካሚና የበሰለ ታክቲክ የሚጠይቀው ነው፡፡ ያንን ለማድረግ የሚችለው ደግሞ አሥራ አንዱም ተጨዋቾች ‹ግቡ የአጥቂው፣ ድሉ የቡድኑ ነው› ብለው ሲሠሩ ብቻ ነው፡፡ ግብ አግቢው ድሉ የኔ ብቻ ነው ብሎ ካሰበ ኳስ የሚያቀብለው አያገኝም፡፡ 

እኛ ‹ለውጡ የማን ነው?› እያልን ስንጨቃጨቅ ድል ያደረግናቸው ችግሮች መልሰው እንዳይከቡንና ከፈንጠዝያው ሳንወርድ ወደ ሽንፈቱ ቀለበት እንዳይከቱን ‹መከራው የጋራችን እንደነበረው ሁሉ፣ ድሉም የጋራ፣ የድሉ ፊታውራሪ ጀግኖችም የጋራ፣ የሚመጣውም ለውጥ የጋራ› ብለን ማመን አለብን፡፡ የጎጥ ጀግኖች ዘመን ይብቃ፡፡

22 comments:

 1. GIRUM EYTA NEW YENISIR AYINOCHI ENDEBERU YINURU

  ReplyDelete
  Replies
  1. ..gibu ye atki dilu ye bufinu .amlak biruh aymirohin yibarkew

   Delete
  2. Egziabher ewuketihin ikensibih yichmirlih ewunet neaw Diakon gin semi tefitoal

   Delete
 2. ምርጥ ፅሁፍ + ምርጥ እይታ

  ReplyDelete
 3. ይግርማል: ማንምሰዉ: ያልትረዳው: ይሕ: የእግዚአብሔር: እንጂ: የሰው: አይደለም: ማንም: አላመጣውም::!!!
  ይልቅስ: ይሄ: የተሰጠን: በረከት: ሳንጠቀምበት: እንዳያልፈን::
  ዲ/ን ዳንኤል:: እግዚአብሔር: ያገልግሎት: ዘመንሕን:ይባርክልህ:
  ልብ:ያለው: ቆም: ብሎ:ያስተውል!!!

  ReplyDelete
 4. ኑርልን ዲቆን ዳንኤል ክብረት!!

  ReplyDelete
 5. እኔነት የማንነት መገለጫ ሳይሆን የምንነት ማሳያ ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ ምንነታችንን በመፈለግና እኛነታችንን በመርሳት መካከል ሆነን እርስ በእርሳችን የምንበላላበትና የእኛ የሆነውን ድልና ክብር የእኔ ለማድረግ የምንሯሯጥበት ሳይሆን፤ጊዜው እኛነታችንን አጉልተን ከፍ ብለን የምንታይበት ዘመን ሊሆን ይገባዋል፡፡በነገራችን ላይ ለዚህ ለውጥ በግልጽም ይሁን በስውር የራሱን አሻራ ያላስቀመጠ ኢትዮጲያዊ የለም፤ጊዜያቸውን ተጠቅመው ክፋት የሰሩብን እንኳን ቢሆኑ ግፍና በደላቸው መሮን የጫኑብንን የእኔ ብቻ ቀንበር አውልቀን ለመጣል ያለፍርሃት ባደባባይ እንድንወጣ አድርገውናል፡፡ ስለዚህ ባናመሰግናቸው እንኳን በጥላቻ ልናያቸውና ልናገላቸው አይገባም፡፡ ባጠቃላይ ድሉን የሁላችንም እንጂ ያንዳችን ባለመሆኑ ኋላ ብቻ መሆን በሚያስከትለው ጣጣ ከመጨነቅ ካሁኑ የነበረውን አብሮነት ማስቀጠል አማራጭ የሌለው ብቻ ሳይሆን ለምርጫ ሊቀርብ የማይገባው ጉዳይ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ ዳኒ እናመሰግናለን!!

  ReplyDelete
 6. Daniel, son of Gomorrah,

  that is the reality that you have to face!!!

  You all are mediocre and selfish souls who does not have any clear objective to uphold, other than advancing your personal interests in the name of the poor Ethiopian people.

  ReplyDelete
 7. Enezih tiwld Adin dink tsihufochihn yetewesenu sewoch bicha manbebachew ejig yasaznegnal!!! Yesew lij lemenor Ayer wuhana Migib endemiyasfelgew hulu Yeferaresew yegna maninet yitegen yidn zend yante tsihuf kurs, misa, rat endihonen Addis Mela yemiyasfelg yimeslegnal yemanbeb limdachin dekama silehone. Egziabher tibebin abzto yeseteh WUDU STOTACHIN, YEMNKORABH,MELKAMU SEW Dani bertalin. 'YEMISEMA JORO YALEW YISMA'

  ReplyDelete
 8. Wow yehen tsehuf be audio melk lhulum sew biders betam girum new!

  ReplyDelete
 9. ‹እኔ ብቻ ነኝ‹ ና ‹ለእኔ ብቻ ነው› የሚለውን ስሜት አጥፍቶ ‹እኛ ነንና ለእኛ ለሁላችን ነው› የሚለውን እውነታ መቀበልና ማስፈን ነው፡፡ Thank you so much Dany!

  ReplyDelete
 10. "የጎጥ ጀግኖች ዘመን ይብቃ፡፡"ግሩም እና ድንቅ እይታ ነው እናመሰግናለን ቃለ ሕይወት ያሰማልን!!!

  ReplyDelete
 11. ረጅም፡እድሜና፡ጤና፡ለዳኒ!

  ReplyDelete
 12. ባለ ድሉ እኔ ነኝ፣ ታጋዩ እኔ ነኝ፣ ለውጡን ያመጣሁት እኔ ነኝ፣ የዚህ ሁሉ ፊታውራሪ እኔ ብቻ ነኝ፣ ሠሪ ፈጣሪው፣ ያዡ ገናዡ እኔ ነኝ፤ የቅድምና ሩጫ የክብር እሽቅድድም፡፡

  ReplyDelete
 13. "የጎጥ ጀግኖች ዘመን ይብቃ"!

  ReplyDelete
 14. በጣም ልክ ብለሃል ዳኒ፡፡ ይሄን መገንዘብ ያቃተው ትውልድ ነው ያለው፡፡

  ReplyDelete
 15. Betam teru eyeta nw Dani... erejim edma ke tena gar

  ReplyDelete