Thursday, September 6, 2018

የማይሰለቹት አባት፤ ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ


ንግግራቸው ምንጊዜም ፈዋሽ ነው፡፡ የትኛውም ቦታ ላይ ሆነው ቢሰሙት ለራስ የተላከ ደብዳቤ ይመስላል፡፡ ሃይማኖታቸውን ከንግግራቸው ማወቅ ከባድ ነው፡፡በቅርብ ለሚያውቋቸው ወይም ልብሳቸውን ለተመለከተ ካልሆነ በቀር፡፡ የሚናገሩት ሁሉንም እምነት የሚመለከት ነውና፡፡ የሁለቱን ሲኖዶሶች ዕርቅ ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የሚሊኒየም አዳራሽ ጉባኤ ላይ ያስተላለፉትን መልእክት ሊቃነ ጳጳሳቱ ከልባቸው ካዳመጡት ‹ሲታረቁ ከሆድ፣ ሲታጠቡ ከክንድ› የሚያደርግ ነው፡፡  
እሑድ ዕለት የበጎ ሰው ሽልማት ፕሮግራም ላይ ለክቡር አቶ ለማ መገርሳ ሽልማቱን ያበረከቱት እርሳቸው ነበሩ፡፡ ቢሮክራሲ የሚባል ነገር የማያውቃቸው፤ ነገርን በጉዳዩ ልክ ብቻ የሚመዝኑ¶ የተጠሩበትን ጉዳይ እንጂ የጠራቸውን ሰው ማንነት ከቁም ነገር የማይቆጥሩ፣ የአለቃ ሳይሆን የአባት ጠባይ ያላቸው ናቸው፡- ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ፡፡


ክቡር አቶ ለማ መገርሳ ወደ ሚሊኒየሙ መርሐ ግብር ሲሄዱ ቀዳሚ ሙፍቲ ብቻቸውን ተቀመጡ፡፡ ነጻነት ተስፋዬ ‹ብቻቸውን ከሚሆኑ አብረኻቸው ሁን› ሲለኝ የዘመናት ምኞቴ ነበርና አጠገባቸው ቁጭ አልኩ፡፡ ከአንድ ሽማግሌ አጠገብ መቀመጥ አንድ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ገብቶ የማንበብ ያህል ነው፡፡ የሃይማኖት አባት ሲሆኑ ደግሞ የመጽሐፉ ቁጥርና ጥራት ይጨምራል፡፡
‹አላህ ይስጥህ ልጄ›  አሉኝ በዚያ ተደማጭ ድምጻቸው
‹ምን አደረግኩልዎት› አልኳቸው፡፡
‹እንኳንም እንዲህ ያለው ቦታ ጠራህኝ› አሉኝ፡፡
‹ደስ አለዎት› አልኩና ጠየቅኳቸው፡፡
‹እይውልህ ልጄ፣ ስለ ሰው ደግ ነገር መስማት ጤና ይሰጣል፡፡ እድሜንም ያስረዝማል፡፡ ስለ ሰው ክፉ ነገር መስማት ግን በሽታ ያመጣል፤ እድሜንም ያሳጥራል፡፡ ስለ ጠላትህ እንኳን ክፉ ክፉውን መስማት አንተኑ ነው የሚጎዳው፡፡ ቀደምቶቻችን እንኳን ስለ ሰው ስለ ሸይጣን እንኳ ክፉ መስማት አይጠቅምም› ይሉ ነበር፡፡ ሸይጣን አንድ ጊዜ ሸይጥኗል፡፡ አይጠቀምምç አይጎዳም፡፡ አንተ ግን የእርሱን ክፉ በመስማትህ ያምሃል፡፡ዛሬ ደስ ያለኝ ስለ ሰው ጥሩ በሚነገርበት ቦታ ስለጠራኸኝ ነው፡፡ ስለ ሰው ደግ ደጉን መናገርና መስማት የሚጠቅመው ሰሚውን ነው፡፡ ሰው ሁሉ ይራራቃል እንጂ አንድ ሥጋ ነው፡፡ ያኛው ሰው ሲያመው አንተንም ያምሃል፡፡ ጣትህ ወይም ዓይንህ ማለትኮ ነው፡፡ ስለዚያኛው ሰው ክፉ መስማት ማለት ስለራስህ አንድ አካል ክፉ መስማት ማለት ነው፡፡ እስኪ ተመልከት ልጄ፡፡ አንድ ሰው መጥቶ እግርህ መጥፎ ጠረን አለው ቢልህ ቀኑን በሙሉ ጤነኛ ሆነህ አትውልም፡፡ ስለ ወንድምህ ክፉ መስማትም እንዲሁ ነው› አሉኝ፡፡ መርሐ ግብሩን ዘንግቼ በተመስጦ ነበር የማዳምጣቸው፡፡
የጃፓኑ ማሳሩ ኢሞቶ ያጠናውና በ2008 በ Journal of Scientific Exploration የታተመው ጥናት ትዝ አለኝ፡፡ በኋላም The Hidden Messages in Water በሚል ርእስ በመጽሐፍ አሳትሞታል፡፡ ሁለት ብርጭቆዎችን በንጹሕ ውኃ ሞላቸው፡፡ በአንደኛው ብርጭቆ ውኃ ላይ መጥፎ መጥፎ ቃላትን ወረወረ፡፡ በሁለተኛው ብርጭቆ ውኃ ላይ ደግሞ ደግ ደግ ቃላትን ተናገረ፡፡ ከዚያም ሁለቱንም የብርጭቆ ውኃዎች ወደ በረዶነት እንዲቀየሩ አደረጋቸው፡፡ በመልካም ቃላት የተባረከው ውኃ አስደሳች ቅርጽ ያላቸው ክሪስታሎችን ሲሠራ በመጥፎ ቃላት የታጀበው ውኃ ደግሞ አስቀያሚ ቅርጽ ያላቸው ክሪስታሎችን ሠራ፡፡ ከሰው ልጅ ሰውነት ውስጥ እስከ 60 በመቶ የሚሆነው ውኃ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ የሰውነት ክፍላችን በምንሰማውና በምናነበው፣ በምናየውና በምናጣጥመው የዓለማችን ሁኔታ አንዴ ሲደስት፣ አንዴ ሲያዝን ብቻ አይደለም የሚውለው፡፡ ሲታመምና ሲድን፣ ሲጣመምና ሲቃና ጭምር እንጂ፡፡ ‹አዎንታዊ ኃይል(positive energy)› የሚባለው ይሄ ነው፡፡
ቀዳሚ ሙፍቲ የነገሩኝም ይሄንኑ ነው፡፡ እድሜ ይስጥዎት ሐጂ፡፡

13 comments:

 1. እድሜ ይስጥልን

  ReplyDelete
 2. ከዚህ በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፥ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፤ እረኛውም አንድ በጎቹም አንድ ይሆናሉ።

  ReplyDelete
 3. Thank you for sharing.
  please remind Dr. Abiy when you can to initiate a program of honoring Ethiopian mothers who have suffered a lot in the hands of Derg & TPLF.

  ReplyDelete
 4. Amen Amen ahunim lewodefitu talalaki sewoch talak negere alachewuna intekemibachewu

  ReplyDelete
 5. ስለ ጠላትህ እንኳን ክፉ ክፉውን መስማት አንተኑ ነው የሚጎዳው፡፡ ቀደምቶቻችን እንኳን ስለ ሰው ስለ ሸይጣን እንኳ ክፉ መስማት አይጠቅምም› ይሉ ነበር፡፡ ሸይጣን አንድ ጊዜ ሸይጥኗል፡፡ አይጠቀምምç አይጎዳም፡፡ አንተ ግን የእርሱን ክፉ በመስማትህ ያምሃል፡፡እናመሰግናለን፡፡

  ReplyDelete
 6. እይውልህ ልጄ፣ ስለ ሰው ደግ ነገር መስማት ጤና ይሰጣል፡፡ እድሜንም ያስረዝማል፡፡ ስለ ሰው ክፉ ነገር መስማት ግን በሽታ ያመጣል፤ እድሜንም ያሳጥራል፡፡

  ReplyDelete
 7. Teziko yemayalk leauanuar zeybe timhertawi honew yemiyagelegelu ababalocheh alehu egzer anten yanurelen Dani especially bezih tirmes gize your role is irreplaceable and priceless. More than ever, now, we need to hear from people that are reasonable and great voices of common sense. Ethiopia desperately needs people like you, now, because we are at the crossroad. Thank you Dani to your great contributions!!!

  ReplyDelete
 8. oh great idea thank you so much.

  ReplyDelete
 9. መልካምነት ትልቁ የእስልምና መርሆ ነው!!!።

  ReplyDelete