Friday, August 3, 2018

ወደ ምዕራብ ሰዎች


የሦስት ወሩን አድካሚና አስደሳች ሩጫ አገባደድነው፡፡ አሁን የቀረን ዝርዝር ሪፖርቱን ተረጋግቶ መጻፍ ነው፡፡ ብዙ አስገራሚ፣ አሳዛኝ፣ አስደሳች፣ አስቂኝ ገጠመኞችን በቀጣዮቹ ቀናት አወጋችኋለሁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በአሜሪካ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለማነጋገር ወደ አሜሪካ እንደሚሄዱ የታቀደው ግንቦት ወር ላይ ነው፡፡ የዳላሱ የኢትዮጵያውያን ስፖርት በዓል ግብዣ ሲመጣ ነገሩ ሌላ መልክ ይዞ ነበር፡፡ ጋባዡ ማን ነበር? ክልከላውስ ከየት መጣ? በብዕር ወደፊት እንራመድበታለን፡፡
ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የርእሳነ መንግሥታት ታሪክ ወደ አሜሪካ የሚደረጉ ጉዞዎች በዋናነት ከአሜሪካ መንግሥት፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከሌሎች ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ጋር የተያያዙ ነበሩ፡፡ የዲያስፖራው ጉዳይ በጎንዮሽ የሚያዝ ነው፡፡ የዚህኛው ጉዞ ዋናው ልዩነቱ በዋናነት ኢትዮጵያውያንን ለማግኘት የተዘጋጀ መሆኑ ነው፡፡
ለአዲስ ሐሳብ አዲስ አካሄድ በሚል ጉዞውን የሚያስተባብረው ኮሚቴ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከባለ በጎ ፈቃድ ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዲቋቋም ተደረገ፡፡ የዳሰሳ ጥናት ተዘጋጀ፡፡ ዝርዝር ዕቅድ ወጣ፡፡ መጀመሪያ በዋሽንግተን ዲሲ በመቀጠል በሎስ አንጀለስ በመጨረሻም በሚነሶታ ኮሚቴዎች ተቋቋሙ፡፡
እንግዳው ነገር ተጀመረ፡፡ የኢሕአፓ፣ የመኢሶን፣ የቅንጅት፣ የኢሕአዴግ፣ የሰማያዊ፣ የግንቦት ሰባትና የሌሎቹም ፓርቲዎች አባላት በአንድ ኮሚቴ ውስጥ እንዲሰበሰቡ ጥሪ ቀረበ፡፡ አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው መጡ፡፡ በፓርቲ ውስጥ የሌሉ ነገር ግን ዋነኛ የፖለቲካ አቀንቃኞች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ጎረፉ፡፡ ተያይተው የማያውቁ፣ ተደማምጠው የማያውቁ፣ በአንድ ላይ ተቀምጠው የማያውቁ፣ ቢገናኙ የሚደባደቡ ኃይሎች ተሰበሰቡ፡፡ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ሐረሪ፣ ሶማሊ፣ ጋምቤላ፣ ጉሙዝ፣ አፋር፣ ኮሙኒቲዎች ሰዎችን ላኩ፡፡ 

ይህ ክስተት ለኤምባሲውም፣ ለተሰብሳቢውም፣ ለእኛም፣ ለመንግሥትም፣ ለማኅበረሰቡም አዲስ ነው፡፡ የመንግሥት ባለ ሥልጣናትም ሆኑ ኤምባሲዎቹ ከጥቂት፣ ብዙ ጊዜ ተመሳሳይ ከሆኑ ሰዎች ጋር እንጂ እንዲህ እንደ ነዳይ ምግብ ውጥንቅጣቸው ከወጣ ዳያስፖራዎች ጋር በሰላም ተገናኝተው አያውቁም፡፡ የመጀመሪያዎቹ ቀናት በሽምግልናና በልመና ነው ያለቁት፡፡ አንዱ አንዱን ማየት አይፈልግም፡፡ ‹እገሌ ከመጣ እኔ እወጣለሁ› ይላል፡፡ ‹ስሜ ሲጠራ ከነ እገሌ ቀጥሎ መጠራት የለብኝም› ብሎ ያኮርፋል፡፡ የአማርኛም ሆነ የእንግሊዝኛ አልፋቤትን ለመጠቀም ተሞከረ፡፡ መጀመሪያ የሚጠሩት ሲደሰቱ መጨረሻ የሚጠሩት ቅር ይላቸዋል፡፡ ችግሩን በኮሚቴው ውስጥ ተነጋግሮ በስምምነት ወይም በድምጽ ብልጫ ከመወሰን ይልቅ ‹ይህንን ካልተቀበላችሁ መግለጫ አወጣለሁ፣ ሰልፍ አደርጋለሁ፣ ቦይ ኮት አደርጋለሁ› የሚለው ብዙ ነው፡፡ እገሌን እዚህ ቦታ እንዳናያው ብሎ በማኅበር፣ በኮሙኒቲ፣ በፓርቲ፣ አስወስኖ፣ የሺዎችን ፊርማ አሰባስቦ የሚመጣ አለ፡፡
ይህ በየምሽጉ ሲታኮስ የኖረ ማኅበረሰብ ተግባብቶ፣ ተስማምቶ፣ ተጣጥሞና ተማምኖ ያንን አስደናቂ ሥራ እንዲሠራ ሌት ተቀን መሰብሰብ፣ ጆሮ እስኪቃጠል በስልክ ማውራት፣ በየሆቴሉና ካፍቴሪያው እየዞሩ ማግባባት፣ በሚያውቋቸው ሰዎች በኩል ማስረዳት፣ አንዳንዱን እንዳላዩ ማለፍ፣ ሌላውን ፊት ለፊት መጋፈጥ፣ ከአንዳንዶች ጋር መከራከር፣ ከአንዳንዶችም ጋር መደራደር አስፈልጎ ነበር፡፡ ለሁሉም የሚሆን፣ ሁሉም የሚሰማው፣ ቢያንስ ልብ የሚሰጠው ሁነና ሰው ማግኘት እንዴት ከባድ ነበር፡፡ አንድነቱ ዶክተር ዐቢይን በመቀበል የተመሠረት ቋሚ (vertical) እንጂ እርስ በርስ በመግባባትና በመተማመን የተገነባ የጎንዮሽ(horizontal) አልነበረም፡፡
ተቦክቶ፣ ተንተክትኮ፤ በጭድና በውኃ ተጣብቆ አንድ እንደሚሆን ጭቃ፣ ከብዙ ውይይት፣ ክርክር፣ ጭቅጭቅና ትግትግ በኋላ የጎንዮሹ አንድነት እየተገነባ መጣ፡፡ ከ70 በመቶ በላይ የኮሚቴዎች አባላት ኤምባሲና ቆንስላ መጥተው አያውቁም፡፡ አንዳንዶቹም የሚመጡት ለተቃውሞ ነው፡፡ ለቆንስላ ጉዳዮች የሚመጡትም ወደ ውስጥ ገብተው አያውቁም፡፡ እዚያ ኤምባሲ ወይም ቆንስላ መግባት ዋጋ ያስከፍል ነበር፡፡ ያስወግዛል፣ ያሰድባል፤ ያስገልላል፡፡ ‹እንዳያልፍ የለም ያ ሁሉ አለፈ፡፡› መግባባቱ ሲመጣ ኤምባሲው ለሥራ በሚሠማሩ ዜጎች ተሞላ፡፡ በሚወያዩ፣ በሚያቅዱና መፍትሔ በሚያፈላልጉ የኮሚቴ አባላት የሚያሸበርቀውን ኤምባሲ ያየ ለኮንደሚኒየም ምዝገባ የመጡ እንጂ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል የሚተጉ ናቸው ብሎ ለማመን ይቸገራል፡፡ የዲሲ ኤምባሲና የሎስ አንጀለስ ቆንስላ የተቃውሞ ሰልፍ ሲናፍቀው ማየት አስገራሚ ነበር፡፡ ያቺ መከረኛ ሰንደቅም ሰላም ውላ ሰላም ማደር ጀመረች፡፡ በባለ ኮከቡ ባንዴራ ያልተስማሙም እናውርድ ብለው አያስቸግሩም፡፡ የራሳቸውን ባንዴራ ይዘው መጥተው ትከሻቸው ላይ ያውለበልባሉ፡፡
ክርስቶስ በምድር ላይ በሚያስተምርበት ጊዜ የነበሩ ሰዎች በብሉይ አመለካከት ሐዲስን እየተቀበሉ ነበር፡፡ የተማሩት፣ የኖሩበት፣ የለመዱትና የሚያውቁት ብሉይን ነው፡፡ ጠባያቸው፣ ባሕላቸውና አሠራራቸው ብሉይ ነው፡፡ ነገር ግን በሐዲስ ኪዳን መንገድ ውስጥ ናቸው፡፡ በአሜሪካ የነበረውም እንዲህ ነው፡፡ከዚህ በፊት መሪን መቃወም እንጂ ከመሪ ጋር መሥራትና መሪን መደገፍ አልተለመደም፡፡ መሪን ለመቃወም ድርጅቶች ተመሥርተዋል፣ ቡድኖች ተዋቅረዋል፤ መፈክሮች ተዘጋጅተዋል፣ ሚዲያዎች ተፈጥረዋል፤ ዜማዎች ተዚመዋል፤ ፖስተሮች ተቀምረዋል፡፡፡ ቢያንስ የ40 ዓመት ልምድ አለ፡፡ የአንድ ትውልድ ልምድ፡፡ መሪን ለመቀበልና መሪን ለመደገፍ ግን የተዘጋጀ ነገር የለም፡፡ ምንድን ነው የሚባለው? እንዴት ነው የሚደረገው? ብዙዎቹ በዚህ ጉዳይ ላይ የዐፄ ኃይለ ሥላሴን ዘመነ ነው የሚያስታውሱት፡፡ ዕንቁላልና ቲማቲም ከውርወራ ተርፈው ሳንዱች ተሠራባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ባለ ሥልጣናትም በአሜሪካ ከተሞች ላይ እጃቸውን ኪሳቸው ውስጥ ከትተው ያለ መሸማቀቅ መራመድ ጀመሩ፡፡  
እስከዛሬ ድረስ ስንቃወም ‹ሼም ኦን ዩ› እንላለን፡፡ አሁን ለድጋፍ ‹ምን ኦን ዩ› ነው የምንለው? ብሎ እንዳሳቀኝ ልጅ፡፡
አስተሳሰባችንና አሠራራችን፣አደረጃጀታችንም የድሮ ነው፡፡ ፍላጎታችን ግን የዛሬ፡፡ አዲሱን ሐሳብ በድሮው መንገድ ነበር የምንሠራው፡፡ ተስፋው እንጂ ባሕሉ ገና አልመጣም፡፡ አንድ የሆነ ቡድን ቅሬታ አለኝ ብሎ ሊያናግረን ቀጠረን፡፡ ሚኒስቴር ዲኤታዋና አምባሳደሩ ከፕሮቶኮሉ መሥመር ወርደው ሰዎቹ የፈለጉት ቦታ ላይ ተገኙ፡፡ ቅሬታ ያሉትን አቀረቡ፡፡ እንዴው መቼም ቅሬታ እጥረት ስለተፈጠረ እንጂ ነገሩስ እዚያው በኮሚቴ የሚያልቅ ነበረ፡፡ በመጨረሻ ተስማማን፡፡ ከውይይቱ ስንወጣ እነዚያው ሰዎች ከኛ ጋር እየተወያዩ ባሉበት በዚያ ሰዓት በጎን የተቃውሞ መግለጫ አውጥተው ጠበቁን፡፡ አልገረምን፡፤ አንዳንድ ጥይት ይባርቃል፡፡ ነጥብ ማስቆጠር የኖርንባት ስልት ናት፡፡ ሤራ ተሠርቷል፣ ሼር ተሸርቧል፤ በምሥጢር እንዲህ ተደርጓል፣ እነ እገሌ ‹ሃይጃክ› አድርገዋል፣ ሰነድ ወጣ ሰነድ ገባ፣ የሚሉት ነገሮች አዲሱን የወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ለማስቀመጥ ሲታሰብ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ያው አባታችን ጴጥሮስ ከፍቅር መምህሩ ከክርስቶስ ጋር እየዋለ በመጨረሻ ሰይፍ መዝዞ አልነበር? የኖሩበት ነገር በአንዴ አይተውም፡፡
በፖለቲካ ድርጅቶች መድረክና በምሁራን መድረኮች የታዩ አስደሳችና አስገራሚ፣ አሳዛኝና ልብ አውላቂ ነገሮችን ወደፊት እመጣባቸዋለሁ፡፡ በፊደላውያንና በምሁራን መካከል ያለውን ሰፊ ርቀት ለማየት እነዚህ መድረኮች ምቹ ነበሩ፡፡ ዕውቀታቸው የተደላደለ፤ ብስለታቸው የነጠረ፤ ሐሳባቸው የጠራ፤ ጥበባቸው የላቀ ምሁራንን አይተናል፡፡ ኢትዮጵያ እነርሱን በማግኘቷ የሚቆጫት፡፡ በዚያ ማዶ ደግሞ እነ ሆድ ይፍጀውንም ታዝበናል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲ አባላትና በፖለቲከኞች መካከል ያለውን እንደ አልዓዛርና ነዌ ማዶ ለማዶ የተቀመጠ ልዩነት ለመገንዘብ ከዚህ የተሻለ ዕድል አልገጠመኝም፡፡ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ከቅዱስ አትናቴዎስ ተሾሞ ሲመጣ የኦሪት ትምህርት እያስተማሩ ያገኛቸውን የኢትዮጵያን ሊቃውንት እንዴት የሐዲስ ሊቃውንት እንዳደረጋቸው ከታሪካችን መማር ያስፈልገናል፡፡ በኢትዮጵያ የዕውቀትና የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ብሉይን ከሐዲስ የማጣጣም ችግር አለ፡፡ ከታሪክ ተቆርጦ ትናንት ላይ የመቅረት ዕጣ፡፡    
በዚህ ሂደት ያየናቸው ለሀገራቸው ያለ ምንም ዋጋ ለማገልገል በእሳትና በውኃ መካከል የሚያልፉ ጀግኖችም አሉ፡፡ የትውልድ ድልድይ አባላት እስከ ቀራንዮ ያደረጉት ተጋድሎ ዕጹብ ዕጹብ ያሰኛል፡፡ ብዙዎቹ የዲሲ ግብረ ኃይል አባላት ጫናዎችን ሁሉ ተቋቁመው የታገሉት ትግል አስደናቂ ነበር፡፡ ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ባለቀ ሰዓት የተቀበለችውን ኃላፊነት ለመወጣት የለፋችው ልፋት የማይረሳ ነው፡፡ የቪኦኤ፣ የኢሳት፣ የዓባይ ሚዲያ፣ የአዲስ ድምጽ፣ የኦ.ኤም.ኤን፣ የቲጂ ቲቪ፣ ጋዜጠኞች ከግራ ከቀኝ የሚመጣውን ሁሉ እየታገሉ ለዝግጅቱ መሳካት የከፈሉት ዋጋ በታሪክ የሚመዘገብ ነው፡፡ በጄኔቫ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ የነበረው ዝግጅት እንዲሳካ ባሕር ማዶ እየተሻገሩ ለማወያየት፣ ለማቀራረብ፣ አንዳንዶችንም ለመምከርና ለመገሠጽ የሄዱበት ርቀት እንኳን ዐወቅናችሁ የሚያሰኝ ነበር፡፡ ከሆቴል እስከ ኮንቬንሽ ሴንተር የነበረው ቅንጅት ከ ‹ዩ ስትሪት ፓርኪንግ› ባለቤት ከሄኖክ ተስፋዬ ውጭ አይታሰብም ነበር፡፡ ከመቶ በላይ መኪኖችን በማቅረብ ያለ ዕረፍት የሠሩት የዲሲዎቹ ባለ መኪኖች፣ ሕዝቡን በትጋት ያመላለሱት የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ባለ ታክሲዎች አገልግሎት እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭን ነው፡፡ ለመስተንግዶውና ለቅንጅቱ የደከሙት የዋሽንግተንና አካባቢዋ ወጣቶች ተስፋን የሚፈነጥቁ ናቸው፡፡  
የአቶ ነአምን ዘለቀ ባለቤት ሕይወት ለሀገሯ የሠራችውን ታላቅ ሥራ ይህ ትውልድ ሲያስታውሰው እንዲኖር ወደፊት በዝርዝር እጽፈዋለሁ፡፡ የኢሳቱ ብሩክ ይባስና አበበ ገላው ወዲያና ወዲህ የቆሙ ኃይሎች ለአንድ ዓላማ እንዲሰለፉ ሌት ተቀን የደከማችሁትን ድካም መቼም አልዘነጋውም፡፡ በዲሲው የኮንቬንሽ ሴንተር ጉባኤ የነበረው የፍቅር ትዕይንት ከእናንተ ውጭ ሊታሰብ አይችልም ነበር፡፡ አምልጦን የነበረውን ያንን ክስተት ወደ ተገቢው ቦታ የመለሳችሁት እናንተ ናችሁ፡፡
ያንን እንደ ሐምሌ ማዕበል እየተጎማሸረ የሚመጣ ዲያስፖራ በትዕግሥትና በጥበብ፣ ሳይታክቱ በማገልገል፣ ስድቡንና ርግማኑን፣ ቁጣውንና ተቃውሞውን ችለው፣ ከላይና ከታች እንደ ገና ዳቦ እየተለበለቡ ታሪክ የሠሩት የዲሲ ኤምባሲ ዲፕሎማቶችና ሠራተኞች ናችው፡፡ በዚህ የታሪክ መለወጫ ምዕራፍ ላይ ብዙዎቹ ነገሮች ያለ እነርሱ ሊሳኩ አይችሉም ነበር፡፡ ተጨቆንን፣ ተገለልን፣ ኮታችን አነሰ፣ ለኛ ኮሙኒቲ በቂ ቦታ አልተሰጠም፣ ከሥልጣን ድልድሉ ተገቢውን ሥፍራ አላገኘንም፣ የሚለውን ፍላጎት ሁሉ ማቀራረብ እንዴት ፈታኝ ነበር?
ውቧ ከተማ ሎስ አንጀለስ፣ የጨዋዎች ሀገር፡፡ ትምህርት ለሀገር ምን ያህል እንደሚጠቅም በተግባር አሳያችሁን፡፡ ምዕራቡ አሜሪካ ለትምህርት የሚመረጠውን ያህል ለኑሮ ይቆነጥጣል፡፡ ውድ ነው፡፡ አብዛኞቹ የኮሚቴዎቻችን አባላት ዕውቀት ቀመስና ጥበብ ጠገብ በመሆናቸው ሎስ አንጀለስ ላይ ሺ ዓመት መሥራት አይከብድም፡፡ ሥራቸውን ሁሉ በሰነድ አዘጋጅተው፣ በዕቅድ ተመርተው፤ ለመግባባት ፈጥነው፤ እንዴት ያስደንቁ ነበር፡፡ ከቆንስላ ጄነራሉ ጀምሮ በየሥራው የተሰለፉት የቆንስላው ዲፕሎማቶችና ሠራተኞች  በመካከል ገጥሟቸው የነበረውን ፈተና አልፈው እንዲያ ለዘላለም ከዓይነ ኅሊና የማይጠፋውን መርሐ ግብር ሠርተዋል፡፡ እንደነ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረ ማርያምና ኤልያስ ወንድሙ(ፀሐይ አሳታሚ) ያሉ ሊቃውንት ለሎስ አንጀለስ ሞገሶቿ ነበሩ፡፡ ጥያቄን ሎስ አንጀለሶች ይጠይቁት፡፡ ቁም ነገር፣ ወደ ገደለው፣ በሰዓቱ፣ ያለ ረብሻ፡፡ በጥበቧ ከተማ ጥበብን አይተንባታል፡፡  
ሚነሶታ መጀመሪያ ስንደርስ በአሥራ አንድ ስታዲዮም የነበረው ሕዝብ ነው ብዙ ተደክሞበት ወደ አንድ ስታዲዮም የመጣው፡፡ ብዙ ያልታከሙ ቁስሎች ያሉባት ከተማ ናት ሚነሶታ፡፡ በኦሮሞ ኮሙኒቲ ስም ችግር ፈጥረው ሕዝብን ሊያቃቅሩ የነበሩትን ሰዎች ኮሚኒቲው ራሱ ታግሏቸዋል፡፡ ምንም እንኳን አልፎ አልፎ ሽቱው ውስጥ የገቡት ዝንቦች ለማበላሸት ቢሞክሩም ሁሉን አቀፍ የሆነውን ዝግጅት ለማዘጋጀት የሚቻላቸውን ሁሉ ያደረጉ፣ የሀገሪቱ አንድነት ጉዳይ የሚያስጨንቃቸው፣ ጽንፈኝነት የሚያበሳጫቸው፣ ማዶ ለማዶ መሆን የሰለቻቸው አያሌ ወገኖቻችን ነበሩ በሚነሶታ፡፡ በአንድ በኩል የቆንስላ ጽ/ቤት በቦታው አለመኖር የተቀናጀ አመራር እንዳይኖር አድርጎታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተፋጠጡ ኃይሎች መኖር ሥራውን ፈትኖታል፡፡ የሌሎች ኮሙኒቲዎች ጠንካራ አለመሆንም ሥራውን ወደ ተወሰኑ ሰዎች ትከሻ ጭኖታል፡፡ ከተንኮልና ከወረደ ሥራ ጋር በአንድ በኩል፤ ከጽፈኝነትና እኔ ብቻ ከሚለው ስሜት ጋር በሌላ በኩል ስንገዳደር ነው ሁለቱ ቀን ያለቀው፡፡
ዶክተር ዐቢይና ኦቦ ለማ መገርሳ በቆራጥነት ያስተላለፏቸው መልእክቶች ወሳኞች ነበሩ፡፡ ይህንን ዓይነት መልእክት በተለይ አዲሱ ትውልድ መስማት ነበረበት፡፡ የዚያ መድረክ አንዱ ጥቅም ይህንን መልእክት እንዳይሰማ ተጋር የነበረው ትውልድ በግላጭ መልእቱን ለማግኘት መቻሉ ነው፡፡ በሦስቱም የሚነሶታ ፕሮግራሞች ጽፈኝነት የሚያደርሰንን የመጨረሻ ገደል ለማሳየትና አንድነታችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መሪዎቹ በአጽዖት አስረድተዋል፡፡ በጎንዮሽ ውይይቶችም ይሄንኑ አስረግጠውታል፡፡
ይህ ግን የረዥሙ መጀመሪያ ነው፡፡ በተለይም ማክሰኞ በተደረገው የኦሮሞ ኮሙኒቲ ስብሰባ ላይ ዶክተር ዐቢይም ሆኑ አቶ ለማ አሰፍስፎ የነበረውን፣ ዐቅም ቢያጣም ችግር ለመፍጠር የሞከረውን አክራሪ ኃይል ተሻግረው ትውልዱን በሀገሩ አንድነት ላይ ወሳኝ ሚና እንዲጫወትና ዕድሉን አሳልፎ እንዳይሰጥ ድልድዩን ሠርተውለታል፡፡
ክርስቶስ በመስቀል ላይ በከፈለው ዋጋ ሰይጣን ነጻ አልወጣም፡፡ የብሉዩም ሆነ የሐዲሲ ሰይጣን ተመሳሳይ ነው፡፡ ሰይጣን ይዟቸው የነበሩ ሰዎች ግን ነጻ ወጥተዋል፡፡ በዚህ ጉዞ ጽፈኞች፣ አክራሪዎች፣ እኔ ከሞትኩ ባዮችና ከሕዝብ መከራ አትራፊዎች ነጻ አልወጡም፡፡ እነርሱ በነበሩበት ናቸው፡፡ እነርሱ ይዘውት የነበረው ሕዝብ ግን ነጻ ወጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ እንጀራ መግዛት ትልቅ ፖለቲካ በነበረበት አሜሪካ፣ መንግሥት በሚጠራው ስብሰባ መገኘት በደል በነበረበት አሜሪካ፣ አገር ቤት ቶሎ ቶሎ መመላለስ በሚያስጠቁርበት አሜሪካ፣ ያ ሁሉ አልፎ ሕዝብና መንግሥት በአንድ አዳራሽ ውስጥ በሰላም ሲገናኙ ማየት ‹በሕልሜ ነው በእውኔ ወይስ በቴሌቭዥን› ያሰኛል፡፡
ዕንቅልፍ አልነበረም፡፡ በቀን ከሁለት ሰዓት በላይ አልተኛንም፡፡ አንዳንዱን ሆቴል ሳንተኛበት ከፍለንበታል፡፡ ብዙ ጊዜ ቁርስና ምሳ አልፎናል፡፡ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያና የአሜሪካ አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ሌት ተቀን ተደክሟል፡፡ በሰኔ 16ቱ ክስተት የተነሣ አሜሪካኖቹ ጥበቃውንን ከፍ አድርገውታል፡፡ በዚህም የተነሣ ረጃጅም ሰልፎች ተፈጥረዋል፡፡ አንዳንድ ሰልፎችም ተቆርጠዋል፡፡ እገሌ እንዲህ ሊያደርግ ነው ተጠንቀቁ፣ እነ እገሌ እንዲህ አስበዋልና ንቁ የሚባሉ ወሬዎች አሁንም አሁንም ይመጣሉ፡፡ በተለይ ደግሞ የእሳት ማንቂያ (Fire alarm) ጥበቃ ላይ የነበረው የተሳካ ሥራ ስብሰባዎቻችንን ከዕንቅፋት የታደገ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት በሚደረጉ ስብሰባዎች የሚቃወሙ ሰዎች የእሳት ማንቂያ ያለበትን የመስተዋት ሳጥን ሰብረው ደወሉን(አላርሙን) በማስጮህ ሕዝቡ አደጋ መጣ ብሎ እንዲበተን ያደርጉ ነበር፡፡ ይህን ለመከላከል እያንዳንዱ የደወሉ ሳጥን በተመደቡ ሰዎች ትከሻ እንዲሸፈን ተደርጎ ነበር፡፡
ከ14 በላይ ሕዝባዊ መድረኮች ተከናውነዋል፡፡ ከልዩ ልዩ ታላላቅ ግለሰቦችና አካላት ጋር ከ23 በላይ የጎንዮሽ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ ‹ወዳጅህ ጠላት እንዲሆን አንድም ዕድል አትስጠው፣ ጠላትህ ግን ወዳጅህ እንዲሆን አንድ ሺ ዕድል ስጠው› የሚለውን በተግባር አይተናል፡፡ ከተጠቀምንበት አሁን አዲስ ነገር ተፈጥሯል፡፡ ተስፋ የሰነቀው የማዶው ወገን የአዎንታዊ ለውጥ አካል እንዲሆን በርትተን ከሠራን ኢትዮጵያን እናሻግራታለን፡፡ መልሰን ከተኛን ግን ከዚህ በኋላ ቀስቃሽ ማግኘታችንንም እንጃ፡፡  
   

22 comments:

 1. በእውነት ብዙ ደክማችኃል የፍቅር አምላክ ዋጋችሁን ይክፈላችሁ

  ReplyDelete
 2. ዳኒ፣ሌሎች ፁሁፎችን በጉጉት እንጠብቃለን እግዚአብሄር ዘርህን እንደምድር አሸዋ ያብዛው እረጅም እድሜን ከእንጀራ እንዲሠጥህ እመኛለሁ.

  ReplyDelete
 3. Interesting article. It was an honor to have you here in Washington DC. Thank you for your hard work. You and your team (committee) did an amazing job.

  ReplyDelete

 4. ዲያቆን ዳኒ ለሀገርህ ሥለምታበረክተው በጎ ምግባር ሁሉ እግዚአብሄር አብዝቶ ይባርክህ ብርታት እና ጥንካሬውንም ያድልክ ሥላንተ ብዙ ነገር ለማለት በ ወደድኩ እሱን ለጊዜው ላቆየውና አሁን ባለው ወቅታዊ ጉዳይ ላይ አፅንኦት ሰጥቼ የተሠማኝን አስተያየት ልሠንዝር እዚህ ላይ አንድ ሣላነሳ ማለፍ የማልችለው ጉዳይ አንድን ነገር የምታይበት አድማሥና ከትበክ ለኛ ለአንባቢያን የምታሥነብበትን መንገድ አለማድነቅ ርእሥ እንደሌለው መፀሐፍ ይሆንብኛልና አርእሥቴን አሥፍሬ ወደ ጉዳዬ፦ በመጀመሪያ በማንኛውም ሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከምትገልፃቸው መፍትሄ አዘል ሀሣቦች ባለፈ የትግበራውም አንድ አካል ሥለሆንክ የልፋትህም ፍሬ ሥለሆነ እንኩዋን ደሥ ያለክ ይበል የሚያሠኝ ነው እዚህ ላይ ግን ሁኔታዎችም ከቀድሞ በተልየ መልኩ ቀንበሩ እየከበደ እንደሚሄድ መግለፅ ኢትዮጵያን በካርታ ብቻ ለሚያውቃት ባእድ እንደማሥረዳት ይሆንብኛልና ይለፈኝ ከምክንያታዊነት ይልቅ በሥሜት የሚፈርድ ለመውደድ ብዙ ሺህ ቅድመሁኔታዎች ያሉት እና ለመጥላት ቁንፅል ነገር የሚበቃን ኩሩ ህዝብ መሀል የተፈጠርን ነንና በሀሳቡም በተግባሩም በጀመርከው መንገድ ትበረታ ዘንድ ጥንካሬውን ያብዛልህ እላለው አድናቂህ ሰለሞን ነኝ አበቃው::


  ReplyDelete
 5. ጽሑፉ ለዝግጅቱ የተደከመዉን ድካም በመጠኑ አሳይቶናል ከዚህ በላይምጠብቅብህክሥተቱእግግዚአብሔርበኢትዮጵያ ያለውንግፋናየህዝቡንለቅሶእደራሔልእንባበመቀበልየሀገራችንትንሳኤ የሚያሳይበት ሰለሆነ ይኸን የአምላክ በረከት እዳናጣው በሒደቱ ከሀገር ውሥጥ እስከ ውጭ ድረስ ህዝቡ የአሳየውን መልካምና አላስፈለጊ ምግባሮች በአጠቃላይ ወደፊት ከሚጠበቅብንም አንጻር ልዩ ታሪክ ነውና ለሁሉም በሚመጥን በመጸሐፍ ብታዘጋጀው

  ReplyDelete
 6. Another beautiful master piece by the one and the only Deacon Daniel to all "እንደ ሐምሌ ማዕበል እየተጎማሸረ የሚመጣ ዲያስፖራ"

  ReplyDelete
 7. ‹ወዳጅህ ጠላት እንዲሆን አንድም ዕድል አትስጠው፣ ጠላትህ ግን ወዳጅህ እንዲሆን አንድ ሺ ዕድል ስጠው›...ከተጠቀምንበት አሁን አዲስ ነገር ተፈጥሯል፡፡

  ReplyDelete
 8. lega bezew endedkamacheue aytenale wanawe btkerstenachen and mhanew enantem egzabher amlak erdtocheu salam mfaterew new enge yeza sawe men betaderglat mach yrekale salamewen ymfelegaw yegzabher menfs yderabet new eng lelewem endhew eytremas menwer ner ymflegaw ahenem mechersawen ysamerlenn yethiopian mlow tensawen ysayen ydengle Maryam legewech solatachen tsemetoal egzabher amlk endeza kifat sayhewen yechen kedest ager asbatale bye asbalehew!!!

  ReplyDelete
 9. ለሁሉም ጊዜ አለው እንዲል መጽሀፍ እነሆ ስለ ሀገራችን በአንድነት የምንወያይበት ዘመን አሁን ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካዉን የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ይወዳቸዋል፡፡ ግን እርሳቸውን ስንወድና ስናደቅ ስራቸውንም ልንጋራ ይገባል፡፡ ማለትም ከ 27 ዓመት የነጻነት ትግል በተጨማሪ የሚታወቁበት አንዱ ጉዳይ ይቅርታ ማድረግን ነው፡፡ ምክንያቱም ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ እነዚያን ጨቋኝና ተንኮለኛ ነጮችን ከመበቀል ይልቅ ይቅርታ በማድረግ የሁሉም ደቡብ አፍሪካውያን አንድነት እንዲመጣ አድርገዋል፡፡
  ስለዚህ እኛም ካሁን በፊት እጅግ በጣም በመረረ ሁኔታ እንኳ የበደሉንና ያሳዘኑንም እንኳ ቢሆን አሁን ወደ መልካም መስመር እስከ መጡ ድረስ በቅን ልቡናና በፍጹም ይቅርታ ይቅር በማለት እውነተኛ የሰውን ልጅ ክብር በመረዳት፤ ልባዊ መግባባትና መከባበር ወደ አንድነት፡ በመምጣት ሁላችንም በየተሰማራንበት ሙያ ፍጹም ሰባዊ ርህራሄ የተሞላበት፤ ቅንና ፍትሃዊ አገልግሎት ልንሰጥ ይገባናል፡፡ ምክንያቱም እውነተኛ የሀገር ፍቅር የሚገለጸው በዚህ ስለሆነ፡፡
  ኢትዮጵያ ጅራት ሳይሆን የአለም ቀንድና ሻኛ ሁና ለዘላለም ትኑር፡፡

  ReplyDelete
 10. ክርስቶስ በመስቀል ላይ በከፈለው ዋጋ ሰይጣን ነጻ አልወጣም፡

  ReplyDelete
 11. ሰሞኑን የለውጥ መሪዎቻችን የአሜሪካንን ምድር ያንቀጠቀጠ ሥራ ሰርተው ዛሬ ውድ አገራቸው መጥተዋል፡፡ (ተራራውን ያንቀጠቀጠ ትውልድ የሚለውን መፅሐፍ አስታወሰኝ) ይህኛው ትውልድ ተራራን ሳይሆን ታላላቆቹን የአሜሪካ ከተሞች፣ በጦር መሣሪያ ሳይሆን በፍቅር፣ በመደመር፣ የልዩነትን ግንብ በማፍረስ ነው፡፡ ይኸኛው ትውልድ በህሊና ውስጥ ያለ ከራስ እና ከወገን ጋር ያለን የጥል ግድግዳ ያፈረሰ፣ በዘር እና በዘረኝነት ያለን የማይታይ ግንብን የደረመሰ፣ በድል ያሸበረቀ፣ የአገሪቱን ዜጎች ሕብር ቀለማት ያሳየን በብርሃን ያንቆጠቆጠ እጅግ ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡
  የይቅርታ ልብ ያለው ሕዝብ ታላቅ ነው! ትናንት የነበረውን የተበላሸ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እና ታሪካዊ ስህተቶች ምንም እንዳልተፈፀመ ማየት እና በአዲስ ልብ፣ በአዲስ ተስፋ አገርን ከመበተን ለመታደግ መተማመን ላይ መድረስ እጅግ የሚያረካ ነው፡፡ ተስፋ ባጣንበት ሰዓት በዘራችን ምክንያት ተቧድነን መደጋገፍን፣ መተጋገዝን ትተን መገዳደል የጀመርንበት ጊዜ ላይ ይህ ሁኔታ መምጣቱ ፈጣሪ እንዳሰበን ማንንም ከጥርጣሬ የሚያስገባ አይደለም፡፡
  አብያችን እና ለማችን በአሜሪካ ያደረጉትን የሠላም ፎኖት እኛ ሁላችንም እንደ አገር ልተገብረው ይገባል፡፡ ማን ከማን ተጣላ እንዳንል ያልተጣላ የለም፡፡ በእያንዳንዱ መንደር በእያንዳንዱ ቀዬ፣ በእያንዳንዱ ቤተ-እምነት በዘር በሃይማኖት ልዩነትን ፈጥረን ተማምተናል፣ በጥላቻ ዓይን ተያይተናል፣ አልፈንም ደም ተፋሰናል፡፡ ይህንን ይዘን ፈፅሞ ወደ 2011 ዘመን ማሳለፍ የለብንም፡፡ የአንድ አመት ብቻ አይደለም፡፡ የብዙ ዓመታትን ውድቀት መከራ ችግር ሰቆቃ ግድያ ሁሉ ጥለን፤ሁሉን የጥል ግድግዳ ንደን በ2011 በአዲስ ዓመት፣በአዲስ አስተሳሰብ፣ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ አዲስ ተስፋ ይዘን ብቅ ማለት አለብን፡፡
  የተሠራልንን የይቅርታ ፍኖት ልክ እንደ ቀይ ግምጃ ልንሄድበት ስለሚገባን ማናችንም በቤተ-እምነት፣ በአደባባዮች እና በተገናኘንበት ቦታ ሁሉ ይቅርታን እንዝራ! ወደ ታላቋ ኢትዮጵያ በይቅርታ ድልድይ እንሸጋገር እና እናግኛት፡፡ያች ኢትዮጵያ እንደ ቀድሞ ልማዷ ስደተኞችን የምትቀበል የራሷን ዜጎች ስደት የምታስቀር ፍፁም ሠላም የሆነች ፖለቲካዋ በዘር ማንነት ሳይሆን በፖለቲካ ብስለት የሚመራ የአፍሪካ ፈርጥ የሆነች አገር እንፍጠር!

  ReplyDelete
 12. always I read admire like and get rest by u!

  ReplyDelete
 13. God bless you deacon daniel kibret...!!!
  We miss the next chapter...!!!

  ReplyDelete
 14. God bless you, and your family again,and again, forever. I saw and heard your ideas, writings being implemented throughout this event. I am glad that our new government officials are listening, and as a matter of fact have been listening. I hope that God will bless you with health, long life, strength,
  and wisdom so you and others like you will continue to be the voice of our kindhearted people.

  ReplyDelete
 15. Akerarebbu Betam Dess YElal Dani Bertalen Endate Ayenet Sewoch Lehagerachin Betam Tekami Nachew Beyaskew Ketlehe Bertithe Abertan

  ReplyDelete
 16. dani, eyitawocheh yeteshale sew endhon redtewugnal betam amesegnalehu

  ReplyDelete
 17. አንተ ሰው መቼም እማታውቀው የለም ለሁሉ ፊት ነህ በዚያው ሰዓት ኋላም ነህ ።እኔም ሁሌ ስህተትህን እናገራለሁ።
  አ ት ነ ፋ ማ . አ ት መ ቸ ኝ ማ።
  ...ነገር ግን በትህትና ወይስ በቁጣ ልምጣብህ???
  (ዳኒ ዘወልደ አራዳ ነጎድጓድ)ያንቺም ዲሞክራሲ ይታያ... እእእ

  ?(ከ14 በላይ ሕዝባዊ መድረኮች ተከናውነዋል?

  ?(ከልዩ ልዩ ታላላቅ ግለሰቦችና አካላት ጋር ከ23 በላይ የጎንዮሽ ውይይቶች ተካሂደዋል)?
  ተከወኑ ተካሄዱ የሚለው ይቅር ብልህ እንኳ የሕዝቡን ትናንሽ እና ግለሰቦች ታላላቅ ያልከው ምን ለማለት ብለህ ነው ???

  ReplyDelete
 18. Thank you for Sharing the details!
  God Bless you!!

  ReplyDelete
 19. The legend !!! Long live Deacon Daniel Kibret.

  ReplyDelete
 20. ለሀገር አንድነት መስዋዕትነትን መክፈል ዋጋዉ እጅግ የላቀ ነዉ፡፡ ትዉልዱ በታሪክ ስዘክረዉ ይኖራልና፡፡ዲ/ን ዳንኤል ክብረት እግዝአብሔር አንተን ረዥም እድሜ ሰጥቶ ይጠብቅልን

  ReplyDelete