Thursday, June 7, 2018

አንድ መዝገብ ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ

የደጃዝማች ገርማሜ የሕይወት ታሪክ
ተጻፈ  ከቀኛዝማች ኃይሌ ዘለቃ
1937 ዓ.ም
1.     ባለ ታሪኩ
ይህ ቀጥሎ የቀረበው በእጅ የተጻፈ ታሪካዊ መዝገብ የዐፄ ምኒልክን መንግሥት በሸዋዎች ብርታት(በአማራና በኦሮሞ መኳንንት) ስላቆሙት ስለ ደጃዝማች ገርማሜ ወልደ ሐዋርያት የተጻፈ ነው፡፡ በ1799 ዓ.ም. የተወለዱት ደጃዝማች ገርማሜ ከአቤቶ ኃይለ መለኮት እስከ ዳግማዊ ምኒልክ ድረስ የኢትዮጵያን መንግሥት ያገለገሉ ባለሟል ናቸው፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ሸዋ ዘምተው ምኒልክን ሲይዙ ግርማሜ በቤተ መንግሥት ነበሩ፡፡ በኋላም ዐፄ ምኒልክ ከቴዎድሮስ ጋር ወደ ጎንደር ሲሄዱ እርሳቸው ተጉለት ቀሩ፡፡ አስቀድመው ግን ምኒሊክን የሚያስመልጡበትን መንገድ ተናግረው ነበር፡፡ የሸዋ መኳንንት አልሰሟቸውም እንጂ፡፡ የተናገሩት ደርሶ ምኒልክ በቴዎድሮስ እጅ ገቡ፡፡ ገርማሜ የመከረው ምክር ጠብ አይልም የተባለው ከዚህ በኋላ ነው፡፡  
ገርማሜ ሱባኤ ገብተው ሕልም ሲያዩ ተነሥተው ጎንደር ገቡና ከዐፄ ቴዎድሮስ ተገናኙ፡፡ እዚያም ከምኒልክ ጋር ተቀመጡ፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ በተወሰኑ ጊዜ ምኒልክ ያመለጡበትን ዘዴ የቀየሱት ገርማሜ ናቸው፡፡ በኋላም በወርቂት እጅ ሲገቡ አታለው ያወጡበትን ብልሃት ያመጡት እርሳቸው ናቸው፡፡ የዐፄ ምኒልክን አልጋ ሸዋ ላይ የተከሉት፤ መንግሥቱን ያደላደሉት፤ ባለሟሎቹን ያስተካከሉት ገርማሜ ነበሩ፡፡ 

ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ መሠረት ከሆኑት አንዱን ራስ ጎበናን ወደ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ያመጡትና ዐፄ ምኒልክ ከኦሮሞ መኳንንት ጋር ኅብረት ከሌላቸው መንግሥታቸው እንደማይጸና የተናገት ገርማሜ ነበሩ፡፡ በቤተ መንግሥቱ አካባቢ የሚነገረውን የኦሮምኛ ቋንቋ የሚያውቅ ሰው የግድ ካልተሾመ ነገሩ እንደሚበላሽ ቀድመው ዐውቀውታል፡፡
ዐፄ ዮሐንስ ወደ ሸዋ ሲመጡ፣ ዐፄ ምኒልክ በደርቡሽ ምክንያት ወደ ጎንደር ሲዘምቱ ገርማሜ በምክርም በሐሳብም ነበሩበት፡፡ ጮሬ በተባለ ቦታ ቀጨማ ላይ የቅዱስ ላሊበላን ታቦት እንዲተክሉ ያደረጋቸውም ይሄው የጎንደር ዘመቻ ነው፡፡ በ91 ዓመታቸው ሐምሌ 23 1890 ዓም ቀን ዐርፈው በተከሉት ደብር በቀጨማ ላሊበላ ተቀበሩ፡፡ የእርሳቸው ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ በኋላ የነበረውን የኢትዮጵያ መንግሥት ታሪክ፣ የቤተ መንግሥቱን ሁኔታና አጠቃላይ ሕይወት ያስቃኘናል፡፡  
ጸሐፊው
 ቀኛዝማች ኃይሌ ዘለቃ በእናታቸው ስም ነው የሚጠሩት፡፡ አባታቸው ሀብተ ሥላሴ ይባላሉ፡፡ እናታቸው የደጃዝማች ገርማሜ ልጅ ወ/ሮ ዘለቃ ናቸው፡፡ የተወለዱት ሚያዝያ 7 ቀን 1869 ዓ.ም. መሆኑን ያገኘነው መዝገብ ይገልጣል፡፡ ከዐፄ ምኒልክ ጋር ያገናኟቸው አያታቸው ደጃዝማች ገርማሜ ናቸው፡፡ የ22 ዓመት ልጅ ሆነው በወላይታ ዘመቻ፣ የ23 ዓመት ልጅ ሆነው ደግሞ በአድዋ ዘመቻ ተሳትፈዋል፡፡ ብዙ ጊዜ የሠሩት በወኅኒ አዛዥነት ነበር፡፡ ከርስታቸው በሚያገኙት እየተጠቀሙ፣ ድኻ እየረዱ የሚኖሩ ሰው መሆናቸውን መርሥኤ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ይነግሩናል፡፡ በ1928 ዓ.ም. ጣልያን ሲገባ ወደ ሞቃድሾ ተወስደው ሁለት ዓመት ታሥረዋል፡፡
‹መጻሕፍትን መመርመር፣ ዕውቀት የሚገኝበትንም መከታተል ይወዱ ነበር፡፡ ያመኑበትንም በግልጽና በድፍረት መናገር አይቸግራቸውም› ይሏቸዋል መርሥኤ ኀዘን፡፡ በሕይወታቸው መጨረሻ ስለ ተዝካር ባሰፈሩት ኑዛዜ ላይ ‹ከሞትኩ በኋላ እንኳን የሚጠቅመኝ የሚጎዳኝም ነገር የለም› ማለታቸውን ስናይ ከዘመኑ ሰዎች ያፈነገጡ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡
ይህንን አሁን የምናነበውን ታሪክ ጽፈው በ1937 ዓ.ም. ለብላታ መርሥኤ ኀዘን ስለሰጧቸው እኛም ልናገኘው ቻልን፡፡ ያረፉት ጥር 24 ቀን 1954 ዓ.ም. ሲሆን የተቀበሩትም በአያታቸው መቃብር በቀጨማ ቅዱስ ላሊበላ ነው፡፡
ይህንን ታሪክ ለእኔ የሰጠኝ ደግሞ የልጅ ልጃቸው ኃይሌ ግርማ ነው፡፡ ጽሑፉ የተጻፈው የዛሬ 73 ዓመት ነው፡፡ የተጻፈበትም ቋንቋ በዚያው ዘመን ቋንቋ በመሆኑ አሁን የማንጠቀምባቸውን ቃላትና የማኅበረሰብ መጠሪያ ስሞችን ይዟል፡፡ ይህም የነበረውን እንዳለ ለተመራማሪ ከማስቀመጥ አንጻር እንጂ የዚህን ጸሐፊ ሐሳብና አቋም አይወክልም፡፡
መልካም ንባብ፡፡ 

4 comments:

  1. ሸጋ ደስ ይላል በርታ

    ReplyDelete
  2. GOOD INTERESTING WORK KEEP IT UP

    ReplyDelete
  3. Dani yewenet betam telek sew neh sehufochik beyam arif nachew fetari yevarkh hiywetan ebdlewet adrghgnal ye ethiopia amlk kante gar yehun abatachin

    ReplyDelete