Tuesday, June 5, 2018

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወንበሮች


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጠዋት ወደ ቢሯቸው ማልደው ሲገቡ የእንግዳ መቀበያ ክፍሉ ወንበሮች ተሰልፈው ጠበቋቸው፡፡ ነገሩ እንግዳ ሆነባቸው፡፡ የዚህን ቤተ መንግሥት ባሕል ገና አልለመዱትም፡፡ የተለመዱ ችግሮችን ባልተለመደ መንገድ እፈታለሁ ብለው ለተነሡት ጠቅላይ ሚኒስትር ነገሩ ከተለመደውም የወጣ መሰላቸው፡፡
‹ምንድን ነው?› አሉ ሳቅ ይዟቸው፡፡
‹አሰናብቱን› አለ ደንዳሳ ትከሻ ያለው የቆዳ ወንበር፡፡በታሪኩ ለመንግሥት ቅርብ የሆኑ እንግዶችን በማስተናገድ ይታወቃል፡፡
‹ለምን? የት?› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ
‹በቃ እኛንም ጡረታ ያውጡና› አለ ሌላ እምቡር እምቡር የሚል ወንበር፤ የባለሥልጣን መቀመጫ መሆኑን የሥላሴን ዙፋን ከተሸከሙት ኪሩቤል በላይ ይኮራበታል፡፡ ‹እንትናኮ እኔ ላይ ነው የሚቀመጠው› እያለ መጎረር ይወዳል፡፡
‹ምን ሆናችሁ› አሏቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እጃቸውን አገጫቸው ላይ አድርገው፡፡
‹እኛ ከመጀመሪያው ስንገዛ ለዚህ ዓይነት ነገር መሆኑን የነገረን የለም፡፡ አሁን እየተሠራ ያለው ከለመድነው ውጭ ነው፡፡ ከተገዛንበት ዓላማ ውጭ ነው፡፡ የመርሕ መደባለቅ እያየን ነው› አለ ባለ ደንዳሳ ትከሻው ወንበር፡፡
‹ለምን ዓላማ ነበር የተገዛችሁት?› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልሰሙት የቤተ መንግሥት ምሥጢር መኖሩን እየጠረጠሩ፡፡

‹እኛኮ እዚህ ቦታ ብዙ ጊዜ ኖረናል› አለቺ አንዲት ቆንጠር ቆንጠር የምትል ድፉጭፉጭ ወንበር፡፡ ‹እዚህ ስንኖር እነማን ይታሠሩ፣ ይባረሩ፣ አገር ጥለው ይጥፉ፤ ምን ዓይነት አሣሪና ጨምዳጅ ሕግ ይውጣ፣ እነማን ይመቱ፣ እነማን ይገለሉ፣ እነማን ይታገዱ፣ እነማን ይወገዱ፣ እነማን ይውደሙ፣ እነማን ይጋደሙ የሚል ነገር ነው ስንሰማ የኖርነው፡፡ እኛ የተገዛነው ይሄን የመሰለ ምክር ሊመከርብን ነው፡፡ እኛ እዚህ ቢሮ ስንኖር የተቀመጡብን ሰዎች በጣም የተከበሩ ናቸው፡፡ እዚህ እኛ ላይ በተመከረ ምክር ስንት አገር ተተራምሷል፤ ስንቱ ታሥሯል፣ ስንቱ ተገድሏል፤ ስንቱ ቀምሷል፣ ስንቱ ነፍዟል፡፡ አሁን የምንሰማው ነገር ግን የሚያዛልቀን አይደለም› አለቺ መሬቱን በስፒል እግሯ እየፈተገች፡፡
‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን እርስዎ የሚናገሩት ቋንቋ እኛን ሊገባን አልቻለም፤ ለዚህ ቢሮ አዲስ ቋንቋ ነው፡፡ ለኛም ለወንበሮቹ አዲስ ልሳን ነው፡፡ ስናየው በልሳን እየተናገሩ ይመስለናል› አለ፤ ሁለት ሰው እንዲይዝ ሆኖ የተሠራው አጭሬ ወንበር፡፡
‹እንዴት ነው ቋንቋዬ የማይገባችሁ፡፡ የማወራው አማርኛ ነው፤ ትግርኛ ነው፤ ኦሮምኛ ነው፤ እንዴት ነው ቋንቋዬ የማይገባችሁ?› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ ወደ ውስጠኛው ቢሮ መግባቱን ተዉትና በሩ ላይ ቆሙ፡፡ የጽ/ቤት ኃላፊያቸውና አጃቢዎቻቸው በአግራሞት የሚሆነውን ሁሉ ይከታተላሉ፡፡
‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር› አለ ባለ ደንደሱ ትከሻ፡፡ ‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ይሄ የምናውቀው ቋንቋ አይደለም፡፡ በእርስዎ ደረጃ ሰምተንም አናውቅም፡፡ ምናልባት ዶክተር ሲባሉ ሰምተናልና ከውጭ ተምረውት ያመጡት ይመስለናል፡፡ እዚህ ሀገር እዚህ ቢሮ በዚህ ቋንቋ ሲወራ ሰምተን አናውቅም፡፡ ጭራሽ ማሠር እንጂ መፍታት የሚባል በዚህ ቢሮ መዝገበ ቃላት ውስጥ የለም፡፡ ውጡ እንጂ ግቡ የሚል ቃል አዲስ ነው ያመጡብን፡፡ ተለያዩ መባል ሲገባው ታረቁ፣ ተስማሙ፣ አንድ ሁኑ የሚባል መጋኛ እየመጣብን ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ በአማርኛ፣ በትግርኛና በኦሮምኛ ካሉ ለምን እስከዛሬ እዚህ ቢሮ ውስጥ አልሰማናቸውም?› ባለ ደንደሱ ትከሻ የአንገት መደገፊያውን በኀዘን ነቀነቀው፡፡
‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር› አለ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መቀመጫነት የተዘጋጀው ወንበር፡፡
‹ጭራሽ አሁን ስንሰማማ በሽብር የተከሰሰን ሰው፣ ሞት የተፈረደበትን ሰው መፍታት ሳያንስዎት እዚህ ጠርተው እጁን ሊጨብጡት፤ እኛ ላይ አስቀምጠው ሊያናግሩት ነው አሉ? ይኼንን ከምናይ ምነው ድሮ ተቀዳደን በወደቅን ወይም በሐራጅ በተሸጥን? እና ይሄ ሰውዬ መጥቶ የት ሊቀመጥ ነው? ከኛ ማናችንም ብንሆን እንዲቀመጥብን አንፈቅድም፡፡ ለእርስዎም ለስምዎ ጥሩ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትርኮ እቆርጣለሁ፣ እፈልጣለሁ፣ አሥራለሁ፣ እቀፈድዳለሁ፣ ሲል ነው የሚያምርበት፡፡
‹እና እንዋጋለን፣ እንሸፍታለን፣ መንግሥት እንገለብጣለን፣ ሲሉ የኖሩት ሁሉ ብረታቸውን እያስቀመጡ እየመጡ ሊቀመጡብን ነው? ትናንትና እኛ ላይ ቁጭ ባሉት ባለ ሥልጣናት አሸባሪ፣ አደናባሪ፣ አቀናባሪ፣ ሲባሉ እንዳልነበር ዛሬ ዘመን ተቀየረ ብለው መጥተው ሊቀመጡብን?› ሞት ይሻለናል› አለ ሁለት ሰው የሚይዘው አጭሬ ወንበር፡፡
‹ክብራችን ተነክቷል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር› አለቺ ድፉጭፉጯ ወንበር፡፡ ‹ጭራሽኮ አሁንማ ቤተ መንግሥቱን ሰው መጎብኘት አለበት እያሉ ነው፡፡ ታድያ በኛና በሰፊው ወንበር መካከል ምን ልዩነት አለው? የቤተ መንግሥት ወንበር በመሆንና የቤት ወንበር በመሆን መካከል ምን ልዩነት ሊኖር ነው? መከበራችን፣ መታፈራችን፣ መፈራታችን፣ ሊቀርኮ ነው፡፡ ተራውን ሕዝብ ሁሉ ቤተ መንግሥት ጠርተው መጋበዝዎት ሳያንስ ጭራሽ የቤተ መንግሥቱን ቆሌ ገፍፈው ሊያስጎበኙት? እና የየሠፈሩን ሰዎች እዚህ ግቢ ውስጥ በመስኮት ልናያቸው? ሞተናላ!›
‹ሲደበደብ ከኖረ ቆዳ የተሠራ ከበሮ ዜማው ሁሉ በለው በለው ይመስለዋል› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
‹አባቶቻችን ድንበር ሲያስከብሩ ኖሩ፤ እርስዎ ግን ድንበሩን ሁሉ ናዱት› አለ ዝም ብሎ ሲመለከት የነበረ በአገልግሎት ብዛት አርጅቶ አናቱ የተላጠ ወንበር› ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውስጥ የሚሰሙትን የስልክ ጥሪ የጽ/ቤት ኃላፊያቸው እንዲያነሣ አዝዘው ማዳመጥ ቀጠሉ፡፡
የቱን ድንበር ነው የናድኩት?› አሉት ፈገግ ብለው በትዕግሥት ቆመው፡፡
‹በተቃዋሚና በደጋፊ፣ በገዥና በተገዥ፣ በውጭና በውስጥ መካከል የጸናውን ድንበር ናዱትኮ፡፡ እግዜር ያሳይዎና ኢቲቪና ኢሳት አንድ ዓይነት ዜና እንዲያቀርቡ አደረጓቸውኮ፡፡ አሁን ጭራሽ ውጭ ሊሄዱ ነው አሉ፡፡ ዕንቁላል መወርወሩ ቀርቶ የዕንቁላል ሳንዱች ሊቀርብልዎት ነው አሉ? ከዚህ በላይ ድንበር መናድ የት አለ?› የተላጠ አናቱን አነቃነቀ፡፡
‹እናም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ያሰናብቱን፤ አመለካከታችንን ከምንለውጥ ጾታችንን ብንለውጥ ይሻለናል፡፡ ዐርባ ዓመት ያልሰማነውን ቋንቋ ከምንሰማ - ጡረታ ወጥታችኋል የሚለውን ብንሰማ ይሻለናል፡፡ አዲሱን ወይን ጠጅ በአሮጌው አቁማዳ ማስቀመጥ አቁማዳውንም መቅደድ ወይኑንም ማፍሰስ ነው፡፡›
ባለ ደንደሱ ትከሻ ወንበር ወደ ውጭ ሲወጣ ሌሎችም ተከትለውት ወጡ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ብዕሮችና ወረቀቶች ግን ጤና አልተሰማቸውም፡፡ ‹እነዚህ ወንበሮች እውን በጤናቸው ነው ቢሮውን ለቅቀው የወጡት? ወይስ በበር ወጥተው በመስኮት ሊመለሱ ነው?› አለ አንዱ እስክርቢቶ፡፡
‹ያኔም አመጣጣቸው ግራ እንዳጋባን ዛሬም አካሄዳቸው ግራ ሊያጋባን ነው መሰል› አለና ሌላኛው እስክርቢቶ መለሰለት፡፡ 

29 comments:

 1. ‹ያኔም አመጣጣቸው ግራ እንዳጋባን ዛሬም አካሄዳቸው ግራ ሊያጋባን ነው መሰል›

  ReplyDelete
 2. ‹ያኔም አመጣጣቸው ግራ እንዳጋባን ዛሬም አካሄዳቸው ግራ ሊያጋባን ነው መሰል›

  ReplyDelete
 3. ጠቅላይ ሚንስትሩ የጀመሩት ይበል የሚያሰኝ ነው ግና ይኽ ነገር እርሳቸው ጋር ብቻ እንዳይኾን እኛም እንነሣ የይቅርታ ዘመን
  ይቅር እንባባል!

  ReplyDelete
 4. አረ ይቀየሩ በአዲስም ይተኩ፡ አስተሳሰባቸው የተጨቆነ ቢሆንም፡ ጥያቄአቸው ትክክል ነው ስለዚህ ይህ የተጨቆነ ( የተጎዳ) አስተሳሰባቸውን እንዲያሻሽሉ የማገገሚያ ሥፍራ ይፈለግላቸውና ይቀመጡ፡፡ በዚህም ማዕከል ባለፉት 27 ዓመት የኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ ተንሰራፍተው ሲሰሩ የነበረውን ከፋይል በማውጣት እያዩ ኢንጆይ ያድርጉ፡፡ አለበለዚያ ይህ አዲሱ ቋንቋ ስለማይገባቸው በአእምሮ በሽታ እየተለከፉና በዚህ እድሜአቸው ከሰውነት ውጪ ሆነው እንዳያልፉ ቢያንስ አወጣጠቸውን በሰላም እንዲሆን እናግዛቸው፡፡ እምዬ ኢትዮጵያን ይመቻት እንጂ ለማንስ ቢሆን ምን የማትሆነው ነገር አለ፡ አሁን እነኳን ተስፋዋም ለምልሞላታል፣ ደስታዋም በደጇ አለ፡፡ እግዚአብሄር ሰምቷታልና ሕዝብን ልትመሩ የተመረጣችሁ እናንተ የዘመኑ የእምዬ ኢትዮጵያ የበኩር ልጆች ከእነዚህ ሊያልፉ ካሉ ብኩኖች፣አባካኞች ፣አመንዝራዎች ፣ እብሪተኞች ወዘተ ተማሩ፡፡ መለካምን በመሥራት እንደነ አጼ ታድሮስ፣ምኒሊክ….. መለካም ሥራችሁ ከትውልድ እስከ ትውልድ እንዲያስተገባ ትጉ፣ እምዬ ኢትዮጵያ ቅን መሪ እንጂ ቅን መሳይ መሪ አይመጥናትም የምታመልከው አምለኳ የቅኖች አምላክ ስለሆነ፡፡ ደህና ሁኚ ህውሃት/ ደኅና ሁኚ አረጌ ወንበር እዳሰበሽው በቀርሽ ደስተኛ ሆነሽ እንድትኖሪ አሁን ባሰበሽው መንገድ ውልቅ ብለሽ ውጭና ቦታውን ለአዲሶቹ ወንበር ልቀቂ፡፡ መልካሙን ሁሉ እመኝልሸለሁ፡፡

  ReplyDelete
 5. ዳኒ የዘወትር የተለየ እይታህ ድንቅ ነው

  ReplyDelete
 6. ewnet alk lega mech yayeten new arba amet melew sekametew yneberet seserew yeyeten new ytenagarewet egzabher ylamhen aheya yanagare geta weneberewem menager men yesanewel gana bezew ensamalen mengad terag egzabher ylakalen ymeslezal yethiopian tensay bekereb kean yasayanal by tesfa adergalh egzabher amlak eythen ybzaleh!amen!!

  ReplyDelete
 7. እውነትም ሙሐዘ ጥበባት እግዚአብሔር ከጥበብ ላይ ጥበብ ይጨምርልህ

  ReplyDelete
 8. Very interesting and educational.

  I wonder how those "chairs" would change their perception.

  ReplyDelete
 9. ቦ ጊዜ ለኩሉ ... ተመስገን የዶ/ሩ ጥረት ፍሬ ሊያፈራ ይመስላል እኔ በእነዚህ ወንበሮች እጅጉን ተገርሜአለሁ እራስን ማወቅ የመሰለ ጥበብ ከወዴት ይመጣል እንዲህ እራሳቸውን ተረድተውት በለውጡ ንፋስ ከመታመስ ለውጡን የሚረዳ መቀመጫ በቦታቸው እንዲተካ እራሳቸውን ለማግለል ያድረጉት ክርክር ደስስስ ይላል ፤ ዛሬ ሀገራችን በአዲስ የለውጥ ማዕበል ውስጥ እየተጥለቀለቀች ነውና ለውጡ ነውጥ የመሰላቸውና ፍርሃት የለቀቀባቸው የቤተ-መንግስት ወንበሮችና ደንገጡሮች ወጥተው ውጭውንም ውስጣችንንም ምን ያህል በደስታ እንደተሞላ ይዩት !! ብዕሮቻችንና ነጫጭ ወረቀቶቻችን ሆይ የተጻፈበት ወረቀት ላይ መጻፍ ውጤቱ ስርዝ ድልዝ መሆን እንጂ ለንባብ አይበቃምና ቀድሞ የነበራቸውን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ፎርማት ካላደረጉ ይውጡ መመለሻቸው አያሳስባችሁ ፡፡
  ዳኒ እግዚአብሔር ይስጥህ!

  ReplyDelete
 10. ‹ሲደበደብ ከኖረ ቆዳ የተሠራ ከበሮ ዜማው ሁሉ በለው በለው ይመስለዋል› Thank you profusely Dani!!!

  ReplyDelete
 11. ዕድሜና ጤና ይስጥልን!!!

  ReplyDelete
 12. አዲሱን ወይን ጠጅ በአሮጌው አቁማዳ ማስቀመጥ አቁማዳውንም መቅደድ ወይኑንም ማፍሰስ ነው፡፡› Thank you dn.dani.MAY GOD BLESS YOU!

  ReplyDelete
 13. ጠ/ሚ አብይ እያደረጉ ላሉት ለውጥ እያመሰገንን እና በለውጡ እንዲቀጥሉ እያበረታታን፤፤ ቤተክርስቲያን የተወረሱባትን ሁሉም ሕንፃዎችና ንብረቶች እንዲመልሱላት በፍቅርና በትህትና ልንጠይቅ ይገባል፤፤ ከሚገኘውም ገቢ ቤተክርስቲያን ህፃናት ማስደጊዎች፤ ትምህርት ቤቶች፤ ሆስፒታሎች፤ ክልኒኮች፤የእካልና የአቅም ውስንነት ያለባቸውን ወገኖች መገንቢያ ለታውለው ይገባል፤፤

  ሌቦችና ዘረኞችም ከቤትክርስትያ መስተዳድር ወስጥ እንዲወጡ ግፍት ልናደርግ ይገባል፤፤


  ReplyDelete
 14. እግዚአብሔር ይባርክህ ዳኒ፡፡ ከቤተ መንግሥት የሚወጡት ወንበሮች ወዴት እንደሄዱ ተከታትለህ ንገረን ሙሐዘ ጥበባት፡፡ እኔ ግን ወደ ቤተ ክህነት ብትሄድ የምታገኛቸው ይመስለኛል፡፡

  ReplyDelete
 15. እርግጠኛ ነኝ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ ይህንን አንብቦ ወደ ቢሮ ሲገባ ቆም ብሎ ያሉትን ወንበሮች ያያቸዋል ያረጁም ካሉ ይቀይራቸዋል

  ReplyDelete
 16. i have never thought a change like this with out blood...‹ያኔም አመጣጣቸው ግራ እንዳጋባን ዛሬም አካሄዳቸው ግራ ሊያጋባን ነው መሰል›

  ReplyDelete
 17. GREAT WORK AND TRUTH THANKS GOD BLESS YOU DIAKON

  ReplyDelete
 18. ሠላም ወንድሜ ዳኒ ጊዜ ለኩሉ የሚባለው ይሄኔ ነው ወንበሮቹኮ አፍ አውጥተው ምርጫቸውን ተናገሩ ምን እየተካሄደ እንደሆነ እንኳን የማያውቁ በየሚንስትር መስራቤቱ የተቀመጡ እንደ ኢቲቪ ምርጫቸውን ያላስተካከሉ አሉ እነሱንም አንድ በልልን አይነቁም ግን መቼስ ወገን አይደሉ ደውሉን ታጫንላቸው ዞሮ ዛሮ ኢትዮጵያዊ መባላቸው አይቀርም አመሰግናለሁ ፡፡

  ReplyDelete
 19. really it is amazing God bless you D/N Daniel

  ReplyDelete
 20. ‹ያኔም አመጣጣቸው ግራ እንዳጋባን ዛሬም አካሄዳቸው ግራ ሊያጋባን ነው መሰል›

  ReplyDelete
 21. ‹ያኔም አመጣጣቸው ግራ እንዳጋባን ዛሬም አካሄዳቸው ግራ ሊያጋባን ነው መሰል›

  ReplyDelete
 22. Simply Brilliant !!
  "Comedy is the funny way of being very serious"
  I also enjoyed Alemneh "Awaze" siyanebew !

  ReplyDelete
 23. ትወናው በድምብ እንደምትችልበት ጥርጥር የለም።
  ደበትራ ኣይድል! ተረት ተረት በመማር ያደገ!!!!

  ኣንድ እውነት ግን ኣለ። እግዚኣብሔር ኣያዳላም፣ ማነው ስለ ፍቅር ዘማሪው፣ ማነው ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪው ሁሉም ያውቀዋል። በግዜው ደግሞ መውጣቱ ኣይቀርም።

  ReplyDelete
 24. God bless you Deacon daniel kibret...!!!

  ReplyDelete
 25. Yesilasen Zufan(Kirubeln) ezih tsihuf wust lenitsitser masgebat tinish aykebdem Dani...

  ReplyDelete
 26. በጣም እሚገርም ጽሁፍ

  ReplyDelete