የደጃዝማች ገርማሜ የሕይወት ታሪክ
ተጻፈ ከቀኛዝማች ኃይሌ ዘለቃ
1937 ዓ.ም
1. ባለ ታሪኩ
ይህ ቀጥሎ የቀረበው በእጅ የተጻፈ ታሪካዊ መዝገብ የዐፄ ምኒልክን መንግሥት በሸዋዎች
ብርታት(በአማራና በኦሮሞ መኳንንት) ስላቆሙት ስለ ደጃዝማች ገርማሜ ወልደ ሐዋርያት የተጻፈ ነው፡፡ በ1799 ዓ.ም. የተወለዱት
ደጃዝማች ገርማሜ ከአቤቶ ኃይለ መለኮት እስከ ዳግማዊ ምኒልክ ድረስ የኢትዮጵያን መንግሥት ያገለገሉ ባለሟል ናቸው፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ
ሸዋ ዘምተው ምኒልክን ሲይዙ ግርማሜ በቤተ መንግሥት ነበሩ፡፡ በኋላም ዐፄ ምኒልክ ከቴዎድሮስ ጋር ወደ ጎንደር ሲሄዱ እርሳቸው
ተጉለት ቀሩ፡፡ አስቀድመው ግን ምኒሊክን የሚያስመልጡበትን መንገድ ተናግረው ነበር፡፡ የሸዋ መኳንንት አልሰሟቸውም እንጂ፡፡ የተናገሩት
ደርሶ ምኒልክ በቴዎድሮስ እጅ ገቡ፡፡ ገርማሜ የመከረው ምክር ጠብ አይልም የተባለው ከዚህ በኋላ ነው፡፡
ገርማሜ ሱባኤ ገብተው ሕልም ሲያዩ ተነሥተው ጎንደር ገቡና ከዐፄ ቴዎድሮስ ተገናኙ፡፡
እዚያም ከምኒልክ ጋር ተቀመጡ፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ በተወሰኑ ጊዜ ምኒልክ ያመለጡበትን ዘዴ የቀየሱት ገርማሜ ናቸው፡፡
በኋላም በወርቂት እጅ ሲገቡ አታለው ያወጡበትን ብልሃት ያመጡት እርሳቸው ናቸው፡፡ የዐፄ ምኒልክን አልጋ ሸዋ ላይ የተከሉት፤ መንግሥቱን
ያደላደሉት፤ ባለሟሎቹን ያስተካከሉት ገርማሜ ነበሩ፡፡