Monday, May 7, 2018

ዳጋ እስጢፋኖስ - የመነነው ገዳም (ክፍል ሁለትና የመጨረሻው)

ዳጋ፣- የጣና ሞገስ

ዳጋ እስጢፋኖስ የኢትዮጵያ ታሪክ ማዕከል ነው፡፡ ከመካከለኛው ዘመን መጀመሪያ አንሥቶ ነገሥታቱ፣ መኳንንቱ፣ ጳጳሳቱና ምእመናኑ የሀገሪቱ ታሪክ ባለ አደራ አድርገውታል፡፡ የመስቀሉን ክፋይ ጨምሮ አያሌ ንዋየተ ቅድሳትን፣ የነገሥታት የወግ ዕቃዎችን፣ ካባዎችንና አክሊሎችን ዳጋ በክብር ጠብቆልናል፡፡ በሀገሪቱ የደረሱ የእርስ በርስ ጦርነቶችና ወረራዎች ወደ ገዳሙ ባለመዝለቃቸው ከ800 ዓመታት በላይ የተጠበቁ ቅርሶችን ዳጋ አቅፎ ይዟል፡፡ ከተገነባ ከ300 ዓመት በላይ የሆነው ሙዝየሙ በእነዚህ ቅርሶች ተጣብቧል፡፡ መጽሐፍ በመጽሐፍ ላይ፣ ዕቃ በዕቃ ላይ ተነባብሯል፡፡ ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ቅርስና ባህል ወዳጆችና አክባሪዎች እንደ አህያ ጆሮ እንደ ጦር ጉሮሮ አንድ ሆነን ልንነሣ የሚገባበት ደረጃ ላይ ነው፡፡ ዕቃ ቤቱ ዘመኑን ጨርሶ በአንድ በኩል ተሰንጥቋል በሌላ በኩል እየተናደ ነው፡፡ በዚህ የተቀደሰ ተራራ ላይ ገዳሙን፣ መንፈሳዊነቱን፣ ታሪኩንና ቅርሱን የሚመጥን ሙዝየም መሥራት አለብን፡፡ ያ ካልሆነ ታሪካችንን ተረት ከመሆን አንታደገውም፡፡

የዳጋ ጥንታውያን ቅርሶች

ዳጋ፣ ዝምተኛ ገዳም ነው፡፡ እንደ ሌሎቹ ገዳማት ምእመናን ሆ እያሉ ለንግሥ እንዲመጡለት የሚቀሰቅስ ገዳም አይደለም፡፡ ጸጥታውንና ርጋታውን ይፈልገዋል፡፡ ከካህናቱ ጸሎት፣ ከአዕዋፉ ዝማሬ፣ ከጣና ውኃ ግምሻሬ ያለፈ ድምጽ አይፈልግም፡፡ ሰው ለጸሎት እንጂ ለሆታ፣ ለሱባኤ እንጂ ለእልልታ እንዲሄድ አይሻም፡፡ የውጭ ቱሪስቶች ከሚገረሙባቸው ነገሮች አንዱ መንፈስን የሚያድስ ልዩ ኃይል የተሰጠው ገዳም መሆኑ ነው፡፡ የገዳሙን ቤተ ክርስቲያን ግንባታ ለመከታተል የመጡት ባለሞያዎች ‹ጂፒኤስ አልሠራ ብሎናል፤ በተራራው ጫፍ ላይ ስንወጣ የጂፒኤስ መሣሪያው መሥራት ያቆማል፡፡ በድሮን አካባቢውን ለመቅረጽ ያደረግነው ሙከራም አልተሳካም፡፡ ድሮኑ በደሴቱ ዙሪያ ይዞራል፡፡ ወደ ተራራው ጫፍ ግን እሺ ብሎ አይወጣም፡፡ ይመለሳል፡፡ ምናልባት ያላወቅነው አንዳች ኃይል ይኖራል› ብለውኛል፡፡ የፊልም ባለሞያው ያሬድ ሹመቴ ይህን ነገር ቦታው ድረስ በመሄድ ለማረጋገጥና የድሮኑን እምቢታ በድሮን ለመቅረጽ ወስኗል፡፡ ከተሣካ ተጨማሪ ነገር ያወጋን ይሆናል፡፡   
 
ከ300 ዓመታት በላይ ያገለገለው የዳጋ ዕቃ ቤትና ሙዝየም
ከዐፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን ጀምሮ እየተሠራ ሲጠገን፣ እየፈረሰም ሲሠራ የኖረው የዳጋ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ በምስጥ ተበልቶ ፈርሷል፡፡ የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ በጥንታዊው ዐቅድ መሠረት እንደገና የመሥራት ሐሳብ አለው፡፡ አከራካሪ የነበረው ጉዳይ ጥንታዊ የዳጋ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ምን ዓይነት ቅርጽ ነበረው የሚለውን የሚመልስ መዝገብ አለመገኘቱ ነው፡፡ ይህን ለመመለስ ባለሞያዎቹ የሞከሩት የቤተ ክርስቲያኑን ጥንታዊ መሠረት በመቆፈር የወለሉን ቅርጽ ማግኘትና ከወለሉ ተነሥቶ ግድግዳና ጣራውን መገመት ነው፡፡ በአኩስም አካባቢ የነበሩትን የዘመነ አኩስም አብያተ ክርስቲያናት መልሶ መገንባት (reconstraction) የተቻለው በዚህ ዘዴ ነውና፡፡
የዳጋ መግቢያ በር
ዳጋ የዕውቀት ማዕከል ነው የተባለው ግን ዝም ብሎ አልነበረም፡፡ ከመቶ ዓመታት በፊት ይህ ጥያቄ እንደሚመጣ ቀድሞ የተገለጠላቸው ጠቢባነ ዳጋ ጥንታዊውን የቤተ ክርስቲያኑን ዐቅድ በገዳሙ ጥንታዊ ማኅተም ላይ በንድፍ አስቀምጠውታል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕንጻ ኮሌጅ የኪነ ሕንጻና የከተማ ቅርስ ክብካቤ (Conservation of Architecture and Urban Heritages) መምህርና የሳይ ኮንሰልት ባለሞያ የሆኑት፣ ላሊበላን ጨምሮ በብዙ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት አርክቴክቸር ላይ ጥናት ያደረጉት ዲያቆን ዮሐንስ መኮንን እንደሚገልጡት ማኅተሙን ያዘጋጀው ጠቢብ በመልሶ ግንባታ(reconstraction) ወቅት እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን ሦስት ነገሮች ያካተተ መረጃ ትቶልናል፡፡ የጣራው ቅርጽና ዓይነት(roof structure)፣ የበሮቹ ቅርጽና ዓይነት፣ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኑን መልክና ቅርጽ የያዘ መረጃ፡፡ 
 
አቡነ ኂሩተ አምላክ ጣናን ያቋረጡባት የድንጋይ ጀልባ
ጣራው ባለ ዐራት ደርዝ ክዳን ወይም ዕንቁላሌ ቅርጽ፣ ቤተ ክርስቲያኑ የጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴን መልክ እንደነበረ እና በሮቹ ከውስጥ ሆነው በዙሪያው ልክ እንደ ዘጌ ገዳማትና እንደ ናርጋ ሥላሴ ባለ ቀስተ ደመና(Arch)በረንዳ እንደነበረው አመልክቷል፡፡ ይህም በገዳሙ ትውፊት ‹ዳጋ እስጢፋኖስ ጥንት የደብረ ብርሃን ሥላሴን ይመስል ነበር› እየተባለ ከሚነገረው ቃላዊ ተረክ ጋር ተስማሚ ነው፡፡ አርክቴክት ዮሐንስ በማኅተሙ ላይ ያለውን ንድፍ ተመልክተው መጀመሪያ የሰጡት ሐሳብም ‹የጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴን ሳይመስል አይቀርም› የሚል ነበር፡፡ ባለሞያው ንድፉ የዳጋ መሆኑን ለማመልከት የዓሣ ምልክትን ከሥሩ አስቀምጧል፡፡ ደብሩ በባሕር ላይ ነው ማለቱ ነው፡፡ 
 
የዳጋ እስጢፋኖስን ጥንታዊ ንድፍ ያዘው ማኅተም
ዳጋ ላይ ግንባታ ማከናወን ቀላል አይደለም፡፡ ድንጋይን ጨምሮ ንብረቱ ሁሉ የሚመላለሰው በጀልባ ነው፡፡ ባለሞያዎች ለተወሰነ ጊዜ ገዳማውያን ይሆናሉ፡፡ ዕቃው ወደቡ ላይ ከደረሰ በኋላ ወደ ተራራው ጫፍ የሚወጣው በሰው ኃይል ነው፡፡ ደግነቱ ሳይደግስ አይጣላም ነውና ገዳሙን እንደ ነፍሳቸው የሚወዱት እንደ ወላጃቸው የሚደግፉት የደቅ ደሴት ክርስቲያኖች አሉለት፡፡ በጀልባ ተሣፍረው መጥተው ‹አፈር ለሚበላው ጉልበት› እያሉ የገዳሙን ዕቃ ተሸክመው ተራራውን እንደ ሜዳ ሲሮጡበት ማየት በራሱ ትንግርት ነው፡፡ 
ብጹዕ አቡነ አብርሃም ድንጋይ ተሸክመው ወደ ዳጋ ተራራ ሲወጡ
 
ብጹዕ አቡነ አብርሃም ድንጋይ ተሸክመው ወደ ዳጋ ተራራ ሲወጡ
 

አሁን ከፊታችን ሁለት ሥራ ይጠብቀናል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑና ሙዝየሙ፡፡ ዛሬ አያሌ ማኅበራት፣ የቅርስና ታሪክ ወዳጆች፣ የደንና አራዊት ተቆርቋሪዎች ያፈራንበት ዘመን ነው፡፡ ዳጋን ከነ እሴቱ ጠብቆ ለማቆት ከዚህ ዘመን የሚሻል የለም፡፡ ጥንታዊው የአባቶቻችን የገዳም ሥርዓት ምን እንደሚመስል፣ አባቶቻችን ዕውቀታቸውና ታሪካቸው፣ አነዋወራቸውና ልማዳቸው እንዴት እንደነበር የዘመን ምስክር ከሚሰጡን አንዱ ዳጋ ነው፡፡ ታሪክ ተረት ከመሆኑ በፊት ይሄው ከፊታችን ‹ታላቅ የሆነ የአገልግሎት በር ተከፍቷል፡፡›
ሊሠራ የታሰበው የዳጋ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ደረጃ ዐቅድ
 
ሥራና ጸሎት፡- የዳጋ መነኮሳት

No comments:

Post a Comment