Thursday, May 31, 2018

<አገር አጥፋ> አረም


ብሽሽቅ ሃይማኖትም፣ ፖለቲካም፣ ወግም ሥርዓትም አይደለም፡፡ ብሽሽቅ ከከሠረ ኅሊና የሚበቅል ‹አገር አጥፋ› አረም ነው፡፡ ‹አገር አጥፋ› አረም የከብቶች ፀር የዕጽዋት ቀበኛ የሆነ ገበሬ አስቸግር አረም ነው፡፡ ‹አገር አጥፋ› አረም መስከረም መጥባቱን የሚያበሥረንን አደይ አበባ ሳይቀር ከሀገር የሚያጠፋ አረም ነው፡፡ አረሙን ከብቶቹ ስለሚያውቁት በአካባቢው ድርሽ አይሉም፡፡ ለስሙ የሚያፈካውን አበባ ንቦች ከቀሰሙት ማር ሳይሆን የሚገድል መርዝ ነው፡፡ ግዛቱን ሲያስፋፋ ከአውሮፓ ቅኝ ገዥዎችም ይብሳል፡፡ አገር ምድሩን ነው የሚወርረው፡፡ ዋናው ተግባሩ ሌላውን ሁሉ እያወደመ ራሱን ብቻ ማስፋፋት ነው፡፡ የግጦሽ መሬቱን ለመቆጣጠር ግልቢያው ከፍተኛ ነው። በተለይም በአውስትራሊያና በአፍሪካ ከፊል አካባቢዎች ተዛምቷል። በሕንድ «የኮንግረሱ ሳር» በሚል መጠሪያው ይታወቃል። 28 ቀን እራሱን የሚተካ ሲሆን፤ ዓመቱን ሙሉ አብቦ ይቆያል። እስከ አንድ ሜትር የሚረዝም ሥር ስላለው ሀገሩን ሁሉ ይቆጣጠረዋል። ዘሩ እስከ ሃያ ዓመት መሬት ላይ መቆየት ይችላል። የዋግ ሕምራ ገበሬዎች ‹አገር አጥፋ› ብለው የሰየሙትን ይሄንን አረም ሳይንቲስቶቹ ‹Parthenium hysterophorus› ብለው ይጠሩታል፡፡

ብሽሽቅም እንደዚሁ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በፖለቲካውና በሃይማኖቱ መስክ ሠፍኖ አገር እያጠፋ ነው፡፡ የምንጽፈው ጽሑፍ፣ የምንለጥፈው ፎቶ፣ የምንሰጠው ትምህርት፣ የምናቀርበው ምስክርነት፣ የምንሠራው ሥራ፣ የምንለግሰው ሐሳብና የምንገልጸው አቋም የቆምንበትን ዓላማ ለማስረዳትና አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት መሆኑ ቀርቶ ሌላውን ለማናደድ፣ ለማቃጠል፣ ለማበሳጨት፣ አንጀቱን ለማሣረርና ቆሽቱን ለማድበን፣ ጨጓራውን ለመላጥና ጥሎ ለማንኮታኮት እየሆነ ነው፡፡ ነገራችን ሁሉ ጠላት ተኮር እየሆነ ነው፡፡  

‹ጠላት እርር ይበል›፣ ‹እነ እንትና ቅጥል ይበሉ›፣ ‹እገሌዎች ዓይናቸው ደም ይልበስ›፣ ‹አንጀታቸው ይረር፣ ደማቸው ይምረር› የሚሉት አገላለጦች ማኅበራዊውን ሚዲያ እያጥለቀለቁ ነው፡፡ አንድ ሊቅ በአንድ ወቅት ‹እኔ መልካም የምሠራው ክርስቶስ ደስ እንዲለው እንጂ ሰይጣን እንዲበሳጭ ብዬ አይደለም› ያሉት ነገር ትልቅ መርሕ ነው፡፡ እኛ የሆንነውንና የተሰማንን ከመግለጥ ይልቅ ‹እንትና ይሄንን ሲያይ እንዴት ይቃጠል ይሆን› እያሉ ከሲዖል ጋር አብሮ ማሰብ ምን የሚሉት ሕመም ነው?  
ብሽሽቅ የሚወድ ሰው ያለ ጠላት መኖር የማይችል ነው፡፡ ካጣ እንኳን ከገዛ ጥላው ጋር ይጣላል፡፡ ብሽሽቅ የሚወድ ሰው እርሱ በመብላቱ ከመደሰትና ከማመስገን ይልቅ በሌላው ጦም ማደር የሚጠግብ ነው፡፡ ብሽሽቅ የሚወድ ሰው ከእርሱ መኖር ይልቅ የሌላው መሞት፣ ከእርሱ መፈታት ይልቅ የሌላው መታሠር፣ ከእርሱ መዳን ይልቅ የሌላው መታመም፣ ከእርሱም መነሣት ይልቅ የሌላው መውደቅ የሚያረካው ነው፡፡
ሀገር እንድትሠለጥን፣ እንድትዘምንና የሁሉም እንድትሆን ትግል የሚደረገው በጥሎ ማለፍ ዋንጫ እየተበሻሸቁ ለመጓዝ አይደለም፡፡ ለውጡ ሁሉንም እንደ ዐቅሙና እንደ ድርሻው ካልጠቀመ፤ አብሻቂና በሻቂ ቡድን ከፈጠረ ‹አገር አጥፋ አረም› ሥር እየሰደደ ነውና ልንነቃ ይገባል፡፡ አረሙን ያጠኑት ሊቃውንት እንደሚሉት ‹አገር አጥፋ› አረም ሥር ከሰደደ በኋላ መንቀሉ ራሱ ሌላ ጉዳት ያመጣል፡፡ ማጥፋት የሚቻለው በመከላከል ነው፡፡ የተነቀለ ሲመስል እንኳን መርዛማ ዘሩን ምድር ላይ በትኖ ደብቆ ያስቀምጠዋል፡፡ ጊዜ ሲያመቸውም ወረራውን ይጀምራል፡፡
የጽሑፋችን፣ የንግግራችን፣ የሥራችን፣ የመግለጫችን፣ የክዋኔያችን፣ የትግላችንና የድላችን ዓላማ ለሰው ዘር የሚጠቅም አንዳች እሴት ለማግኘት እንጂ ከኛ በማዶ ያለውን ለማብሸቅ ከሆነ ‹አገር አጥፋ› አረምን እያስፋፋነው ነው፡፡ በብሽሽቅ የሚገኝ ድኅነት፣ የሚሳለጥ ፖለቲካ፣ የሚገነባ ሀገር፣ የሚሠለጥንም ሕዝብ አይኖርም፡፡ ብሽሽቅ እንደ ‹አገር አጥፋ አረም› መልካሙን ሁሉ አጥፍቶ ብቻውን የሚኖር በሽታ ነውና፡፡
 7 comments:

 1. አጎቴ አረሙን በጣም ስለሚጠላዉ አዉቀዋለሁእና ዳኒ ስለአረሙምን ሊል ነዉ ብዬ ሳስብ ለካ ነገሩ ወዲህ ነዉ። ግሩም
  እይታ!

  ReplyDelete
 2. Thank you D/N Daniel its interesting message

  ReplyDelete
 3. Your article educates those who characterize and label some as friends and others as enemies (that deserves the worst this world offers).I hope everyone will learn the Holines of embracing the other human being, and should strive to do that. This reminded me W. Churchill, once said: "Bring your friends close, bring your enemies closer." That principled approach brings individuals together to listen to each other and find the common humanity first. And the rest of the issues are too minor.

  ReplyDelete
 4. God bless you. I learnt quite a lot.

  Thanks again.

  ReplyDelete
 5. Tiru hasab new,besheshek kefu neger new,
  Ahun ye hagerachin fetena yihe neger yimeslegnal hullum sew sile hageru,wegenu teru simet binorew yishalenal

  ReplyDelete