Wednesday, May 30, 2018

ጥቁር ድንጋይ


የገንዘብን ጠባይ የእነርሱን ያህል የሚያውቀው የለም የሚባሉት ስዊዘርላንዳውያን እንዲህ ይተርካሉ፡፡
አንዲት ውብ ልጅ የነበረቺው አንድ ነጋዴ ነበር፡፡ ከአንድ አራጣ አበዳሪ ከረጢት ሙሉ ብር ተበድሮ ማትረፍ አቅቶት ከሠረ፡፡ የመክፈያውም ጊዜ ደረሰ፡፡ የብድር ውሉ ነጋዴው በጊዜው ብድሩን ካልከፈለ ወደ እድሜ ልክ ወኅኒ እንደሚወረወር ይገልጣል፡፡ ይህ ቀን መድረሱ ለነጋዴውና ለልጁ አስደንጋጭ ሆነባቸው፡፡
የአራጣ አበዳሪው የ80 ዓመት ሽማግሌ፣ ጠባየ ክፉና መልከ ድፉ ነው፡፡ በዚያ አካባቢም እርሱን የሚወደው አንድም ሰው አልነበረም፡፡ ነገር ግን ነጋዴዎች ገንዘብ ሲፈልጉ ከእርሱ ውጭ የሚያበድራቸው አልነበረም፡፡ ይህ አራጣ አበዳሪ ነጋዴው ከወኅኒ የሚተርፍበትን አንድ ሸውክ አቀረበ፡፡ ‹የነጋዴው ልጅ እኔን ለማግባት ፈቃደኛ ከሆነች ነጋዴው ከወኅኒ ይተርፋል፤ ያለበለዚያ ግን እድሜ ልኩን ይማቅቃል› አለ፡፡
ነጋዴውም ልጁም ደነገጡ፡፡ ሁለቱም ለምርጫ አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ በአንዱ አንደኛው በሌላውም ሌላኛው ይሠዋሉ፡፡ የአንዱ መሠዋት ደግሞ ሁሉንም ይሠዋል፡፡ ምን ይደረግ? በሁለት ሞት መካከል የሚደረግ ምርጫ፡፡ መጨነቃቸውን ያየው አራጣ አበዳሪ ሁለተኛ አማራጭ አቀረበ፡፡ ‹እዚህ ማሠሮ ውስጥ ሁለት የባሕር ድንጋዮች እከታለሁ፡፡ ነጭና ጥቁር፡፡ ልጅህም እዚያ ባሕሩ ውስጥ ሆና ዓይኗን ተጨፍና እጇን ወደ ማሠሮው ውስጥ ትከታለች፡፡ ነጩን ካወጣች እኔን አታገባም፣ አንተም አትታሠርም፤ ጥቁሩን ካወጣች ደግሞ እኔን ታገባለች አንተ ግን አትታሠርም› አላቸው፡፡ አራጣ አበዳሪው ውርርዱ ባሕሩ ውስጥ እንዲሆን የፈለገው ልጂቱ ባሕሩን ፈርታ ያቀረበላትን ጥያቄ እንድትቀበል አስቦ ነው፡፡ አባት ተጨነቀ፡፡ ልጁ ግን ስለ ችግሩ ብቻ ማሰብ ጥቅም እንደሌለው ገባት፡፡ ችግሩን ተረድታ መፍትሔውን ማሰብን መረጠች፡፡

‹የጊዜህን ሃያ ከመቶ ችግሩን ለመረዳት አውለው፤ ቀሪውን ሰማንያ ከመቶ ደግሞ መፍትሔውን ለመፈለግ› ይባል የለ፡፡ ከወደቁ በኋላ ለመነሣት መሞከር እንጂ መንፈራገጥ ትርፉ መላላጥ ነው፡፡ ጥርስን ነክሶ ቁስልን ማከም እንጂ ስለ ቁስል ማልቀስ ቁስልን አያድነውም፡፡ ልጅቱ ተስማማች፡፡ አባቷ ግን በኀዘን ልቡ ተሰበረ፡፡ አራጣ አበዳሪውም ‹በሂደቱ ላይ ምንም ዓይነት ጥያቄ ማቅረብ አይቻልም፤ ይህንንም በዳኞች ፊት እናደርገዋለን› አላት፡፡ ነገሩን አሰበችና ተስማማች፡፡ አራጣ አበዳሪው የልጂቱን መስማማት ሲመለከት ደስ አለው፡፡ አያሌ ሕዝብ ነገሩን ሊያይ ተሰበሰበ፡፡ አራጣ አበዳሪውም ከሕዝቡ ተነጥሎ ብሎ ወደ ባሕሩ ዳር ሄደና ድንጋዮችን መፈለግ ጀመረ፡፡ ልጂቱ እንዳያውቅባት አድርጋ በንቃት ትከታተለዋለች፡፡ ሆን ብሎ ሁለት ጥቁር ድንጋዮችን ወደ ማሠሮው ውስጥ ሲጨምር አየቺው፡፡ አሁን የበለጠ ነገሩ ተወሳሰበ፡፡ ስለ ሂደቱ ደግሞ ቅሬታ ማቅረብም ሆነ ጥያቄ መጠየቅ አይቻልም፡፡ ወዲያው መፍትሔውን ወደማሰብ ተሸጋገረች፡› ‹በችግር ላይ መቆዘም ወደ ድቅድቅ ጨለማ ይነዳል፤ በመፍትሔ ላይ ማምሰልሰል ግን ወደ ብርሃን አዳራሽ ይወስዳል› ይባላልና፡፡
አራጣ አበዳሪው አባትና ልጅን ወደ ባሕሩ ዳር ጠራቸው፡፡ የልጂቱ ዓይን ተሸፈነ፡፡ እጇንም ወደ ማሠሮው ውስጥ ከተተችው፡፡ ሕዝቡ ልቡ ቀጥ ብሎ የሚፈጠረውን መከታተል ጀመረ፡፡ ልጂቱ ወደ ማሠሮው ውስጥ የከተተቺውን እጅ አወጣችውና ያመለጣት አስመስላ የባሕሩን ድንጋይ ባሕሩ ውስጥ ጣለቺው፡፡ አራጣ አበዳሪው ደነገጠ፡፡ ልጂቱም ‹አትደንግጥ፡፡ በማሠሮው ውስጥ አንድ ነጭና አንድ ጥቁር ድንጋይ ነው አይደል የከተትከው?› አለቺው፡፡ እርሱም ማጭበርበሩ እንዳይታወቅበት ‹አዎን፤ በተባባልነው መሠረት አንድ ነጭና አንድ ጥቁር ድንጋይ ነው የከተትኩት› አላት፡፡ ‹ያ ከሆነ ነገሩ ቀላል ነው፡፡ ማሠሮው ውስጥ የቀረው ድንጋይ ይታይ፤ የቀረው ነጭ ከሆነ ያወጣሁት ጥቁሩን ነበረ፤ የቀረው ጥቁር ከሆነ ደግሞ ያወጣሁት ነጩን ነበረ ማለት ነው› አለቺው፡፡ አራጣ አበዳሪው መበላቱ ገባው፡፡ ዳኞቹም ‹ልጂቱ ትክክል ናት› አሉና ወደ ማሠሮ እጃቸው ከትተው ጥቁሩን ድንጋይ አወጡት፡፡ የወደቀውም ነጩ መሆኑን ተናገሩ፡፡ አራጣ አበዳሪውም ሁለቱንም ከሠረ፡፡
ማንኛውም ችግር መፍትሔ አለው፡፡ ብቻውን የተፈጠረ ችግር የለም ይባላል፡፡ እንዲያውም አንድ ችግር በሥሩ ከዐሥር በላይ መፍትሔዎችን ደብቋል የሚባል ነገርም አለ፡፡ በችግሩ ላይ አትዘን፣ አትናደድ፣ አትቆዝም፤ አታላዝን፤ ስሜትህን ተቆጣጠረው፤ መሆን አልነበረበትም እያልክ አትብገን፤ ለመፍትሔው ተነሥ፤ አካባቢህን ቃኘው፤ ቀዳዳዎቹን ተመልከት፤ ስንጥቆቹን አስተውል፤ ችግሩን በሚገባ ተረዳው፤ ከዚያም መፍትሔውን ለመውለድ አምጥ፡፡ ፈታኝህን ሙሉ፤ ፈተናህንም ፍጹም አድርገህ አትቁጠራቸው፤ ፈታኙም ክፍተት፤ ፈተናውም ንቃቃት አለው፡፡ የተዘጉ የሚመስሉ በሮች ሁሉ የተከፈተ ቦታ አላቸው፤ የተደፈኑ የሚመስሉ ግንቦች ሁሉ የተሸነቆረ ቀዳዳ አላቸው፤ የሞሉ የሚመስሉ ወንዞች ሁሉ የሚጎድሉበት ቦታ አለ፤ አንተ ብቻ መፍትሔ ከማሰብ አታቋርጥም፡፡ ጥቁር ድንጋይ ብቻ ሲቀርብልህ፤ አንተ በጥበብህ ነጭ አድርገው፡፡  

19 comments:

 1. "እንዲያውም አንድ ችግር በሥሩ ከዐሥር በላይ መፍትሔዎችን ደብቋል የሚባል ነገርም አለ፡፡ በችግሩ ላይ አትዘን፣ አትናደድ፣ አትቆዝም፤ አታላዝን፤ ስሜትህን ተቆጣጠረው፤ መሆን አልነበረበትም እያልክ አትብገን፤ ለመፍትሔው ተነሥ፤ አካባቢህን ቃኘው፤ ቀዳዳዎቹን ተመልከት፤ ስንጥቆቹን አስተውል፤ ችግሩን በሚገባ ተረዳው፤ ከዚያም መፍትሔውን ለመውለድ አምጥ፡፡ ፈታኝህን ሙሉ፤ ፈተናህንም ፍጹም አድርገህ አትቁጠራቸው፤ ፈታኙም ክፍተት፤ ፈተናውም ንቃቃት አለው፡፡ የተዘጉ የሚመስሉ በሮች ሁሉ የተከፈተ ቦታ አላቸው፤ የተደፈኑ የሚመስሉ ግንቦች ሁሉ የተሸነቆረ ቀዳዳ አላቸው፤ የሞሉ የሚመስሉ ወንዞች ሁሉ የሚጎድሉበት ቦታ አለ፤ አንተ ብቻ መፍትሔ ከማሰብ አታቋርጥም፡፡ ጥቁር ድንጋይ ብቻ ሲቀርብልህ፤ አንተ በጥበብህ ነጭ አድርገው፡፡" ግሩም ምክር ነው። እግዚአብሔር ይስጥልን መምህራችህን

  ReplyDelete
 2. "እንዲያውም አንድ ችግር በሥሩ ከዐሥር በላይ መፍትሔዎችን ደብቋል የሚባል ነገርም አለ፡፡ በችግሩ ላይ አትዘን፣ አትናደድ፣ አትቆዝም፤ አታላዝን፤ ስሜትህን ተቆጣጠረው፤ መሆን አልነበረበትም እያልክ አትብገን፤ ለመፍትሔው ተነሥ፤ አካባቢህን ቃኘው፤ ቀዳዳዎቹን ተመልከት፤ ስንጥቆቹን አስተውል፤ ችግሩን በሚገባ ተረዳው፤ ከዚያም መፍትሔውን ለመውለድ አምጥ፡፡ ፈታኝህን ሙሉ፤ ፈተናህንም ፍጹም አድርገህ አትቁጠራቸው፤ ፈታኙም ክፍተት፤ ፈተናውም ንቃቃት አለው፡፡ የተዘጉ የሚመስሉ በሮች ሁሉ የተከፈተ ቦታ አላቸው፤ የተደፈኑ የሚመስሉ ግንቦች ሁሉ የተሸነቆረ ቀዳዳ አላቸው፤ የሞሉ የሚመስሉ ወንዞች ሁሉ የሚጎድሉበት ቦታ አለ፤ አንተ ብቻ መፍትሔ ከማሰብ አታቋርጥም፡፡ ጥቁር ድንጋይ ብቻ ሲቀርብልህ፤ አንተ በጥበብህ ነጭ አድርገው፡፡" ግሩም ምክር ነው። እግዚአብሔር ይስጥልን መምህራችህን

  ReplyDelete
 3. May you hear the words of Life!

  ReplyDelete
 4. Thank you Dn it just build up my hope.

  ReplyDelete
 5. May you hear the words of Life.

  ReplyDelete
 6. DANI EGZABHERE YETEBKHE BTAME ASMTMARI NWE

  ReplyDelete
 7. Dani may God Bless you .continue feeding the wisdom for this Generation .
  Thank you very much Sir,

  ReplyDelete
 8. EBAKEH HULE TSAFELEN.....THNAKS A LOT DANI

  ReplyDelete
 9. ጥቁር ድንጋይ ብቻ ሲቀርብልህ፤ አንተ በጥበብህ ነጭ አድርገው፡፡

  ReplyDelete
 10. መጨነቅ መጠበብን ትወልዳለች ማለት ይህ ነው

  ReplyDelete
 11. u inspired me as always .Thank u Dan.

  ReplyDelete
 12. "Problem is the mother of invention"

  You can't change without a challenge.

  Take challenges in your life as a source of change and progress.

  ReplyDelete
 13. እግዚአብሄር መፍትሄ የሚያዩ ዓይኖችን ያድለን::

  ReplyDelete
 14. ድንቅ ነው፤ እናመሰግናለን።

  ReplyDelete