Friday, May 25, 2018

የትውልድ አደራ


ልዑል ራስ መንገሻ
የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ
2010 ዓም
እኔ ከአዲስ አበባ ወደ ስዊዘርላንድ፣ ልዑል ራስ መንገሻ ከቀበና ወደ ዘጠነኛ ዓመት የእድሜ ባለጸጋነት አብረን እየተጓዝን ነው፡፡ ‹የትውልድ አደራ› የሚለውን መጽሐፋቸውን ማንበብ ከአንድ የታሪክ መዝገብ ከያዘ አረጋዊ ጋር ተቀምጦ እንደ ማውጋት ያለ ነው፡፡ ትገረማላችሁ፣ ትመሰጣላችሁ፣ ታለቅሳላችሁ፣ ትስቃላችሁ፣ ከዚያም አልፋችሁ ግን ለምን? ትላላችሁ፡፡
ልጅ ሆነው ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ በሰው ትከሻ እንዴት እንደተጓዙ ሲተርኩላችሁ የዛሬ መቶ ዓመት አካባቢ በእግር ይደረግ የነበረውን ጉዞ እየቃኛችሁ አብራችሁ ታለከልካላችሁ፡፡ በትግራይ የነበረውን የመሳፍንት ልጆች አስተዳደግ ሲተርኩት በልጅ ልባቸው ውስጥ ትገረማላችሁ፡፡ አውሮፕላንና መኪና ሲታይ የነበረውን ግርምታ ሲነግሯችሁ በሳቅ ትፈርሳላችሁ፡፡ በሰባት ዓመታችው ራስ  ሥዩም መንገሻ ለራስ መንገሻ ሥዩም ደጃዝማችነት ለማሰጠት ዐፄ ኃይለ ሥላሴን ጠየቁ፡፡ መልሱ የመጣው በስልክ ነበር፡፡ ራስ መንገሻ ሥዩም በስልክ ተጠርተው ሲቀርቡ ለዐፄ ኃይለ ሥላሴ እጅ እየነሡ ነበር ወደ ስልኩ የሚሄዱት፡፡ ንጉሡ በሌሉበት በስልክ እጅ ሲነሣ ማየት ለሕጻኑ መንገሻ አስገራሚ ነገር ነበር፡፡ ‹ልዑል ጌታዬ› ይሏቸዋል አባታቸውን፡፡
የ1928ቱን የጣልያን ወረራን ለመመከት በሰሜን በኩል ተደርጎ የነበረውን ዝግጅት መንገሻ ይተርኩልናል፡፡ በተለይ ‹ልዕልት እመቤቴ› የሚሏቸው ወ/ሮ ዐጸደ አስፋው ያደረጉት የስንቅ ዝግጅት ምነው በዝርዝር በተተረከ ኖሮ ያሰኛል፡፡ በአንድ በኩል ሀገር ወዳዱ ራስ ሥዩም መንገሻ፣ በሌላ በኩል ከጣልያን የተባበሩት ደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሣ በዚያው በትግራይ ምድር ያደረጉትን የተቃረነ ዝግጅት ስናይ ‹የእናት ሆድ ዥንጉርጉር› እንላለን፡፡ 

በዘመቻው ላይ የመጀመሪያው ገፈት ቀማሽ ከነበሩት መካከል በልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ የተመራው ትግራይ ጦር ሰባት ወራት ያህል ጣልያንን ገትሮ የተዋጋውን ውጊያ ስናስታውስ ነጻነታችን በጋራ የከፈልነው መሥዋዕትነት ውጤት መሆኑን እናይበታለን፡፡ ራስ ሥዩም ወደ ማይጨው ተጠርተው በዚያ ግምባርም ዘምተው፣ በኋላም ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ሲያፈገፍጉና ወደ ጀኔቭ ሲሄዱ መንገዱ እንዳይያዝ ጣልያንን የመከላከል ግዳጅ ተሰጥቷቸው የከፈሉት ዋጋ ታላቅ ነው፡፡ የንጉሡ ትእዛዝ ራስ ሥዩም መንገሻ አድዋ ቀርተው ራስ እምሩ እንዲመለሱ ነበር፡፡ መልክተኛው ግን ‹ሁለታችሁም ኑ› ብሎ ተናገረ፡፡ ሁለቱም ሲሄዱ ግን ንጉሡ ራስ ሥዩምን ‹ለምን መጣህ› ብለው ተቆጡ፡፡ ይህ በራስ ሥዩም ላይ ቅሬታ ፈጠረ፡፡ ቅሬታቸው ግን ለሀገራቸው መሥዋዕትነት እንዳይከፍሉ አላደረጋቸውም፡፡ በኋላም ተማርከው ጣልያን ድረስ ተጋዙ፡፡
አዳጊው ልዑል ራስ መንገሻም አብሮ ጣልያን ወረደ፡፡
ራስ ሥዩም ጣልያን እድሜው ሊያጥር ጥቂት ወር ሲቀረው ተፈትተው ወደ ሀገር ሲመለሱ ራስ መንገሻም አብረው ገቡ፡፡ ራስ ሥዩም በአምባላጌው ጦርነት ጣልያንን ከጉድጓድ በማውጣት ታሪክ የማይረሳውን የጀግንነት ተግባር ፈጸሙ፡፡ እንግሊዝ ከዐፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር የነበራቸውን ቅራኔ ተጠቅሞ የትግራይና የኤርትራ ገዥ አድርጎ ሊያስኮበልላቸው ሲያባብላቸው ‹ወግድልኝ› አሉት፡፡ ራስ ሥዩም በሀገር አይደራደሩም፡፡ ያም ቢሆን ግን ከነጻነት በኋላ ለራስ ሥዩም መንገሻ በጎ አልተከፈላቸውም፡፡ ይኼንንም ልጃቸው በኀዘን ይተርኩታል፡፡ ለሀገራቸው መሥዋዕትነት የከፈሉት ጀግናው ራስ ሥዩም መንገሻ የቁም እሥር በሚመስል ሁኔታ አዲስ አበባ እንዲቀመጡ ተደረጉ፡፡
ራስ መንገሻ ከቀዳማዊ ወያኔ ዐመጽ ጀምረው የሀገሪቱን ሂደት እንደገና ያወጉናል፡፡ በሹመት በዞሩባቸው በአምቦ፣ በአርሲ፣ በሲዳሞ፣ የሠሩትን ሲተርኩ የሕዝቡን ታሪክ፣ ባሕልና ትጋት ያነሡልናል፡፡ በቦረና የነበረውን የኢትዮ ኬንያ የድንበር ጉዳይ፣ ሲዳሞን ቡና ለዓለም ገበያ ለማስተዋወቅ የተደከመውን ድካም፣ ያመጡታል፡፡ በዚያው አያይዘውም ጅባትና ሜጫን ሲያስተዳድሩ ያጋጠማቸውን የጨሊያ ባላባት ታሪክ ያወጉናል፡፡ ይህ አገር የሚሰግድለት ባላባት ‹ልጄን አስተምሩልኝ› ብሎ ሰጣቸው፡፡ ተቀበሉ፡፡ ልጁ ክርስትና ተነሥቶ ተማረ፡፡ በኋላ ራእይ እስከማየትና ትንቢት እስከመናገር በቅቶ ነበር፡፡ የአብዮቱን መምጣትና የራስ መንገሻንም ዕጣ ፈንታ ቀድሞ ነግሯቸው ነበር፡፡
የሥራና መገናኛ ሚኒስቴር ሹመታቸውን ሲያወሩን የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ታሪክ ይዞን ይነጉዳል፡፡ ከአፍሪካ አዳራሽ እስከ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የተሠራውን መንገድ አስደናቂ ታሪክ ይነግሩናል፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽና ሕንጻ እንዴት እንደተሠራ ያወሩናል፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላ ወደ ትግራይ ጠቅላይ ግዛት ተዛውረው 14 ዓመት አገልግለዋል፡፡ በአብዮቱ ዋዜማ የነበውን የትግራይና የኤርትራ ሁኔታ ያስቃኙናል፡፡ በሕዝቡ ዘንድ የነበረውን ስሜት፣ በየጊዜው ሳይታረሙ የተከማቹ ችግሮች ያመጡትን ጣጣ፣ ቤተ መንግሥቱ ከየ አቅጣጫው የተሰጠውን ሐሳብ ባለመቀበሉ በመጨረሻ የገባበትን ማጥ ያሳዩናል፡፡ በፍጻሜውም አብዮቱ ሲፈነዳ እንዴት ከሀገር እንደወጡና እንዴት በኢዲዩ በኩል እንደተዋጉ ይነግሩናል፡፡ ኢዲዩ እየደከመ ሲመጣም አሜሪካ ገብተው ኑሯቸውን ቀጠሉ፡፡ ከዚያም ለውጡን ተከትለው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡

ቀሪውን እናንተ አንብባችሁ በታሪክ ባሕር ውስጥ ዋኙ፡፡

2 comments:

  1. Zemeta work aydelem, Betam wodejewalehu, ewnet new yegna wondoch specially amhara region ayredutem, eneim yih neger dersobegn neber.
    Thanks a lot!!!

    ReplyDelete