Monday, May 14, 2018

ዳግማዊውን አለቃ ተክሌ መልሱልን


‹አራቱ ኃያላን› የተባለውን መጽሐፍ በ2006 ዓ.ም. ጎንደር ላይ ስንመርቅ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤልሳዕ መሪጌታ እንደ ሥራቸው ስለሚባሉ የተክሌ አቋቋም ሊቅ አንሥተው ‹የተክሌ አቋቋም ከጊዜ በኋላ ቢጠፋ ወይም እኔ አንድ ነገር ብሆን ብለው 9 ካሴት የሚሆን ዜማ በካሴት ቀርጸው አስቀምጠዋል› ሲሉ ተናገሩ፡፡ ሌሎች ሊቃውንትም ‹እንደሥራቸው መቋሚያ ይዞ ሲዘም እንኳን ሰዎች ንቦች ይመሰጣሉ› ሲሉ ስለ እርሳቸው መሰከሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ‹እንደሥራቸው› ማን ናቸው? የሚል ጥያቄ በአእምሮዬ ይመላለስ ጀመር፡፡ በተለያየ አጋጣሚ የደብረ ታቦርና የተክሌ አቋቋም ሊቃውንትን ባገኘሁ ቁጥር እኒህን ሊቅ በተመለከተ እጠይቃቸው ነበር፡፡ ሁሉም የሚመሰክሩልኝ ‹ከአለቃ ተክሌ በኋላ የመምህር እንደሥራቸውን ያህል አቋቋምን የሚያውቀው የለም› በማለት ነው፡፡ ዛሬ በቦታው የሚገኙት የደብረ ታቦር ኢየሱስ አለቃ መልአከ ታቦር ኃይለ ኢየሱስ ፋንታሁንና የተክሌ ምስክሩ የኔታ መርሻ መምህር እንደሥራቸውን ሲያነሡ ዕንባ ይቀድማቸዋል፡፡ በምስክር ትምህርት ቤቱ ዛሬም ‹የእንደ ሥራቸው ዜማ› እየተባለ የእርሳቸው ስልት ይሰጣል፡፡ እንደ ብዙዎቹ የድጓና የአቋቋም ሊቃውንት አስተያየት ሊቁ እንደሥራቸው በዜማ ዕውቀታቸውና ስልታቸው ከተድባበ ማርያሞቹ አዛዥ ጌራና አዛዥ ራጉኤል፣ ከቤተ ልሔሙ እጨጌ ቃለ ዐዋዲ ጋር የሚተካከሉ ናቸው፡፡  

ከአቶ አግማሴ መኮነንና / ሙሉነሽ ይናለም 1939.ም. ሚያዚያ 23 ቀን በደብረ ታቦር አካባቢ ልዩ ስሙሰላምኮበተባለ ቦታ ተወለዱ፡፡ በዚህም ተነሣ አምኃ ጊዮርጊስ ተባሉ፡፡
በእናት አባታቸውና በዘመድ አዝማድ በጣም ብርቅና ድንቅ የሆኑ ልጅ ነበሩ፡፡ መጀመሪያ በአካባቢያቸው ከነበሩ መምህር አባ ባያፈርስ ከመምህር መርሻ ዓለሙ ጋር ከፊደል እስከ ፆመ ድጓ ተምረዋል፡፡ ቀጥለዉም ፀዋትዎ ዜማ ከአለቃ ማኅተም ጌጤ፤ ቅኔ ወረታ አካባቢ ከሚገኙት መሪጌታ ጌቴ ተምረዋል፡፡ እንደገናም ከመምህር ጥበቡ ቅኔና ምሥጢር አደላድለዋል፡፡ የተክሌን አቋቋም ከአለቃ ማኅተም ጌጤ ካጠኑቁ በኋላ አዛወር ኪዳነ ምሕረት ከመሪጌታ ጀንበር ድጓን እንደ ገና ተምረውታል፡፡ ቀጥለውም ታች ጋይንት ከምትገኘው ኢትዮጵያ የድጓ ዩኒቨርሲቲ ቅድስት ቤተ ልሔም ገብተው ድጓን ከመምህር ጥበቡ አስመስከረው የድጓ መምህር ሆነዋል፡፡

ሊቁ እንደሥራቸው ድጓን አስመስክረው ከተመረቁ በኋላ በደብረ ታቦር ኢየሱስ የተክሌ አቋቋም ምስክር ከሆኑት ከአለቃ ቀለመ ወርቅ ይማም የተክሌ ዝማሜን ጥሩ አድርገው ተምረው አስመስክረዋል፡፡ በቅድስት ቤተልሔም በዐቢይ ጾም ዝማሜ ይሰጥ የነበረው ለመምህር እንደሥራቸው እንደ ነበር የሚያስታዉሱ ሊቃውንት አሉ፡፡ መምህር እንደሥራቸው ደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጸሎተ ሃይማኖትን በዝማሜ በሚዘምሩበት ጊዜ ንብ ከእጃቸው ላይ ያርፍባቸው እንደ ነበር የዓይን ምስክሮች ዛሬም በአድናቆት ይተርኩታል፡፡
ወደ ጎንደር ከተማ ከመጡ በኋላ በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በጎንደር ለማንም የማይሰጠው የተክሌ ዝማሜ ለመምህር እንደሥራቸው ይሰጥ ነበር፡፡ ጎንደር በነበሩበት ጊዜ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ፣  የታሪክ፣ የሂሳብና የዜማ መምህር በመሆን ሰፊ አገልግሎት ፈጽመዋል፡፡ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ፤ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የሊቃውንት ጉባዔ ሰብሳቢ፤ ብጹዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ክቡር ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮነን የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም የአራቱ ጉባኤ መምህር የነበሩት፤ ክቡሩ ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሐዲስ የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም የአራቱ ጉባዔ መምህር እኒህን ሊቅ ሲያስታውሱ በቁጭት፣ በግርምትና በዕንባ ነው፡፡
ከዚህ አልፈው በጎንደር የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ዋና የአስተዳዳር ክፍል ሆነው ያገለገሉት ሊቁ እንደሥራቸው 2 ሴት ልጆችና 7 ወንድ ልጆች አሏቸው፡፡

እኒህ በጳጳሳቱ የተፈቀሩ፤ በሊቃውንቱ የተደነቁ፣ በካህናቱ የተወደዱና በምእመኑ ተናፈቁ ሊቅ ድንገት በሐምሌ 1986 ዓ.ም. የውኃ ሽታ ሆነው ጠፉ፡፡ ይህም የተክሌ ዝማሜ ሊቃውንትንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን አስደነገጠ፡፡ አንዳንዶቹ መንነዋል ሲሉ አንዳንዶቹ ተሠውረዋል ሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ሞተዋል ሲሉ ደመደሙ፡፡
ቤተሰቡ፣ ወዳጆቻቸው፤ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፣ ምእመናንና ታሪክና ኪነ ጥበብ ወዳጆች ሊቁን እንደሥራቸውን ፍለጋ አገሩን ማሰሥ ጀመሩ፡፡ በመጨረሻም ጉዳዩ እንዲህ ሆኖ ተገኘ፡፡
ሐምሌ 12 ቀን 1986 ዓ.ም. ሲሠሩበት ከነበረው የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ቢሮ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የሆኑ ሰዎች ይቀርቧቸውና ወደ መኪናቸው ያስገቧቸዋል፡፡ ከሌሎች የታፈኑ ሰዎች ጋር ጎንደር ራስ ግንብ ተብሎ ወደሚጠራው እሥር ቤት ይወሰዳሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ያያቸው የለም፡፡ ከሦስት ቀናት በኋላ ቤተሰቦቻቸው ጭንቀት ውስጥ ወደቁ፡፡ ‹‹የእስር ቤቱ ጠባቂ ያውቃቸው ስለነበር፣ ማታ ማታ የታሠሩበትን ሰንሰለት ያላላላቸው ነበር፡፡ በቅዳጅ ወረቀት መታሠራቸውንና ከእርሳቸው ጋር የነበሩት እንደተገደሉ፣ ከእርሳቸው ላይ ሲደርስ ግድያ አቁሙ የሚል ትእዛዝ መድረሱን፣ ጠቅሰው መልእክት በእሥር ቤት ጠባቂው በኩል ለቤተሰብ ላኩ፡፡ በወቅቱም ባለቤታቸውና ትልቁ ልጃቸው ለማስፈታት ጥረትም ቢያደርጉ የሚሰማቸው አካል አጡ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የት እንደተወሰዱ ሳይታወቅ እንቆቅልሽ ሆኖ ቀረ› ይላሉ ታሪኩን የሚያውቁት የአካባቢው ሰዎችና ቤተ ዘመዶች፡፡

መምህር እንደሥራቸው ዛሬም በሕይወት በአንድ እሥር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ከእሥር ተፈትተው ለቤተሰቦቻቸው መረጃ የሰጡ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ አንዳንዶችም በአካል ባያዩዋቸውም ዜማቸውን መስማታቸውን መስክረዋል፡፡ እነሆ ከተሠወሩ 24 ዓመት ሆነ፡፡ ሀገሪቱ ብዙ ዘመናትን አሳለፈች፡፡ አሳልፋም አይለቀቁም የተባሉ የፖለቲካ እሥረኞችንም ለቀቀች፡፡ እኒህ ሰው ቢፈረድባቸው እንኳን እስከ ዛሬ ሊፈቱ ይገባ ነበር፡፡ ሀገሪቱ ካለፉት ዘመናት ችግሮቿ ራሷን ለማላቀቅ በምትጥርበት በዚህ ዘመን ሊቁን መምህር እንደ ሥራቸውን ያሠረ አካል እንዲፈታቸው በልዑል እግዚአብሔር ስም እጠይቃለሁ፡፡ በሕይወት መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እኒህን ሊቅ በዚህ ሁኔታ ጠፍተው እንዲሞቱ ማድረግ የተክሌ አቋቋምን መግደል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይም የሞት ፍርድ መፍረድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ መከራ መሸመት ነው፡፡ ምናልባት ያጠፉት ነገር አለ ቢባል እንኳን 24 ዓመት ከበቂ በላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ የእድሜ ልክ የተፈረደበት ሰው እንኳን የሚታሠረው 25 ዓመት ነው፡፡ ይህ ወቅት የይቅርታና ንስሐ ነው ይባላል፡፡ ይቅርታና መሻሻል ደግሞ ያለፉትን ስሕተቶች ከማረም ይጀምራል፡፡ አያሌ ሊቃውንትና ደቀ መዛሙርት ‹ወደፊት የኔታ እንደ ሥራቸው ሲመጡ እንቀጽለዋለን› እያሉ ዛሬም በጉጉትና በጸሎት ይጠብቋቸዋል፡፡
ዳግማዊውን አለቃ ተክሌን መልሱልን፡፡


13 comments:

 1. Eyetaw des yilal ...neger gen 24 amet mulu yetaserebet eserbeet mawek lemen altechalem? Be ketays men yisera?

  ReplyDelete
 2. አግዚአብሄር ያክብርልኝ ዳንኤል እኒህ ሊቅ ታሪካቸው ከገለጥከው በላይነው እኔ ታላቁን ሊቅ መላከታቦር ልብሰወርቅ ወርቁን(የተክሌ ሊቅ ናቸው) ጠይቄአቸው ነበር እንባቸው ቁጭታቸው አላናግር ብሎአቸው ቆይተተተተው ሀገሩ ቤተክርስቲያናችን ነው የሞቱት አሉኝ አሁንም ከዚህ የበለጠ ስራ ሰርተን እንዲፈቱ ማድረግ አለብን አንተም ዝም እንዳትል ካሉበት ለማድኘት ሞክር (እኒህን ሊቅ በዚህ ሁኔታ ጠፍተው እንዲሞቱ ማድረግ የተክሌ አቋቋምን መግደል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይም የሞት ፍርድ መፍረድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ መከራ መሸመት ነው) እውነተ ብለሀል ይጠብቅህ

  ReplyDelete
 3. dani ante liyu neh !!! amlak erejim edmie yistih!

  ReplyDelete
 4. ኢትዮጲያና ቤተክርስቲያናችን አሁን ላይ የሚያስፈልጓት እንደነዘህ ያሉ ሊቃውንቶች ለመሆናቸው አስረጂ መቁጠር አያስፈልገውም በእውነትም እኒህ ታላቅ መምህር በሕይወት ካሉ ለመጪዋ የተሻለች ኢትዮጲያ እና የሊቃውንት መፍለቂያ ለሆነችው ቤተክርስቲያናችን ያስፈልጓታልና እባካችሁ ፍቱልንና እሳቸውና በተስፋ የሚጠብቋቸው ተስፋቸውን እውን ያድርጉ የሁላችንም ጥያቄም መልዕክትም ነው ፡፡ ዲ/ን ዳንኤል ለእነዚህ የንስር አይኖችህ ፈጣሪ ሌሎች የተሰወሩና መገለጥ ያለባቸውን ነገሮች አብዝቶ ይግለጽልህ ... ተባረክ!!!

  ReplyDelete
 5. Minwagaw TemesgenMay 16, 2018 at 4:51 PM

  ዳኒ፣ "አያሌ ሊቃውንትና ደቀ መዛሙርት ‹ወደፊት የኔታ እንደ ሥራቸው ሲመጡ እንቀጽለዋለን› እያሉ ዛሬም በጉጉትና በጸሎት ይጠብቋቸዋል፡፡" ያልኸው በተለይ አንጀት ይበላል፡፡ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ይስማልን፤ ተምኔታቸውን ይፈጽመልን!

  ReplyDelete
 6. እጅግ በጣም እያዘንኩ ነው ያነበብኩት በህይወት ኖረው ተፈተው ለማየት ያብቃን፡ ዳኒ መልካም ስራ ነው አመሰግናለሁ

  ReplyDelete
 7. ሊቁን በአስቸኳይ ፍቱልን።

  ReplyDelete
 8. የእኚህን ታላቅ ሊቅ: ሊቁ እንደሥራቸውን ሁኔታ በተመለከተ የጻፍኸውን ሳነብ እጅግ በጣም ተነካሁ። አሁንም ዳግማዊ አለቃ ተክሌን መልሱልን የሚለውን መልዕክት ለሚመለከተው ሁሉ አድርስ። እኒህን ታላቅ ሊቅ በዓይን ለማየት ያብቃን።

  ReplyDelete
 9. Dn Daniel , Kalehiwot Yasemalen.Ye Taserut Dagimawi Alek Tekel Bicha Ayidelum, Tewahido Emenetachin Ena Ye Aleka Tekel Akuakem Chimer new, Egnem Teketayachu Andken Enqun Betselote Sanasibachem Bemenfes Taserenal, Ye Abereham Selasei Yitadege , Abatachine Yasefetalin,Esache Sifetu Ortodoxawit Tewahido Emenetachi Ena , Ye Tekele Akuka Aero YIfela. Embetachin Kides Dingel Marial Tamaleden, Cheru Amelakachi Like Melayikitun Kidus Michael Liku Aregagito Yasefetalen. Berketachewu Yiderben

  ReplyDelete
 10. ይድረስ ለጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ፡፡እባኮትን ሊቁን ያስፈቱልን፡፡ እንዲህ አይነቱን ሰው ለብዙዎች እንዲያበራ ከፍ ተደርጎ ይቀመጣል እንጂ እንዴት ከእንቅብ በታች ያኖሩታል፡፡

  ReplyDelete
 11. ሰሚ ስኖር አይደል...

  ReplyDelete
 12. እባካችሁ እሳቸውን በመፍታት መልካም ነገር አድረጉ ከዚህ በላይ ይቅርታ ከዚህ በላይ የሀገር ፍቅር የለምና

  ReplyDelete