Thursday, May 10, 2018

ስድስተኛው የበጎ ሰው ሽልማት መርሐ ግብር የእጩዎች ጥቆማ ተጀመረለሀገርና ለሕዝብ አርአያነት ያለው ታላቅ ተግባር ያከናወኑ ሰዎችን ዕውቅና የሚሰጠው የበጎ ሰው ሽልማት ስድስተኛው መርሐ ግብሩን ከግንቦት 2 ቀን 2010 ዓ.ም አንሥቶ የእጩዎች ጥቆማ በመቀበል በይፋ ይጀምራል፡፡ ስድስተኛው የበጎ ሰው ሽልማት ነሐሴ 27 ቀን 2010 ዓ.ም በደማቅ ሥነ ሥርዓት የሚካሄድ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 
ለዚህ የሽልማት መርሐ ግብር በአሥር ዘርፎች ማለትም
     1.  በመምህርነት ዘርፍ
     2.  ንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ
     3.  ማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ
     4.  ሳይንስ ዘርፍ
     5.   ቅርስና ባሕል ዘርፍ
  6.   መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት ዘርፍ
     7.   ኪነ ጥበብ (በሙዚቃ ዜማ ድርሰት ዘርፍ) 
     8.   ሚዲያና ጋዜጠኛነት ዘርፍ
     9.   ለኢትዮጵያ በጎ ሥራ የሠሩ የውጭ አገር ዜጎች ዘርፍ
    10.  በጎ አድራጎት ዘርፍ
ከሕዝብ የእጩዎችን ጥቆማ ለመቀበል ተዘጋጅተናል፡፡


በበጎ ሰው ሽልማት ከ2005 ዓ.ም አንሥቶ በተካሄዱት አምስት የሽልማት ወቅቶች፤ አገራችን የምትኮራባቸውና የላቀ አርአያነት ያለው ተግባር ያከናወኑ ሰዎች ዕውቅና የተሰጣቸው ከሕዝብ በቀረቡ ጥቆማዎችና በዳኞች ውሳኔ መሠረት ነው፡፡ የበጎ ሰው ሽልማትን ለዚህ ያበቃውም በሽልማቱ ሂደት የሕዝብ ተሳትፎ በመኖሩና ይህም ከዓመት ዓመት እያደገ በመሄዱ የተነሣ በአክብሮት እንገልጻለን፡፡ ይህ ተሳትፎ አሁንም እንደሚቀጥል ጽኑ እምነት አለን፡፡

የበጎ ሰው ሽልማት ዓላማ ለሀገራችን ለኢትዮጵያ መልካም የሚሠሩ፣ ሀገራዊ ተልዕኳቸውን በብቃትና በልዩ ልዕልና የሚወጡ፣ የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል ለውጥ አምጪ ተግባር የፈጸሙ፤ በብዙ ሰዎች የማይደፈረውን ተግባር በተነሣሽነት የከወኑ፣ለድጋፍ ፈላጊ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ትኩረት በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነት ወስደው የሠሩ፣ የሀገሪቱ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባሕል፣ እንዲጠበቅ፣ የሀገሪቱ  ሥልጣኔ  ከፍ  እንዲል  የሠሩ  ኢትዮጵያውያንን  በማበረታታት፣  ዕውቅና  በመስጠትና በመሸለም ሌሎች በጎ ሠሪዎችን ለሀገራችን ማፍራት ነው፡፡

ስለዚህ ይህን የበጎ ሰው ሽልማትን ዓላማ ከግምት ውስጥ በማስገባት ከላይ በተገለጹት መስኮች ግንቦት 2 ቀን 2010 ዓም እስከ ሰኔ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ሕዝቡ ለዚህ ሽልማት ብቁ ናቸው የሚላቸውን እጩዎች ከሁሉም የሀገራችን ክልሎች እንዲጠቁም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ጥቆማ የምንቀበለው በስልክ፣ በኢሜይልና በፖስታ ነው፡፡ አድራሻዎቹም፤

1. ስልክ፡- 0960402990
2. ኢሜይል፡ begosew2010@gmail.com
3. ፖስታ፡ 150035 አዲስ አበባ
4. በአካል ለሚመጡ፡- ለም ሆቴል፣ ማትያስ ሕንጻ፣ ቢሮ ቁጥር 408
 www.facebook.com/Begosew Prize


የሕዝቡ የመምረጫ መመዘኛዎች
1. ለሀገር ሰላም፣ ለሕዝቦች መቀራረብና መደጋገፍ፣ ለውጥ አምጭ አስተዋጽዖ ያደረጉ፣
2. በበጎ አድራጎትና ሰብአዊ ተግባራት ተሠማርተው የሰው ልጅን ሕይወት የለወጡ፣
3. በሥነ ጽሑፍ፣ በኪነ ሕንጻ፣ በሥነ ጥበብና በመሳሰሉት መስኮች ለኢትዮጵያውያን የሚጠቅሙ፣ የኢትዮጵያን ስም ከፍ የሚያደርጉ፣ የሀገሪቱን ሥነ ጥበብ ወደ አንድ የላቀ ደረጃ የሚያደርሱ ሥራዎች የሠሩ፣
4. በግብርና፣ በቢዝነስ፣ በኢንዱስትሪና በመሳሰሉት መስኮች አዲስ፣ የራሱ ወጥነት ያለውና ያልተደፈረ የሚመስለውን ሥራ ያከናወኑ፣ ለሀገሪቱ ዕድገትና ሥልጣኔም ለውጥ አምጭ አስተዋጽዖ ያደረጉ፣
5. በጋዜጠኛነት መስክ ተሠማርተው ሙያውን የጠበቀ፣ ለሌሎች አርአያ የሚሆን፣ የሕዝቡን ኑሮ የሚለውጥ ሥራ ያከናወኑ፣
6. በዲፕሎማሲው መስክ የሀገሪቱን ክብርና ደረጃ ያስጠበቁ፣ የሀገሪቱንም መብት ያስከበሩ፣
7. በመንግሥትና በሥራ ተቋሞቻቸው የተሰጧቸውን የተለያዩ ሀገራዊ ግዳጆችን በብቃት የተወጡ፣ መሥዋዕትነት የሚጠይቁ ተልዕኮዎችን ያከናወኑ፣ ለትውልድ አርአያ የሚሆኑ ብቁ አመራሮችን የሰጡ፣ በአመራሮቻቸውም ድርጅታቸውንና መሥሪያ ቤቶቻቸውን የለወጡ፣
8. ሀገራዊ ዕውቀቶችን በማስተማር፣ ቅርሶችንና ባህልን በማስጠበቅና በመከባከብ ለውጥ አምጭ ተግባር ያከናወኑ፣
9. በጥናትና ምርምር መስክ ተሠማርተው ችግር ፈች የሆኑ ውጤቶችን ያስመዘገቡ፣
10. በሌሎችም መስኮች የሚጠቀስ፣ ለሀገር የሚጠቅም፣ ለትውልድ አርአያነት ያለው፣ የሀገርን ክብር የሚጨምር፣ ታሪክና ማንነትን የሚያጎላ ተግባር ያከናወኑ ሌሎችንም ኢትዮጵያዊ ዜጎችን ይጠቁሙ፤
ጠቋሚዎች እጩዎችን በሚጠቁሙበት ጊዜ እጩው ግለሰብ ለአገርና ለህዝብ ያከናወኑትን ተግባር በዝርዝር እንዲገልጹልንና የሚገኙበትንም አድራሻ እንዲጠቁሙን እንጠይቃለን፡፡ ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኋላ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ ለመጨረሻው ውድድር ተመርጠው ስማቸው ለዳኞች የሚላከውን እጩዎች ማንነት ሕዝብ እንዲያውቀው ለማድረግ፤ ዐውቆም ለሀገርና ለሕዝብ ባበረከቱት አስተዋጽዖ እንዲያከብራቸው ለማድረግ ዝርዝራቸውን በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ይፋ እናደርጋለን፡፡  
የመጨረሻውን የየዘርፎቹን የበጎ ሰው ተሸላሚ ምርጫ የሚያደርጉት ለእያንዳንዱ የሽልማት ዘርፍ በዳኝነት የተመረጡ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ዳኞቹ በዕውቀታቸውና በሙያቸው አንቱ የተባሉ፣ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸውና በታማኝነት ምርጫውን ያከናውናሉ ተብለው የታመነባቸው ናቸው፡፡ ለእያንዳንዱ ዘርፍም ሦስት ዳኞች ተመርጠው ምርጫውን ያከናውናሉ፡፡  

በጎ ሠሪዎችን በማክበርና በመሸለም ሌሎች በጎ ሠሪዎችን እናፍራ

ለበለጠ መረጃ ይደውሉ፡ ዳንኤል ክብረት - 0911-474503 ወይም ነጻነት ተስፋዬ - 0911485961                                                       
የበጎ ሰው ሽልማት አስተባባሪ ኮሚቴ
በተቻለ መጠን ሁሉ ለሌሎች እንዲደርስ ‹ሼር› ያድርጉት

3 comments:

  1. Its better if you list out (Notify us) those Individuals who win the prize before.. so that there will not be a duplication of choice.

    ReplyDelete
  2. Bemengistawi halafinetin bebiqat bemewexat - DR Abiy Ahimed! 100%%%%%%%%%%%%%%%%%%%%%%

    ReplyDelete
  3. I want to admire he who established the prize BC it make us to see the ''begosew'' from the far

    ReplyDelete