Wednesday, May 2, 2018

ውስጠ ወይራ


ነፍስ ሔር አቡነ ጴጥሮስ እንዲህ ነግረውኝ ነበር
ሰውዬው ቅኔ ሊቀኝ ቅኔ ቤት ይሄዳል፡፡ የገጠሙት መምህር ቀናነት አልነበራቸውምና ተቀኝቶ እንዲወጣ አልፈለጉም፡፡ ‹ሶበ› ብሎ ተቀኝቶ ሲመጣ፣ ‹እስመ› ብለው ያርሙታል፡፡ ‹እስመ› ብሎ ሲቀኝ ‹አምጣነ› ብለው ያስተካክሉታል፤‹አምጣነ› ብሎ ሲመጣ ‹አኮኑ› ይሉታል፡፡ ተሰቃየ፡፡ በዚህ ቢላቸው በዚያ የሚፈልገውን ዕውቀት አግኝቶ የሚፈልግበት ደረጃ እንደማይደርስ ገባው፡፡ በብዙ መንገዶች ለማባበልም፣ ለመለማመጥም፣ ጽሙድ እንደ በሬ ቅኑት እንደ ገበሬ ሆኖ ሊያገለግላቸውም ሞከረ፡፡ አልሆነም፡፡ በመጨረሻ መረረው፡፡
አንድ ቀን አራቱንም አስገብቶ አንድ ቅኔ አዘጋጀና ወደ መምህሩ ዘንድ ሄደ፡፡ ሲሄድም ባዶ አጁን አልነበረም፡፡ በጋቢው ውስጥ የወይራ ፍልጥ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ከተቀበሉት ይቀበላሉ፤ ካልተቀበሉትም ወይራው ሥራውን ይሠራል፡፡
መምህሩ ዘንድ ሲቀርብ በጋቢው ውስጥ የተሸፈነውን የወይራ ፍልጥ አዩት፡፡ እርሱም ድምጹ ከፍ አድርጎ ‹ሶበ፣ አኮኑ፣ እስመ፣አምጣነ፣› ብሎ ቅኔውን ተቀኘ፡፡ከዚያም መምህሩን ‹እንዴት ነው?› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ መምህሩም ‹ምንም አይል ውስጠ ወይራ ነው› አሉት አሉ፡፡
ሕዝብም እንደዚህ ነው፡፡ በዚህም በዚያም ሲል መንገዱን ሁሉ ከዘጋህበት የመረረው ቀን ‹ሶበ፣ አኮኑ፣ እስመ፣አምጣነ፣› ብሎ ሁሉንም አከታትሎ ያመጣዋል፡፡ በዚያ ጊዜ መርጠህ የመቀበያህ ጊዜ ስለሚያልፍ ብቸኛው አማራጭህ ሁሉንም መቀበል ይሆናል፡፡ ምክንያቱ? ያልክ እንደሆነ ነገሩ ውስጠ ወይራ ነውና፡፡ ሰሞኑን በየከተማው ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች የሚያሳዩን ይሄንን ነው፡፡ ሕዝቡ መንገዱ ሁሉ ተዘግቶበት፣ ያቀረበውን ሁሉ የሚቀበለው አጥቶ ከመኖሩ የተነሣ ‹ሶበ፣ አኮኑ፣ እስመ፣አምጣነ፣› እያለ አንድ ላይ አመጣው፡፡ ግን ቅኔውን ብቻ አይደለም ‹ውስጠ ወይራ ነው›፡፡ መስቀል ተሰላጢን ይዟል፡፡ በመስቀሉ ይባርካል፤ በሰላጢኑ ይወጋል፡፡
ብልህ መሪ ‹ሶበ፣ አኮኑ፣ እስመ፣አምጣነ፣› አንድ ሆነው ሲመጡ ውስጠ ወይራ መሆኑን ዐውቆ ማድረግ ያለበትን በጊዜው ያደርጋል፡፡    


7 comments:

  1. "ሕዝብም እንደዚህ ነው፡፡ በዚህም በዚያም ሲል መንገዱን ሁሉ ከዘጋህበት የመረረው ቀን ‹ሶበ፣ አኮኑ፣ እስመ፣አምጣነ፣› ብሎ ሁሉንም አከታትሎ ያመጣዋል፡፡"

    ReplyDelete
  2. ምንም አይል ውስጠ ወይራ ነው

    ReplyDelete