ብሽሽቅ ሃይማኖትም፣ ፖለቲካም፣ ወግም ሥርዓትም አይደለም፡፡ ብሽሽቅ ከከሠረ ኅሊና የሚበቅል
‹አገር አጥፋ› አረም ነው፡፡ ‹አገር አጥፋ› አረም የከብቶች ፀር የዕጽዋት ቀበኛ የሆነ ገበሬ አስቸግር አረም ነው፡፡ ‹አገር
አጥፋ› አረም መስከረም መጥባቱን የሚያበሥረንን አደይ አበባ ሳይቀር ከሀገር የሚያጠፋ አረም ነው፡፡ አረሙን ከብቶቹ ስለሚያውቁት
በአካባቢው ድርሽ አይሉም፡፡ ለስሙ የሚያፈካውን አበባ ንቦች ከቀሰሙት ማር ሳይሆን የሚገድል መርዝ ነው፡፡ ግዛቱን ሲያስፋፋ ከአውሮፓ
ቅኝ ገዥዎችም ይብሳል፡፡ አገር ምድሩን ነው የሚወርረው፡፡ ዋናው ተግባሩ ሌላውን ሁሉ እያወደመ ራሱን ብቻ ማስፋፋት ነው፡፡ የግጦሽ መሬቱን ለመቆጣጠር ግልቢያው ከፍተኛ ነው። በተለይም በአውስትራሊያና በአፍሪካ ከፊል አካባቢዎች ተዛምቷል። በሕንድ «የኮንግረሱ ሳር»
በሚል መጠሪያው ይታወቃል። በ28 ቀን እራሱን የሚተካ ሲሆን፤ ዓመቱን ሙሉ አብቦ ይቆያል።
እስከ አንድ ሜትር የሚረዝም ሥር ስላለው ሀገሩን ሁሉ ይቆጣጠረዋል። ዘሩ እስከ ሃያ ዓመት መሬት ላይ መቆየት ይችላል። የዋግ ሕምራ ገበሬዎች ‹አገር አጥፋ› ብለው የሰየሙትን ይሄንን አረም ሳይንቲስቶቹ
‹Parthenium hysterophorus› ብለው ይጠሩታል፡፡
ብሽሽቅም እንደዚሁ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በፖለቲካውና
በሃይማኖቱ መስክ ሠፍኖ አገር እያጠፋ ነው፡፡ የምንጽፈው ጽሑፍ፣ የምንለጥፈው ፎቶ፣ የምንሰጠው ትምህርት፣ የምናቀርበው ምስክርነት፣
የምንሠራው ሥራ፣ የምንለግሰው ሐሳብና የምንገልጸው አቋም የቆምንበትን ዓላማ ለማስረዳትና አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት መሆኑ ቀርቶ
ሌላውን ለማናደድ፣ ለማቃጠል፣ ለማበሳጨት፣ አንጀቱን ለማሣረርና ቆሽቱን ለማድበን፣ ጨጓራውን ለመላጥና ጥሎ ለማንኮታኮት እየሆነ
ነው፡፡ ነገራችን ሁሉ ጠላት ተኮር እየሆነ ነው፡፡