Wednesday, April 25, 2018

የሙሴ + አሮንና ሖር = ድል
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ የመሪና የተባባሪ ድርሻን ከሚገልጡ ታሪኮች አንዱ የሙሴና፣ የአሮንና የሖር ታሪክ ነው(ዘጸ. 17÷8-16)፡፡ 
 
አማሌቃውያን ከእስራኤል ጋር ሲዋጉ ኢያሱ ጎልማሶቹን ይዞ ከአማሌቃውያን ጋር ይዋጋ ነበር፡፡ ሙሴ ደግሞ ወደ ኮረብታው ወጣ፡፡ ሙዜ እጁን ባነሣ ጊዜ እስራኤል ድል ያደርጋሉ፡፡ ሙሴ ደክሞት እጁን ባወረደ ጊዜ ደግሞ አማሌቅ ድል ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሙሴ ቀኑን ሙሉ ዋለ፡፡ በመጨረሻ ግን የሙሴ እጆች ከበዱ(ደከሙ)፡፡ ይህን የተመለከቱት አሮንና ሖር ለሙሴ የድንጋይ ወንበር አዘጋጁለት፤ ሙሴም እዚያ ድንጋይ ላይ ተቀምጦ እጁን ዘረጋ፡፡ ድሉም ለእስራኤል ሆነ፡፡ ነገር ግን አሁንም ሙሴ እጆቹ እየደከሙ መጡ፡፡ አሮንና ሖርም በግራና በቀኝ ሆነው የሙሴን እጆች ከፍ አድርገው ደገፏቸው፡፡ ያን ጊዜ ሙሴ እጆቹን አነሣ፡፡ እስራኤልም አማሌቅን ፈጽመው ድል አደረጉ፡፡
 
አንድ መሪ ውጤታማ የሚሆው ብቻውን አይደለም፡፡ እንኳንና በሰዎች የተመረጠ መሪ እግዚአብሔር የመረጠው ሙሴ እንኳን ብቻውን ውጤታማ መሆን አልቻለም፡፡ መሪ ምን ጠቢብ፣ ጎበዝ፣ ውጤታማ፣ ተወዳጅና ዐቅም ያለው ቢሆንም እንኳን እንደ ሙሴ እጆች መዛሉ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህም እንደ አሮንና እንደ ሖር መንገዱን አይቶ የሚደግፈው ይፈልጋል፡፡ መልካም መሪ ውሳኔዎቹ፣ የለውጥ ሐሳቦቹ፣ ዕቅዶቹና ቃል ኪዳኖቹ ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያበረቱት አሮንና ሖር ይፈልጋል፡፡ አሮንና ሖር ለሙሴ የተሰጠው አልተሰጣቸውም፡፡ ነገር ግን ሙሴን ደግፈው የሚፈልጉትን ውጤት አመጡ፡፡ ሁሉም ሰው መሪ ባይሆንም የመልካም መሪን ሐሳብ፣ ዕቅድ፣ ራእይና ውሳኔ በመደገፍ ግን ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡
 
ሁሉም ሰው ደራሲ ባይሆንም የደራሲውን እጆች መደገፍ ግን ይችላል፡፤ ሁሉም ሰው ተመራማሪ ባይሆንም የተመራማሪውን እጆች ግን መደገፍ ይችላል፡፡ ሁሉም ሰው የበጎ አድራጎት ማኅበር መመሥረት ባይችልም የበጎ አድራጎት ማኅበራቱን እጆች መደገፍ ግን ይገባል፡፡ ሁሉም ሰው የፖለቲካ ፓርቲ መመሥረት አይገባውም፡፡ የፓርቲዎቹን እጆች መደገፍ ግን ይቻላል፡፡ ሁሉም ሰው ሐሳብ ላያመነጭ ይችላል፡፡ የሐሳብ አመንጭዎችን እጆች ግን መደገፍ ይገባል፡፡ ሁሉም ሰው ታጋይ ላይሆን ይችላል፤ የታጋዮችን እጆች መደገፍ ግን ይገባል፡፡ 
 
ሙሴ አንድ ደጋፊዎቹ ግን ሁለት ነበሩ፡፡ ምንጊዜም ከደጋፊዎች ተደጋፊዎች ያንሳሉ፡፡ ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለምን የለወጧት ጥቂት ባለ ተሰጥዖዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ሐሳባቸውን፣ መንገዳቸውን፣ ድርሰታቸውን፣ ምርምራቸውን፣ ሙከራቸውን፣ አመራራቸውን፣ ትምህርታቸውን፣ ጥረታቸውን የሚደግፉ ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ ሚዲያዎች፣ መንግሥታትና ማኅበረሰቦች በማግኘታቸው ውጤታማዎች ሆኑ፡፡ 
 
ብዙ ሙሴዎች አሮንና ሖርን አጥተው እጃቸው ዝሎ ድል ሆነዋል፡፡ መንገዱ፣ ሐሳቡ፣ ውጣ ውረዱ፣ ሙግቱ፣ ጭቅጭቁ፣ የሰው ትችትና ወቀሳ፣ ስድብና ዕንቅፋትነት አዝሏቸው ድል ከማድረግ ድል ወደመሆን ወርደዋል፡፡ ክብሪቱን የሚያግዙት እንጨቶች ጠፍተው ቦግ ብሎ ጠፍቷል፡፡ በታሪካችን ብዙ ሙሴዎች መጥተው ነበር፡፡ ነገር ግን የሚያግዛቸውና ክንዶቻቸውን የሚደግፍ፤ ቢያንስ የድንጋይ መቀመጫ እንኳ የሚሰጥ አጥተው በሞትና በሽፈት ድል እየሆኑ ተገቢውን ለውጥ ሳያመጡ ቀርተዋል፡፡ 
 
ድል የማድረጊያ አንዱ መንገድ ብርቱዎቹን መደገፍ ነው፤ ክንዳቸው፣ ድምጻቸው፣ ሥራቸው፣ ጥረታቸው፣ ሐሳባቸው፣ ትግላቸው፣ ከፍ ሲል ድል የሚያደርጉትን መደገፍ ነው፡፡ መጥፎ ሠሪዎችን ከምንቃወመው በላይ መልካም ሠሪዎችን የማንደግፍ ከሆነ ውጤት አናመጣም፡፡ 
 
የሙሴም ታላቅነት ምን መሪ፣ እጆቹ ታላቅ ሥራ የሚሠሩና ድል አድራጊ ቢሆንም ሊደክም፣ ሊሸነፍ፣ ሊያቅተውና ሊዝል እንደሚችል አመነ፡፡ ያለ ሌሎች ድግፋ ብቻውን ለውጥ እንደማያመጣ ተቀበለ፡፡ ታላቅነት ማለት የታናናሾችን አስተዋጽዖ መናቅ አይደለም፡፡ ሁሉን ብቻዬን አደርገዋለሁ አላለም፡፡ አሮንና ሖር እንደሚያስፈልጉት ተቀበለ፡፡ ጎበዝ ሰው እንዲህ ነው፡፡ ሁሉንም ለብቻዬ እችለዋለሁ አይልም፡፡ የአንድ ሰው ውጤታማነት የብዙ ሰዎች አስተዋጽዖ ውጤት ነውና፡፡ ድል የሙሴም፣ የአሮንና የሖርም የየብቻ ውጤት አይደለም፡፡ ድል የሙሴ፣ የአሮንና የሖር የኅብረት ውጤት ነው፡፡

13 comments:

 1. አንድ መሪ ውጤታማ የሚሆው ብቻውን አይደለም፡፡ እንኳንና በሰዎች የተመረጠ መሪ እግዚአብሔር የመረጠው ሙሴ እንኳን 'ብቻውን ውጤታማ መሆን አልቻለም፡፡ መሪ ምን ጠቢብ፣ ጎበዝ፣ ውጤታማ፣ ተወዳጅና ዐቅም ያለው ቢሆንም እንኳን እንደ ሙሴ እጆች መዛሉ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህም እንደ አሮንና እንደ ሖር መንገዱን አይቶ የሚደግፈው ይፈልጋል፡፡

  ReplyDelete
 2. ከታሪኩ እንደተረዳነው ሙሴ ይደግፉት ዘንደ አልተጣራም ነገር ግን መደገፍ እንዳለበት የተረዱት አሮንና ሖረ ሊደግፉት መጡ ድሉም የጋራቸው ሆነ!
  የዛሬው ሙሴያችን ግን የኛን ድጋፍ እንደሚሻ አበክሮ በመናገር ላይ ይገኛልና የእስራኤላውያንን ድል ለመድም እንትጋ!!! ዲ/ን እናመሰግናለን

  ReplyDelete
 3. ህዝባችንን አሮንንና ሆርን ዶክተር አቢይን ኢትዮጵያዊ ሙሴ ያድርግልን።አሜን።

  ReplyDelete
 4. መጥፎ ሠሪዎችን ከምንቃወመው በላይ መልካም ሠሪዎችን የማንደግፍ ከሆነ ውጤት አናመጣም ግሩም ነው፡፡ መተባበርን የመሰለ አቅም የለም ቀና መሆን ነገሮችን እንዲከናወንልን ያደርጋል፡፡

  ReplyDelete
 5. በጣም ትክክል ነው ዲ/ዳንኤል፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ጥሩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ያሉን ቢሆንም፡ ጥሩ የሚሠራን ጥሩ ሠርተሃል መጥፎ ግብር ላይ ያለውን ይህ ጥሩ አይደለም ወደ በጎ ተመለስ ብሎ በጎውን ማሳየት የሚባል በህላችን ግን በጣም እጅግ በጣም የወረደ በመሆኑ፡ እንደውም በተቃራኒው ጥሩ የሚሠራውን የምናደናቅፍበትን ስናወጣና ስናወረድ ስንባዝን እንደምንውል በየመስሪያ ቤቱ ያሉ ታሪኮች አስረጂ ናቸው፡ በተለይም ይህ ክፉ መንፈስ ባለፉት 27 ዓመት ውስጥ የተከተልነው ሥራዓት ያመጣብን ደዌ ነው፡ ስለሆነም የነበረንን ቀና አስተሳሰብ ይዘው የቆዩት ጥቂቶች ሲሆኑ ብዙዎች ግን በዚህ ክፉ ደዌ ተመተናል፡፡ ከዚህ ሥርዓት በፊት ግን ምናልባትም ክፉዎች ጥቂት ነበሩ፡፡ የሆነው ሆኖ ይህን የነሙሴን ነገር ያነሳህበት ጉዳይ ወቅታዊው በሀገራችን በሚታየው የብርሃን ጭላንጭል ላይ በማወቅም ባለማወቅም ለማኮሰስ የሚተቹ ሰዎችን ስለሚመለከት ነው፡ በእኔም አስተያት አብዛኛው እንደውም አዋቂዎች ወይም የተመራመሩ የምንላቸው ሰዎች እያደናቀፉ እንደሆነ እየተሰማኝ ነው፡፡ ለምን ብትለኝ አሁን መንበረ ስልጣኑን የተረከቡት ሰው 27 ዓመት ሙሉ በመዋቅር፣ ታስቦበት ስትፈርስ ስትወድቅ ስትነሳ ስትጎሳቆል የኖረችን ሀገር በአንድ ለሊት ወደ ከዛ በፊቷ የነበረችውን ኢትየጵያ እንዲያመጧት መፈለጋቻው እውነቱን ለመነገር ለእኔ ምስጢር ሆኖብኛል፡ እያንዳንዱ ምሁር ይሁን ተፎካካሪ፣ ጋዜጠኛ ይሁን አስተማሪ ማንም ይሁን ራሱን በእሳቸው ቦታ እያስቀመጠ ቢተች ምኞቱን ሳይሆን በተጨባጭ ሊሆን የሚችለውን በጥንቃቄ በመተንተን መሪውንም ተመሪውንም የሚደግፍ የሚያበረታ ሀሳብ ያወጣል ያስተምራል ይማራል፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ግን እኔ እንዳሰብኩት አንዳንዶቹ ስለኢትዮጵያ ሀሳቢ ተቆርቋሪ በሚመስል ሃሳብ ውስጥ እነዚህ የለውጥ ኃይል እያልን የምንጠራቸውን እነ ለማን ገዱን ጨምሮ እና ሌሎችንም የያዙትን መስመር ላመደናቀፍ እየመሰለኝ ነው፡ ይህንን ያልኩበት ዋና ነጥቦች ላንሳ፡-
  1. እኛ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ሁለት ሥርዓት ( የኢህአዴግና የዘመነ ደርግ ማለቴ ነው) የለመድነው የሥርዓት እና የፖለቲካ ለውጥ በመበቃቀልና የነበረውን ድራሹን አጥፍቶ በፍርስራሹ ላይ አዲስ ሥርዓትን በመገንባት እራሳቸው መሪዎቹ እየተደናበሩ የሚመሩትንም ህዝብ እያደናበሩ ህዝቡን እየመሩት ሳይንሆን እንደ ከብት ከኃላ ሆነው በጅራፍ እየነዱ ስለሚያስተዳደርን እና ይህንን ልምድ እንደ ትክክል አድርገን በመቁጣረችን ዛሪም በምሁራኑም ይሁን በአንዳንድ ሰዎች የሚታየው አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ሰው ይህንኑ እንዲደግሙ የሚማጸኑ ናቸው፡፡ ግን ሰውየው እየሠሩ ያሉት መጀመሪያ መሥራት ያለባቸውን እየሠሩ መሆኑን ማወቅ ያለብን ይመስለኛል ይህ ህዝብ 27 ኣመት የስነልቡና ጉዳት የተጫጫነው፣ የተጎዳና በአብዛኛው ተስፋ ቆርጦ አሁንስ በዛ እያለ በአምላኩ ላይ እያጉረመረመ ያለን ህዝብ ህዝቡ መሀል እየገቡ የማረጋገትና ተስፋ እንዲሰንቅ ማድረግ ወደ ኖርሙ መመለስ የመጀመሪያውና ትልቁ ሥራ እንደሆነ እኔም በግሌ ትክክል እንደሆነ አምኜበታለሁ፡ ስለዚህም ይህ ትክክል ስለሆነ ልንደግፈው እንጂ ልናደናቅፈው አይገባም፡ ምንም እንኳን ይሀን ስል ከልቤ የሚያሳዝነኝም ቢሆን አሁን እየተጠየቀ ያለው የስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይነሳ፣ ነበሮቹ ባለሥልጣንት ተመልሰው ለምን ወደ ስልጣን መጡ፤ ጉብኝቱ ይብቃዎት ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ወይም ትችቶች ያደናቅፋሉ ብዬ አስቤአለሁ፡ ምክንያቱም ሁሉም ነገር በቅደም ተከተል በጊዜው የሚሆን ስለሚሆን፡ ነባር ባለሥልጣነትን እንዳለፉት ሥርዓት እስርቤት መወርውር ወይም እንደው መበቀል የብልህ መሪ አስተሳሰብ ሳይሆን ያለፈውን መድገም ነው፡ ሰውዬው የሥራ ሰው ይመስሉኛል ስለዚህ እኒህን ወደ ሥልጣን ያመጠዋቸውን ሰዎች በትክክለኛው የመሥራትና የማሠረት መስመር አምጥቶ በሥራ መፈተሸ ትልቅ ብልህነት ነው፡ ይችለዋል ሥረውን ይሠራል ከሠራ እሰየው ካልሠራ ለሚሠራ እንዲለቅ የሚያደርጉ ይመስለኛል ነገር ግን ሌላ ወንጀል ካለበት ደግሞ ራሱን የቻለ ሥርዓት ስላለ በዛ ሥርዓት (በህግ )ይስተናገዳል፡ ስለዚህ ያለ ብቀላ ያለ ግጭት መምራት ማለት ይህ አይመስላችሁም፡ ቢዘህ ጉዳይ ላይ ፐሮፈ. መስፍንና አቶ አብዱ (በሸገር የሚቀርቡት ምሁር ) የሰጡት ሀሳብ ዳጋፊ አበረታችና አስተማሪ በመሆኑ ሁሉም ሰው ወደዚህ ቀልብ ቢመለስ ጥሩ ይመስለኛል፡፡
  2. እኚህ ሰው በጥንቃቄ በተተነተነ ሃሰብ ድጋፍ የሚፈልጉበት ሌላው ዋና ጉዳይ( ለሌሎቹም በሥርዓት ውስጥ የተፈጠሩ ለውጥ ፈላጊዎች በሙሉ) በማያሠራ ሥርዓት ውስጥ 27 ዓመት በጉልበት እየገዛ፤ እየገደለ፤ እያሰረ እያሳደደ ፍጹም አምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ ሆነው ይህ አካሄድ ኢትዮጵያን የትም አያደርሳትም በማለት ፊት ለፊት ተጋፍጠው የሞትና የህይወት ትንቅንቅ ውስጥ የገቡ አስተሳሰብን በመለወጥ ቀስ በቀስ ኢትዮጵያ ወደ ሚያስፈልጋት ሥርዓት ውስጥ ለማስገባት በየጊዜው እየተንጠባጠበ የሚከፈል መስዋዕትነትን በማስቀረት ለኢትዮጵያን ወገኖቻቸናነ ለኢትዮጵያ መስዋዕትነት ለመክፍል የተዘጋጁ ናቸው ብዬ አምኛለሁ፡ ስለዚህ በፊት እንዳልኩት የጠቅላይ ሚኒስተርነትን ቦታ ስለያዙ እኛ እንደምንመኘው የነበሩትን ወደ እስር ቤት በማስገባት ሥራ መጀመር ትክክልም ተገቢም አይደለም ዞሮ ዞሮ እሰከአሁንም ቢሆን የህዝብ ሳይሆን የመሳሪያ ኃይል ያለው በእነዚሁ 27 ዓመት ግራ በገባውቸው መሪዎች እጅ በመሆኑ የስርዓቱ መዋቅርም ያው ስለሆነ፡፡ ስለዚህ ተቺዎች፣አስተያት ሰጪዎች ጋዜጠኞች ምሁራኖች፣በውጭም በሀገር ውስጥም ያላችሁ ተፎካካሪ ድርጅቶች ሰወየው የተቀመጡበት ወንበር ላይ ለደቂቃ እራሳችሁን እያስቀመጠችሁ የሚያበረታ፣ የሚገነባ፣ የበለጠ ስለኢትዮጵያችን ኃላፊነትን የሚጭንባቸውን ገንቢ አስተያት ብትሰጡ ሁላችንም ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡ ሁላችንም እንደ ድርጅት ወይም እንደግለሰብ በሚየስገኝልን የጥቅም ዕይታ ላይ ብቻ ቁጭ ብለን አፍራሽ ሃሳቦችን አንሰንዝር እላለሁ፡፡ እንደ ሀገር-ሀገር የምትጠቀምበትን ነገር በህብረት ሥንሥራ እንደግለሰብ እና እንደድርጅት አብዝተን ተተቃሚዎች እንሆናለን፡፡
  3. ሌላው ያለኝ አስተያየት እንደ ጥላቻ ወይም ደግሞ እንደ ጽንፈኛ አይቆጠርብኝ ግን እውንት ስለሆነ እንዲህ እላለሁ፡፡
  ህውሃቶች ምን አልባት ዳግም ከ3000 ዘመን በኋላ ወደ ስልጣን የመምጣት እደሉ ቢገጥማችሁ እንዴትት ህዝብን መንዳት ሳይሆን ህዝብን መምራት እንዳለባችሁ እባካችሁ እራሳችሁን በትህትና ትንሽ ዝቅ አድርጉና ጠቅላይ ሚ/ር አቢይ እግር ስር ቁጭ ብላችሁ ተማሩ እግዚአብሄር የርዳችሁ፡

  ReplyDelete
 6. Daniel meche MN malet endalebh yemtawk bkat yaleh sew nehi

  ReplyDelete
 7. We are part of the positive side. We have been advocating for good things to be on the top of the mountain. We have been encouraging people to give a chance for the Leader. But on the other side, the change has to be continuous to convince the people that tired of lies for the last 26 years. The Leader looks good and good things have been coming out from his speech. WE would like to say Thank you for that.

  Justice has to be prevaile, the corrupt bad apples has to resign. Institution has to be rebuild to assure the public...

  ReplyDelete
 8. ሚያዝያ 19 ቀን 2010 ዓ.ም.

  ወንድሜ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፡- ከነቤተሰብህ እንደምን ሰነበትክ? እኔ እና ቤተሰቤ በጣም ደህና ነን፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
  ዳኒ፡- መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት አድርገህ የመሪ እና ተመሪን ድርሻ የገለጽክበት መንገድ እንደወትሮው ሁሉ በጣም አስተማሪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡ አሁንም ደግመህ ደጋግመህ የምትጽፍበትን ዕድሜ እና ጤናውን ያድልህ፡፡ በምክረ ሃሳብህ እንደገልጽከው አንድ መሪ ምንም ጠንካራ ቢሆን ብቻውን የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አይችልም፡፡ በታሪካችን እንደምናየው በተለያዩ ጊዜ ለኢትዮጵያ ትንሣኤ እና ዕድገት ጥሩ ራእይ የነበራቸው መሪዎች በየጊዜው ከነበረው ሕዝብ እና በመሪዎቹ ዙሪያ ከተሰበሰቡት ሹመኞች ድጋፍ ከማጣታቸው የተነሳ (በማወቅም ባለማወቅም ሊሆን ይችላል) በየዘመናቸው የሚፈለገውን ለውጥ ሳያመጡ እንዳለፉ እናስተውላለን፡፡ ከዚህ የምንረዳው የአንድ መሪ አመራሩ የሰመረ ሊሆን የሚችለው በዙሪያው ያሉ ሹመኞች፣ አማካሪዎች እና ወረድ ሲል ደግሞ ሕዝቡ የመሪውን ሐሳብ እና ዓላማ ተረድተው ድርሻቸውን ተገንዝበው የሐሳብ እና የተግባር ድጋፍ ሲሰጡ ነው፡፡

  መሪን የመርዳት በጎ ተግባር ደግሞ የሚመነጨው ለሀገር እና ሕዝብ ከሚኖረን እውነተኛ ፍቅር ነው፡፡ ሙሴ ጥልቅ የሀገር እና የወገን ፍቅር እንደነበረው እና ለዚያም የከፈለውን ዋጋ እዚህ ጋ ማስተዋሉ ይጠቅማል፡፡ ረዳቶቹም እንዲሁ፡፡ እንዲያውም ካነሳው ዘንዳ እዚህ ላይ የሚገርመው ነገር ሙሴ እና ረዳቶቹ ሕዝባቸውን ከአስከፊ ባሪነት ነጻ አውጥተው በእጃቸው ወዳልነበረችው ከነዓን ለመድረስ ያሳዩት የመሪነት ብቃት እና የተባባሪዎች ድርሻ ከምንገምተው በላይ ሲሆን ነው፡፡ እኛ ግን ኢትዮጵያ በእጃችን ናት፡፡ እጅግ በጣም ድንቅ የሆነ የሀገር ፍቅር ያለው ኩሩ ሕዝብ እና ኢትዮጵያን ከፍ አድርጎ የሚጠራት፤ ሕዝቧንም የሚያከብር ባለራእይ መሪ ሲያገኝ እንዴት ወደየ አደባባዮቹ እንደተመመ እና ደስታውን እንደገለጸም ተመልክተናል፡፡ ስለሆነም አሁንም የመሪው እና ተመሪው ተናቦ፣ ተግባብቶ እና ተረዳድቶ መጓዝ ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ከፍታዋ ሊወስዳት ይችላል፡፡ ለነገሩ የነሙሴስ አማካሪዎች ኢትዮጵያዊያን አልነበሩምን?

  ReplyDelete
 9. እኔ ሁሌም ከአንተ ጽሑፎች እማራለሁ። ሳነባቸውም በዘርፍ በዘርፉ የሚሰጡትን ትርጉም በመመርመር ጭምር ነው (situational analysis) እንደሚሉት። ይህም ጽሑፍ መልከ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፤ እንደዘረዘርከው። እኔ ግን የመርጥኩት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መነፅርነት መመልከትን ነው።

  ዴሞክራሲ በሚባል 27 ዓመት እንደ መስቲካ ተላምጦ ጣዕመን ባጣ ቃል ከዳሸን ተራራ የገዘፈውን የኢትዮጵያን ችግር ማስወገድ ቀርቶ ጥቂቱን እንኳን መቅረፍ እንደማይቻል የ27ቱ የስካር ፖለቲካ ከበቂ በላይ ያስረዳል። ይኼ ቀልድ የገባቸው (ያሳዘናቸው) የመገርሣ ልጅ ለማ፥ የአሕመድ ልጅ አብይ፥ የአንዳርጋቸው ልጅ ገዱ - ሠለስቱ ተነሱ። ወይ ጉድ፥ይሄ "ሠለስቱ" በአብዮቱ ጊዜም ገጥሞን ነበር። አጋጣሚ ነው ወይስ እውነታ፥ ለልማት ነው ለጥፋት? እንጃ።

  የሆነው ሆኖ፥ አንተው በሰጠኽን ምሳሌ ልሞግታ። አብይ ደጋፊዎች ያስፈልጉታል፥ መርሐ ዕቅዱን የሚያስፈጽሙለት (executive cabinet)፥ አብይ ሃሳብ ጠሊቃን ያስፈልጉታል (Think Tank)፥ የተሰወረውን የሚከስቱ፥ የጨነቀውን (ያበጠውን) በመፍትሔ ወጌሻ የሚፈውሱ።

  እስከ አሁን ያየሁት ግን ይህን አያመላክትም። ባለፉት 40ዓመታት በተለይም በ27ዓመታት ኢትዮጵያ ያፈራቻቸው "ምሑራን" ዐባይ ፀሐዬ፥ አባዱላ ገመዳ፥ በረከት ስምዖን፥አርከበ ዑቊባይ፥ፕሮፌሰር ጀነራል ሳሞራ የኑስ፥ስዩም መስፍን፥የእርሻው "ሳይንቲስት" ሽፈራው ሽጉጤ፥ደመቀ መኮንን፥የመሳሰሉትን ብቻ ነው። እነዚሁ ሰዎች አይደሉም እንዴ ለአገር በቀል ስደት (ዘር ተኮር መፈናቀል)፥ለሜጋ ፕሮጀክቶች መውደም (Sugar Development Projects)፥ ለሙስና መስፋፋት (think of 10k tones of export grade coffee robbed from warehouse on vivid daylight, 5 billion birr considered bad debts; embazzled from DBE)፥ በቁጥር ብቻ ለሚፋፋ "አስደናቂ" እድገት፥ ለመጠን የለሽ ጭፍጨፋ የዳረጉን።

  እነዚህን ሰዎች የመሴ እጆች ደጋፊ፥ የብርታት መቀመጫ አናጺ አድርጎ መቀበል ይቻላል? ካቢኔው፥አማካሪዎቹ እኮ 27 የምናውቃቸው ቀድሞም ጥልቅ እሳቤ ያልፈጠርባቸው፥ እርጅናው ተጨምሮ ኡ ኡ የሚያሰኙ ዲሽቃዎች ናቸው። ዲሽቃ የጎረሰውን መልሶ ይተፋል። የአብዮታዊ ዴሞክራሲ "መንፈስ" እነሱ ላይ ሰርፆ ወደ በጎ መለውጣቸውን ሳያሳዩን፥ እኛም ለውጡን ሳንመሰክር እነሱም አረጁ ኢትዮጵያም መቀመቅ እየወረደች ነው።
  ዳን ኤል ሆይ፥ እየወቀስክ ነው? ወይስ ደግፉ እያልክ? ዶር አብይን ለመደገፍ የፖለቲካ ጮሌ መሆን አይጠበቅብኝም። ኢትዮጵያዊነቴ ያስገድደኛል። ግን በእነዚህ የካቢኔ አባላት ተስፋ ላድርግ፧(በእነሱ ዲሽቃ በቀላሉ የሚበረቀስ mindeset የለኝም)አልሞክረውም።

  ReplyDelete
 10. እኔ ሁሌም ከአንተ ጽሑፎች እማራለሁ። ሳነባቸውም በዘርፍ በዘርፉ የሚሰጡትን ትርጉም በመመርመር ጭምር ነው (situational analysis) እንደሚሉት። ይህም ጽሑፍ መልከ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፤ እንደዘረዘርከው። እኔ ግን የመርጥኩት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መነፅርነት መመልከትን ነው።

  ዴሞክራሲ በሚባል 27 ዓመት እንደ መስቲካ ተላምጦ ጣዕመን ባጣ ቃል ከዳሸን ተራራ የገዘፈውን የኢትዮጵያን ችግር ማስወገድ ቀርቶ ጥቂቱን እንኳን መቅረፍ እንደማይቻል የ27ቱ የስካር ፖለቲካ ከበቂ በላይ ያስረዳል። ይኼ ቀልድ የገባቸው (ያሳዘናቸው) የመገርሣ ልጅ ለማ፥ የአሕመድ ልጅ አብይ፥ የአንዳርጋቸው ልጅ ገዱ - ሠለስቱ ተነሱ። ወይ ጉድ፥ይሄ "ሠለስቱ" በአብዮቱ ጊዜም ገጥሞን ነበር። አጋጣሚ ነው ወይስ እውነታ፥ ለልማት ነው ለጥፋት? እንጃ።

  የሆነው ሆኖ፥ አንተው በሰጠኽን ምሳሌ ልሞግታ። አብይ ደጋፊዎች ያስፈልጉታል፥ መርሐ ዕቅዱን የሚያስፈጽሙለት (executive cabinet)፥ አብይ ሃሳብ ጠሊቃን ያስፈልጉታል (Think Tank)፥ የተሰወረውን የሚከስቱ፥ የጨነቀውን (ያበጠውን) በመፍትሔ ወጌሻ የሚፈውሱ።

  እስከ አሁን ያየሁት ግን ይህን አያመላክትም። ባለፉት 40ዓመታት በተለይም በ27ዓመታት ኢትዮጵያ ያፈራቻቸው "ምሑራን" ዐባይ ፀሐዬ፥ አባዱላ ገመዳ፥ በረከት ስምዖን፥አርከበ ዑቊባይ፥ፕሮፌሰር ጀነራል ሳሞራ የኑስ፥ስዩም መስፍን፥የእርሻው "ሳይንቲስት" ሽፈራው ሽጉጤ፥ደመቀ መኮንን፥የመሳሰሉትን ብቻ ነው። እነዚሁ ሰዎች አይደሉም እንዴ ለአገር በቀል ስደት (ዘር ተኮር መፈናቀል)፥ለሜጋ ፕሮጀክቶች መውደም (Sugar Development Projects)፥ ለሙስና መስፋፋት (think of 10k tones of export grade coffee robbed from warehouse on vivid daylight, 5 billion birr considered bad debts; embazzled from DBE)፥ በቁጥር ብቻ ለሚፋፋ "አስደናቂ" እድገት፥ ለመጠን የለሽ ጭፍጨፋ የዳረጉን።

  እነዚህን ሰዎች የመሴ እጆች ደጋፊ፥ የብርታት መቀመጫ አናጺ አድርጎ መቀበል ይቻላል? ካቢኔው፥አማካሪዎቹ እኮ 27 የምናውቃቸው ቀድሞም ጥልቅ እሳቤ ያልፈጠርባቸው፥ እርጅናው ተጨምሮ ኡ ኡ የሚያሰኙ ዲሽቃዎች ናቸው። ዲሽቃ የጎረሰውን መልሶ ይተፋል። የአብዮታዊ ዴሞክራሲ "መንፈስ" እነሱ ላይ ሰርፆ ወደ በጎ መለውጣቸውን ሳያሳዩን፥ እኛም ለውጡን ሳንመሰክር እነሱም አረጁ ኢትዮጵያም መቀመቅ እየወረደች ነው።
  ዳን ኤል ሆይ፥ እየወቀስክ ነው? ወይስ ደግፉ እያልክ? ዶር አብይን ለመደገፍ የፖለቲካ ጮሌ መሆን አይጠበቅብኝም። ኢትዮጵያዊነቴ ያስገድደኛል። ግን በእነዚህ የካቢኔ አባላት ተስፋ ላድርግ፧(በእነሱ ዲሽቃ በቀላሉ የሚበረቀስ mindeset የለኝም)አልሞክረውም።

  Tesfaye Aman

  ReplyDelete
 11. ጎበዝ ሰው እንዲህ ነው ፡ ሁሉንም ለብቻዬ እችለዋለሁ አይልም፡፡ I WOULD LIKE TO APPRECIATE YOU.THANKS DANIE FOR YOUR BEST ADVICE.

  ReplyDelete
 12. Weel said Daniyee! let's help the guy.

  ReplyDelete