Monday, April 16, 2018

ከመጽሐፈ ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ ጋር የተገኘው ለዐፄ ዘርአ ያዕቆብ የቀረበው ሙገሳ:- ስለ ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ መጽሐፍ የግእዝ ትርጉም ምን ይነግረናል?ይህ ከዚህ ቀጥሎ የተጻፈው ሙገሳ በፈረንይ ቤተ መጻሕፍት በቁጥር BNF ethiopien 68 ተመዝግቦ በተቀመጠው መጽሐፈ ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ መጽሐፉ ክፍለ ክርስቶስ በተባለ ሰው አስጻፊነት፣ ዘወልደ ማርያም በተባለ ጸሐፊ፣ በብርሃን ሰገድ ዐፄ ኢያሱ ጊዜ(1723-1747 ዓ.ም.) የተገለበጠ ነው(fol. 107b)፡፡ በመጽሐፉ መጨረሻ የሚገኙት የኅዳግ ማስተዋሻዎች በንጉሥ ኢያሱና በንጉሥ ኢዮአስ(1747-1761 ዓ.ም.) ዘመን የተመዘገቡ የመጻሕፍት ዝርዝሮችን ይዘዋል፡፡ ‹ኆልቆ መጻሕፍት ዘፃና› ይላል(107b,108a)፡፡ ፃና የተባለችው ገዳም ማን እንደሆነች የጠየቅን እንደሆነ በመጽሐፉ መጨረሻ ላይ ‹ተወጥነት መሠረተ ሕንጻሃ ለመቅደሰ ቂርቆስ ዘፃና[1]› የሚል ንባብ አለ(108b)፡፡ ይህም መጽሐፉ የጣና ቂርቆስ ንብረት እንደነበረ ያስረዳናል፡፡ በነዚያ የመጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ በሁለቱም የቆጠራ ዘመናት 2 መጽሐፈ ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ እንደነበረ ይገልጣል፡፡ እንግዲህ በኋላ ዘመን አንዱ ወቶ ፈረንሳይ ተሻግሯል ማለት ነው፡፡ በመቅድሙ ላይ ንጉሥ ዘርአ ያዕቆብን(fol.1a) በጸሎቱ ላይ ደግሞ አድያም ሰገድ ኢያሱን ያነሣል፡፡ 

ጊዮርጊስ ወልደ ዓሚድ(1199-1267ዓ.ም.) ክርስቲያን ዓረብ የታሪክ ጸሐፊ ነው፡፡ በግብጽና በሶርያ በቤተ መንግሥት ታላቅ ቦታ ነበረው፡፡ ከ1255-1261 ዓ.ም. ባለው ዘመን ውስጥ ከአዳም አንሥቶ ዓለም ዐቀፋዊ የሆነውን ታሪክ የያዘ ዜና መዋዕል አዘጋጅቶ ነበር፡፡ መጽሐፉ በዐፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት(1500-1533 ዓ.ም.) ወደ ግእዝ እንደተተረጎመ በብዙዎቹ ሊቃውንት ዘንድ ይታመናል[2]፡፡ ለዚህ አንዱ መነሻ ተርጓሚው የእስክንድርያ ፓትርያርኮችን ታሪክ በዐፄ ልብነ ድንግል ዘመን እስከነበሩት እስከ ፓትርያርክ አቡነ ገብርኤል(95ኛው) ድረስ ተርኮ ማቆሙ ነው[3]፡፡  ይህ ያገኘነው የፓሪሱ ቅጅ ግን ግብጽ በዐረቦች በተወረረችበት ዘመን ነው ታሪኩን የሚፈጽመው፡፡
ብራናው እንዲህ ይላል ‹ዘንተ መጽሐፍ ዘተከሥተ በኃሢሥ መፍቀሬ እግዚአብሔር ንጉሥነ ዘርአ ያዕቆብ ዘተሰምየ ቈስጠንጢኖስ[4] - ይህ መጽሐፍ የእግዚአብሔር ወዳጅ በሆነ፣ ቈስጠንጢኖስ በተባለ በንጉሣችን በዘርአ ያዕቆብ ፍለጋ ተገለጠ(ተገኘ)›(1a):: እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ተተረጎመ ከሚባልበት ከልብነ ድንግል ዘመን ቢያንስ 60 ዓመታት ይቀድማል ማለት ነው፡፡ የመጽሐፉ ቀደምት ጸሐፊ መጽሐፉን ፈልጎ ላስገኘው ለዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ረዥም የሙገሳ ግጥም አቅርቧል፡፡ በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን የገለበጠው ዘወልደ ማርያም ይህንን ሙገሳ በዐፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን ከተጻፈው መጽሐፍ እንዳለ ገልብጦ አቆይቶናል፡፡ በዚህ እናመሰግነዋለን፡፡ መጽሐፉ መጀመሪያ የተተረጎመው በዐፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን መሆኑን የሚጠቁሙ ፍንጮች በዚሁ ግጥም ውስጥ ይገኛሉ፡፡
1.    መጽሐፉ በዘመኑ ባይጻፍ ኖሮ ከ60 ዓመታት በኋላ አስታውሶ ይህን ምስጋና ዘወልደ ማርያም አይጽፍለትም ነበር፡፡ አንድም ቦታ ላይ በሕይወት ያለው ንጉሥ ልብነ ድንግልን ሳይጠቅስ በሞት ያለፈውን ዐፄ ዘርአ ያዕቆብን አያመሰግነውም፡፡
           2.     በዘመኑ ባይጻፍ ኖሮ ቀጥሎ የቀረበውን ሊጽፈው አይችልም ነበር
            ‹ዘከሠተ ግጻዌ ሥላሴ በበጾታሁ
            አብኒ ዘከመ ሰብሖ ለወልድ በስብሐቲሁ
            ወልድኒ ዘከመ ሀለወ ውስተ ሕጽነ አቡሁ
            መንፈስ ቅዱስኒ ዘከመ ይትቄደስ በሥላሴሁ
            ዘመሀረ ዘንተ ለሕዝበ ዚአሁ
           ከመ ኢያምልኩ ባዕደ ዘእንበለ እግዚአብሔር ፈጣሪሁ
           ዘመተሮ ለደስክ እም ሥረዊሁ
           ለማሪትኒ ወለ ጠፈንት
           ለመቃውዘይኒ ወለ ዲኖ
          ለጠንቃልያን ወለኩሎሙ እለ ያመልኩ ጣዖተ ወሥርያቲሁ› 
ምክንያቱም ዐፄ ዘርአ ያዕቆብ በምሥጢረ ሥላሴ የሥላሴን ገጻት በተመለከተ የተከራከረ፤ የጻፈና ያስተማረ መሆኑን በዘመነ ልብነ ድንግል የሚገለብጥ ጸሐፊ በዚህ ጥልቀት አይገልጠውም ነበር፡፡ ደግሞስ በዚህ ዘመን ከመጽሐፉ ጋር የማይሄድ ይህንን ምስጋና ለምን ያስገባዋል? መጽሐፉን ያስጻፈው ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ቢሆን ነው እንጂ፡፡ ዐፄ ልብነ ድንግል በዘመኑ በዚህ ረገድ ያደረገው ነገር አልነበረምና፡፡ በሌላ በኩልም ከላይ የተገለጡት ‹ደስክ፣ ማሪት፣ ጠፈንት፣ መቃውዘይና ዲኖ› በዐፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን ባደረገው አምልኮ ጣዖትን የማጥፋት ትግል ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡ በኋላ ዘመን የመጣ ጸሐፊ በዚህ መጠን አያስታውሳቸውም፡፡ በዘመኑ ያየና የተካፈለ ነው እንዲህ የዘረዘራቸው፡፡
           3.     ዐፄ ዘርአ ያዕቆብ በሕይወት እያለ ባይጻፍ ኖሮ ‹እግዚአብሔር ይፅብዖሙ በሰይፈ እዴሁ፤ወይውርዎሙ ለገሃነም እስከ ዕመቂሁ - እግዚአብሔር በእጁ ሰይፍ ይጣላቸው፤ ወደ ገሃነምም እስከ ጥልቁ ይወርውራቸው› የሚለውን አገላለጥ አይጠቀምም ነበር፡፡ ይህ አገላለጥ በሕይወት ለሌለ ሰው አይነገርምና፡፡
          4.     ቀጥሎ ያለው አገላለጥም መጽሐፉ ሲጻፍ ዐፄ ዘርአ ያዕቆብ በሕይወት እንደነበረ ያስረዳናል፡፡ ቢያንስ ዐፄ ዘርአ ያዕቆብ በሕይወት ባይኖር ኖሮ ‹ይዕቀቦ - ይጠብቀው› አይለውም ነበር፡፡
                          ‹ይዕቀቦ በኩሉ ፍናዌሁ
                            (በመንገዱ ሁሉ ይጠብቀው)
ኀበ ሀለየ በኅሊናሁ
                            (በኅሊናው ባሰበበት)
ወኀበ አንጸረ በአዕጻቢሁ
                           (በጣቶቹም ባመለከተበት (ቦታ ሁሉ))
ወይባርክ አክሊለ ዓመተ ዚአሁ
                             (የተቀዳጀውን ዘመን ይባርክለት)
ሕይወተ ትጉኃን ይኩን መዋዕሊሁ
                             (ዘመኑ የትጉኃን ዘመን ይሁን)
ወከመ ኆፃ ዘድንጋገ ባሕር ይብዝኁ ፍሬሁ
                           (ፍሬዎቹም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ይብዙ)
                             ወኩሉ ዘኢያፈቅሮ ለዝንቱ ነጋሢ
                             (ይህንን ንጉሥ የማይወደው ሁሉ)
ዘአዕበዮ እግዚአብሔር በጸጋሁ
((ይህንን) እግዚአብሔር በጸጋው ከፍ ከፍ ያደረገውን (ንጉሥ))
ከመ ይኩን አበ ለቅዱሳኒሁ ወለ አግብርቲሁ
                           (ለቅዱሳኑና ለአገልጋዮቹ አባት ይሆን ዘንድ)
ወዘይሴፎ ባዕደ ዘእንበሌሁ
                         (ከእርሱ(ከእግዚአብሔር) በቀር ማንንም ተስፋ የማያደርገውን)
በውስጡ ወበአፍአሁ
                             (በውስጡና በውጩ)
                             በነፍሱ ወበ ሥጋሁ
                             (በነፍሱና በሥጋው)
                          (እግዚአብሔርን ብቻ ተስፋ የሚያደርገውን ይህንን ንጉሥ  የማይወድ ቢኖር))
ባቢሎናዊ ብእሲሁ
                            (ሰውነቱ ዝርው ይሁን)
ይትፈጸም አፉሁ
                              (አፉም ይዘጋ)
ወይትኃተም ጉርዔሁ
                            (ጉሮሮውም ይደፈን)
ለዓለም እስከ ፍጻሜሁ፡፡
                             (እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ፡፡)

በመሆኑም የጊዮርጊስ ወልደ አሚድ መጽሐፍ የተተረጎመው በዐፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን እንጂ በዐፄ ልብነ ድንግል ዘመን ነው ለማለት ይህ ማስረጃችን አያስኬድም፡፡ በዐፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት ሁለት ነገሮች ተጨምረው ይሆናል፡፡
           1.      ዓረቦች ግብጽን ከወረሩበት ዘመን በኋላ ያለው ታሪክ ከጣባሪ መጽሐፍ ተወስዶ ተጨምሮበት ይሆናል
          2.     ከኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክ ጋር የማስተሣሠር ሥራ እንደገና ተሠርቶበት ይሆናል፡፡
ግእዝ

(1a)ቅቡዕ ንጉሥ ዘተሰምየ ቈስጠንጢኖስ
ዕንቈ ዳዊት ወርቀ ተርሴስ
ወልብነ መዓዛ ዘቤተ መቅደስ
ቅድው ዕፍረት ከመ ጵስጥቂስ
ወርኁየ ሥን ከመ ናርዶስ
ወዕጸ ቄድሮስ
ልዑል በውስተ ሊባኖስ
ወነዊኃ አዕጹቅ ከመ ጠርቤንቶስ
ኅንባበ ረዳ በውስተ ኢያሪኮ ዘወርኃ ኔዮስ
ዘይመልዕ ጥበበ ትምህርቱ ከመ ማየ ተከዜ ዘኤፍራጥስ
ዘልህቀ በጠለ አርሞንኤም ጠለ ፈውስ
እም ከናፍሪሁ ዘይትከዓው ሞገስ
መኑ እም ነገሥት ዘተንሥአ ከማሁ
ኢ እም ቀደምት አበዊሁ
ወኢ እም ኄራን አኃዊሁ
ዘከሠተ ግጻዌ ሥላሴ በበጾታሁ
አብኒ ዘከመ ሰብሖ ለወልድ በስብሐቲሁ
ወልድኒ ዘከመ ሀለወ ውስተ ሕጽነ አቡሁ
መንፈስ ቅዱስኒ ዘከመ ይትቄደስ በሥላሴሁ
ዘመሀረ ዘንተ ለሕዝበ ዚአሁ
ከመ ኢያምልኩ ባዕደ ዘእንበለ እግዚአብሔር ፈጣሪሁ
ዘመተሮ ለደስክ እም ሥረዊሁ
ለማሪትኒ ወለ ጠፈንት
ለመቃውዘይኒ ወለ ዲኖ
ለጠንቃልያን ወለኩሎሙ እለ ያመልኩ ጣዖተ ወሥርያቲሁ
እግዚአብሔር ይፅብዖሙ በሰይፈ እዴሁ
ወይውር(1b)ዎሙ ለገሃነም እስከ ዕመቂሁ
ይቤ ቈስጠንጢኖስ ለእግዚአብሔር መሲሑ
ወተሐጽየ በደመ ገቦሁ
ዘኀረየ መስቀለ ለክላሌሁ
ጸዳለ መብረቅ ወልታሁ
ወብርሃነ ማዕበል ሱራሔሁ
ይዕቀቦ በኩሉ ፍናዌሁ
ኀበ ሀለየ በኅሊናሁ
ወኀበ አንጸረ በአዕጻቢሁ
ወይባርክ አክሊለ ዓመተ ዚአሁ
ሕይወተ ትጉኃን ይኩን መዋዕሊሁ
ወከመ ኆፃ ዘድንጋገ ባሕር ይብዝኁ ፍሬሁ
ወኩሉ ዘኢያፈቅሮ ለዝንቱ ነጋሢ
ዘአዕበዮ እግዚአብሔር በጸጋሁ
ከመ ይኩን አበ ለቅዱሳኒሁ ወለ አግብርቲሁ
ወዘይሴፎ ባዕደ ዘእንበሌሁ
በውስጡ ወበአፍአሁ
በነፍሱ ወበ ሥጋሁ
ባቢሎናዊ ብእሲሁ
ይትፈጸም አፉሁ
ወይትኃተም ጉርዔሁ
ለዓለም እስከ ፍጻሜሁ፡፡አሜን፡፡
ወኩሉ ዘሰምዐ ለይበል አሜን ወአሜን
በእንተ ሥጋሁ ወደሙ ለክርስቶስ ለይኩን ለይኩን፡፡

የአማርኛ ትርጉም
ቈስጠንጢኖስ[5] ተብሎ የተጠራ ቅቡዕ ንጉሥ
የዳዊት ዕንቁ የተርሴስ ወርቅ[6]
በቤተ መቅደስ ያለ የነጭ ዕጣን መዓዛ
እንደ ጵስጥኪስ[7] ያማረ ሽቱ
እንደ ናርዶስ[8] የሚያውድ
የቄድሮስ[9] ዛፍ
በሊባኖስ[10] ውስጥ ከፍ ከፍ ያለ
እንደ ጠርቤንቶስ[11] ቅርንጫፎቹ የረዛዘሙ
በኢያሪኮ[12] በኔዮስ[13] ወር የሚያፈራ ጽጌረዳ
የትምህርቱ ጥበብ እንደ ኤፍራጥስ[14] ወንዝ የመላ
በአርሞንዔም[15] ጠል ያደገ የፈውስ ጠል
ከከንፈሮቹ ሞገስ የሚፈስ
ከነገሥታት መካከል እንደ እርሱ ሆኖ የተነሣ ማነው?
ከቀደምት አባቶቹም ሆነ
ከተመረጡት ወንድሞቹ (መካከል እንደ እርሱ ያለ ማነው?)
እርሱ የሥላሴን መልክ በየወገናቸው ገለጠ
አብ ወልድን በሚገባው ክብር እንዳከበረው
ወልድም በአባቱ ዕቅፍ ህልው ሆኖ እንደሚኖር
መንፈስ ቅዱስም በሦስትነት (ቅዳሴ) እንደሚቀደስ
ይህንን ለሕዝቡ ያስተማረ
ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ እንዳያመልኩ[16]
ደስክን ከሥር መሠረቱ የቆረጠው
ማሪትንና ጠፈንትንም
መቃውዘይንና ዲኖ[17]ንም
ጠንቋዮችንና ጣዖትንና ሟርትን የሚያምልኩትን ሁሉ
እግዚአብሔር በእጁ ሰይፍ ይዋጋቸው
ወደ ገሃነምም እስከ ጥልቁ ይጣላቸው
እግዚአብሔር የቀባው ቈስጠንጢኖስ እንዲህ አለ
ከጎኑ በፈሰሰው ደም የታጨ
መስቀልንም ከለላዉ እንዲሆን የመረጠ
የመብረቅ ጸዳልም ጋሻው እንዲሆን
የብርሃን ማዕበልም ክብርና ጌጡ (እንዲሆን የመረጠ)
በመንገዱ ሁሉ ይጠብቀው
በኅሊናው ባሰበበት
በጣቶቹም ባመለከተበት (ቦታ ሁሉ)
የተቀዳጀውን ዘመን ይባርክለት
ዘመኑ የትጉኃን ዘመን ይሁን
ፍሬዎቹም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ይብዙ
ይህንን ንጉሥ የማያፈቅር ሁሉ[18]
(ይህንን) እግዚአብሔር በጸጋው ከፍ ከፍ ያደረገውን (ንጉሥ)
ለቅዱሳኑና ለአገልጋዮቹ አባት ይሆን ዘንድ
ከእርሱ(ከእግዚአብሔር) በቀር ማንንም ተስፋ የማያደርገውን
በውስጡና በውጩ
በነፍሱና በሥጋው(እግዚአብሔርን ብቻ ተስፋ የሚያደርገውን ይህንን ንጉሥ የማይወድ ቢኖር)
ሰውነቱ ዝርው ይሁን
አፉም ይዘጋ
ጉሮሮውም ይደፈን
እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ፡፡ አሜን፡፡
የሰማ ሁሉ አሜን ወአሜን ይበል
ስለ ክርስቶስ ስለ ሥጋውና ደሙ፤ይሁን፣ ይሁን፡፡


[1] መታነጽ የጀመረችው በ1761 ዓ.ም. በዘመነ ማቴዎስ፣ በጥቅምት 12 ቀን ረቡዕ፣ ኢዮአስ በነገሠ በ13ኛው ዓመት መሆኑን ይገልጣል፡፡
[2] Encyclopedia Aethiopica, Vol. II,813
[3]Ibid
[4] Catalogue of Dilman,1878, Ms. 62,fol.73b
[5] ዐፄ ዘርአ ያዕቆብ የንግሥና ስም ነው፡፡ ቆስጠንጢኖስ ክርስትናና በዐዋጅ ተቀብሎ ለቤተ ክርስቲያን ልዕልና እንደሠራው ሁሉ ዐፄ ዘርአ ያዕቆብም ቤተ ክርስቲያንን አንድ አድርጎ ከፍ ለማድረግ እንዳሰበ ስመ ንግሥናው ያሳያል፡፡
[6] ከሜዲትራንያን 20 ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ በመግባት በዛሬዋ ቱርክ ማዕከላዊ ደቡብ የምትገኝ የቅዱስ ጳውሎስ የትውልድ ከተማ፡፡ በወርቅ ምርቷ ጥራት የታወቀች ከተማ ናት፡፡
[7] በጽርዕ ፒስቲኪስ ካለው የተወሰደ፡፡ ያማረ፣ ውድ፣ ክቡር ሽቱ ማለት ነው(ኪወክ 907)
[8] በደቡብ እሥራኤል ከዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ከቆሮንቶስ ተራራ ሥር የምትገኝ ጥንታዊት ከተማ፡፡ ከተማዋ ሞቃታማ ናት፡፡
[9] ረዥም፣ ታላቅ፣ ገናና ባለ ብዙ ቅርንጫፍ ዛፍ(ኪወክ 784)
[10] አርዘ ሊባኖስ የተባለው ረዥም ዛፍ የሚበቅልበት የሊባኖስ ተራራ
[11] በጽርዕ ተርቤንቶስ ከሚለው የተወሰደ፡፡ ቡጥ መልካም ሽታ እና ብዙ ቅጠል ደም ወተት ያለው፡፡ ቅጠሉና ፍሬው ታናሽ ቁንዶ በርበሬ የሚመስል፡፡ (ኪወክ 510)
[12] እስራኤል ውስጥ በስተ ደቡብ ከዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ የምትገኝ ቆላማ ከተማ፡፡
[13]  የኢያሪኮ ጽጌረዳ በሙት ባሕር ቆላ በኢያሪኮ ድንበር የሚበቅል የበረሓ ጽጌረዳ ነው፡፡ ለብዙ ዘመናት ድርቅን ተቋቁሞ በመኖር ይታወቃል፡፡ እስከ 50 ዓመታት ድረስ ራሱን ደብቆ ኑሮ አስፈላጊ ነገሮችን ሲያገኝ መልሶ ያብባል፡፡ በዚህ የተነሣም ‹የትንሣኤው ጽጌረዳ› በመባል ይታወቃል፡፡
[14] በጥንቱ ሜሶጶታምያ ከሚገኙ ሁለት ወንዞች አንዱ፡፡ በምዕራብ እስያ ረዥሙና ታሪካዊው ወንዝ ነው፡፡ ወንዙ በጠቅላላው 2800 ኪሎ ሜትር ይደርሳል፡፡
[15] በእስራኤል፣ ሊባኖስና ሶርያ ድንር የሚገኝ ረዥም የተቀጣጠለ ተራራ፡፡ ብዙ ጊዜ ጫፉ በበረዶ ተሸፍኖ ይታያል፡፡ ረዥሙ የተራራው ጫፍ 2814 ሜትር ይደርሳል፡፡
[16] ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ አምልኮ ጣዖትን ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት በብርቱ ጥሯል፡፡ በዚህ ጉዳይ ለገዛ ልጆቹ እንኳን አልራራም፡፡ መጽሐፈ ብርሃንና መጽሐፈ ምዕላድ የተሰኙት መጻሕፍቱ ጥረቱን በሚገባ ይገልጣሉ፡፡
[17] እነዚህ በመካከለኛው ዘመን የነበሩ ልዩ ልዩ ባዕድ አምልኮዎች ናቸው፡፡ በየገድላቱና በዐፄ ዘርአ ያዕቆብ መጽሐፈ ብርሃንና መጽሐፈ ምዕላድ ላይ እነርሱን ለማስቀረት የተደረገው ተጋድሎ ተገልጧል፡፡ ከቱርክ ተነሥቶ ኢራቅ ይደርሳል፡፡
[18] ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ አራት ዓይነት ተቃዋሚዎች ነበሩት፡፡ 1) ከገዛ ቤተሰቦቹና ባለሟሎቹ መካከል የሚቀናቀኑት፣ 2) በሐሳብ ካልተግባቡት መካከል በየጉባኤው የተከራከራቸው ደቂቀ እስጢፋኖስን ገማልያልን የመሰሉ፣ 3) ከአዳል ሡልጣኖች መካከል ግዛቱን የሚቀናቀኑ፣ 4) አምልኮ ጣዖትን የሚወዱና የአምልኮው አገልጋዮች

1 comment:

  1. Dn Daniel PDF madreg bichal silkachin yemayaneb endanresa bye new.
    Egzabher ystilgni

    ReplyDelete