Monday, March 26, 2018

ኀሠሣ መጻሕፍት


በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ከሚገርሙኝ ነገሮች አንዱ አባቶቻችን ለመጻሕፍት የነበራቸው ፍቅር ነው፡፡ የሌሉትን ካሉበት አስመጥተው አስተርጉመው፤ ለደራስያኑ ቀለብና ቤት ሰጥተው፣ ሲጨርሱም ሹመውና ሸልመው እንዴት ያስጽፉ እንደነበር የተረፉት መዛግብት የሚነግሩን አስደናቂ ነገር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ዛሬም በየአድባራቱና ገዳማቱ ከ240ሺ በላይ መጻሕፍት መኖራቸው ይገልጣል፡፡ በመላው ዓለም ተበትነው ከ30 ሺ በላይ መጻሕፍት እንዳሉ ይነገራል፡፡
አንዳንዶቹ መጻሕፍት ስማቸውን እንጂ ራሳቸውን መጻሕፍቱን አላገኘናቸውም፡፡ መጽሐፈ ከሊላ ወዲምናህ፣ መጽሐፈ ዮሴፍ ወእስኔት እስካሁን አልተገኙም፡፡ ከሊላ ወዲምናህ ከ16ኛው መክዘ በፊት እንደነበረ አባ ባሕርይ በመዝሙረ ክርስቶስ ያነሣዋል፡፡ የሐይቅ እስጢፋኖሱ የመጻሕፍት ዝርዝር ከሊላ ወድምናሕን ይጠቅሳል፡፡ መጽሐፉ ግን ዛሬ በሐይቅ የለም፡፡ አባ ጊዮርጊስም በልዩ ልዩ ድርሰቶቹ መጽሐፈ ዮሴፍ ወእስኔትን ያነሳዋል፡፡

ጥንት ምን ዓይነት መጻሕፍት እንደነበሩን መዝግበው ካስቀመጡልን መዛግብት መካከል ዛሬ በብሪትሽ ሙዝየም የሚገኘው የሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የብራና መጽሐፍ አንዱ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንዋ በመካከለኛው ዘመን ታዋቂ ነበረች፡፡ ነገሥታቱም እየተገኙ ያከብሯታል፤ ርስትና ስጦታም ይሰጧታል፡፡ ኋላ ግን በግራኝ ጊዜ ፈርሳለች፡፡ ይህቺ ቤተ ክርስቲያን አንድ ትልቅ የብራና መጽሐፍ ነበራት፡፡ መጽሐፉ ገድለ ቅዱስ ፋሲለደስ ይባላል፡፡ መጽሐፉ ከቅብጥ ቋንቋ ወደ ግእዝ የተተረጎመው የአባ እንጦንስ ገዳም መነኮስ በሆነ በኢትዮጵያዊው አባት በአባ ስምዖን ነው፡፡ በነገራችን ላይ በግብጽ ገዳማት የነበሩ የኢትዮጵያ መነኮሳት አንዱ ተግባራቸው መጻሕፍትን መተርጎምና መጻፍ ነበረ፡፡ ስለ እነርሱ ወደፊት እመለሳለሁ፡፡ የጠፉት ጠፍተው የተረፉት የእነርሱ መጻሕፍት ዛሬ ፈረንሳይና ቫቲካን ይገኛሉ፡፡ አባ ስምዖን ገድለ ፋሲለደስን የተተረጎመውም በ6889 ዓ.ዓ. ማለትም በ1397 ዓም ነው፡፡ በመጽሐፉም ዐፄ እስክንድርን(1471-1487ዓ.ም.) ያነሣዋል፡፡ ከገድለ ፋሲለደስ ጋር ገድለ አባ ኖብንም ይዟል፡፡
ቀጥሎ ደግሞ ዐፄ ናዖድ በመጋቢት 1 የልደታ ቀን በዚህችው ደብር ተገኝቶ የተቀኘውን ሥላሴ ቅኔ ጽፎታል፡፡ አከታትሎም ለመስቀል፣ ለመጋቢት 21 ቀን(በምድረ ዘበር እያለ)፣ ለዕርገት፣ ለደብረ ምጥማቅ(በምድረ ወይ እያለ) የተቀኛቸውን ቅኔዎች መዝግቦታል፡፡
ዐፄ ናዖድ (1488-1500 ዓ.ም.) መጋቢት 1 ቀን 1495 ዓም. በደብረ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የልደታ ዕለት በተገኘ ጊዜ የተቀኘው ሥላሴ ቅኔ ይህ ነው፡፡
መሶበ ወርቅ ንጽሕት መሥዋዕተ አዕርጎ
እሳተ አርያም ሠምረ በማኅጸንኪ ይሠጎ
ለአእምሮ ጥበብ ተረወይኪ ሕጎ
በዓለ ልደትኪ ዮም ማርያ ለኅሊናየ መዘጎ
በቅድመ ሕዝብ በአንገልጎ
ስብሐተኪ እሕሊ በኢያንትጎ
አዕትቲ እም ዐውድየለዲያብሎስ ፁጎ
በዚህ ቀን ዐፄ ናዖድ ቅኔ ብቻ ተቀኝቶ አልቀረም፡፡ 25 መጻሕፍትንም ሰጥቷል፡፡ አንዳንዶቹን በወርቅ አስለብጦ፡፡ ይህ አሁን እንግሊዝ የገባው መጽሐፍም ንጉሡ ለደብረ ብርሃን ቅድስት ማርያም የሰጠው ነበር፡፡ በየት በየት ዞሮ መቅደላ እንደደረሰና ለንደን እንደገባ የመቅደላው መድኃኔዓለም ይወቀው፡፡
                1.      ኦሪት - 1
                2.     ነገሥት -1
                3 .   መቃብያን-1
               4  .    ወንጌል -1
               5.     ገድለ ሐዋርያት -1
               6.     ግብረ ሕማማት- 1
               7.     ሐሳብ -1
               8.     ተአምረ ማርያም -1
               9.     ክብረ ነገሥት -1
              10.   መጽሐፈ ዕንቁ - 1 
               11.     ሲኖዶስ -1
               12.    መጽሐፈ ምሥጢር -1
               13.    መጽሐፈ ዘላፌ እስጢፋኖስ - 1
               14.   ጸዳለ ፀሐይ -1
               15.    ገድለ ሐዋርያት - 1
               16.   ስንክሳር -1
               17.    መጽሐፈ ብርሃን - 1
               18.   ድርሳነ ጾም -1
               19 .   ገድለ ፋሲለደስ(ወአባ ኖብ ወለ እግዚአብሔር አብ) – 1
              20.  ጦማረ ትስብእት -1
              21.    ገድለ ሐዋርያት - 1
              22 .   ወንጌል -1
              23.   ሲኖዶስ- 1
              24.  የወርቅ ወንጌል -1
             25.   ተአምረ ሚካኤል በወርቅ የተለበጠ -1
ከመጻሕፍቱ መካከል ሐሳብ፣ መጽሐፈ ዕንቁ፣ መጽሐፈ ዘላፌ እስጢፋኖስ፣ ጸዳለ ፀሐይና ድርሳነ ጾም የሚሉት ትኩረታችንን ይስባሉ፡፡ ሌሎቹን ስለምናውቃቸው፡፡ በርግጥ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ መጻሕፍት የሆኑት መጽሐፈ ብርሃንና ጦማረ ትስብእት ተጽፈው መሰጠታቸው በ50 ዓመታት ውስጥ መጻሕፍቱ የነበራቸው ተቀባይነት ያሳየናል፡፡ የአባ ጊዮርጊስን መጽሐፈ ምሥጢር ማግኘታችንም አባ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በ15ኛው መክዘ የተደላደለ ቦታ መያዙን ያሳየናል፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት አንቀበለውም የሚሉ ተቀናቃኞች ነበሩና፡፡ ወንጌሉ ሁለት ዓይነት ነው፡፡ ለዘወትር አገልግሎት የሚለውና የወርቅ ወንጌሉ፡፤ የወርቅ ወንጌሉ ለበዓላት የሚነበብ፣ የቤተ ክርስቲያኑ ስጦታና ሀብት የሚመዘገብበት ነው፡፡ ሲኖዶስና  ገድለ ሐዋርያት፣  ለየብቻ አንዳንድ ሆነው ነው የተጻፉት ወይ አንዱ ባለ ሥዕል ስለሆነ ነው አለያም ደግሞ በተለያዩ ሰዎች የተጻፉ ናቸው፡፡
ሐሳብ፡- ምናልባት ባሕረ ሐሳቡን ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ርእስ የሚጠራ መጽፍ እስካሁን አላገኘሁም፡፡
መጽሐፈ ዕንቁ፡- ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ‹በውስጡ ከብሉይና ከሐዲስ ከሊቃውንትም መጽሐፍ የተውጣጣ ነው› ይላሉ፡፡(አማርኛ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት፣ ቅጽ 2፣ ገጽ 151)
መጽሐፈ ዘላፌ እስጢፋኖስ፡- ከስሙ አባ እስጢፋኖስን ለመውቀስ የተዘጋጀ መጽሐፍ መሆኑን ያሳያል፡፡ ምናልባት በደቂቀ እስጢፋኖስ ክርክር ወቅት የተጻፈ ሳይሆን አይቀርም፡፤ እስካሁን ግን ተገኝቶ ሲጠቀስ አላየሁትም፡፡
ጸዳለ ፀሐይ፡- ይህንን መጽሐፍ እስካሁን ለማግኘት አልተቻለም፡፡
ድርሳነ ጾም፡- ስለ አጽዋማት የሚናገር ይመስላል፡፡ እስካሁን ግን አላገኘሁትም፡፡ የሚጠቅሰውም አላገኘሁም፡፡
እነዚህን መጻሕፍት የምዘረዝረው ስለ ሀገራችንም፣ ስለ ሃይማኖታችንም፣ ስለማንነታችንም፣ ስለ ታሪካችንም የተሟላ ነገር ማወቅና ውይይታችን ሁሉ በዕውቀት የታሸ የሚሆነው እነርሱን ፈልገን ስናገኝ በመሆኑ ነው፡፡ የያዙትን ስንፈትሽ፤ ፈትሸንም ስንጠቀምባቸው ውይይታችን በተረዳ ልቡና በሰላ ኅሊና ይከናወናል፡፡ ዕውቀትን ፍለጋ ዘመቻ ያስፈልጋል፡፡ ከነበረን ነገር ተነሥተን ያልነበረንን ነገር እንፈልግ፡፡ 
ሲያትል ፣ ዋሽንግተን

6 comments:

 1. Wid D/n Daniel,
  Enameseginalen,Asasabi Guday Ahunim endalu metekom efelgalehu. enie balegn mereja meseret bejanamora woreda bemtgegnew Deresgie Mariam Biete-Kirstian getsochun anind-be-anind befoto camera tenesto yetewesede yebrana metshaf endale
  bakababiw yalu yekrib sewoch achawtewgnal. bekrbum wede semien teraroch lesira hiejie beneberebet wokt hulet ye Engliz hager gazietegnoch be biete-Kirstianua yemigegnut wid metsahft ke simien-lodge(Mr. Nick Crane) balebiet kehonew sew gar besfraw dersew bimetum betederegew yemereja liwiwit Biete Kirstyanua kemezeref dinalech. Bezih guday min yimekrunal? Egziabhier befekede meten yebekulien gdieta mewetat efelgalehu.
  Melswon Etebkalehu.
  Egziabhier Yistlign.

  ReplyDelete
 2. Hodam honehal bakih.

  Tera werehin yemisemah yelem.
  Yekelelku weyane. Dolar kemokebet bicha hedeh ende wusha mitalakik. Benetsa yetekebelkewun bedolar yemitished yebahirdar achberbari endehonik tenektobihal.

  ReplyDelete