Tuesday, March 20, 2018

‹የግእዝ ሥነ ጽሑፍ በየዓይነቱ›


ስለ ግእዝ ሥነ ጽሑፍ የተሰበሰቡ አንዳንድ ማስተዋሻዎች 


ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እነዚህን ማስተዋሻዎች የሰበሰብኩት በዋሽንግተን ዲሲ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ስለ ግእዝ ሥነ ጽሑፍ ለማቅረብ ነበር ይላሉ፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዘመናት በየአድባራቱና በየአዳራሹ ብንጋብዛቸው ኖሮ ስንት መጽሐፍ እናተርፍ ነበር? በሀገራችን አንድ ሊቅ ሲሞት ብቻውን አይሄድም

አራት ሰው ሞተ ተቀበረ ዛሬ
ድጓ ጾመ ድጓ መዋሥዕት ዝማሬ
ተብሎ ለአንድ ሊቅ የተገጠመው ይሄንን ይነግረናል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው ያሉ በሁለት እጅ የማይነሡ ሊቃውንት እንደ ጥገት ላም ሊታለቡ፣ እንደ ወይን ዛላ ሊለቀሙ ይገባል፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከጎተራቸው መዝገን ይገባል፡፡ 

‹ስለ ግእዝ ሥነ ጽሑፍ የተሰበሰቡ አንዳንድ ማስተዋሻዎች› የሚለው መጽሐፋቸው ከዘመነ አኩስም እስከ 20ኛው መክዘ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ መልክና ዓይነት ምን እንደሚመስል፤ ሥነ ጽሑፉን ማጥናት የሚሰጣቸውን ጥቅሞች፣ በውስጡ የያዛቸውን ነገሮች፤ እነማን እንደ ደከሙበት፣ ሳናውቃቸው ስለቀረነው ቀደምት ሊቆቻችን የሚነግሩን ነገር እንደ ወንዝ ይዞ የሚፈስ ነው፡፡

ከዓይነት ከዓይነቱ እየተረጎሙ ያቀረቡልን የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ዓይነቶች ሦስት ጥቅሞች አሏቸው፡፡ የግእዝን የረዥም ዘመን የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ያሳያሉ፤ በጽሑፎቹ ውስጥ ብዙ ጊዜ ያልታወቁ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና መልክአ ምድራዊ መረጃዎችን ይዘዋል፤ ለተጨማሪ ንባብ ልብን ይጎተጉታሉ፡፡ ‹የግእዝ ሥነ ጽሑፍ በየዓይነቱ› በሉት፡፡

ከፕሮፌሰር መጽሐፍ ውስጥ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ምንጮችን ብቻ ሳይሆን የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ምንጮችን እንዴት ማጥናት እንደሚቻልም መንገድ ያመለክቱናል፡፡ ለታሪክ፣ ለእምነት፣ ለባሕል፣ ለመልክአ ምድርና ለማኅበራዊ ጥናት እንዴት መጠቀም እንደምንችል ከውስጣቸው ምሳሌ እያወጡ ያሳዩናል፡፡ በግእዝ ሥነ ጽሑፎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት አሳይተው የእኛን እንቅልፍ እንደ መርፌ በሚወጋ ትዝብት ጠቅ አድርገው ይቀሰቀሱናል፡፡

በአንዳንድ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ብቻ ታሪካቸው ተጥሶ የሚያልፍ፤ ለሀገራቸውና ለቤተ ክርስቲያናቸው መሥዋዕት የከፈሉ፤ በሊቅነታቸው መጻሕፍትን ተርጉመውና አስተምረው ያለፉ፤ በሰማዕትነት ተሠይፈው ዋጋ የከፈሉ ሊቃውንትን እየጠቀሱ ያስቆጩናል፡፡ አንድም ለትኅትና አንድም ነቢይ በሀገሩ አልከበር በማለቱ የተነሣ በኢትዮጵያ ሊቃውንት ተጽፈው በውጭ ጸሐፊዎች ስም የሚጠሩ ድርሰቶቻችንን እያነሡ ያንገበግቡናል፡፡ ፈረስ የማይችለው መጽሐፍ ጽፈው ስማቸውን ሳይገልጡ የሄዱ ደጋግ ሊቃውንትን ነግረው ያስቆዝሙናል፡፡ 

ይህንን መጽሐፍ ማንበብ በአንድ ትልቅ ውቅያኖስ ጥግ እንደመዋኘት ነው፡፡ የበረታ ወደ ውቅያኖሱ እየዋኘ ይገባል፡፡ ያልበረታ በዚያው በውቅያኖሱ ጥግ እየዋኘ ሰፊውን ውቅያኖስ ያደንቃል፡፡ 

‹በዚሁ ርእስ የማዘጋጀው ሰፋ ያለ ድርሰት እስኪደርስልኝ(ገጽ 9)› ብለው ይህንን እንዳሳተሙልን ገልጸዋልና እንጎቻው እንዲህ ከጣፈጠ ዋናው እንጀራማ ምን ይሆን ይሆን? ብለን በተስፋ እንጠብቃለን፡፡

5 comments:

 1. ስላደረሳችሁን መረጃ እናመሰግናለን ፡፡ ነገር ግን የአንድ ሰው ወይም ሁለት ሰው ስራ ብቻ ተደርጎ ሳይወሰድ ሁሉንም ከሲኖደስ /ከሊቀ ጳጳሱ እስከ ታች ምእመናን ድረስ ደርሶ ታሪኮችን ፤የጠፉ በጣም ብዙ የሃይማኖት መጸሓፍትን ፤አንደ አዲስ የማሰባስብ እና የጥንት አባቶቻቸንን የብዕር አጣጣል ስረዓተ ነጥብ ቃላቶችም በዘመናዊ መልክ ሳይለወጡ ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፉበትን መንገድ ተቀርጾ ስራ ላይ ቢወርድ እላለሁ ፡፡

  ReplyDelete
 2. ዳኒ፣ እባክህ አታስጎምዠን! አግኝተን እንድናነበው ፕሮፌሰርን መጽሐፋቸውን ወደኢትዮጵያም እንዲልኩት ንገርልን፡፡ አደራ! ስለምንዋኝበት ባሕር ነግረህ ብቻ አስጎምዥተኸን አትቅር፡፡ ካደለን እንዳንተ ወደባሕሩ ገብተን እንዋኛለን፤ ካልሆነም ከዳር ሆነን “እግዚኦ ሚ መጠን ከመ ዝ መጠን! እግዚኦ ሚ ድረሰት ከመ ዝ ድርሰት! እግዚኦ ሚ ትጋህ ከመ ዝ ትጋህ! እግዚኦ ሚ ባሕር ከመ ዝ ባሕር!” እያልን እናደንቃለን፡፡ በጊዜው ወደባሕሩ እንደምንቀርብ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ዋናው ዋና የሚያለማምዱ ብዙ ሰዎች መኖራቸው ነው፡፡ ከብዎቹ አንዱ ደግሞ አንተ ነህ፡፡ እየዋኙ ማስተማር፤ እያስተማሩ መዋኘት ችለህበታል፤ የምር! ሁለታችሁንም አምላክ ያክብርልን!

  ReplyDelete
 3. መጽሐፉን ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?

  ReplyDelete
 4. 1. ዲ.ዳንኤል በጽሁፍ ያሰፈርከው መረጃ ጥሩ ሆኖ ሳለ ግእዝን ለመታደግ በሰፊው ስራ መሰራት ይኖርበታል፤1 ለመምህራኖቹ በቂ ደመወዝ፤ለተማሪዎቹ በቂ የማረፊያ ቦታና ምግብ፤የትምህርተ አሰጣጡን በዘመናዊ መልክ ማድረግ ቢሆን በጣም ጥሩ ነው ይህን ያልኩበት ምክንያት አሁን ተማሪ ቢለምንም በቂ ምግብ ስለማያገኝ ፤ተምሮም በቂ ደመወዝ ስላማይከፈለው፤የዘመኑ ትውልድ ድናጋይ ላይ ሆኖ ለመማር ዝግጁ ሳላልሆነና ቤተሰብም ለማስተማር ፍቃደኛ ባለመሆኑ ነው ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ እኔ የጀመርኩት አለ ይሁንታን ካገኝሁ እየተደዋወልን እንሰራለን ፡፡ ለአሁን በዚህ ኢሜል እንገናኝ ለተጨማሪ መረጃ 0910992513 ዲ በኃይሉ ምትኩ ደብረሲና ሰሜን ሸዋ ጣርማበር

  ReplyDelete
 5. መጽሐፉን ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?

  ReplyDelete