በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ
ውስጥ ከሚገርሙኝ ነገሮች አንዱ አባቶቻችን ለመጻሕፍት የነበራቸው ፍቅር ነው፡፡ የሌሉትን ካሉበት አስመጥተው አስተርጉመው፤ ለደራስያኑ
ቀለብና ቤት ሰጥተው፣ ሲጨርሱም ሹመውና ሸልመው እንዴት ያስጽፉ እንደነበር የተረፉት መዛግብት የሚነግሩን አስደናቂ ነገር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ዛሬም በየአድባራቱና ገዳማቱ ከ240ሺ በላይ መጻሕፍት መኖራቸው ይገልጣል፡፡
በመላው ዓለም ተበትነው ከ30 ሺ በላይ መጻሕፍት እንዳሉ ይነገራል፡፡
አንዳንዶቹ መጻሕፍት ስማቸውን እንጂ
ራሳቸውን መጻሕፍቱን አላገኘናቸውም፡፡ መጽሐፈ ከሊላ ወዲምናህ፣ መጽሐፈ ዮሴፍ ወእስኔት እስካሁን አልተገኙም፡፡ ከሊላ ወዲምናህ
ከ16ኛው መክዘ በፊት እንደነበረ አባ ባሕርይ በመዝሙረ ክርስቶስ ያነሣዋል፡፡ የሐይቅ እስጢፋኖሱ የመጻሕፍት ዝርዝር ከሊላ ወድምናሕን
ይጠቅሳል፡፡ መጽሐፉ ግን ዛሬ በሐይቅ የለም፡፡ አባ ጊዮርጊስም በልዩ ልዩ ድርሰቶቹ መጽሐፈ ዮሴፍ ወእስኔትን ያነሳዋል፡፡