Thursday, February 1, 2018

የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ (ክፍል አምስት)

ለመሆኑ ሐተታዎቹ ምን ይነግሩናል?
1.  ዘርአ ያእቆብ የተወለደው ከአክሱም ካህናት ወገን መሆኑን ይነግረናል፡፡ በአኩስም የትኛው ክፍል ወይም ቦታ እንደሆነ ግን አይገልጥም፡፡ ይህ ግን ዘርአ ያእቆብ በሌሎች ነገሮች ከሚሰጠን ዝርዝር የተለየ ነው፡፡ የወደቀበትን ገደል ሥፍር ሳይቀር 25 ክንድ ከስንዝር መሆኑን ይነግረናል፡፡ እንዲያውም በእኛ ድርሳናት ያልተለመደ የተወለደበትን ቀንና ዘመንም ይገልጥልናል፡፡ ልጁ የተወለደበትን ቀንና ዘመንም ይገልጥልናል፡፡ አኩስም ውስጥ የተወለደበትን ቦታ ግን አይነግረንም፡፡ ኡርቢኖ አኩስም አካባቢ ስለነበረ ነው ይህን የትውልድ ቦታ የመረጠው ብሎ መገመት ይቻላል፡፡
2. የዘርአ ያእቆብ የዓለም ስሙ ‹ወርቄ› ነው፡፡ ‹ወርቄ፣ ብርቄ፣ ድንቄ› የሚሉ የስም አወጣጦች በአማራው አካባቢ እንጂ በአኩስም አካባቢ የተለመዱ ስሞች አይደሉም፡፡ ኡርቢኖ በደብረ ታቦር አካባቢ ሲኖር የሰማውን ስም መሆን አለበት የተጠቀመው፡፡
3.   ዘርአ ያእቆብ ትርጓሜ መጻሕፍት እንደተማረ ይነግረናል፡፡ በቤተ ክርስቲያን የመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርት ብሉይ፣ ሐዲስ፣ ሊቃውንትና መጻሕፍተ መነኮሳት ናቸው፡፡ ዝርዝር ማቅረብ የሚወደው ዘርአ ያእቆብ ጠቅልሎ ‹መጻሕፍትን ተማርኩ› የሚለውን ለመቀበል አስቸጋሪ ነው፡፡ ያውም ‹የሀገራችን መምህራን እንዴት እንደሚተረጉሟቸው፣ ፈረንጆችም እንዴት እንደሚተረጉሟቸው ተማርኩ› ነው የሚለው፡፡ በጥንቱ የትምህርት አሰጣጥ ይህንን ሁሉ ለመማር ዐሥር ዓመት በቂ አይደለም፡፡ የሐዲሳት ትርጓሜ ብቻ አምስት ዓመት ይፈጃልና፡፡ ስለ መምህርነቱ ሲነግረን ‹በዚያም መጻሕፍትን ለአራት ዓመት አስተምር ነበር› ይላል፡፡ የመጻሕፍት አስተማሪ የሚባል መምህር በቤተ ክርስቲያን የለም፡፡ የሐዲሳት መምህር፣ የብሉያት መምህር፣ የሊቃውንት መምህር፣ የመጻሕፍተ መነኮሳት መምህር እንጂ፡፡
4.   ዘርአ ያእቆብ ባልንጀሮቹ ለምን እንደጠሉት ሲገልጥ ‹እኔ በትምህርትና በባልንጀራ ፍቅር ከእነርሱ እበልጥ ነበርና› ይላል፡፡ ይህ ግን እውነቱን አይደለም፡፡ ዘርአ ያእቆብ በመጽሐፉ ውስጥ 43 ቦታ ላይ ቅዱሳት መጻሕፍትን ጠቅሷል፡፡ ከእነዚህም መካከል 32 ከዳዊት፣ 5 ከምሳሌ/ መክብብብ/ ጥበብ፣ 4 ከሐዲስ ኪዳን፣ 1 ከኦሪት፣ አንድ ደግሞ ከትንቢተ ኢሳይያስ የተጠቀሱ ናቸው፡፡ ከ43ቱ ጥቅሶች 32 ከመዝሙረ ዳዊት የተጠቀሱ ናቸው፡፡ ከሐዲስ ኪዳን ይልቅ ከመጻሕፍተ ጥበብ (መክብብ፣ምሳሌና ጥበብ) የጠቀሰው ይበዛል፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መጻሕፍተ ጥበብ ከመዝሙረ ዳዊት ጋር አብረው የሚጻፉና የሚደገሙ የጸሎት መጻሕፍት ናቸው፡፡ ይህም የዘርአ ያእቆብ ትምህርት ከመዝሙረ ዳዊት ያልዘለለ መሆኑን ያሳያል፡፡ እርሱንም ቢሆን በነጠላው እንጂ በትርጓሜው መንገድ አልጠቀሰውም፡፡ ኡርቢኖ ለአንቶንዮ ዲ. አባዲ ከላካቸው መጻሕፍት መካከል አምስቱ የሰሎሞን መጻሕፍት(ምሳሌ፣ ተግሣጽ፣ መክብብ፣ መኃልይ እና ጥበብ) ይገኙበታል፡፡ 
      5. ·     ትንቢተ ኢሳይያስንም(ኢሳ.29÷13) ሲጠቅስ በሐዲስ ኪዳን በተጻፈበት መንገድ እንጂ በብሉይ ኪዳን በተጻፈበት መንገድ አይደለም፡፡ ትንቢተ ኢሳይያስ እንዲህ ይላል፡- ዝንቱ ሕዝብ ይቀርቡኒ በከናፍሪሆሙ ወበልቦሙሰ ነዋኅ ይርኅቁ እምኔየ
·     የማቴዎስ ወንጌል(ማቴ. 15÷8)፡- ዝንቱ ሕዝብ በከናፍሪሆሙ ያከብሩኒ ወበልቦሙሰ ነዋኅ ይርኅቁ እምኔየ
·     ሐተታ ዘርአ ያእቆብ፡- ዝንቱ ሕዝብ በአፉሆሙ ያከብሩኒ ወበልቦሙሰ ነዋኅ ይርኅቁ እምኔየ(251,28a) 
   ከትንቢተ ኢሳይያስ ከራሱ ቢጠቅስ ኖሮ ‹ይቀርቡኒ በከናፍሪሆሙ› ነበር ማለት የነበረበት፡፡ይህም ብሉይን እንደማያውቀው ምስክር ነው፡፡
6.     ዘርአ ያእቆብ ዳዊትን በነጠላ ያውቀዋል፣ ሐዲስን አንብቦታል፡፡ ዘርአ ያእቆብ ሊቃውንቱ ከሚታወቁበት ከትርጓሜ ሊቃውንት፣ ከመጻሕፍተ መነኮሳት፣ ከፍልስፍና መጻሕፍት ፈጽሞ አይጠቅስም፡፡ በዚያው ምእተ ዓመት በ1528 ዓም የተወለዱት አባ ባሕርይ በ1574 ዘርአ ያእቆብ ከመወለዱ 18 ዓመት ቀደም ብለው በጻፉት ‹መዝሙረ ክርስቶስ› በተሰኘው ድርሰታቸው ላይ የሚጠቅሱትን የመጻሕፍት ብዛትና ዓይነት ከዘርአ ያእቆብ ጋር ማስተያት ነው፡፡ የቱ ነው የመጻሕፍት መምህር?
 1. ከኦሪት ዘልደት - 17፤
 2. ከኦሪት ዘጸአት - 17፤
 3. ከኦሪት ዘሌዋውያን  -7፤
 4. ከኦሪት ዘኊልቈ -2፤
 5. ከኦሪት ዘዳግም -11፤
 6.  ከመጽሐፈ መሳፍንት-2፤
 7.  ከመጽሐፈ ኦሪት ዘሆሴዕ-1፤
 8. ከመጽሐፈ ኩፋሌ-2፤
 9.  ከመጽሐፈ ሄኖክ-7፤
 10.  ከመጽሐፈ ኢዮብ-1፤
 11.  ከመጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ-7፤
 12.  ከመጽሐፈ ነገሥት ዳግማዊ-2፤
 13.  ከመጽሐፈ ነገሥት ሣልስ-9፤
 14. ከመጽሐፈ ነገሥት ራብዕ-2፤
 15.  ከመዝሙረ ዳዊትና ከሰሎሞን ምሳሌያት-8፤
 16.  ከመጽሐፈ ተግሣጽ-3፤
 17. ከመጽሐፈ ጥበብ-17፤
 18. ከመጽሐፈ መክብብ-8፤
 19. መኃልየ መኃልይ-2፤
 20.  ከመጽሐፈ ሲራክ-10፤
 21. ከትንቢተ ኢሳይያስ-18፤
 22.  ከትንቢተ ኤርምያስ-7፤
 23. ከትንቢተ ሕዝቅኤል-5፤
 24. ከትንቢተ ዳንኤል-13፤
 25.  ከመጽሐፈ እዝራ-4፤
 26. ከመጽሐፈ መቃብያን-2፤
 27.  ከራእየ ኤልያስ-1፤
 28. ከትንቢተ ሆሴዕ -3፤
 29. ከትንቢተ አሞጽ-2፤
 30. ከትንቢተ ሚክያስ-3፤
 31. ከትንቢተ ኢዩኤል-1፤
 32. ከትንቢተ ዮናስ-1፤
 33.  ከትንቢተ ዕንባቆም-2፤
 34.  ከትንቢተ ዘካርያስ -4፤
 35. ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ፣ ዮሐንስ (ከአራቱ ወንጌላውያን በድምሩ)–103፤
 36.  ከመቅድመ ጳውሎስ-1፤
 37. ከሮሜ መልእክት-27፤
 38. ከቀዳማዊ ቆሮንቶስ-10፤
 39. ከዳግማዊ ቆሮንቶስ መልእክት-7፤
 40.  ከገላትያ መልእክት-7፤
 41. ከኤፌሶን መልእክት-10፤
 42. ከፊልጵስዩስ መልእክት-2፤
 43. ከቆላስይስ መልእክት-7፤
 44. ከቀዳማዊ ተሰሎንቄ መልእክት-2፤
 45. ከዕብራውያን መልእክት-15፤
 46. ከያዕቆብ መልእክት-7፤
 47. ከአንደኛው የጴጥሮስ መልእክት-7፤
 48. ከ2ኛው የጴጥሮስ መልእክት-4፤
 49. ከቀዳማዊ የዮሐንስ መልእክት፤
 50. ከዳግማዊ ዮሐንስ መልእክት፤
 51. ከሣልሳዊ ዮሐንስ መልእክት (በድምሩ ከሦስቱ መልእክቶች)-5፤
 52.  ከሐዋርያት ሥራ-7፤
 53. ከዮሐንስ ራእይ-9፤
 54. ከመጽሐፈ ሲኖዶስ-2፤
 55. ከዲድስቅልያ- 8፤
 56. ከመጽሐፈ ኪዳን- 15፤
 57. ከመጽሐፈ ቀሌምንጦስ-1፤
 58. ከባስልዮስ - 12፤
 59. ከአትናቴዎስ ሐዋርያዊ -9፤
 60. ከሃይማኖተ አበው -3፤
 61. ከዮሐንስ አፈወርቅ -7፤
 62. ከመጽሐፈ ሠለስቱ ምእት ርቱዐነ ሃይማኖት-7፤
 63. ታሪክ-7፤
 64. ፍትሐ ነገሥት-1፤
 65. ጎርጎርዮስ-2፤
 66. ኤጲፋንዮስ-2፤
 67. ያዕቆብ ዘእልበረዲ -2፤
 68. መጽሐፈ ባሕርይ - 2፤
 69. ረድእ ወመምህር -1፤
 70. ስንክሳር -7፤
 71. ኤፍሬም ሶርያዊ - 11፤
 72. ያዕቆብ ዘሥሩግ -1፤
 73. ድርሳነ አባ ብንያሚ -3፤
 74. ድርሳነ አባ ሕርያቆስ -3፤
 75. ሳዊሮስ ዘእስሙናይ -11፤
 76. አረጋዊ መንፈሳዊ -2፤
 77. ፊልክስዮስ -2፤
 78. ተአምረ ኢየሱስ -4፤
 79. ዜና አይሁድ -1፤
 80. ፈላስፋ -7፤
 81.  ከሊላ ወድምና -3፤
 82. ፊሳልጎስ -5፤
 83. በረላም -3፤
 84. ዜና አበው -5፤
 85. ተአምረ እግዝትነ -1፤
 86. መጽሐፈ ምስጢር -1፤
 87. አክስማሮስ -2፤
መውሰዳቸውን ይነግሩናል፡፡ እነዚህን መጻሕፍትም በጠቀሱባቸው ቦታዎች ላይ ሲደርሱ በጎን ኅዳግ ላይ ምንጮቹን አሥፍረዋቸዋል፡፡አባ ባሕርይ ለማስረጃነት የጠቀሷቸውን መጻሕፍት ብዛትና ዓይነት በአራት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡
1.  ከብሉይና ሐዲስ
2. ከሊቃውንት መጻሕፍት
3. ከጠቢባን መጻሕፍትና
4. ከታሪክ መጻሕፍት ናቸው፡፡  
ይህንን የአባ ባሕርይን የመጻሕፍት ዕውቀት ከዘርአ ያእቆብ ጋር ስናነጻጽረው ‹መጻሕፍት ተምሬያለሁ› ያለውን ለመቀበልና ‹በትምህርት ከባልንጀሮቼ እበልጥ ነበር› ያለውን ለማመን እንቸገራለን፡፡
7.   ዘርአ ያእቆብ መጻሕፍት ሲያስተምር ‹ፈረንጆች እንዲህ ይላሉ፣ ግብጻውያን እንዲህ ይላሉ እላለሁ› ብሏል፡፡ ለመሆኑ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የግብጽ ትርጓሜ አለ ወይ? የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትርጓሜ የራሳቸው የኢትዮጵያውያን ትርጓሜ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን ‹ኮፕቲክ - ግብጻውያን› የሚሉት የውጭ ሰዎች እንጂ ራሳቸው ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ግብጻውያን አይሉም፡፡
8.  ‹ለግብጻውያን ፈረንጅ፣ ለፈረንጆችም ግብጻዊ እመስላቸው ነበር› ይላል፡፡ ለመሆኑ ግብጻውያን ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ወይ? ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን ‹ግብጻውያን› ብለው የሚጠሩት የውጭ ሰዎች ናቸው፡፡ ዘርአ ያእቆብ አኩስማዊና የመጻሕፍት መምህር ቢሆን ኖሮ እንዲህ ኢትዮጵያውያንን ግብጻውያን አይላቸውም ነበር፡፡ እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር ይቁመናል፡፡ ኡርቢኖ ከካቶሊኮችም ከኢትዮጵያውያንም ወገን አይደለም፡፡ አባ ማስያስና አባ አየለ ተክለ ሃይማኖት እንደሚነግን ኡርቢኖ ከካቶሊክ ሚስዮናውያን ርቋል፡፡ በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመንም የካቶሊክ ሚስዮናውያን ሲወጡ ለአባ ሰላማ በጻፈው ደብዳቤ ካቶሊክ አለመሆኑን ገልጦ ነበር፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ፈረንጆቹ ግብጻዊ፣ ግብጻውያንም ፈረንጅ የመሰላቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም፡፡
9.  ዘርአ ያእቆብ ስለ ወልደ ሕይወት በተረከበት ቦታ ላይ ‹መዝሙር 34ንና መዝሙር 108ን ቁጥራቸውን ይጠቅሳል፡፡ በኢትዮጵያ ሊቃውንት ባህል መዝሙረ ዳዊትንም ሆነ ሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍትን በቁጥራቸው አይጠቅሱትም፡፡ ዳዊትንም የሚጠቅሱት በመጀመሪያ ሐረጋቸው ነው፡፡ 
10.  ‹ወልደ ዮሐንስ የተባለ አንዱ ጠላቴ ሊከሰኝ ሄደ› ይላል፡፡ አንድን ‹የመጻሕፍት መምህር› ለመክሰስ የአካባቢው ገዥ አንሶ ነው ወልደ ዮሐንስ ደንቀዝ ድረስ የሚጓዘው? እንደዛሬው መኪና፣ አውሮፕላንና ሌላም መጓጓዣ የለ፡፡
11.  ‹ዘርአ ያእቆብ ከአኩስም ወጥቶ ሁለት ዓመት ዋሻ ውስጥ ተቀመጠ›፡፡ በመካከል ግን ዋሻ ዘግቶ ከተቀመጠበት ቦታ ‹ዳግመኛም ከንጉሡ ዘንድ ዘወትር እየሄዱ የሚያጣሉኝ ነበሩ› ይላል፡፡ (ያሬድ 22)፡፡ አንደኛ ዋሻ ዘግቶ ተቀምጧል? ለምንድን ነው ሰዎች የሚያጣሉት? አላስተማረ፣ አልተከራከረ፡፡ ሁለተኛ ያለው በተከዜ በረሓ ዋሻ ውስጥ ነው እንዴት ነው ‹ዘወትር ከንጉሡ እየሄዱ የሚያጣሉት?› መንገዱን የውኃ መንገድ አደረገውኮ፡፡ በዚያ ዘመን ከተከዜ ወደ ደንቀዝ ለመጓዝ ላስታን ተሻግሮ ወደ ጨጨሆ በመምጣት በደንቢያ በኩል ወደ ጣና ዳር መምጣትን ይጠይቃል፡፡ ዘርአ ያእቆብ ከተሸሸገም የተሸሸገው እዚያው ደንቀዝ አካባቢ መሆን አለበት፡፡
12.  ቀጥሎ ደግሞ ‹እኔም የንጉሡ ቁጣ በእኔ ላይ እንደነደደ ዐወቅኩ› ይላል፡፡ መጀመሪያ ነገር እዚያው ቤተ መንግሥቱ አካባቢ ካልነበረ እንዴት ሊያውቅ ቻለ? ሁለተኛስ በአንድ ዳዊት ብቻ በሚያውቅና ዋሻ ውስጥ በተከተተ ሰው ንጉሡ ምን ያናድደዋል? በዚያ ዘመን እንደነ እምነ ወለተ ጴጥሮስ ያሉ እሳት የለበሱ ገድል ፈጻሚዎች እየተቃወሙት ዋሻ ውስጥ በገባ ሰው ምን ያናድደዋል?
13.  ‹ከዕለታት በአንዱ ቀን የንጉሡ መልእክተኛ ወደ እኔ መጥቶ ‹ንጉሡ ፈጥነህ ወደ እኔ ና ይልሃል› አለኝ፡፡ እኔም እጅግ ፈራሁ፡፡ የንጉሡ ሰዎች ይጠብቁኝ ነበርና እሸሽ ዘንድ አልተቻለኝም› ይላል (ያሬድ 22) ዘርአ ያእቆብ የአንድ ገበሬ ልጅ፣ ዳዊት ይዞ የሸሸ፣ ዋሻ ውስጥ የገባ ሰው ነው፤ ለእርሱ የአካባቢው ጭቃ ሹሙ አንሶ ነው ንጉሡ መልእክተኛ የሚልክበት? ምንስ ስለያዘ ነው የንጉሥ ሰዎች ከበው የሚጠብቁት? ለአንድ ሰው ሲባልስ የበሽሎ በረሓን ተሻግሮ፣ ላስታን አቋርጦ አምሐራ ድረስ(የአምሐራ ጥንታዊ ድንበር የሚጀምረው ከሐይቅ ነው) እንዴት የንጉሥ ሰው ይላካል? የማይመስል ነገር ነው፡፡
14.  ዘርአ ያእቆብ ነበርኩ የሚለው በተከዜ በረሓ ዋሻ ውስጥ ነው፡፡ ወደ ንጉሥ ሱስንዮስ እንዴት እንደሄደ ሲነግረን ግን ‹በጠዋት ተነሣሁና ሄጄ ወደ ንጉሡ ገባሁ› ይላል (ያሬድ፣ 22) እንዴት አድርጎ ነው ከተከዜ በረሓ በጠዋት ተነሥቶ ደንቀዝ የሚገባው፡፡ እዚያው ቤተ መንግሥቱ አጠገብ የሚኖር ሰው ካልሆነ በቀር?
15.  ዘርአ ያእቆብ ከአኩስም ሸሽቶ ሲወጣ ‹ሦስት ወቄት ወርቅ፣ የምጸልይበትን መጽሐፍና መዝሙረ ዳዊት ያዝሁ› ይላል፡፡ ቀደም ብሎ ዘርአ ያእቆብ ‹በአኩስም ከአንድ ድኻ ገበሬ ተወለድኩ› ካለን ጋር ስናነጻጽረው አስገራሚ ይሆናል፡፡ ሦስት ወቄት ወርቅ ከየት አገኘ? በዚያን ጊዜ የመጻሕፍት መምህራን ቢበዛ እህል፣ ከብትና መሬት ይኖራቸዋል እንጂ ‹ሦስት ወቄት ወርቅ› ከየት ያገኛሉ?
16.  ዘርአ ያእቆብ ከአኩስም ተሰዶ የተከዜ በረኻ ውስጥ ገባ፡፡ በዚያም 2 ዓመታት ቆየ፡፡ ልዩ ቦታውን አይነግረንም፡፡ ወደ አምሐራ አውራጃዎች(በሐውርት) እየሄደ ይለምን ነበር፡፡ የት ነው ቦታው? አይናገርም፡፡ ሌላውን ነገር በዝርዝር የሚገልጠው ሰው እዚህ ላይ ለምን መጠቅለል ፈለገ? ንጉሥ ሱንዮስ ሲሞት ከዋሻው ወጥቶ ‹ወሖርኩ ቅድመ በሐውርተ አምሐራ - ወደ አምሐራ አውራጃዎች አስቀድሜ ሄድኩ› (ያሬድ 25) ይላል፡፡ የአማራ አውራጃዎች የሚባል ቦታ አለ? ለምን ልዩ ስሙን አልነገረንም? ስለ በጌምድር ሲናገርም ‹ወድኅረ ዐደውኩ በጌምድር - በኋላም ወደ በጌምድር ተሻገርኩ› ይላል (ያሬድ 25) በጌምድር የት? ዘርአ ያእቆብ የነገረን ልዩ ቦታ እንፍራንዝን ብቻ ነው፡፡ ለምን ቢሉ ኡርቢኖ ስለኖረበት ነው፡፡
17.  ዘርአ ያእቆብ ወደ ሸዋ ለመሄድ ተከዜን ነው የተሻገረው፡፡ ትልቁን ወንዝ ዓባይን የት ትቶት ነው? መንገዱን በሚገባ አያውቀውም፡፡
18.  ዘርአ ያእቆብ ዘመናትን የገለጠበትን መንገድ እንየው፡፡ ‹በ፲፻ወ፭፻ወ፺፪(234፣2b፤215፣1b)እም ልደተ ክርስቶስ› ይላል፡፡ ቀደምት ሊቃውንት የዘመንን ቁጥር የሚገልጡት በልዩ ልዩ መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ ገድሉ በ1580 ዓ.ም. የተጻፈለት እጨጌ ዕንባቆም የተጻፈበትን ዘመን እንዴት እንደገለጠው እንይ ‹አመ ፴ሁ ለቱት በቅብጣውያን፣ ወአይሉል በዕብራውያን ወሮማውያን፣ ወሰንመሪ በአፍርጋውያን፣ ወሸአባን በዓረባውያን፣ ወሴብቴሮስ በዮናናውያን፣ ወማስያስ በሶርያውያን፣ ወቲቶ በጽርአውያን፣ ወመስከረም በኢትዮጵያውያን፡፡ እንዘ ሀሎ ፀሐይ በኆኅተ ሚዛን ወወርኅኒ በማኅፈደ ቀውስ ወእንዘ አበቅቴ ወርኅ ፩ በዘመነ ዮሐንስ ወንጌላዊ፣፸፻ወ፹ ዓመተ ዓለም፣ በ፳ወ፭ ዓመተ መንግሥቱ ለመፍቀሬ እግዚአብሔር ንጉሥነ ሠርጸ ድንግል› ይላል፡፡
 አለቃ ወልደ ማርያም የጻፉት የዐፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ሲጀምር እንዲህ ይላል ‹እግዚአብሄር ይህንን ዓለም ከፈጠረው ፯ሺ ከ፫፻፵፭ ዓመት ሲሆን በዘመነ ማቴዎስ ልጅ ካሣ ሲባሉ ሺፍታ ሁነው ወጡ፡፡› (BNF, ethiopien, 257, 3b) ዘርአ ያእቆብ ‹እም ልደተ ክርስቶ› የሚለውን ብቻ የተጠቀመው ‹Anno Domini> የሚለውን ወስዶ መሆን አለበት፡፡  
19. ዘርአ ያእቆብ ሙሴን ሲወቅስ ‹ወሙሴሰ ይቤ ኩሉ ሩካቤ ርኩስ ውእቱ - ሙሴም ሩካቤ ሁሉ ርኩስ ነው አለ› ይላል(215,9a)፡፡ ነቢዩ ሙሴ ራሱ በጋብቻ ጸንቶ የኖረ ነቢይ ነው፡፡ በምን መልኩ ይህንን ሊል አይችልም፡፡ ሙሴ ይህንን ነገር ለመናገሩ መጽሐፋዊም ትውፊታዊም ማስረጃ የለም፡፡ ዘርአ ያዕቆብ ዳዊት ከማወቅ(እርሱንም ሲደበቅ ደጋግሞ በማንበቡ)፣ ሐዲስን ከማንበብ የዘለለ የብሉይ ትምህርት የለውም፡፡ ስለዚህም ከብሔረ ኦሪት አሟልቶ መጥቀስ አልቻለም፡፡ የካቶሊክ ሚስዮናውያን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ቤተ ክርስቲያኒቱን የከሰሱበት አንዱ ክስ ‹ኦሪታዊት ናት› የሚል ነው፡፡ ለእነርሱ በንጉሥ ገላውዴዎስ ዘመን የነበሩት ሊቃውንት መልስ ሰጥተዋቸዋል፡፡ ዘርአ ያእቆብ የእነርሱ ወገን ካልሆነ በቀር ሙሴን በዚህ መልኩ አይጠቅሰውም፡፡
20. ዘርአ ያእቆብ ‹እስልምናን፣ ክርስትናንና አይሁድነትን› የሚተች መስሎ ቢቀርብም ትችቱ ግን በኢትዮጵያውያን ላይ ይከፋል፡፡ ለምሳሌ፡-
·   ‹የሀገሩ ሰዎች ከእነርሱ ይልቅ ይከፉ ነበር›(ያሬድ ፈንታ፣ሐተታ፣ 6)
·   ‹የኢትዮጵያ መምህራን ትርጓሜያቸው ብዙ ጊዜ ከኅሊናየ ጋር አይስማማም ነበረ› ይላል፡፡
· የንጉሥ ሱስንዮስንና የአቡነ እንፍንስን ሃይማኖት የተቀበሉ፣ ሃይማኖታቸውን ያልተቀበሉትን ወንድሞቻቸውን አስቀድመው አሳደዱ፣ ገደሉም፡፡ በኋላም ተሰደው የነበሩት ጠላቶቻቸውን ሰባት እጥፍ ተበቀሉ (ያሬድ፣30)፡፡ ዘርአ ያእቆብ ኢትዮጵያውያንን በዚህ መጠን ቢከስም በዘመነ ሱስንዮስ ግን ጳጳሱ አቡነ ስምዖን ተገድለዋል፣ እጨጌው ዘትረ ወንጌል ተሠውተዋል፣ ታቦታት(አኩስም ጽዮንን ጨምሮ) ተሰደዋል፣መጻሕፍት ተቆነጻጽለዋል[1]፤ ምእመናን ታርደዋል፡፡ ይህ ሁሉ ለ‹አኩስማዊው› ዘርአ ያእቆብ አይታየውም፡፡ እንዲያውም ‹እንደዚህ ከሀገር ወደ ሀገር ስሄድ ወደ አኩስም እመለስ ዘንደ አልፈቀድኩም፤ የካህኖቿን ክፋት ዐውቅ ነበርና›(ያሬድ፣25) ይላል፡፡ ዘርአ ያእቆብ በምንም መልኩ አኩስማዊ አይደለም፡፡ አኩስምን በዚህ መጠን የሚጠላ አኩስማዊም ሊኖር አይችልም፡፡ በምክንያት የሚያምን ሰው ለዚህ ጥላቻው በቂ ምክንያት አላቀረበም፡፡ ዋና ማዕከላቸውን በአድዋ አድርገው ለነበሩት ካቶሊካውያን አኩስማውያን ቦታ ሊሰጧቸው አልፈቀዱም ነበር፡፡ የካቶሊክ ሚስዮናውያን መሠረት ሊጥሉ የፈለጉት በአኩስም ነበር፡፡ነገር ግን የአኩስም ካህናት አልፈቀዱም፡፡ይህንን ጥላቻ ነው ኡርቢኖ ያንጸባረቀው፡፡
·         ዘርአ ያዕቆብ ንጉሥ ፋሲለደስ(ፋሲል)ን አምርሮ ይጠላዋል፡፡ ንጉሥ ሱስንዮስ የኢትዮጵያ ሊቃውንትን እንዴት እንዳስፈጃቸው ለማየት የማኅደረ ማርያምና የደብረ መዊዕ ታሪክ ብቻ በቂ ነው፡፡ ሱስንዮስ ካቶሊክን ብሔራዊ ሃይማኖት ማድረጉን ተከትሎ በምዕራብ ጎጃም በምትገኘው ደብረ መዊዕ ከፍተኛ የሊቃውንት ጉባኤ ተደርጎ ነበረ፡፡ በጥቅምት 19 ቀን 1621 ዓም ጉባኤው በመካሄድ ላይ ሳለ ንጉሡ ያዘመተው ጦር ደርሶ 7000 መነኮሳትን፣ ካህናትንና ምእመናንን ፈጃቸው፡፡ እንዲያውም አባ ዘጊዮርጊስ ዘዋሸራ የተባሉት አባት ጦሩን ሳይነቅሉት ከደብረ መዊዕ ዋሸራ ዐርባ ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዘው የዋሸራ መነኮሳት ጦሩን ሲነቅሉላቸው ዐርፈዋል፡፡
·         ዐፄ ሱስንዮስን በቅርቡ ሆነው ከተቃወሙት መካከል የማኅደረ ማርያም ሊቃውንት፣ ካህናትና ምእመናን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በ1615 ዓ.ም. ሱስንዮስ ካቶሊክነትን ሲያውጅ የመጀመሪያውን ተቃውሞ አሰሙ፡፡ የንጉሡም ጦር ከተማዋን ከብቦ አቃጠላት፤ ቤተ ክርስቲያኑም አብሮ ተቃጠለ፡፡ ካህናቱም ታረዱ፡፡
·         ይህንን ሁሉ እንዳላየ አልፎ ዘርአ ያእቆብ ፋሲልን ብቻውን ይወቅሰዋል፡፡ ‹በዐመሉና በደም ማፍሰስ ጸና፣በጎ ላደረጉለት፣ ቤተ መንግሥትንና ያማሩ ቤቶችን ለሠሩለት፣ በጥበብ ነገር ሁሉም መንግሥቱን ላሣመሩለት ፈረንጆችን ጠላቸው› ይላል፡፡(ያሬድ፣31) ፈረንጆቹ የሠሩትን ግፍ ከማንሣት ይልቅ በሠሩት ሕንጻ እንዲታወሱ ይፈልጋል፡፡ ለመሆኑ ፈረንጆቹ ይህን ብቻ ነው ሲሠሩ የኖሩት? የገደሉትስ፣ ያቃጠሉትስ፣ የዘረፉትስ መጽሐፍ? ታቦታቱ ከየደብሩ እንዲወጡ ያወጁትስ? ሃይማኖተ አበው መጽሐፍን ለማጥፋት ያወጁትስ ዐዋጅ?
·         ንጉሥ ፋሲለደስን ‹ያም ፋሲለደስ ክፉን ነገር የሚሠራ ሆነ፡፡ ሰዎችን ያለ ፍርድ ይገድል ነበር፡፡ አመንዝራነትም ያበዛ ነበር፡፡ ሴቶችንም ከእነርሱ ጋር ካመነዘረ በኋላ ይገድላቸው ነበር፡፡ ዐመጻን የሚያደርጉ ሠራዊትንም ልኮ የድኾችን ሀገሮችና ቤቶች እንዲቀሙ ያደርግ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለክፉዎች ሕዝቦች ክፉውን ንጉሥ ሰጥቷቸው ነበርና፡፡ ስለ ንጉሡና ስለ ሕዝቡም ኃጢአት ረሀብና መቅሰፍት መጣ፡፡ ከረሃብ በኋላም ቸነፈር ሆነ፡፡ ብዙዎችም ሞቱ፡፡ ሌሎችም ፈሩ፡፡›(ያሬድ፣31) ይላል፡፡ ፋሲልን ለምን ጠላው? መልሱ ቀላል ነው፡፡ የፖርቹጋል ካቶሊኮችን ከሀገር ያስወጣውና፣ የመግቢያ በራቸውንም የዘጋው፣ የተዋሕዶን እምነትም የመለሰው ዐፄ ፋሲል ነው፡፡ ቢጠሉት አይገርምም፡፡ ‹በአመክንዮ አምናለሁ› የሚለው ‹ፈላስፋው› ዘርአ ያእቆብ እንዲህ ሲል ግን ይገርማል፡፡ ሱስንዮስ ሲገድል ያልመጣ መቅሰፍት እንዴት በፋሲል ዘመን መጣ?
·         አንድ ታሪክ እናንሣ በንጉሥ ሱስንዮስ ላይ የሚደርሰው ተቃውሞ እያየለ ሲመጣ ንጉሡ እጨጌ ዘወንጌልን በ1616 ዓ.ም. ከመንበሩ አውርዶ በግዞት ወደ ምጽርሐ ደሴት ላከው፡፡ በግዞትም እያለ የካቲት 24 ቀን 1621 ዓ.ም. ዐረፈ፡፡ እጨጌ ዘወንጌል ከዕረፍቱ በኋላም መከራው አልቀረለትም፡፡ እጨጌ ዘወንጌል ሲያርፍ የተቀበረው በምጽርሐ ገዳም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነበረ፡፡ አልፎንዙ ሜንዴዝ ይህንን ሲሰማ ‹‹መናፍቅ ተቀብሮበታልና የቤተ ክርስቲያኑ ቅድስና ጠፍቷል፤ ስለዚህም ቅዳሴ ማከናወን አይቻልም›› ሲል ቁጣውን ገለጠ፡፡ በዚህ ምክንያትም ዐጽማቸው ከመቃብር ወጥቶ ተጣለ፡፡ በዚህ ዘመን ያልመጣ መቅሰፍ ነው በፋሲል ዘመን የሚመጣው?
21.  ዘርአ ያእቆብ ‹የክርስቲያን ሕግ ግን ከጋብቻ ምንኩስና ትበልጣለች ባለች ጊዜ ሐሰትን ተናገረች፤ ከእግዚአብሔር የተገኘች አይደለችምና› (ያሬድ፣12) ይላል፡፡ ከየት እንዳመጣው ራሱ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የሚለው ‹ያላገባ ጌታን እንዴት ደስ እንደሚያሰኝ ያስባልና መልካም አደረገ› ነው(1ኛቆሮ. 7) ስለ ምንኩስና አልተናገረም፡፡ ከየት አምጥቶ ይከራከራል? ቀደም ብለን እንዳየነው ኡርቢኖ ምንኩስናውን ትቶ ትዳር መሥርቷል፡፡ በዚህም ከሌሎች ሚስዮናውያን ተለይቷል፡፡ ለዚህ መሸሻ ነው የሚፈልገው፡፡
22.  ዘርአ ያእቆብ በእንፍራንዝ ባዕለ ጸጋውን ሀብቱን ሲያገኘው ‹በማግሥቱ አኩስም ወዳሉ ዘመዶቼ ደብዳቤን እጽፍ ዘንድ ቀለምና ብራናን ጠየቅሁት› ይላል (ያሬድ 26) ሀብቱ ባዕለ ጸጋ የእንፍራንዝ ሰው ነው፡፡ ብራናና ቀለም የሚገኘው ወይ ከጸሐፊ ቤት አለበለዚያም በቤተ መንግሥት ነው? በኢትዮጵያ ባህል ብራናና ቀለም የሚገኘው ከቁም ጸሐፊው ነው፡፡ ይህ አሁን ዘርአ ያእቆብ የሚነግረን ባህል የፈረንጆቹ ነው፡፡ ደግሞስ ‹ቀለመ ወሰሌዳ› ለምን አለ? ጌታቸው ኃይሌ ‹ሰሌዳ›  የሚለውን ‹ክርታስ› ብለውታል( ሐተታ፣37)
23.  ዘርአ ያእቆብ ልጅ የወለደበትን ጊዜ ጥቅምት 11 ቀን 1631 መሆኑን ይነግረናል፡፡ ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ ቢሆን ይህ ልማድ አይኖረውም ነበር፡፡ እንኳን ያኔ በዐፄ ምኒልክ ዘመንም የልጆች ልደት አይታወቅም ነበር፡፡የነገሥታቱ ካልሆነ በቀር፡፡
24.   ወልደ ዮሐንስ ዘርአ ያእቆብን እንፍራንዝ ድረስ ይከታተለዋል፡፡ ዘርአ ያእቆብ እንፍራንዝ ውስጥ ከሀብቱ ዘንድ ተጠግቶ በጽሕፈትና በድጉሰት ነበር የሚኖረው፡፡ ያንን ያህል የታወቀና ተጽዕኖ ፈጣሪ አልነበረም፡፡ ታድያ ወልደ ዮሐንስ ለምን ይከታተለዋል? ሁለቱም እዚያው ደንቢያ ውስጥ የሚኖሩና ቀድመው  የሚተዋወቁ ሰዎች ካልሆኑ በቀር፡፡
25. ዘርአ ያእቆብ እንደሚለው ወልደ ዮሐንስ አኩስማዊ ነው፡፡ በኋላ ግን በደንቢያ አድባራት ላይ ተሾመ፡፡ ነገሥታት በባህላቸው አብዛኛውን ጊዜ ሰውን የሚሾሙት በተወለደበት ቦታ ነው፡፡ እናም ወልደ ዮሐንስ የዚያው የደንቢያ ሰው ቢሆን ነው ደንቢያን የተሾመው፡፡
26. ዘርአ ያእቆብ የነገሥታቱንና በሀገሪቱ ላይ የደረሱትን ነገሮች ጊዜያቸውን በሚገባ ነው የመዘገበው፡፡ ምናልባትም ለነገሥታቱ ዜና መዋዕልና ታሪከ ነገሥት ቅርበት ሳይኖረው አይቀርም፡፡ ኡርቢኖ ይኖር የነበረው የነገሥታቱ ታሪከ ነገሥትና ዜና መዋዕል ከሚገኝባት ከማኅደረ ማርያም አጠገብ በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም፡፡
(ይቀጥላል)


[1] ዝርዝሩን ለማወቅ የፈለገ ይህንን ፈልጎ ያንብብ፡- The Missionary Factor in Ethiopia: Papers from a Symposium on the Impact of European Missions on Ethiopian Society, Lund University, August 1996. Edited by Haile Getatchew, Lande Aasulv, and Rubenson Samuel. Studies in the Intercultural History of Christianity 110. Frankfurt am Main: Peter Lang, 1998.
8 comments:

 1. ቁጥር ፪ ና ቁጥር ፩፱ ሀሳቡ ይጋጫል።

  ReplyDelete
  Replies
  1. If you have a proof against his idea; Please disproof each of his source and logic individually. You may need the guy be an Ethiopian bcs we have heard a lot about him and may be we have talked about him for many people assuming his Ethiopian. Whether he is Ethiopian or not it is better to be rational and see the logic behind his (zera yacob) writing. Finally it is not Daniels right of duties to make zera yacob an Ethiopian or others; it is the fact and their evidence proves his citizenship.

   Delete
 2. "ዲያቆን"ዳኒኤል ክብረት "ባልበላውም ጭሬ ላፍሰው" ከሚል የደሮ አስተሳሰብ በመነሳት ይመስላል ፈላስፋው ዘርአያቆብን የወንዙ ልጅ ማድረግ ስላልቻለ ‹‹የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ›› የሚል ርዕስ በሰጠው ሐሰተኛና ሸረኛ ተከታታይ ፅሑፍ "ፈላስፋው ዘርዓ ያእቆብም ተማሪው ወልደ ህይወትም ኢትዮጵያውያን አይደሉም›› ብሎ መጣ።
  እንዲህም አለ፤ "ሐተታ ዘርዓ ያእቆብ› ዲ. ኡርቢኖ በተባለ ፈረንሳዊ የተፃፈ እንጂ የአክሱም ተወላጅ እንደሆነ በሚታወቀው ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ የተፃፈ አይደለም›› አለ፤
  "ምክንያቶቹን" ሲገልፅ ደግሞ፤
  አንደኛው ‹‹ ዘርአ ያዕቆብና ዳ. ኡርቢኖ የተወለዱት በተመሳሳይ ቀን ስለሆነ ፤ ሁለተኛ ወርቄ የክርስትና ስሙ ‹ዘርአ ያእቆብ› ሲሆን የዳ. ኡርቢኖ ደግሞ ‹Jacques - ያዕቆብ ስለሆነ" ብሎ ፃፈ።

  ዳኒኤልየ፦ ወደድክም ጠላህም ከዘመኑ እጅግ ቀድሞ የተወለደው ጠቢቡ፣ አዋቂው፣ ጥልቅ አሳቢው፣ ልበ-ብርሀኑ፣ ፈላስፋው ዘርአያቆብ ከአክሱም የገበሬ ልጅ ተወልዶ ለዐለም የተሰጠ ጠቢብ ነው። ዘርአያቆብ ምስጋና ይግባውና ስለማንነቱ፣ ስለውልደትና ዕድገቱ በማያወላዳ ሁኔታ ፅፎ ትቶልናል።

  ይኸውና፦

  ጥንተ ትውልዴ ከአክሱም ካህናት ነው። ሆኖም እኔ የተወለድኩት አክሱምበ አካባቢ ከአንድ ደኻ ገበሬ፥ በነሐሴ 25 ቀን፥ በያዕቆብ መንግሥት በ3ተኛው ዓመት፥ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ1592 ዓመት ነው። ክርስትና ስነሣ ዘርአ ያዕቆብ ተባልኩ፤ ሰዎች ግን ወርቄ ነው የሚሉኝ።

  ባደግሁ ጊዜ እንድማር አባቴ ትምህርት ቤት አስገባኝ። ዳዊት ስደግም አስተማሪዬ ላባቴ፥ "ይኽ ሕፃን ልጅህ ልበ ብሩህ ነው። ትምህርትም አይሰለቸውም። (ከፍተኛ) ትምህርት ቤት ብታስገባው ሊቅና መምህር ይሆናል" አለው።

  አባቴ ይኸንን ሰምቶ ዜማ እንድማር (ዜማ ትምህርት ቤት) አስገባኝ። ግን ድምፄ ጥሩ አይደለም፤ ጉሮሮዬም ጎርናና ነው። በዚህም ምክንያት ለጓደኞቼ ሣቅና ስላቅ ሆንኳቸው። እዚያ 3 ወር ቆየሁ፤ ከዚያ በኋላ በልቤ እያዘንኩ ተነሥቼ ቅኔና ሰዋስው ወደሚያስተምር ወደሌላ መምህር ሄድኩ። (እዚያ) ከጓደኞቼ እያፈጠንኩ እንድማር እግዚአብሔር ጥበቡን ሰጠኝ። ይኸም በፊት ባሳዘነኝ ፈንታ አስደሰተኝ። እዚያ 4 ዓመት ቆየሁ።

  በዚያን ዘመን እግዚአብሔር ከሞት አፍ ተፋኝ፤ ምክንያቱም ከጓደቼ ጋራ ስጫወት ገደል ገብቼ ነበር። እግዚአብሔር በተአምር እንደአዳነኝ እንጂ ሌላስ እንዴት እንደዳንኩ አላውቅም። ከዳንኩ በኋላ ገደሉን በረጅም ገመድ ለካሁት፤ 25 ክንድ ከ1 ስንዝር ሆኖ ተገኘ። ምንም ሳልሆን ተነሥቼ ያዳነኝን እግዚአብሔርን እያመሰገንኩ ወደመምህሬ ቤት ሄድኩ።

  ከዚያ በኋላ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜ ለመማር (ወደ መጽሐፍ ትምህርት ቤት) ሄድኩ። በዚህ ትምህርት 10 ዓመት አሳለፍኩ።9 መጻሕፍቱን ፈረንጆች10 እንደሚተረጒሟቸው፥ እንደገና ደግሞ ያገራችን መምህራን እንደሚተረጒሟቸው ተማርኩ። ግን ትርጓሜያቸው ብዙ ጊዜ ከኅሊናዬ ጋራ አይስማማም ነበረ። ሆኖም ዝም አልኩ፤ አስተያየቴን ሁሉ በልቤ ደበቅሁ።

  ከዚያ በኋላ ወደ አክሱማዊት ሀገሬ ተመልሼ 4 ዓመት መጻሕፍት አስተማርኩ። ይህ ዘመን መጥፎ ዘመን ነበረ፤ ምክንያቱም በሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት በ19ነኛው ዓመት ከፈረንጆች ወገን አቡነ እፎንስ11 የሚባል ጳጳስ) መጥቶ ነበረ። (ከመጣ) ከ2 ዓመት በኋላ በሞላ ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ስደት ሆነ፤ ምክንያቱም ንጉሡ የፈረንጆቹን ሃይማኖት ወዶ ነበረ። ስለዚህ ይኽንን ሃይማኖት ያልተቀበሉትን ሁሉ ያሳድዳቸው ጀመረ።

  እኔም ሀገሬ ሆኜ መጻሕፍት ሳስተምር ከጓደኞቼ ብዙዎች ጠሉኝ፤ ምክንያቱም በዚህ ዘመን የጓደኛ ፍቅር ጠፍቶ ነበረ። ቅናትም ያዛቸው፤ ምክንያቱም በትምህርትና ጓደኛ በማፍቀር ከነሱ እበልጥ ነበረ። ከሰዎች ሁሉ ጋራም፥ ከፈረንጆቹም12 ሆነ ከግብጻውያን (ጋራም)፥ እስማማ ነበረ። ሳስተምርና መጻሕፍቱን ስተረጒም ፈረንጆች እንዲህ፥ እንዲህ ይላሉ፤ ግብጻውያን እንዲህ፥ እንዲህ ይላሉ" እላለሁ፤ እኛ ጥሩዎች ስንሆን ሁሉም ጥሩ ይሆናልî እላለሁ እንጂ ይኸኛው ደኅና ነው፤ ይኸኛው መጥፎ ነው"" አልልም። በዚህም ምክንያት ሁሉም ጠሉኝ፤ ምክንያቱም ለግብጻውያኑ ፈረንጅ ስመስላቸው ለፈረንጆቹ ግብጻዊ እመስላቸው ነበረ። (ሰዎች) ብዙ ጊዜ

  ከንጉሡ ዘንድ የውሸት ክስ አቀረቡብኝ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አዳነኝ።
  ከዚያ በኋላ ግን ከአክሱም ካህናት አንዱ ጠላቴ የሆነ ወልደ ዮሐንስ የሚሉት (ሊያጣላኝ) ወደንጉሡ ሄደ። የንጉሡ ወዳጅም ሆነ፤ መቸም የንጉሦች ወዳጅነት የሚገኘው በሸንጋይ ምላስ ነው። ይህ ሸንጋይ ወደንጉሡ ሄዶ ስለኔ (እንዲህ) አለው፥ "በውነት ይህ ሰው ሰዎችን ያሳስታል፤ ለሃማኖታችን ልንነሣና ንጉሡን ልንገድለው፥ ፈረንጆችንም ልናሳድዳቸው ይገባል ይላቸዋል" (በሚልና) ይኸንንምበሚመስል ደጋግሞ ከሰሰኝ። እኔም ይኸንን በጊዜው ዐውቄ ፈራሁ። ያለኝን ሦስት ወቄት ወርቅ፥
  የምጸልይበትን መጽሐፍ፥ መጽሐፈ መዝሙረ ዳዊትን ይዤ ሸሸሁ። ወዴት እንደምሄድ ለማንም አልገለጥኩም። በሌሊት
  ወደ ተከዘ ወንዝ አቅጣጫ (ሄጄ) ከዱር ገባሁ። በማግሥቱ ረኀብ ያዘኝ። በፍርሃት ወጥቼ ከአገሩ ሀብታሞች [አንዱ] ዘንድ የሚበላ እንጀራ ልለምን ሄድኩ። ሰጡኝ፤ በልቼ በሽሽት ሄድኩ። ብዙ ጊዜ እንደዚሁ አደረግሁ።

  ReplyDelete
  Replies
  1. ምንም እንኳን የሀይማኖትም ሆነ የታሪክ ዕውቀት ባይኖረኝም እስካሁን የተጻፈው የዲያቆን ዳንኤል ፅሁፍ የተለያዩ የመረጃ ምንጮችን በማጣቀስ የዘመኑን የሀይማኖት አስተምህሮ አካሄድን እና አጻጻፍ ስልትን ከግምት በማስገባት ዘርያዕቆብ የሚባል ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ የለም የሚል መከራከሪያ ሀሳብ (hypothesis) ይዞ እሱን ለማስረገጥ የተጻፈ ፅሁፍ ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ የምርምር ሥራ መሰረታዊ መርህ ተከትሎ የተፃፈ ፅሁፍ እንደመሆኑ የእሱን ድምዳሜ የተሳሳተ ነው ብሎ የሚያስብ ምሁር እሱ የአስቀመጣቸውን የመከራከሪያ ነጥቦች በማንሳት እና እሱ የአስቀመጣቸውን ማጣቀሻ የታሪክ እና የኃይማኖት መፅሀፍት እንዲሁም ወቅታዊ አካባቢያዊና ማህበራዊ ሁነቶችን በማንሳት መሞገትና የእሱን ድምዳሜ ማፋረስ እንዲሁም ቀደምት ጸሃፊያን ዘርያዕቆብ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ነው ብለው የአመኑበትን መከራከሪያ በማጣቀስ እንኳን መሞገት ይቻላል እራሱ ዘርያዕቆብ በፅሁፍ አስቀምጦልናል ብለው በአስተያየቶ ከጻፉት ሀተታ ባሻገር፡፡
   ነገር ግን ፅሁፉን ለማጣጣል ከመነሻው የአስቀመጡት ብሄር ተኮር መልዕክት አስተያየቶ በጭፍን የተሰጠ እና ለጸሀፊው (ብሎም ለብሔሩ) ከአሎዎት የተዛባ የጥላቻ አመለካከት የተቀዳ እና ያንንም ለማንጸባረቅ የተጻፈ እንጂ የፅሁፉን ሀሳብ ለመሞገት አለመሆኑን ስለሚያመላክት የጤናማ ሰው አመለካከት ነው ብሎ ለመውሰድ ያስቸግራል፡፡
   ፍልስፍና በመሰረታዊ ባህሪው (እኔ ሲገባኝ) በሃሳብ ልዕልና በምክንያታዊ ጠያቂነት እና መልስ ፍለጋ የሚደረግ ግለሰባዊ ጉዞ ሲሆን ግለሰቡ በፍልስፍናው የሚያነሳቸው ወይም የደረሰባቸው ኃልዮት (logic) ሌላው ሊማርባቸውና ሊጋራቸው አልያም ላይስማማባቸው የሚችል ዕይታዎች ናቸው (ዕውነታዎች ለማለት ስለሚያስቸግር ነው)፡፡ ስለዚህ እንደ ፈላስፎቹ መንገድ የሚነሱትን ሀሳቦች በሀሳብ እና በጥያቄ መሞገት ወደ ትክክለኛ መንገድ የሚመራ ይመስለኛል፡፡
   በተረፈ ግን ፈላስፋው የአስተያየት ሰጪው ወይም ጸሀፊው የወንዝ ልጅ ሆነ አልሆነ ዕውቀት በወንዜያዊነት የሚጋባ ስላልሆነ የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡ የግሪክ ፍልስፍና ለዓለም ሕዝቦች ግለሰባዊ ፍልስፍና የምክንያታዊ ጠያቂነትን ፈር ቀዳጅ በመሆን ሰዎች የአዕምሮ ብቃታቸውን በመጠቀም ነገሮችን እንዲመረምሩ አስተማረ እንጂ ለግሪካውያን በዘር የተላለፍ ዕውቀት የለም ሊኖርም አይችልም፡፡ በመሆኑም አስተያየት ሰጪው የዘር መነጽሮን አውልቀው የአስቀምጡና ቢቻል የአዕምሮ ልዕልና እንደ ሰብዓዊ ፍጡር እንዲኖሮ ቢተጉ ይመረጣል፡፡ የተሳሳተ መልዕክት በማስተላለፍ ለጽሁፉ ጎራ መለየት ማንንም አያንፅም፡፡

   Delete
 3. I read all the five parts sofar and also reviewing other literatures I came accross. Daniel's research is so comprehensive on Zara Yakob that we will know Zera Yakob in a much different light than before.I am very eager to read the remaining parts of this research, especially the conclusion and the leason we learn. One I picked here is how foreign influence was trying to sip into our history and more...

  Kidanemariam

  ReplyDelete
 4. ሙሐዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ሰላም ለአንተ ይሁን!
  በጡመራ መድረክህ ላይ ‹የሌለውን ፈላሰፋ ፍለጋ!› በሚል ዐቢይ ርእስ በተከታታይ የጻፍከውን ጽሑፍህን እየተከታተልኩ ነው፡፡ እነዚህ በተከታታይ እየጻፍካቸው ያሉትን ጽሑፎች ሌሎች ምሁራዊ ሙግቶችን አካቶ በመጽሐፍ መልኩ ቢቀርብ ደግሞ እጅጉን መልካም ነው እላለኹ፡፡ ‹‹ዋኖቻችንን እናስብ!›› በሚል በብሔራዊ አዳራሽ በተደረገው ጉባኤ ላይ ዘርዓያቆብን በተመለከተ ከቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎችና ዲስኩሮች በተለየ መልኩና እንደውም የታቃረነ በሚመስል አቀራረብ ያቀረብከውን ንግግር በተመለከተ ከምስክር ጋር በአንድ ጉዳይ ተገናኝተን አውግቶኝ ነበር፡፡ ሌላ አንድ ወዳጄም አንተን ሙግት ተቃርኖ በዘርዓያቆብ ፍልስፍና እሳቤዎች ላይ የራሱን ጥቂት ሐሳቡን አካፍሎኝ ነበር፡፡ በጊዜው በብሔራዊ አዳራሽ አልነበርኩም ነበር፤ ግና የዘርዓያቆብ ሐተታ/ፍልስፍና በሚል የተጻፈው ሐሳብ ኢትዮጵያዊና ኦርቶዶክሳዊ በኾነ ሰው የተጻፈ አይደለም የሚለው ሙግት ጠንክርና መረር ብሎ ሲሰማ ይህ የአንተ ሙግት ምናልባት ለእኔ የመጀመሪያዬ ነው ማለት እችላለኹ፡፡ ከዚህ በኋላ በጡመራ መድረክህ በብሔራዊ አዳራሽ ያነሣኸውን ሙግት ሰፋና ተንተን አድርገህ በማቅረብህ ሙግትህን ይደግፉልኛል ያልካቸውን መረጃዎችና ምሁራዊ አስተያየት የታከለባቸውን ጽሑፎችህን በጉገት እየተከታተልኩ ነው፡፡

  ስለ ኢትዮጵያዊው ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብም ኾነ ስለ ሐተታ ዘርዓያዕቆብ በመጀመሪያ የሰማኹት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለኹ ነበር፡፡ በጊዜው የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ለበርካታ ዓመታት ተዘግቶ የተከፈተበት ስለነበር በግቢው ውስጥ የነበርን ተማሪዎች ስለ ፍልስፍና ለማወቅ ጉጉታችን ጣራ ነክቶ እንደነበር ነው የማስታውሰው፡፡ በወቅቱም በካናዳዊው ፕ/ር ክላውድ ሳምነር የተጻፈውን ባለአምስት ቅጽ መጽሐፍ በተለየ ጉጉትና ስሜት ውስጥ ኾኜ አለፍ አለፍ እያለኩ ማንበቤብ አስታውሳለኹ፡፡ ክላውድ ሳምነር ዘርዓያዕቆብን የአውሮፓን ዘመናዊ ፈላስፎች ሳይቀር የቀደመ ‹‹ሂዩማን/ሂዩማኒስት ፊሎሶፈር›› ሲሉ ነው በዚህ መጽሐፋቸው ዘርዓያዕቆብን የሚያሚካሹት፡፡
  ከዛ በኋላ የተለያዩ ምሁራንና ጸሐፊዎች ስለ ዘርዓያዕቆብ በጋዜጣና በመጽሔቶች ያስነበቧቸውን ጽሑፎች ለማንበብ ዕድሉ ገጥሞኛል፡፡ በአንድ አጋጣሚም ደቡብ አፍሪካ ትምህርት ላይ እያለኹ ለዶክትሬት ዲግሪው እየተማረ የሚገኝ አንድ ናይጄሪያዊ ወዳጄ ስለ ዘርዓያቆብ ፍልስፍና ‹አፍሪካዊ ፍልስፍና› በሚል ርእስ ዶ/ር ቴዎድሮስ ኪሮስ የሚባል ኤርትራዊ ምሁር በሀገረ አሜሪካ ለዶክትሬት ዲግሪው መሟያ ያዘጋጀውን የጥናት ድርሳኑን ማሳተሙን በተመለከተ ይኸው መጽሐፉን አሳይቶኝ ነበር፡፡ የዚህን የዶክትሬት ድርሳን ጥናት መጽሐፍ ርእስና የጸሐፊውን ሰው ስም ግን መቶ በመቶ እርግጠኛ አይደለኹም፡፡ ምናልባት ዳኒ ይህን መጽሐፍ ለማየት ዕድሉ አጋጥሞህ እንደሆነ ግን አላውቅም፡፡

  ወንድማችን የጀመረከው ምሁራዊ ሙግት መልካም ነው፡፡ በጥናትህ የደረስክበትን የመጨረሻ ድምዳሜህን ለማንበብም ጓጉቻለኹ፡፡ ይህ ሙግትህን የሚዳኝ፣ አንተንም ኾነ ሌሎች ምሁራንን የሚያከራክር ኢትዮጵያዊ የ‹‹አርዮስፋጎስ›› አደባባይ ቢኖር ደግሞ ሸጋ በኾነ ነበር፡፡ በተለይ እንደእነ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ፕ/ር መስፍን ኃ/ማርያም እና የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው የፍልስፍና መምህሩ ብሩህ ዓለምነህ ያሉ አፍቃሪ-ዘርዓያዕቆብ ምሁራንን በሐሳብ የሚሞገቱበት የክርክር መድረክ ያስፈልገናል፡፡ ለዚህ ሙግትህ/ጽሑፍህ እነዚህ ምሁራን የመከራከሪያ ሐሳባቸውን እንደሚወረውሩም ተስፋ አድርጋለኹ፡፡
  ነገሬን ላሳጥረውና ወንድማችን እንዲህ እንደአንተ ዘርዝር ያለ ባይሆንም ሮማዊው ኮንቶ ሮሲኒ ‹‹ሐተታ ዘርዓያዕቆብ›› የኢትዮጵያ ሰው ጽሑፍ/ፍልስፍና አለመኾኑን ሞግቶ ጽፏል፡፡ በእርግጥ የእርሱ አጻጻፍ ከአንተ የሚለየው ሮሲኒ ሐተታ ዘርዓያዕቆብን የጻፈው ኢትዮጵያዊ አይደለም ሲል ክርክሩን ፈር ለማስያዝ ከዘረኝነት አስተሳብ/ምልከታና እንዲሁም ጥቁር እንዲህ ዓይነት የተራቀቁ እሳቤዎችን ለማሰብና ለመፈላሰፍ የሚያበቃ አእምሮ የለውም ከሚል ስሑት ድምዳሜና ንቀት የሚነሣ መኾኑ ነው፡፡ የአንተው አጻጻፍ/ምሁራዊ ሙግት በእጅጉ የተለየ የሚያደርገው ደግሞ የኢትዮጵያን የረዥም ዘመናት ታሪክ፣ ግዙፍ ሥልጣኔ፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ ባህልና ለዚህ ለሀገራችን ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ባህልና ትውፊት ትልቅ አሻራ ያላትን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መጻሕፍቶች፣ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና/አስተምህሮ፤ የዘመኑን የቤተክርስቲያኒቱን ሊቃውንት ሥራዎች መሠረት ያደረገና ያመሳከረ መኾኑ ነው፡፡

  ወንድማችን ወደፊትም እንዲህ ዓይነት ‹እውነታው የቱ ጋር ነው?!› በሚል ፈታሽና ሞጋች የኾኑ ጽሑፎችን በሰፊው እንጠብቃለን!!

  ReplyDelete
 5. It is so good deacon Daniel. from the binging i try to read it.Your research is more dependent on evidences that are concentrated on ancient Ethiopian literature. it is obvious that your goal is the truth.

  ReplyDelete