Thursday, February 15, 2018

ከማስታገሻው ወደ መፈወሻው

የሚፈቱትን ለመቀበል የወጣው ሕዝብ
መንግሥት መረራ ጉዲናን፣ እስክንድር ነጋን፣ አንዱዓለም አራጌን፣ በቀለ ገርባንና ሌሎችንም የፖለቲካ እስረኞችን መፍታቱ አንድ ርምጃ ወደፊት ነው፡፡ ቢያንስ ያንዣበበውን የሥጋት ደመና ይገፈዋል፡፡ የሀገሪቱንም ዜና ከ‹ታሠሩ› ወደ ‹ተፈቱ› ይቀይረዋል፡፡ የተስፋ ብልጭታም በሕዝቡ ላይ ይጭራል፡፡ ከታሠሩት ጋር አብሮ ለታሠረውም ወገን ትልቅ እፎይታ ነው፡፡ አብሮ ግን ሁለት ነገሮች ተያይዘውና ቀጥለው መምጣት አለባቸው፡፡

Monday, February 12, 2018

የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ (ክፍል ስድስት እና የመጨረሻው)

በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ ይህንን ይጫኑ
የጌታቸው ኃይሌ መከራከሪያ
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ዘርአ ያእቆብን በተመለከተ በቅርቡ ሁለት ጽሑፎችን አውጥተዋል፡፡ የመጀመሪያው በ2006 ዓ.ም. ባሳተሙት ‹ሐተታ ዘዘርአ ያእቆብ› በሚለው መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ የሰጡት ትንታኔ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በ2017 ባወጡት Ethiopian Studies in Honor of Amha Asfaw በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ያቀረቡት ጥናት ነው፡፡
ጌታቸው ኃይሌ ዘርአ ያእቆብ በካቶሊክ ሚስዮናውያን ተጽዕኖ ውስጥ የወደቀ፣ ፍልስፍናውንም በአብዛኛው ከእነርሱ የወሰደ ኢትዮጵያዊ ዳዊት ደጋሚ ደብተራ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡ ለዚህ ድምዳሜ መድረሻ ያነሷቸው ነጥቦች አሉ፡፡ አንድ በአንድ እንያቸው፡፡
1.      ኡርቢኖ የሐተታ ደራሲ ከሆነ ለምን በግእዝ ይጽፈዋል? ምክንያቱም የጻፈው ለኢትዮጵያውያን ነው እንዳንል ሁለቱንም ቅጅዎች ወደ ፈረንሳይ ልኳቸዋል፡፡ በሐተታዎቹ ውስጥ ያሉት ሐሳቦች ደግሞ ለአውሮፓውያን አዲስ አይደሉም፡፡
2.     የቅጅ ቁጥር 234 በኡርቢኖ የእርማት ሥራ ተሠርቶበታል፡፡ ኡርቢኖ የራሱን ሥራ ለምን ያርመዋል?
3.     ሐተታ ኢትዮጵያዊውን መዝሙረ ዳዊት በሚገባ በሚያውቅ ሰው የተዘጋጀ ነው፡፡ ‹በዳዊት ደጋሚ ደብተራ›፤ መዝሙረ ዳዊት የዕለት የጸሎት መጽሐፉ ካልሆነ በዚህ መጠን አይጠቅሰውም፡፡ ይህ ደግሞ ዳዊትን በቃላቸው የሚይዙት የኢትዮጵያውያን ልማድ ነው፡፡
4.     ወለተ ጴጥሮስን እንዴት በበጎ ያነሳታል?
5.     ኡርቢኖ ሊያርመው የተነሣው የዘመን አቆጣጠር
6.     ‹ፋሲለደስ› እና ‹ወልደ ፋሲለደስ› በሚሉት ስሞች ላይ የሠራው ስሕተት
7.     ሌሎች ዝርዝር ማስረጃዎች
ኡርቢኖ ጽሑፎቹን ደጋግሞ የማረም ጠባይ እንዳለው በቅርጣግና ሌሊቶች የትርጉም ሥራው ላይ ታይቷል፡፡ ከማርች 1852 ጀምሮ የኢትዮጵያን ሊቃውንት ሊያስደስት የሚችል ቅጅ ለማውጣት የተለያዩ ቅጅዎችን አዘጋጅቷል፡፡ ኡርቢኖ አንዱን ቅጅ (215) የላከው ኢትዮጵያ ሆኖ ሲሆን ሌላኛውን (234) የላከው ግን ካይሮ ሆኖ ነው፡፡ ለምን? ኡርቢኖ ካይሮ የገባው ከኢትዮጵያ ተባርሮ ነው፡፡ አንደኛውን ቅጅ ለዲ. አባዲ የላከው ከዲ. አባዲ ገንዘብ ለማግኘትና የዕውቀቱን ልክ ለማሳየት ነው፡፡ ለዚህም ደብዳቤው ይነግረናል፡፡ ሌሎቹን ቅጅዎች ያዘጋጃቸው ግን ለኢትዮጵያውያን አገልግሎት ነበር፡፡ እንዳጋጣሚ ግን ከሀገር ሲባረር ይዞት ሄደ፡፡ በዚያውም ካይሮ ላይ የመመለስ ሐሳቡ የማይሳካ ሲመስለው ለዲ. አባዲ ላከለት፡፡ የዚህ ዓላማም ገንዘብ ማግኘት እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡ ሁለቱም ወደ አውሮፓ የተላኩት በተለያየ ዓላማ ነው፡፡ የመጀመሪያው ለዲ. አባዲ አዳዲስ መዛግብት የማግኘት ፍላጎቱን ለማርካት፤ ሁለተኛው ደግሞ ካይሮ ላይ ተስፋ ሲቆርጥ የላካቸው ናቸው፡፡
‹ዘርአ ያእቆብ› ከዳዊት በላይ እንደማያውቅ ቀደም ብለን አይተናል፡፡ ይህ ግን ዘርአ ያእቆብ ተማርኩ ካለው የመጻሕፍት ትምህርትና ‹ባልንጀሮቼ በዕውቀቴ የተነሣ ቀኑብኝ› ከሚለው ገለጣው ጋር የሚጣረስ ነው፡፡ ዘርአ ያእቆብ ለምን በዚህ መጠን መዋሸት ፈለገ? ደግሞስ ያንን ያህል ‹የሚፈላሰፍ› ሰው እንዴት በዕውቀት ይህንን ያህል ደከመ? በውሸትስ ይህንን ያህል በረታ? እንፍራንዝስ ቁጭ ብሎ ምንድን ነው ሲያስተምር የነበረው? የማያውቀውን መጽሐፍ ነው ሲያስተምር የነበረው? እንደ እኔ ግምት እነዚያን የዳዊት መዝሙራት ያስገቡለት አብረውት የሠሩት ደባትር ናቸው፡፡ እርሱም በኋላ ጥቅሶቹን በኅዳግ ጨምሮባቸዋል፡፡

Thursday, February 1, 2018

የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ (ክፍል አምስት)

ለመሆኑ ሐተታዎቹ ምን ይነግሩናል?
1.  ዘርአ ያእቆብ የተወለደው ከአክሱም ካህናት ወገን መሆኑን ይነግረናል፡፡ በአኩስም የትኛው ክፍል ወይም ቦታ እንደሆነ ግን አይገልጥም፡፡ ይህ ግን ዘርአ ያእቆብ በሌሎች ነገሮች ከሚሰጠን ዝርዝር የተለየ ነው፡፡ የወደቀበትን ገደል ሥፍር ሳይቀር 25 ክንድ ከስንዝር መሆኑን ይነግረናል፡፡ እንዲያውም በእኛ ድርሳናት ያልተለመደ የተወለደበትን ቀንና ዘመንም ይገልጥልናል፡፡ ልጁ የተወለደበትን ቀንና ዘመንም ይገልጥልናል፡፡ አኩስም ውስጥ የተወለደበትን ቦታ ግን አይነግረንም፡፡ ኡርቢኖ አኩስም አካባቢ ስለነበረ ነው ይህን የትውልድ ቦታ የመረጠው ብሎ መገመት ይቻላል፡፡
2. የዘርአ ያእቆብ የዓለም ስሙ ‹ወርቄ› ነው፡፡ ‹ወርቄ፣ ብርቄ፣ ድንቄ› የሚሉ የስም አወጣጦች በአማራው አካባቢ እንጂ በአኩስም አካባቢ የተለመዱ ስሞች አይደሉም፡፡ ኡርቢኖ በደብረ ታቦር አካባቢ ሲኖር የሰማውን ስም መሆን አለበት የተጠቀመው፡፡
3.   ዘርአ ያእቆብ ትርጓሜ መጻሕፍት እንደተማረ ይነግረናል፡፡ በቤተ ክርስቲያን የመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርት ብሉይ፣ ሐዲስ፣ ሊቃውንትና መጻሕፍተ መነኮሳት ናቸው፡፡ ዝርዝር ማቅረብ የሚወደው ዘርአ ያእቆብ ጠቅልሎ ‹መጻሕፍትን ተማርኩ› የሚለውን ለመቀበል አስቸጋሪ ነው፡፡ ያውም ‹የሀገራችን መምህራን እንዴት እንደሚተረጉሟቸው፣ ፈረንጆችም እንዴት እንደሚተረጉሟቸው ተማርኩ› ነው የሚለው፡፡ በጥንቱ የትምህርት አሰጣጥ ይህንን ሁሉ ለመማር ዐሥር ዓመት በቂ አይደለም፡፡ የሐዲሳት ትርጓሜ ብቻ አምስት ዓመት ይፈጃልና፡፡ ስለ መምህርነቱ ሲነግረን ‹በዚያም መጻሕፍትን ለአራት ዓመት አስተምር ነበር› ይላል፡፡ የመጻሕፍት አስተማሪ የሚባል መምህር በቤተ ክርስቲያን የለም፡፡ የሐዲሳት መምህር፣ የብሉያት መምህር፣ የሊቃውንት መምህር፣ የመጻሕፍተ መነኮሳት መምህር እንጂ፡፡
4.   ዘርአ ያእቆብ ባልንጀሮቹ ለምን እንደጠሉት ሲገልጥ ‹እኔ በትምህርትና በባልንጀራ ፍቅር ከእነርሱ እበልጥ ነበርና› ይላል፡፡ ይህ ግን እውነቱን አይደለም፡፡ ዘርአ ያእቆብ በመጽሐፉ ውስጥ 43 ቦታ ላይ ቅዱሳት መጻሕፍትን ጠቅሷል፡፡ ከእነዚህም መካከል 32 ከዳዊት፣ 5 ከምሳሌ/ መክብብብ/ ጥበብ፣ 4 ከሐዲስ ኪዳን፣ 1 ከኦሪት፣ አንድ ደግሞ ከትንቢተ ኢሳይያስ የተጠቀሱ ናቸው፡፡ ከ43ቱ ጥቅሶች 32 ከመዝሙረ ዳዊት የተጠቀሱ ናቸው፡፡ ከሐዲስ ኪዳን ይልቅ ከመጻሕፍተ ጥበብ (መክብብ፣ምሳሌና ጥበብ) የጠቀሰው ይበዛል፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መጻሕፍተ ጥበብ ከመዝሙረ ዳዊት ጋር አብረው የሚጻፉና የሚደገሙ የጸሎት መጻሕፍት ናቸው፡፡ ይህም የዘርአ ያእቆብ ትምህርት ከመዝሙረ ዳዊት ያልዘለለ መሆኑን ያሳያል፡፡ እርሱንም ቢሆን በነጠላው እንጂ በትርጓሜው መንገድ አልጠቀሰውም፡፡ ኡርቢኖ ለአንቶንዮ ዲ. አባዲ ከላካቸው መጻሕፍት መካከል አምስቱ የሰሎሞን መጻሕፍት(ምሳሌ፣ ተግሣጽ፣ መክብብ፣ መኃልይ እና ጥበብ) ይገኙበታል፡፡