Thursday, January 25, 2018

የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ (ክፍል አራት)

የፍልስፍናው ይዘታዊ ማስረጃዎች
ኮንቲ ሮሲኒ እንደሚለው የሐተታ ዘርአ ያእቆብን ፍልስፍና ከዳ. ኡርቢኖ ደብዳቤዎች ጋር ለማስተያየት ሞክሮ ነበር፡፡ ዳ. ኡርቢኖ በግንቦት 1854 ለአንቶንዮ ዲ. አባዲ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሰውን የዚህ ዓለም ማዕከል አድርጎ የሚያይበትን አመለካከቱን አንጸባርቆ ነበር፡፡ ይህም አስተሳሰብ በሐተታ ዘርአ ያእቆብ ላይ በዚያው መልኩ ይገኛል፡፡ ኡርቢኖ ‹አንዳች ነገር ባውቅ ያ ከእግዚአብሔር ያገኘሁት ነው፡፡ ማንም አላስተማረኝም.. ስለ ፈጣሪና ሀልዎቱ እውነት የሆነ ሐሳብ እንዳለኝ አምናለሁ፡፡ ይህንንም ከማንም ባለመቀበሌ እኮራለሁ› ሲል በደብዳቤው ላይ ገልጦታል፡፡ በመስከረም 1854 በጻፈው ሌላ ደብዳቤ ደግሞ ብቸኝነቱ ከፈጣሪና ከዓለማት ጋር ለመገናኘትና በደስታ ለመኖር የሚቻልበትን መንገድ ለመመርመር እንደገፋፋው ይገልጣል፡፡ ‹እግዚአብሔር መኖሩን አምናለሁ፤ ሌላው ነገር ግን ሊያረካኝ ስላልቻለ እቃወመዋለሁ› ሲል ገልጦ ነበር፡፡ ይህን መሰሉ ሐሳብ በሐተታ ዘርአ ያእቆብም ውስጥ ይገኛል፡፡ በርግጥ ይህንን ደብዳቤ የጻፈው ሐተታ ዘርአ ያእቆብን ካገኘ ከሁለት ዓመታት በኋላ በመሆኑ ማን ከማን እንደወሰደው ግልጽ አይደለም የሚል ትችት ቀርቦበታል፡፡ ነገር ግን ቀደም ብሎ ከጻፋቸው ብቸኝነቱን ከሚጠቅሱት ደብዳቤዎቹ ጋር ስናነጻጽረው ይህ ሐሳብ የ ዳ. ኡርቢኖ ውስጣዊ ሐሳቡ መሆኑን እንረዳለን፡፡

ዘርአ ያእቆብ ተፈላስፎ የእግዚአብሔርን መኖር ያመነው ‹ፍጡር ያለ ፈጣሪ ሊኖር አይችልም› ከሚለው ሐሳብ ተነሥቶ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ደግሞ በካቶሊክ ትምህርት ቤቶች በስፋት ይሰጥ የነበረው የቶማስ አኩዊኖስ ፍልስፍና ነው፡፡ ‹ይህን ከቅዱስ ቶማስ አኩዊኖስ ዘመን ጀምሮ በካቶሊኮች ዘንድ የገነነ ‹ምክንያትና ውጤቱ(The law of Casuality)› ፍልስፍና ወርቄ የካቶሊኮቹ ተማሪ በነበረ ጊዜ አልሰማውም ማለት ይቸግረኛል[1](1)፡፡› ጌታቸው ኃይሌ ያነሡት ሌላ ሐሳብም አለ፡፡ ‹ከሁሉም የሚገርመው ‹የኮከቦችን ቁጥር፣ ርቀታቸውን፣ ስለ ርቀታቸው ታናናሽ የሚመስሉን ትልቅነታቸውን ማን ያውቃል?› ማለቱ ነው፡፡ ኮከቦች ትናንሽ የሚመስሉት በርቀታቸው ምክንያት መሆኑን በቴሌስኮፕ እንጂ በመፈላሰፍ የሚደረስበት አይደለም፡፡ ይኸንንም የካቶሊኮቹ ተማሪ በነበረበት ጊዜ ከእነርሱ አፍ አልሰማውም ማለት ያዳግተኛል[2](2)፡፡› ‹በቅዱስ አውግስጢኖስና በቶማስ አኩዊኖስ መካከል የተነሣ› የሚባለውን የአንሰለምን ‹Scholastic Thinking› በሐተታው ውስጥ እናገኘዋለን[3](3)፡፡
ዘርአ ያእቆብ ዐፄ ፋሲልን(ፋሲለደስን) አይወደውም፡፡ ስለ እርሱ የሚያቀርባቸው ክሶች አሉ፡፡ ለአሁኑ አንዱን ብቻ እንመልከት ‹ከሴቶቹ ጋር ዝሙት ከሠራ በኋላ ገደላቸው› ይላል[4](4)፡፡ ዘርአ ያእቆብ ያቀረበውን ይህን ክስ የሚመሰክር ማስረጃ የለም፡፡ ዳ. ኡርቢኖ ይህንን ሐሳብ የወሰደው ከአንድ ሺ አንድ ሌሊት (One Thousand and One Nights) ድርሰቶች ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በዚያን ጊዜ በአውሮፓውያን እንጂ በኢትዮጵያውያን ዘንድ አይታወቅም፡፡
ኮንቲ ሮሲኒ የዘርአ ያእቆብን ድርሰት ከ‹ቅርጣግና ሌሊቶች› ጋር ለማስተያየት ሞክሯል፡፡ ‹የቅርጣግና ሌሊቶች (The Carthage Nights)› በ19ኛው አጋማሽ ላይ የተዘጋጀ የካቶሊኮች የፕሮፓጋንዳ መጽሐፍ ነው፡፡ በአንዲት መነኩሲት፣ በካቶሊክ ካህን፣ በሙስሊም ሙፍቲና በቃዲ መካከል በቅርጣግና (የዛሬይቱ ቱኒዚያ) የተደረገ የእምነት ውይይትን የሚገልጥ መጽሐፍ ሲሆን የታተመው በ1847 እኤአ በፓሪስ ከተማ ነው፡፡ የመጽሐፉ ዓላማ ክርስትና በእስልምና ላይ ያለውን የበላይነት በክርክር ማሳየት ነው፡፡ 

በአባ ማስያስ የሚመራው የካቶሊክ ሚሽን ይህን መጽሐፍ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት ፈለገ፡፡ በግእዝ እንዲተረጉመውም ለዳ. ኡርቢኖ ኃላፊነቱ ተሰጠ፡፡ ኡርቢኖ ከ1852 ጀምሮ(በ1844 ዓ.ም.) (ይህ ዓመት ሐተታ ዘርአ ያእቆብን አገኘሁበት ያለው ዘመን ነው) የተለያዩ ትርጉሞችን በግእዝ ሲሠራ ነበር[5](5)፡፡ ዓላማው ሊቃውንቱን ሊያረካ የሚችል የግእዝ ትርጉም ማዘጋጀት ነው፡፡ በሰኔ 1852 እኤአ የትርጉሙን ሥራ አጠቃልሎ ኢፋግ ላይ ለአባ ማስያስ አስረከበ፡፡ አባ ማስያስ ይህንን መጽሐፍ ኢትዮጵያውያን እንደወደዱት፣ በብዛትም እንደተገለበጠ ይገልጣሉ[6](6)፡፡ ኡርቢኖ ይህንን መጽሐፍ በአማርኛ እንደተረጎመውም ተናግረዋል፡፡ አባ ማስያስ በ1861 ወደ ኦሮሞ ሕዝብ ባደረጉት ሚሲዮናዊ ጉዟቸው ከጠፉባቸው መጻሕፍት ጋር የግእዙ ቅጅም አብሮ ጠፋ፡፡ ነገር ግን በአስገራሚ ሁኔታ በ1926 ሲልቫይን ግሬባውት (Grébaut, Sylvain) አዲስ አበባ ላይ አግኝቶት ወደ ቫቲካን ወሰደው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ መዝገብ ቁጥር 165 ተመዝግቦ በቫቲካን ቤተ መጻሕፍት የሚገኝ ብቸኛ የግእዝ ቅጅ ሆኗል፡፡
የአማርኛውን ቅጅ አለቃ ታየ በ1905 ወደ ጀርመን ሲሄዱ ይዘውት ሄደው ነበር፡፡ በ1934 ሚቶች(E.. Mittwoch) ይህንን ቅጅ  ከሐተታ ጋር ወደ ጀርመንኛ ተረጎመው፡፡ ሌላው የአማርኛ ቅጅ ደግሞ በኢትዮጵያ የብራና ማይክሮ ፊልም ቤተ መጻሕፍት (EMML 1470) ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በመጽሐፉ ላይ እንደተገለጠው በደጃዝማች ሚካኤል ገርሙ በ20ኛው መክዘ የተሰበሰበ ነው፡፡
ሚቶች ያሳተመው የመጽሐፉ ቅጅ ‹ዝንቱ ቀሲስ ፊልጶስ ዘተከሐደ ምስለ ሙፍቲ ወቃዲ በልሳነ ዓረቢ፡፡ ወድኅረዝ ጸሐፈ ዘንተ መጽሐፈ በልሳነ ፍራንስ፡፡ ወአባ ዮስጦስ[7](7) ተርጎሞ በልሳነ ግእዝ በ፲ወ፰፻ወ፵፬ ዓመት እም ልደተ እግዚእነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት በዘመነ ዮሐንስ ወንጌላዊ - ይህ ቀሲስ ፊልጶስ በዐረብኛ ቋንቋ[8](8) ከሙፍቲና ከቃዲ ጋር ተከራከረ፡፡ ከዚህም በኋላ ይህንን መጽሐፍ በፈረንሳይኛ ጻፈ፡፡ አባ ዮስጦስ ወደ ግእዝ ቋንቋ በ1844 ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በኋላ በዘመነ ዮሐንስ ወንጌላዊ ተረጎመው› ይላል[9](9)፡፡
   ሚቶች በመጽሐፉ መግቢያ፣ ኮንቲ ሮሲኒም ስለሐተታ ዘርአ ያእቆብ በገለጠበት ጥናቱ እንዳሳዩት በሐተታ ዘርአ ያእቆብና በቅርጣግና ሌሊቶች መካከል ሊዘለሉ የማይችል ተመሳስሎዎች አሉ፡፡ እስኪ በዝርዝር እንያቸው፡፡ 
   1.    ሚቶች እንዳጠናው በቅርጣግና ሌሊቶችና በሐተታ ዘርአ ያእቆብ መካከል ተመሳሳይ የሆኑ የሰዋሰው አገባቦችና አገላለጦች አሉ፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ
·      ህሊናህን ብታቀና(ቅርጣግና፣22,11f) ---- አልዕል ኅሊናከ(ሐተታ ዘር; 3,22)
·      እዝነ ልቡና(ቅር;4,24) ------ ዓይነ ልቡና(ሐተታ ወልደ;30,23)
·      በሃይማኖት መሠረት(ቅር;95,4) ----- መሠረተ ኩሉ ሃይማኖት(ሐተታ ወልደ33,19)
·      ኅቡዕ ምሥጢር(ቅር95,26) ----- ምሥጢራት ኅቡዓት(ሐተታ ወልደ;37,10)
·      መሐሪ ወመስተሣሕል(ቅር;22,12) ------- መሐሪ ወመስተሣሕል (ሐተታ ወልደ;38,23)
·      ሥርዓተ ዝሙት(ቅር;69,1) -------- ሥርዓተ አውስቦ(ሐተታ ወልደ;55,14)
·      ክቡድ(ቅር;45,10;69,30;71,25) ------ ክቡድ (ሐተታ ዘር;11,3 እና ወልደ;55,34;63,15)
·      ምግባር(ቅር;24,29;55,6) ------ ምግባር (ሐተታ ዘር;8,24;12,29;15,27;22,31;27,23; እና ወልደ; 33, 19;39,29;45,33;46,19;47,14-24; 48,5;56,21;58,32;61,5)
·      ተግባር(ቅር; 20,11;32,7;40,8;46,10) ------ተግባር(ሐተታ ዘር;5,23;19,33;20,2)
·       ፍቅረ ቢጽ (ቅር;20,8;102,3;104,23;) -----ፍቅረ ቢጽ(ሐተታ ዘር;4,20-21;24,24;2517;26,11)
·      ድኩማን ፍጥረቶች(ቅር;22,29) ----- ኩላ ፍጥረት  ውስንት ይእቲ ወድክምት(ሐተታ ወልደ፤31፣26) - ብእሲት ድክምት ፍጥረት ይእቲ (ሐተታ ወልደ57፣10)
  2. ንቲ ሮሲኒ ደግሞ እነዚህን ሐሳቦች ይጨምራል
  ·  እስልምና ብዙ ሴቶችን ማግባትን ይፈቅዳል ሲል የቅርጣግና ሌሊቶች ያወግዛል፤ ‹መሐመድ ሐሰተኛ ነቢይ ነው› የሚለውን ለማጠናከርም ተጠቅሞበታል፤ በሐተታ ዘርአ ያእቆብ(ምዕራፍ 5)ይህንኑ ክስና ሐሳብ እንዳለ እናገኘዋለን፡፡ ሐተታ ነገሩን አስረዝሞ በኦሪት ይህ ሐሳብ በመገኘቱ ነቢያት ትክክል ላለመሆናቸው ማስረጃ ያደርገዋል፡፡
  ·   በቅርጣግና ሁለተኛ ቀን ክርክር፣ ዐንቀጽ 2 ላይ የሚገኘው ‹ሰው ሁሉ እኩል ስለሆነ ባርነት ስሕተት ነው› የሚለው ሐሳብ በሐተታ ዘርአ ያእቆብም እንዳለ ይገኛል(ሐተታ ምእራፍ 5)፡፡
  ·   በቅርጣግና ሌሊቶች ላይ የሙስሊሞች ጾም የተወገዘበት መንገድ ሰፍቶ በሐተታ ዘርአ ያእቆብ በተመሳሳይ መንገድ የክርስቲያን፣ የአይሁድና የሙስሊም ጾም ተወግዞበታል፡፡

 ለመሆኑ በሁለቱ ሐተታዎች ውስጥ የሚገኙት መረጃዎችስ ስለ ደራሲው ምን ይነግሩናል? (ክፍል አምስት ይቀጥላል)፡፡


[1] ጌታቸው ኃይሌ፣ ሐተታ ዘርአ ያእቆብ፣ 2006፣ 10
[2] ዝኒ ከማሁ፣ 11
[3] Getatchew Haile, Ethiopian Studies In Honor of Amha Asfaw,2017, 69
[4] ሐተታ ዘርአ ያእቆብ ክፍል 13፤ ጌታቸው ኃይሌ፣ ሐተታ ዘርአ ያእቆብ፣ 2006፣ 40
[5] NAF 23852, fol. 19-20.   
[6] G. M assaja 1984, vol. 1, p. 278. (Massaja,G.,1984 (repr.), Memory storiche del Vicariato Apostolico dei Galla: 1845-1880: manoscritto autografo Vaticano,Vatican City, Archivio vaticano [Collectanea archivi Vaticani 10-11], vol. 1 and Vol. 2.)
[7] አባ ዮስጦስ የዳ. ኡርቢኖ ሌላው ስሙ ነው፡፡ Giusto የሚለውን ነው ዮስጦስ በሚል የተጠቀመበት ሙሉ ስሙ Padre Giusto da Urbinoነው፡፡
[8]  ኡርቢኖክርክሩ በዐረብኛ ተደርጎ በፈረንሳይኛ ተጻፈ ይበል እንጂ የመጽሐፉ ውርጅናሌ ቅጅ ይህንን አይልም፡፡ በመካከለኛው ዘመንና ከዚያ በኋላ ወደ ግእዝ የተተረጎሙ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ከዐረብኛ ስለተተረጎሙ ያንን ለመከተል ብሎ ያደረገው መሆን አለበት፡፡
[9] Die amharische Version der Soirees de Carthage. (The Amharic Version of the Soirees de Carthage). 1932, 109-110

No comments:

Post a Comment