Monday, January 22, 2018

የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ (ክፍል ሦስት)


አባ አየለ ተክለ ሃይማኖትና ዳ. ኡርቢኖ
አባ አየለ ተክለ ሃይማኖት በዳ. ኡርቢኖ ዘመን የነበረ ካቶሊካዊ ሚሲዮናዊ ነው፡፡ በአቡነ ያዕቆብ ይመራ የነበረው የትግራይ ካቶሊክ ሚሲዮናዊ ልዑክ አባል ነበር፡፡ ከትግራይ ወደ ጎንደር መጣ፡፡ ምንም እንኳን ዳ. ኡርቢኖ የተመላለሰበትን መሥመር በሚገባ ቢያውቀውም የእርሱ ዋናው ትኩረት ግን የሚሲዮን አገልግሎት ላይ ነበር፡፡ ዳ. ኡርቢኖ ግን ሚሲዮናዊ ተልዕኮውን ትቶ በቤተ ልሔም አጠገብ ይኖር ነበር፡፡ ይሠራ የነበረው ሥራ ግን ለሌሎቹ የሥራ ባልደረቦቹ ግልጽ አልነበረም፡፡ 

ኮንቲ ሮሲኒ እኤአ በ1916 የአባ ተክለ ሃይማኖትን ማስታወሻ አሳትሞ ነበር[1]፡፡ በዚህ ማስታወሻቸው ላይ ዳ. ኡርቢኖ ከቤተልሔም ደባትር ከደብተራ አማርከኝ(ምናልባት ደብተራ አሰጋኸኝ ይሆናል) እና ከሊቀ ካህናት ጎሹ ጋር የቀረበ ግንኙነት እንደነበረው ይገልጣሉ፡፡ ከእነርሱም የፍሪ ማሶናውያንንና የመናፍቃንን መጽሐፍ መግዛቱን ይናገራሉ፡፡ በዚህ ማስታወሻ ላይ ዳ. ኡርቢኖ ብዙ መጻሕፍትን እንደሚያስጽፍ፤ የእነዚህ መጻሕፍት ደራሲ ራሱ ቢሆንም ነገር ግን የብእር ስም እንደሚጠቀም፣ ይህም መጽሐፍ ወርቄ እንደሚባል፣ ስምሙ የተሰጠው ደራሲው ነው ተብሎ በታሰበው ሰው ስም መሆኑን ያትታሉ፡፡ አባ ተክለ ሃይማኖት ‹ሐተታ ዘርአ ያዕቆብን› አላነበቡትም የሚነግሩን ግን ስለ እርሱ መሆኑ ርግጥ ነው፡፡ የዘርአ ያዕቆብ ሌላው ስሙ ‹ወርቄ› ነውና፡፡ አባ ተክለ ሃይማኖት ዳ. ኡርቢኖ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በፍልስፍናና በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተሻለ ዕውቀት እንዳለውም ይናገራሉ፡፡ አባ ተክለ ሃይማኖት ዳ. ኡርቢኖን በመልካም አያዩትም፤ የሚያጠራጥር ሕይወትና እምነት እንደነበረው ይገልጣሉ፡፡ 


ዳ. ኡርቢኖ ከአንቶኒዮ ዲ. ኣባዲ ጋር ባደረጋቸው የመልእክት ልውውጦች ስለ ዕውቀቱ አንዳንድ ነገር ገልጧል፡፡ ከግእዝ መምህሩና ከሌሎች ሊቃውንት ጋር በየቀኑ ውይይት ያደርግ እንደነበር ገልጦለታል[2]፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የግእዝ ሰዋስው መጽሐፍ አዘጋጅቶ ነበር፣ የግእዝ፣ አማርኛ፣ ላቲን መዝገበ ቃላት ሠርቶ ነበር፤ በመስከረም 1850 በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‹ግእዝን በደንብ እየተማርኩ ነው፤ (ግእዝ) እንድማር የሰጠህኝን የአንተን ምክር በመከተሌ ደስ ብሎኛል፤ ብዙ አደከመኝ፤ ነገር ግን ይህ ጥቅስ ድካሜን አረጋግጦልኛል - ትዕግሥትሰ በጊዜሁ ይከውን መሪረ ወድኅሬሁ ይጥዕም እመዓር[3]› ብሎት ነበር[4]፡፡
ዳ. ኡርቢኖ በመልእክቶቹ አብረውት ስለሚሠሩት ሌሎች ሚሲዮናውያን እምብዛም አያነሣም፡፡ የተለየ ነገር ካልገጠመው በቀር፡፡ ከአንቶኒዮ ዲ. አባዲ ወንድም ከአርኖርድ ጋር በአንድ ወቅት ተጋጭቶ ነበር፡፡ ምናልባትም ሌሎች ሚሲዮናውያን ከእርሱ ጋር መልካም ግንኙነት አልነበራቸውም፡፡ ይህም ስሙን እንዲደብቅና ብዕር ስም እንዲጠቀም ሊያስገድደው እንደቻለ ከአባ ተክለ ሃይማኖት ማስተዋሻ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ዳ. ኡርቢኖ እነዚያን የቤተ ልሔም ደባትር በደብዳቤው ላይ ለምን ማንሣት አልፈለገም? ብለን ከጠየቅን ደግሞ ዳ. ኡርቢኖ ሊደብቀው ወይም ሊዋሸን የሚፈልገው ነገር እንዳለ እንድናሸት ያደርገናል? ምን ይሆን የሚለው ለማየት የ ኮንቲ ሮሲኒን ትችት እንይ፡፡
የኮንቲ ሮሲኒ ትችቶች
ኮንቲ ሮሲኒ በ1920 ‹ሐተታ ዘርአ ያእቆብን› የተመለከተ አንድ ጥናት አቅርቦ ነበር[5]፡፡ በዚህ ጽሑፉ ላይ ያቀረባቸው ዋና ዋና ትችቶች እንመልከታቸው፡፡
ኡርቢኖና ዘርአ ያእቆብ
1.  በመጋቢት 1852 ዳ. ኡርቢኖ ለዲ አባዲ የላከውና በግእዝ የጻፈው የገንዘብ መጠየቂያ ደብዳቤውና በሐተታ ዘርአ ያዕቆብ ላይ ዘርአ ያዕቆብ ሀብቱን ድግፋ የጠየቀበት መንገድ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁለቱም የዕለት ጉርስና የዓመት ልብስ የሚሰጧቸውን ሰዎች ይፈልጋሉ፤ ከጌቶቻቸው የሚፈልጉትም የበላይ ጠባቂነትን ነው፡፡  
በዚሁ በመጋቢት 1852 በጻፈው ደብዳቤ ላይ ዳ. ኡርቢኖ ረዥም የግእዝ መልእክት አካትቶበታል፡፡ ይህም በዳ. ኡርቢኖ ደብዳቤዎች መካከል የመጀመሪያው ነው፡፡ ይህንን ሐሳብ ከሐተታ ዘርአ ያእቆብ ምእራፍ 11 ጋር ማነጻጸር ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-
‹ወአንሰ ተሰፈውኩ ከመ ታብአኒ ቤተከ አመ ርስዕየ ወትረስየኒ አንባቤ ወዐቃቤ መጻሕፍትከ ዘኢትዮጵያ ወጸሓፌ ወተርጓሜ ዚአሆሙ ወአንተሰ መተርከ ተስፋየ ዮም በአርምማትከ እመሰ ትፈዲ ሊተ እኩየ በእንተ ዘተብህለ ቅድመ አመ ነገሩ ለአቡነ ሰላማ ኢይሤኒ ለከ እስመ ምክንያተ ምጽአትየ ኀበዝ ብሔር አንተ ውእቱ ወእምዝ አሰፈውከኒ በብዙኅ ነገር ይጌጊኑ ነዳይ አመ ይስእሎ ለብዑል ምጽዋተ ወአንሰ ኢየኀሥሥ እንበለ ዕሤተ ፃማየ ወንስቲተ ብሩረ የአክለኒ ዮም ወእፈድዮ በአእምሮትየ ውስተ ኵሉ ነገረ ግዕዝ ዘይትኀሠሥ እምኔየ እመሰ አንተ ኢትኀሥሥ እምኔየ እግዚአብሔር ተስፋሆሙ ለነዳያን ይከውን ተስፋየ ወእሠይጥ ፍሬ ፃማየ ለዘይሴስየኒ. እግዚአብሔር ይበርከከ ወያስተፈሥሐከ ወይፈጽም ለከ ኵሎ ፈቃደከ. አሜን›
2.   በደብዳቤውና በመጽሐፉ ውስጥ ተመሳሳይ የግእዝ ቃላት ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ‹ፍሬ ጻማየ› የሚለው አገላለጥ በሐተታ ዘርአ ያዕቆብ ሁለት ጊዜ፣ በሐተታ ወልደ ሕይወት አንድ ጊዜ ይገኛል፡፡ በዳ. ኡርቢኖ ደብዳቤም ይሄው አገላለጥ ይገኛል፡፡ ኡርቢኖ ከሐተታ ዘርአ ያዕቆብና ከሐተታ ወልደ ሕይወት ወስዶት ነው እንዳይባል ደብዳቤው የተጻፈው ኡርቢኖ መጽሐፉን ማግኘቱን ከመግለጡ 6 ወር በፊት ነው[6]፡፡
3. በ1852 በመጋቢት ወር ርዳታን አስመልክቶ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‹ሀብታም በከብት ደኃ በጕልበት› የሚል ገለጣ ተጠቅሟል፡፡ ይህ አባባል ለአንቶኒዮ ዲ. አባዲ. በ1853 በተላከው የ‹ሐተታ ዘርአ ያእቆብ› ቅጅ 234 የላቲኑ ደብዳቤ ላይ ይገኛል፡፡
234,32a
 4.  ዳ. ኡርቢኖ ‹አንባቤ ወዐቃቤ መጻሕፍትከ ዘኢትዮጵያ ወጸሓፌ ወተርጓሜ ዚአሆሙ - አንባቢ፣ በኢትዮጵያ የመጻሕፍትህ ጠባቂ፣ የእነርሱም ጸሐፌና ተርጓሚ› ሲል የገለጠበት መንገድ ራሱን ከሚሲዮናዊነቱ ይልቅ በእነዚህ መስኮች አሠማርቻለሁ ብሎ እንደሚያስብና አለቃውና አስተዳዳሪው ዲ. አባዲም በዚህ መንገድ እንዲያስበው እንደሚፈልግ ያሳያል፡፡ ይህም ‹ሐተታ ዘርአ ያእቆብን› ከመላኩ ቀደም ብሎ ነው፡፡ ዘርአ ያእቆብም ተመሳሳይ ሞያ ነበረው፡፡
5.  ዘርአ ያዕቆብና ዳ. ኡርቢኖ የተወለዱት በተመሳሳይ ቀን ነው፡፡ ዘርአ ያዕቆብ የተወለደው በነሐሴ 25 ቀን 1592 ነው፡፡ ኡርቢኖ ደግሞ በኦገስት 30 ቀን 1814፡፡ ለምሳሌ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1851፣ በ1852 እና በ1853 ኦገስት 30 ቀን በነሐሴ 23 ነበር የዋለው፡፡ ይህ እንዴት አጋጣሚ ሊሆን ይችላል?
6. የዳ. ኡርቢኖ እና የወርቄ የክርስትና ስም ተመሳሳይ ነው፡፡ ወርቄ የክርስትና ስሙ ‹ዘርአ ያእቆብ› ሲሆን የዳ. ኡርቢኖ ደግሞ ‹Jacques - ያዕቆብ ነው›፡፡ ይህ ነገር አንድን ጉዳይ መልሰን ልብ እንድንለው ይጋብዘናል፡፡ በክፍል አንድ ጽሑፋችን እንደተገለጠው ዳ. ኡርቢኖ በመስከረም 1552 ስለ ‹ሐተታ ዘርአ ያእቆብ› ለዲ. አባዲ ባበሠረበት ደብዳቤው ላይ መጽሐፉን ሲጠራው ‹ሐተታ ያዕቆብ ወይም መጽሐፈ ያዕቆብ ልንለው እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ባለ ታሪኩ ራሱን ያዕቆብ በማለት ነውና የሚጠራው› በማለት ነበር፡፡ ከዚህ ፍንጭ ስንነሣ የመጽሐፉ ቀዳማዊ ስም ‹ሐተታ ያእቂብ ወይም መጽሐፈ ያእቆብ› ነበር ማለት ነው፡፡ በኋላ ግን መጽሐፉን ሲልክ/ሲያጽፍ ‹ሐተታ ዘርአ ያዕቆብ› ብሎታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የክርስትና ስም የሚሰጠው እንደ አውሮፓውያኑ በተናጠል ሳይሆን በዘርፍ - አምኃ ሥላሴ፣ ወለተ ማርያም፣ ፍቅርተ ክርስቶስ እየተባለ ነው፡፡ ዳ. ኡርቢኖ በኋላ ይህንን ስሕተቱን አርሞ ጸሐፊውን የኢትዮጵያ የክርስትና ስም ቅርጽ ያለው ስም (ዘርአ ያእቆብ) ሰጥቶታል፡፡
7. ዘርአ ያእቆብ ወደ እንፍራንዝ መጥቶ በሀብቱ ቤት መኖር ሲጀምር መልከ ጥፉ፣ ጠባየ መልካምና ልቡና ብሩኅ የሆነች የሀብቱን አገልጋይ ኂሩትን አገባ[7]፡፡ እርሷንም አከበራት፡፡ ከእርሷም ልጆች ወለደ፡፡ ስለ ኂሩት የተሰጠው ገለጻ ዳ. ኡርቢኖ ስለ ቤት አገልጋዩ ሴት ከሚሰጠው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ኡርቢኖ በአንደኛው ደብዳቤው ላይ ከእርሱ ጋር የምትኖርና ቤቱን የምትጠብቅለት ሴት በፈንጣጣ በሽታ መሞቷን ገልጦ ነበር፡፡ ይህቺ ሴት ‹እድሜዋ 30፣ እንደ ጋኔን መልከ ጥፉ፣ ነገር ግን እንደ መልአክ ጠባየ ሸጋ የሆነች፣ ከአቢሲኒያውያንም ሦስት እጥፍ ጠቢብ የምትሆን› ናት ይላል፡፡ በእርሷ ኀዘን የተነሣ መታመሙንና ከኀዘኑ ለመውጣትም እየጣረ መሆኑን ይናገራል[8]፡፡ ይህንን የኀዘኑን ልክ ስናየው በዚያ ዘመን የነበረ ሰው ለቤት አገልጋዩ የሚያዝነው ዓይነት አይደለም፡፡ ሱማሌዎች ‹ይህ ልቅሶ ለፍየል አይመስልም› እንዳሉት ዓይነት፡፡ ምን አልባት ‹ዕቁባቱ› ትሆን ይሆንን? እስኪ ሌላ ፍንጭ እንፈልግ፡፡
የ-ሚሲዮናዊ ቡድኑ መሪ አባ ማስያስ አንድ ነገር ይነግሩናል፡፡ ከ1852 ቀደም ብሎ ኡርቢኖ ኢትዮጵያ ውስጥ ቤተሰብ እንደነበረው ይነግሩናል፡፡ በሰኔ 1852 ኡርቢኖ እና ማስያስ የባሪያ ገበያ በነበረችው በኢፋግ ተገናኝተው በነበረ ጊዜ ኡርቢኖ የዝናቡ ወቅት ሳይገባ በቶሎ ወደ ቤተ ልሔም መመለስ እንዳለበት እንደነገራቸውና የዚህም ምክንያቱ ቤተሰቡን በዚያ ስለተወ እንደሆነ ገልጠዋል[9]፡፡ ኡርቢኖ ከቤተ ልሔም አካባቢ ርቆ መሄድ፣ ሚስዮናዊነቱን መፈጸም ያልፈለገው፤ ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላስ ግብጽ ደርሶ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የፈለገው ‹ኧረ ልጅ ማሠሪያው ኧረ ልጅ ገመዱ› ሆኖበት ይሆንን? በእርሱ ዘመን በተመሳሳይ ሚሲዮናዊነት ላይ የነበሩት አባ ተክለ ሃይማኖትም ቀደም ብለን በጠቀስነው ማስታወሻቸው ላይ አባ ሰላማ የካቶሊክ ሚስዮናውያን እንዲወጡ ሲያውጁ ‹እንደ ሚሲዮናዊ እንዳያዩት› መጠየቁን ይናገራሉ[10]፡፡
8. ዘርአ ያእቆብ ከአኩስም የመጣበትና ዳ. ኡርቢኖ ከአኩስም የመጣበት መንገድ ተመሳሳይ ነው፡፡ ኡርቢኖ በ1847 ወደ ትግራይ ጓላ መጣ፡፡ ጓላ አኩስም አጠገብ ነው፡፡ ከአክሱም በ1849 ወደ ተድባበ ማርያም (አምሐራ) መጣ፡፡ ከአምሐራ ጎጃም ገብቶ፣ በመጨረሻም በ1850 ጎንደር ሠፈረ፡፡ ዘርአ ያዕቆብም ከአኩስም ወደ አምሐራ መጣ፣ በዚያም ሁለት ዓመት ተቀመጠ፡፡ በኋላም ወደ ጎንደር መጣ፡፡ በጎጃምም ሊቀመጥ ፈልጎ ነበር፡፡ የእነዚህ ሁለት ታሪኮች መገጣጠም እንዴት አጋጣሚ ሊሆን ይችላል?

ፍልስፍናዊ ማስረጃዎች
ይቀጥላል…
[1] Conti Rossini, C., 1916, Fonti storiche etiopiche per il secolo xix. I, Vicende dell’Etiopia e delle missioni cattoliche ai tempi di Ras Ali, Deggiac Ubié e Re Teodoro secondo un documento abissino, Rome, Tip. della R. Accademia dei Lincei.
[2] Bibliothèque nationale Victor-Emmanuel, Ms Orient. 134, fol. 98v.
[3] ትዕግሥት በጊዜው መራር ነው፣ በኋላ ግን ከማር ይልቅ ይጣፍጣል - ማለት ነው፡፡
[4] Ms NAF 23852, fol. 13-14
[5] Conti Rossini, C., 1920 "Lo Hatata Zar'a e Yā'qob it padre Giusto da Urbino " Rendiconti della Reale Accademia dei Lincei , 29, ser. 5, p. 213-223.        
[6] E. Littmann , 1904, txt, p. 21- 22: ወአበድር ፍሬ ፃማየ እሴሰይ , p. 48.  
[7] ጌታቸው ኃይሌ፣ ሐተታ ዘዘርአ ያእቆብ፣ 2006፣ 38
[8] ms NAF 23852, fol. 51-54.      
[9] L’histoire d’un vrai faux traité philosophique (Ḥatatā Zar’a Yā‘eqob et Ḥatatā Walda Ḥeywat). Épisode 2 Dove aveva lasciata tutta la sua famiglia, G. Massaja, 1984, vol. 2, p. 279.
[10] C. Conti R Ossini , 1916, p. 77

3 comments:

 1. ቻው ዘርዓያዕቆብ…
  ==============

  ቻው ዘርዓያዕቆብ…
  አልተገኘህምና…
  እንደ ጉም ባዶ ነህና ….
  የፈረንጅ ክፋት ነህና …
  የዳ ኡርቢኖ ቅርሻት ነህና …
  የዳ ኡርቢና ደሞዝ ነህና…

  ቻው ዘርዓ ያዕቆብ አንድም ሁለትም አራትም ነህና፣
  ገመናም የሌለብህ ገመና ራስህ ነህና፣
  ቻው ያዕቆብ፣ ቻው ዘርዓ ያዕቆብ፣ ቻው ወርቄ፣ ቻው ዳ ኡርቢኖ፣
  ሰንብቷልና ያንተ ነገር ሳይበስል እንዲያው ተከድኖ፣
  አንድም ሁለትም አራትም ነህና፣
  ገመናም የሌለብህ ገመና ራስህ ነህና፣

  ቻው ዘርዓ ያዕቆብ..
  ባገኝህም ላወግዝህ እንጅ ጥመኸኝ አታውቅምና፣
  ስላልተገኘህ ደስ ብሎኛል፣ ባቄላ ቀረ ፈስ ቀረ ነውና፣
  እልሃለሁ በኢትዮጵያዊ ቃና፣

  ቻው ዘርዓ ያዕቆብ የፈረንሳይና የጣልያን ሚስዮኑ፣
  የክህደት መልእክተኛው የሰይጣን መኮንኑ፣
  በስጋም በነፍስም ሚዛን ሚሽንህ ከሽፏልና በኢትዮጵያውያኑ፣
  ባገኝህም ላወግዝህ እንጅ ጥመኸኝ አታውቅምና፣
  ስላልተገኘህ ደስ ብሎኛል፣ ባቄላ ቀረ ፈስ ቀረ ነውና፣

  ጥር 16፣ 2010 ዓ.ም.
  መገናኛ፣ ከማቲያስ ህንጻ ብዙም ሳይርቅ፡፡

  ReplyDelete
 2. ቻው ዘርዓያዕቆብ…
  ==========

  ቻው ዘርዓያዕቆብ…
  አልተገኘህምና…
  እንደ ጉም ባዶ ነህና ….
  የፈረንጅ ክፋት ነህና …
  የዳ ኡርቢኖ ቅርሻት ነህና …
  የዳ ኡርቢና ደሞዝ ነህና…

  ቻው ዘርዓ ያዕቆብ አንድም ሁለትም አራትም ነህና፣
  ገመናም የሌለብህ ገመና ራስህ ነህና፣
  ቻው ያዕቆብ፣ ቻው ዘርዓ ያዕቆብ፣ ቻው ወርቄ፣ ቻው ዳ ኡርቢኖ፣
  ሰንብቷልና ያንተ ነገር ሳይበስል እንዲያው ተከድኖ፣
  አንድም ሁለትም አራትም ነህና፣
  ገመናም የሌለብህ ገመና ራስህ ነህና፣

  ቻው ዘርዓ ያዕቆብ..
  ባገኝህም ላወግዝህ እንጅ ጥመኸኝ አታውቅምና፣
  ስላልተገኘህ ደስ ብሎኛል፣ ባቄላ ቀረ ፈስ ቀረ ነውና፣
  እልሃለሁ በኢትዮጵያዊ ቃና፣

  ቻው ዘርዓ ያዕቆብ የፈረንሳይና የጣልያን ሚስዮኑ፣
  የክህደት መልእክተኛው የሰይጣን መኮንኑ፣
  በስጋም በነፍስም ሚዛን ሚሽንህ ከሽፏልና በኢትዮጵያውያኑ፣
  ባገኝህም ላወግዝህ እንጅ ጥመኸኝ አታውቅምና፣
  ስላልተገኘህ ደስ ብሎኛል፣ ባቄላ ቀረ ፈስ ቀረ ነውና፣

  ጥር 16፣ 2010 ዓ.ም.
  መገናኛ፣ ከማቲያስ ህንጻ ብዙም ሳይርቅ፡፡

  ReplyDelete