Thursday, January 18, 2018

ቀውስጦስ - የበረሓ ምንጭ


ሲያምኑ እንደ አብርሃም ነው፣ ሲሠሩ እንደ ላሊበላ፡፡ ሲያስተምሩ እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፣ ሲተጉ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ፤ ከቆረጡ እንደ አቡነ ጴጥሮስ ናቸው፣ ከሞገቱ እንደ ሳዊሮስ፡፡ ከመረቁ የሚጠቅሙትን ያህል ከረገሙም ይጎዳሉ፤ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ከሆነባቸው ክብር፣ ፕሮቶኮል፣ ስምና ዝና አይገድባቸውም፡፡ ከቀበሌ እስከ ቤተ መንግሥት ይሞግታሉ፤ በፍትሕ አደባባይ መፍትሔ ካጡ ‹ይግባኝ ለክርስቶስ‹ ብለው ለሰማያዊው ፍርድ ቤት ያቀርባሉ፡፡
አረጋዊ ናቸው፣ ግን እንደ ወጣት ይሠራሉ፤ ሊቀ ጳጳስ ናቸው ነገር ግን እንደ ሰንበት ተማሪ ይሮጣሉ፣ የአንድ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፣ ግን በሁሉም ይወደዳሉ፤ ትምህርታቸው ከሰው ልብ ዕንባቸው መንበረ ጸባዖት ይደርሳል፡፡ በርሳቸው ዘንድ ትንሽ የለም፣ ትልቅም የለም፡፡
የርሳቸውን ስም የያዘው ቅዱስ የዛሬ 700 ዓመት እንዲሁ እንደርሳቸው ነበር፡፡ ቅዱሱ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሲሆን ያስተምራል፣ ገዳማትን ይተክላል፣ ደቀ መዛሙርትን ያፈራል፣ ነገሥታትን ይገሥጻል፣ ለእምነቱ ጥብቅና ይቆማል፣ ግፍንና በደልን ይጸየፋል፡፡ ቅዱስ ቀውስጦስ ዘመሐግል፡፡ በሰማዕትነትም ያረፈው ንጉሥ ዓምደ ጽዮን ከክርስትናው ወጥቶ ሁለት ሚስት አግብቶ፣ የተቃወሙትን ቅዱሳን በግፍ ባሳደደ ጊዜ ነው፡፡ በንጉሡ ፊት እውነቱን ተናግሮ፣ ስሕተቱን ገልጦ በተናገረ ጊዜ ከቤተ መንግሥቱ አውጥተው በጨለማ ቤት አሠሩት፣ በኋላም ከጨለማው እሥር ቤት አውጥተው ዛሬ በሰሜን ሸዋ እንሣሮ በሚባለው ቦታ ወስደው በግፍ ገደሉት፡፡ እርሳቸውም ስሙን ብቻ ሳይሆን ግብሩንም ወርሰውታል፡፡ 

ከዐሥራ አምስት ዓመታት በፊት፡፡ ትጉኁ ብጹዕ አቡነ ናትናኤል፣ መዶሻው ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ሐዋርያዊው ብጹዕ አቡነ ኤልያስ አንድ ሆነው ወደ ሐረር ዘምተው ነበር፡፡ መልአከ ሰላም ኃይለ ኢየሱስም አጅበዋል፡፡ የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤልና የታእካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ሰንበት ትምህርት ቤቶች መዘምራንም ሐረር ከትመዋል፡፡ ቀሲስ ደጀኔ ሊቀ መዘምራን ኪነ ጥበብ ተከትለዋል፡፡ እኔም እድል ገጥሞኝ በቦታው ነበርኩ፡፡ ተሐድሶ ሐረርጌን ከምዕራብ በአስበ ተፈሪ፣ ከምሥራቅ በሐረር በኩል ሠንጎ ይዟታል፡፡ አቡነ ቀውስጦስ የሐረር ሊቀ ጳጳስ ነበሩ፡፡ እርሳቸው እቴ በሃይማኖት ድርድር አያውቁም፣ ግዴለሽነት አያጠቃቸውም፣ ኖላዊነታቸውን ለአፍታም አይዘነጉት፡፡
በረከታቸው ይደርብንና አቡነ ናትናኤል ‹የሐረርጌ መሬት› በሚል ርእስ ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ ሰምቼው የማላውቅ ድንቅ ትምህርት አስተማሩ፤ ‹የሐረርጌን መሬት ጠይቁት፤ ይመስክር፤ እስኪ ቆፍሩና ጠይቁት፣ ካህኑ ታቦቱን እንደያዘ ዐጽሙን ታገኙታላችሁ፤ መሬቱኮ ክርስቲያን ነው፡፡ አባቶቻችን የተጋደሉበት ነው› አሉ ትጉኁ አቡነ ናትናኤል፡፡ መዶሻው ቄርሎስም ‹ምንጊዜም አዲስ የሆነው እምነታችን ምኑ ይታደሳል? ማንስ ችሎ ያድሰዋል?› የተሰኘውን ትምህርት አወረዱት፡፡ መዝሙርን ከትምህርት የሚያስተጋብሩት አቡነ ኤልያስም በረከታቸው ይደርብንና፡-
መጀመሪያ
ኢኮነ ነግደ ወፈላሴ
ሀገሪቶሙ ለቅዱሳን አትዮጵያ
ሀገሪቶሙ ለቅዱሳን ምድረ ሐረርጌ
የተሰኘውን መዝሙር፣ ቀጥለውም
አደሬ ጢቆ ሥላሴ
እኔ እወድሻለሁ እስኪወጣ ነፍሴ
የተሰኘውን መዝሙር አሸበሸቡት፡፡ ቅዱስ ያሬድን በአካል ያላየን ሰዎች አቡነ ኤልያስን አይተናልና አይቆጨንም፤ ሕዝቡ ያለበትን ቦታ እስኪረሳ ድረስ፣ ከምድር ክንድ ስንዝር ከፍ ያለ እስኪመስል ድረስ አብሯቸው ዘመረ፡፡ ይሄኔ አቡነ ቀውስጦስ መልአኩ ከመንበሩ ተነሡ፡፡ ከቤተ ክርስቲያን በላይ ምን ክብር አለ፣ ከሃይማኖትም በላይ ምን ታላቅነት አለ፣ ከክርስቶስም በላይ ምን ፕሮቶኮል አለ፡፡ መስቀላቸውን ይዘው በዚያ እንደ መላእክት በተመስጦ በተነጠቀው የሐረር ሕዝብ መካከል እያሸበሸቡ ገቡ፡፡ ሕዝቡ ምድሪቱን ለቀቀ፡፡ ሄደ ወደ አርያም፤ የታእካ ነገሥትና የቅዱስ ዑራኤል ሰንበት ተማሪዎች እንደ ቅዱስ ያሬድ እግራቸውን ቢወጉት እንኳን አይሰሙም ነበር፡፡ አቡነ ቄርሎስና አቡነ ኤልያስ ያለቅሳሉ፡፡ አቡነ ናትናኤል ምድር ላይ የሉም፡፡ መልአከ ሰላም ኃይለ ኢየሱስ መድረክ ላይ መሆናቸው ረስተውታል፤ እያሸበሸቡ ከሕዝቡ ጋር ሄደዋል፡፡ መላእክት በዲበ ምድር፡፡ እንደ አባ ቀውስጦስ የዘመረ፣ እንደ እርሳቸውም ያሸበሸበ፣ እንደ እርሳቸውም ለሰማያዊ ክብር ሲል ምድራዊውን ክብር የዘነጋ፣ እንደ እርሳቸውም በሃይማኖት ይህንን ያህል የሚደሰት፣ እንደ እርሳቸውም ኑፋቄን የሚጸየፍ፣ እንደ እርሳቸውም ለወንጌል የሚተጋ ከዚያም ወዲህ አላየሁም፡፡
እኒህን አባት የሚያውቅ ሰው ታላቅ ሰው ነው፡፡ የሚንቅ ደግሞ ራሱን የናቀ፡፡ እንደ ጻድቁ ቀውስጦስ የሚያምኑ ብቻ አይደሉም፡፡ እንደ መልአኩ ቀውስጦስ የሚቀስፉም ናቸው፡፡ ዕንባቸው ከባድ ነው፣ ጸሎታቸው ሥሙር፣ ቃላቸው ሰይፍ ነው፣ መሐላቸው ክቡር፤ ከጀመሩ ሳይጨርሱ፣ ካነሱ ሳያደርሱ፣ ከጨበጡ ሳያጠብቁ፣ ከወረወሩ ሳያርቁ አይመለሱም፡፡
በለገ ጣፎ ከተማ የቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ተሠራ፡፡ ሰውን የማያፍሩ ፈጣሪን የማይፈሩ ባለ ሥልጣናት ተነሡና አፈራረሱት፡፤ ንዋያተ ቅድሳቱንም ወረወሩ፡፡ አላወቁትም እንጂ በጉዳዩ ላይ ሁለት ቆራጦች ተሰልፈውበት ነበር፡፡ በሰማይ ሄሮድስን ያልፈራው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ፣ በምድር ‹ይድረስ ለክርስቶስ› ብለው የሚሞግቱት ቆራጡ አቡነ ቀውስጦስ፡፡ በእነዚህ በሁለቱ እጅ የተያዘ ጉዳይ በስተመጨረሻው በለማ መሬት ላይ መውደቁ አይቀሬ ነበረና፡፡ በለማው ለማ እጅ ወደቀ፡፡ እነሆ እንደ እከ የማይተኙት፣ ላይጨርሱ የማይጀምሩት፣ ላያጸኑ የማይገነቡት አቡነ ቀውስጦስ በትምህርትም፣ በሙግትም፣ በጸሎትም፣ በጥብዐትም፣ በዕንባም ታግለው ለፍሬ አደረሱት፡፡
አባታችን፣
‹ረድኤቴ ከወዴት ይመጣልኛል?› እያለ ምእመናኑ በተሥፋ ሰማዩን በሚያይበት በዚህ ዘመን፣ እንዲህ እንደርስዎ የልብ መጠጊያ የሚሆን አባት ማግኘት መታደልም፣ መመረጥም ነው፡፡ እንዲ ቤተ ክህነታችን በሙስና፣ በዘረኛነት፣ በአስተዳደር ልምሾ ናውዞ ምእመናኑ የመከራ ወሬ በሚሰሙበት ዘመን፣ እንደ እርስዎ ተአምር የሚነግር አባት ማግኘት በበረሓ እንደተገኘ ምንጭ ነው፡፡ እንኳን በዓይን አየንዎት፤ እንኳን በታሪክ አልሰማንዎት፡፡ ለልጆቻችን የምንተርከው ታሪክ ሰጥተውናል፡፡ የአባቶቻችን አምላክ ዛሬም ከእኛ ጋራ መሆኑን የሰማነውን አሳይተውናል፡፡
ኑሩልን አባታችን፡፡
   

22 comments:

 1. በእንባ ነው ያነበብኩት። በዚህ የስጋ ፍላጎት በቤተክርስቲያን በሰለጠነበት ዘመን አኒህንና መሰል አባቶችን ማየት ወልደ አብ ወልደ ማርያም ክርስቶስ ቅድስት ቤተክርስቲያንን እንዴት እንደሚጠብቃት ነው። ወዮ በክብር ተሹመው ቤተክርሲያንን በውርደታቸው ለሚያገለግሉ።

  ReplyDelete
 2. እግዚአብሐር ለአባታችን ረጅም እድሜ ይስጥልን። በዚህ ዘመን አብዝተን ስለአባቶች የምንሰማው መልካም ዜና አይደለም። ነገር ግን ቤቱ የማይተዋት አምላካች ዛሬም እንደ አቡነ ቀውስጦስ ያሉ አባቶችን አላሳጣንም። አሁንም ስለእንደዚህ አይነት አባቶች መጻፍ አለበት ምዕመናኑ እንዲፅናና። አንተም እግዚአብሔር የአገልግሎት ዕድሜህን ያርዝመው። እግዚአብሔር ይስጥልን።

  ReplyDelete
 3. Diakon Dani "zikire abune Kewustos"betam dess bilognal ene begile ye gamo gofa zone hagere sibket like papas beneberubet wekt tinsh lij hogne dershebachew neber enam betam melkam ena ytemaru endihum lemimenanu rasachewn asalifew yemisetu endeneberu awkalehu siletsafkilin enameseginhalen dani gn 1 kir yalegn mn endehone tawkaleh yihe tsuf mn malet new? "እነሆ እንደ እከ የማይተኙት"yihe tsuf bene eyita zemen teshagari lihon ayichilim mikinyatum eke zemen teshagari dirama ayidelem eke manew bilun lijochachin mn enilalen dani?

  ReplyDelete
 4. ዳኒ፣ በጽሑፍህ የተሰማኝ ከደስታ ይልቅ ሐዘን ነው! የምር!


  ውድ ሙሓዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት፣ በቅድሚያ እንኳን ለበዓለ ጥምቀቱ በሰላም አደረሰህ! ስለአባታችን አቡነ ቀውስጦስ የጻፍኸውን ደጋግሜ አነበብሁት፡፡ ስደጋግመው ግን የበለጠ አሳመመኝ፡፡ በቦታው እንዳለሁ ሆኜ አባቶቻችን በመንፈሳዊ ስሜት ውስጥ ሆነው ያደረጉትን ተግባር ስረዳ ደግሞ ልቡናዬ ሸፈተ፡፡ እግዜር ይይልህ! ማየቱንስ አይቶልህ ነው እንዲህ እየመረጠ የሰውን ልቡና የሚነካ ጽሑፍ የሚያስጽፍህ፤ ማየቱንማ አይቶልህ ነው በየጉባኤው የሰውን ስሜት የሚኮረኩር ነገር የሚያናግርህ፡፡ አሁንም ፈጣሪ አብዝቶ ይይልህ፣ አቦ!


  አቡነ ቀውስጦስን በመጠኑም ቢሆን አውቃቸዋለሁ፤ ከሁሉም በላይ እንባቸው ይገርመኛል፡፡ እንዳልኸው ከአረጋዊ ሰውነት እንባ ያለምክንያት አይወጣም፤ መንፈሳዊ ግዳጅ ሊፈጽም እንጂ፡፡ በተለይ ቤተ ክርስቲያናችንን እናድሳለን ብለው ስለተነሡ አካላት በብስጭት ሳይሆን በሐዘኔታ ሲናገሩ የሚያፈሱት እንባ ልብን ይነካል፡፡ ምን ዓይነት መታደል ነው? ምን ዓይነትስ መረዳት ነው? አንተዬ፣ ምን ዓይነት ተመስጦ ምን ዓይነትስ መነካት ነው?


  ዳኒ፣ አንተ ከዛሬ ዐሥራ አምስት ዓመት በፊት ስለሆነው ነገር አንሥተህ የገለጽህበት መንገድ ከደስታ ይልቅ የፈጠረብኝ ሆድ ማስባስን ነው፡፡ ምነው ዳኒ? ምነው እንዲህ በማናውቀው ቦታ ሐረር ወስደህ አብረህ በመንፈስ ታሳትፈናለህ? ምነው ባልነበርንበት ዐውደ ምሕረት አውጥተህ ከመላእክቱ ጋር ታውለናለህ? ምነው አንተዬ? ምነው? ኧረ አስጎመዠኸን!


  ዳኒ፣ በየማኅበራዊ መገናኛው ስለአባቶቻችን የምንሰማው’ኮ እንዲህ አይደለም፡፡ የሚነገረን’ኮ እነርሱ ስለቤተ ክርስቲያን እንደሚያለቅሱ ሳይሆን ምእመናንን እንደሚያስለቅሱ ብቻ ነው፡፡ አባ ቀውስጦስ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያለቅሱ ብናያቸውም በሚያስለቅሱን ተሸፍነው ስለነበረ ማየት ተስኖን ነበር፡፡ አንተ ግን የዛሬ ዐሥራ አምስት ዓመቱን የሀረር ጉባኤ አምጥተህ የአባቶቻችን እንባ ምን ያህል ግዳጅ ይፈጽም እንደነበር አሳየኸን፡፡ ኧረ ተው፣ ዳኒ! ኧረ ተው! ስለበጎዎች እየነገርህ ተው ስለክፉዎች የበለጠ አታሳዝነን!


  ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 81፣1 “እግዚአብሔር ቆመ ውስተ ማኅበረ አማልእክት፤ ወይኴንን በማኅበረ አማልእክት፡፡” ያለው ለካ ይህን ነው! መተርጉማኑም “እግዚአብሔር በበጎዎች ካህናት አድሮ ክፉዎችን ሊገሥጽ በካህናት ማኅበር መካከል ቆመ” ብለው ወስደውታል፡፡ ለካ በጎዎች ያላቸው አንተ እንዳልኸው እነአቡነ ቀውስጦስን፣ እነአቡነ ቄርሎስን፣ እነአቡነ ናትናኤልን፣ እነአቡነ ኤልያስን፣ ወዘተ ነው! ክፉዎች ያላቸው ደግሞ ሌሎችን፡፡


  ጽሑፍህ ግን የምር ሆድ ያስብሳል፡፡ ክፉዎች በበዙበት በዚህ ዓለም ስለበጎ ሰዎች ማውራት ምነው ሆድ አያስብስ! በጊንጥ እየገረፉ የሚያስለቅሱ አካላት በተነሡበት በዚህ ዘመን ስለምእመናን ሕይወት ሌት ተቀን ስለሚያለቅሱ ቅዱሳን መናገር ምነው ስሜት አይነካ! ቤተ ክርስቲያንን እያፈረሱ የራሳቸውን ሕንፃ የሚገነቡ በበዙበት ዓለም የፈረሰ ቤተ ክርስቲያን ስለሚያንጹ አባቶች መስማት ምነው አያሳዝን፣ ዳኒ! በጎ ነገር መስማት የናፈቀው ሰው ስለበጎዎች ሲነገር ሲሰማ ያዝናል፤ ሆድም ይብሰዋል፡፡


  ስለበጎዎች የሚናገሩ ልሳናት፣ ስለበጎዎችም የሚጽፉ ጣቶች ምንኛ የተባረኩ ናቸው! ረጅም እድሜና ጤና በእንባቸው ለሚጠብቁን ብፁዓን አባቶች ይሁን!

  ደግ ደጉን ያስመልክተን፤ አሜን!!

  ReplyDelete
 5. ኑሩልን አባታችን፡፡

  ReplyDelete
 6. እግዚአብሔር ይጠብቅልን:: በጣም እናመሰግናለን::

  ReplyDelete
 7. Aba edmena tena yestot

  ReplyDelete
 8. dani bezi geze endezi abat megegetu yegeremal.gen dani እከ ያልከው የቤቶች እከ ነው ወይስ በታሪከ እከ የሚባል አለ፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. ግሩም! በእውነት መልካም እረኛ ማለት እንዲህ ነው እድሜያቸውን ያርዝምልን ተተኪ አባቶችንም አይንፈገን

   Delete
  2. This comment has been removed by the author.

   Delete
  3. This comment has been removed by the author.

   Delete
  4. እግዚኣብሔር የአባታችንንን እድሜ ያርዝምልን ተተኪ ፅኑአን አባቶችንም አያሳጣን ወንድማችን ዲ/ን ዳንኤል አገላለፅ ነው ጥበቡን ያብዛልህ.

   Delete
 9. thanks betema e enamesegenalene edemewene yadelelene abatachen

  ReplyDelete
 10. Abatachin Abune Kewstos is a Source of inspiration to all of us, I recently visited the Abune Petros Bete Christian in Fiche, which is a witness for Abune Kewstos dedication in garnering local and international support, and the nomination of Abune Petros as one of the 40 Millennium martyrs of the Century. Thank God for raising such saintly leaders. God bless you Daniel.

  ReplyDelete
 11. በታሪክ አጋጣሚ ከበዓታ ለማርያም ገዳም መሠረተ ሃይማኖት ሰንበት ትምሕርት ቤት በመራቄ በቦታው የመገኘት እድል አልገጠመኝም እንጂ ታሪኩን ሰምቼው ነበር፡ አሁን ግን የጻፍከውን ሳነበው በቦታው ሊኖር የሚችልውን ነገር በዓይነ ህሊናዬ ለአፍታ ጎበኘሁት በንባም ታንቄ አንብቤ ጨረስኩት አሁን በቅርቡም በአቡነ ቀውስጦስ የተደረገውን ተጋድሎ ሳነብ በፍጹም ደስታ በውስጤ ተስፋ ለመለመ፡፡ አምላካችን ሆይ እንደነዚህ ያሉ አባቶችን አታሳጣን፡፡ዲ/ን ዳንኤል ጠፈተህ ነበር እባክህ አንተም አትጥፋ ብቅ እያልክ አስተምረን፡ እድሜና ጤና ይስጥህ

  ReplyDelete
 12. ትምህርታቸው ከሰው ልብ ዕንባቸው መንበረ ጸባዖት ይደርሳል!!!

  ReplyDelete
 13. እግዚአብሄር እናመሰግንሀለን!! .

  ReplyDelete
 14. Amen ....EGIZIYABIHER yakoyilen

  ReplyDelete
 15. ምን እንላለን እግዚያብሔር እንደዚህ ያሉ አባቶችን እድሜ ይስጥልን ለእኛ ሲል እንደአጋጣሚ ሆኖ እኔም ደብረዲባኖስ ለንግስ ስሔድ ስለአየኋቸው ሃይላቸውን እረዳለሁ ለሃገራችን እንዲፀልዩላት እድሜ ይስጣቸው ያቆይልን ዳኒ አንተም አይነ ልቦናህን ያብራልህ!

  ReplyDelete
 16. ትክክል ነው! በEOTC በዛሬ ዓመት (2010)ወርሃ ጥር ቃለመጠየቅ ሲደረግላቸው ዕድል ገጥሞኝ ከጓደኛዬ ከዱጓ ተማሪው የየኔታ ተክለ ያሬድ ተማሪ መርሐ ጽድቅ ጋራ ሁኜ አይቻለሁ፤ ያላቸው የእግዚእበሔር ፍቅር፣የቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅር፣ የቅዱሳን ፍቅር፣ የሰው ፍቅር የሃይማኖት ፍቅር፣የአገር ፍቅር ልዩ ነው። ዕንባ እንዲህ ሲሉ ሰማሁ
  "አንጽሕኒ እግዚእትየ እምፍትወተ ዓለም እምርኩሳ፤
  በዲበ ሥጋዬ ኢትንበር ነጊሳ፤
  የምትለውን የመልክዓ ማርያም አርኬና ጸሎት በህፃንነቴ ገና ሳልሞነኩስ በህፃንነቴ ደብረ ሊባኖስ ስማር እወዳት ነበርና ሁሌ እደጋግማት ነበር ብለው በእንባ ሲናገሩ አየሁ ሰማሁኝም። ከዛም ህይወት ታሪካቸው ትልቅ ቀዋሚ መጽሐፍ ነው፤ ገድለ ቅዱሳን እኮ ከዓረፉ በኋላ ብቻ መፃፍ የለበትም እያሉም ከአንደበታቸው ማስቀረት ይገባል። በሚገባ አስፍተህ ብትፅፎው በአንተ ብዕር በእውነት ያምራል። "የሐዋርያው ብጹዕ አቡነ ቀውስጦስ መንፈሰዊ ህይወትና ትምህርቶቻቸው"
  በሚል እባክህ ብታደርገውስ? ... በፓትሪያሪኩ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት እና በእርሳቸው ስለነበረ ወዳጅነትም በጣም ሁድ የሚበላ ደስ የሚል ነው...ከአንደበታቸው ከሰማሁት የተወሰነ "አብዬ ወደየነበርህበት ሀገረ ስበከት እና ሕዝበ ክርስትያኑ .. እርሳቸው ብቻ ነው ምንፈልገው ብለውኛል... ስለዚህ ብትሄድስ አሉኝ...ከገነት ወደ በረሃ አልሁኝ "አዎ" አሉኝ። አባቴ ከፈቀደ ይሁን አልኳቸው.... ኋላ ግን ..የአቡነ ተክለሃይማኖት ክብረ በዓል ስናከብር...ተመልሰው ሆዳቸው ባብቶና "አብዬ..." "አቤት" አልኩ.."በዪ ደብዳቤ ሳይደርስሽ ከዚህች አዲሳባና ከዚህች ደብር ንቅንቅ እንዳትዪ.." አሉኝ። ....ሰላሙ ይብዛልህ ወንድሜ!!!!!!!!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 17. Ende coptic betekirstyan behizb zend tekebayint yalewun abat infeligalen lik ende abune shinouda salsawi. EGZIABIHER tsegawun yabzalot!!!

  ReplyDelete