የመጽሐፉ ታሪክ
(ክፍል ሁለት)
ከስድስት ወር በኋላ በየካቲት 1853(እኤአ) ኡርቢኖ ለአንቶኒዮ ዲ. አባዲ በጻፈው ደብዳቤ
ላይ ‹ሐተታ ዘርዐ ያዕቆብ› በእጁ መግባቱን ገለጠለት፡፡ ‹በመጨረሻ ባለፈው የገለጥኩልህን መጽሐፍ አገኘሁት፡፡ መጽሐፉን ተርጉሜዋለሁ፡፡
ነገር ግን ዋናውን እንጂ ትርጉሙን ላንተ መላክ የለብኝም ብዬ ስላሰብኩ በደብዳቤ መልክ ልልክልህ እንድችል በስስ ወረቀትና በጥቃቅን
ፊደላት መገልበጥ ጀምሬያለሁ፡፡ አመቺ ጊዜ ካገኘሁ እልክልሃለሁ› ብሎታል፡፡ በዚህ ደብዳቤው ላይ መጽሐፉን አሳጥሮ ገልጦታል፡፡
የዘርአ ያዕቆብን የሞቱን ታሪክ የጻፈው ተማሪው ወልደ ሕይወት መሆኑንና ወልደ ሕይወት ሌላ መጽሐፍ መጻፉን በዚህ መጽሐፍ ላይ እንደገለጠ፤
ነገር ግን ኡርቢኖ እንዳላገኘው ይናገራል፡፡ ቤተሰቦቹ በጣና ደሴቶች ውስጥ የሚገኙ አንድ የደብረ ታቦር ደብተራ ግን መጽሐፉን ሊያመጣለት
ቃል እንደገባለት ኡርቢኖ ይገልጣል፡፡
ይህ ኡርቢኖ አገኘሁት ያለውና በአውሮፓውያን ቀለም በወረቀት የገለበጠው ‹የሐተታ ዘርዐ
ያዕቆብ› ቅጅ ዛሬ በፈረንሳይ ቤተ መጻሕፍት የሚገኘውና Ms.234 የተመዘገበው ቅጅ ነው፡፡ ይህ ቅጅ ሐተታ ዘርአ ያዕቆብን ብቻ
የያዘ ሲሆን ‹መጽሐፈ ሐተታ ዘዘርዐ ያዕቆብ› ይላል፡፡ የመጽሐፉን መጨረሻ የጨመረለት ወልደ ሕይወት የተሰኘው ደቀ መዝሙሩ መሆኑንም
እንዲህ ሲል ይገልጠዋል ‹ወአነ ወልደ ሕይወት ዘተብህልኩ ምትኩ ወሰኩ ዝየ ዘንተ ንስቲተ - እኔ ወልደ ሕይወት የተባልኩት ምትኩ፣
እዚህ ላይ ጥቂት ጨመርኩ› ይላል፡፡ የራሱ መጽሐፍ እንዳለው ሲገልጥም ‹ወበእንተ ጥበብየሰ ዘአለብወኒ እግዚአብሔር ወመሀረኒ ዘርአ
ያዕቆብ ፶ወ፱ ዓመተ ናሁ ጸሐፍኩ ወአነሂ ካልእ መጽሐፈ - እግዚአብሔር እንዳውቀው ስላደረገኝ፣ ዘርአ ያዕቆብም 59 ዓመት ስላስተማረኝ
ጥበብ እኔም ሌላ መጽሐፍ ጻፍኩ› ብሏል[1]፡፡
መጽሐፉ ወልደ ጊዮርጊስ የተባለ ሰው ወልደ ዮሴፍ በሚባል ጸሐፊ እጅ ያስገለበጠው መሆኑን በመጨረሻው ላይ ይገልጣል[2]፡፡
ይህ አሁን ኡርቢኖ አገኘሁት የሚለን ቅጅ በታሪክ ሦስተኛው ቅጅ መሆኑ ነው፡፡
1.
የባለ መድኃኒቱ ቅጅ
2.
ኡርቢኖ በወረቀት ገልብጦ የላከው
ቅጅ (Ms. 234)
3.
አሁን ያገኘውና በብራና ተጽፎ
በሚገባ የተደጎሰ፣ በጥሩ የእጅ ጽሑፍ የተጻፈው ቅጅ
![]() |
ቅጅ 215 |
ይህ የኡርቢኖ ገለጣ እውነት ከሆነ በ19ኛው መክዘ
አያሌ የሐተታ ዘርአ ያዕቆብ ቅጅዎች ነበሩ ማለት ነው፡፡ ታድያ የት ሄዱ? አንዳንዶች መጽሐፉ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር ስለሚጋጭ
‹ደባትሩ› አጠፉት ይላሉ፡፡ በዐፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን ውግዘት ገጥሟቸው የነበሩት ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን የጻፏቸው ድርሳናት ተገኝተዋል፡፡
በቦሩ ሜዳ ጉባኤና ከዚያም በፊት በነበሩት ጉባኤያት ሲወገዙ የኖሩት ቅባቶችና ጸጎች ድርሳኖቻቸውን አግኝተናል፡፡ የዚህን ያህል
ውግዘት ያልገጠመው ‹ፈልስፋ‹ና የደቀ መዝሙሩን መጻሕፍት ቅጅዎች ግን ከMs. 234ና ከ215 በስተቀር አላገኘንም፡፡ በተለያዩ
ዘመናት በመጡ አሳሾች፣ የመጻሕፍት ሰብሳቢዎችና አጥኝዎች ሊገኝ አልቻለም፡፡ ከጣና ገዳማትና ከአካባቢው አያሌ መጻሕፍትን ጭኖ የሄደው
ስኮትላንዳዊ ጄምስ ብሩስ አላገኘውም፡፡ ከ12ሺ መጻሕፍትት በላይ በማይክሮ ፊልም ያነሣው የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍት ማይክሮ ፊልም
ድርጅትና በሺዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍትን በአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ ከሰሜን ኢትዮጵያ በዲጂታል ቅጅ የሰበሰበው የሐምቡርግ ፕሮጀክትም
አላገኘውም፡፡ ለምን?
የመጽሐፉን ተጨማሪ ቅጅዎችንም ባናገኝ እንኳን ቢያንስ
ለምን በሌሎች የኢትዮጵያ መጻሕፍት መጽሐፉ ወይም ዘርአ ያዕቆብ ተጠቅሶም አናገኘውም?
እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ ላንሳ፡፡ ከሊላ ወዲምናህ
የሚባል ጥንታዊ መጽሐፍ አለ፡፡ ይህ መጽሐፍ የግእዝ ቅጅው አልተገኘም፡፡ በዚህ የተነሣም ‹በግእዝ ይህ መጽሐፍ አልነበረም› የሚል
አስተያት የሰጡ ሊቃውንት ነበሩ፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ እስካሁን ባይገኝ እንኳን አባ ባሕርይ በመዝሙረ ክርስቶስ ድርሰቱ ጠቅሶት
ተገኝቷል፡፡ በዚህም ከ16ኛው መክዘ በፊት ይህ መጽሐፍ እንደነበረ አንዱ ማስረጃ ሆኗል[4]፡፡
የዐፄ ሱስንዮስ ዜና መዋዕል እስካሁን አንድ ቅጅ ብቻ ነው ያለው[5]፡፡
ነገር ግን የንጉሡ ሕልውናና ታሪክ በሌሎች ታሪከ ነገሥቶችና መዛግብት ተጠቅሶና ተተርኮ እናገኘዋለን፡፡ በዘመናቸው ግማደ መስቀሉ
የመጣው፣ ከዐፄ ዳዊት ጋር ልዩ ቀረቤታ የነበራቸው፣ ከቤተ ኤዎስጣቴዎስ ደቀ መዛሙርት እንደ አንዱ የሚጠቀሱት ግብጻዊው 87ኛ ሊቀ
ጳጳስ አባ ማቴዎስ(1370-1400) ገድል በግእዝ እስካሁን የተገኘው አንድ ቅጅ ብቻ ነው[6]፡፡
ነገር ግን በግሼ አምባ በተገኘው የመጀመሪያው ተአምረ ማርያም[7]
እና ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ታሪኩን በአጭሩ ከማቅረብ በተጨማሪ ስሙን ጠቅሰውት ይገኛሉ፡፡ የ‹ሐተታ ዘርአ ያዕቆብ›ና የ‹ሐተታ
ወልደ ሕይወት› ሁኔታ ግን ከሁሉም ለየት ይላል፡፡ ለምን?
![]() |
ቅጅ 234 |
ኡርቢኖ የመጀመሪያውን ቅጅና ሦስተኛውን ቅጅ አነጻጽሮ ለዲ. አባዲ በላከው ደብዳቤ ላይ
የሰጠው አስተያየት አስገራሚ ነው፡፡ የመጀመሪያውን ቅጅ በሚገባ ለማየትም ሆነ ለመገልበጥ ጊዜ አጣሁ ያለው ሰው ሁለቱን ቅጅዎች
አንድ ባለሞያ በሚያደርገው መንገድ ሲያነጻጽር እናገኘዋለን፡፡ በወልደ ሕይወት ሐተታ መጨረሻ የሠፈረው መግለጫ(Colophon)
በባለ መድኃኒቱ ቤት የተገኘው መጽሐፍ በምእራፍ 15 ላይ አሜን ብሎ እንደሚጨርስ ይናገራል፡፡ በዚህ ጥልቀት እንዴት ጊዜ ያጣበትን
መጽሐፍ እንዳስታወሰው አስገራሚ ነው፡፡
ይህ አሁን ኡርቢኖ ታሪኩን የሚነግረንና ‹ሐተታ ዘርአ ያዕቆብ›ን ከ‹ሐተታ ወልደ ሕይወት› ጋር የያዘው ቅጅ Ms.215 በሚል ቁጥር የሚታወቀውና በፈረንሳይ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት በአንቶኒዮ ዲ.አባዲ
መጻሕፍት ስብስብ ውስጥ የሚገኘው ነው፡፡ ገልባጩ ኢትዮጵያዊ ሲሆን የዘርአ ያዕቆብን መጽሐፍ ‹ገድለ ዘርአ ያዕቆብ› ይለዋል፡፡
ጥርት ያለ አጻጻፍ አለው፡፡ የዲ. አባዲን ስብስብ ስናየው ይህን መጽሐፍ የገለበጠው ሰው ደብተራ ገብረ ማርያም ዘቤተ ልሔም መሆኑን እንረዳለን፡፡ ከዚህ መጽሐፍ በተጨማሪ በMs.211
የተመዘገበውን ‹እግዚአብሔር ነግሠ›፤ በMs. 200 የተመዘገበውን ‹ፍትሐ ነገሥት› የገለበጠ ባለ ውብ እጅ ጸሐፊ መሆኑን የእጅ
ጽሑፉን በማስተያየት ለማወቅ ይቻላል፡፡
በቤተ ልሔም ድጓን ለማስመስከር ድጓን መጻፍና ማመልከት የግድ ነው፡፡ በዚህ የተነሣም
በቤተ ልሔም የእጅ ጽሕፈት ቤት ነበረ፡፡ እንደነ ደብተራ ገብረ ማርያም ያሉት ይህንን ነበር የሚሠሩት[8]፡፡
ኡርቢኖ 5 ዓመታት በዚህ አካባቢ ተቀምጧል፡፤ ወና ዓላማውም ይህንን የሀገርኛ ምሁራን ሀብት ፍለጋ መሆኑን ለመገመት ይቻላል፡፡
ምንም እንኳን ለደባትር የነበረው አመለካከት ዝቅ ያለ ቢሆንም ዕውቀታቸውን ግን ተጠቅሞበታል፡፡ በነገረ ጽሕፈት ጥናት(codicological) የኡርቢኖን ስብስቦች ስናይ የተዘጋጁት በቤተልሔም ነው[9]፡፡
ኡርቢኖ ግን ራሱ እንዳዘጋጀ ነው በየደብዳቤው የሚገልጠው፡፡ ለምን?
ይህ Ms. 215 የተጻፈው በቤተልሔም የእጅ ጽሕፈት ቤት መሆኑን በመልክዐ ጽሕፈት ጥናት
(paleographic analysis) ማረጋገጥ ተችሏል[10]፡፡
ኡርቢኖ በድንገት እንዳገኘው ቢገልጥም መጽሐፉ ግን በቤተ ልሔም የጽሕፈት ቤት ደብተራ ገብረ ማርያም ጊዜ ወስዶ የጻፈው ነው፡፡
ታድያ ኡርቢኖ ለምን መዋሸት አስፈለገው?
![]() |
የኡርቢኖ ማስተዋሻ ቅጅ 234 |
ኡርቢኖ ይህንን ቅጅ ለአንቶኒዮ ዲ.አባዲ የላከለት ከኢትዮጵያ ተባርሮ በሱዳን በኩል ካይሮ
በገባ ጊዜ በ1848 ዓም (እኤአ በ1856) ነው፡፡ አንቶኒዮ ዲ. አባዲ ይህን ቅጅ ሲያገኝ ‹እውነተኛ(Authentic)እና የተሟላ
ነው ብሎ ተቀበለው፡፡ ለ234 የሰጠውንም ቦታ ቀነሰው፡፡ እርሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሊቃውንትም 215ን እንደ ዋና አድርገው ሥራቸውን
ሠርተዋል፡፡ አብዛኞቹ ወደ አማርኛ የተተረጎሙት ቅጅዎችም ይህንን መሠረት አድርገው የተጻፉ ናቸው፡፡ የዚህን ቅጅ ችግር ግን በቀጣይ
የማሳየው ይሆናል፡፡
መጽሐፉ በ1856 ፓሪስ ደርሰ፡፡ በ1904 ኢኖ ሊትማን Ms. 215 እንደ ዋና ቅጅ በመጠቀም
የላቲን ትርጉምና ጥናታዊ ቅጅ አሳተመ[11]፡፡
ሊትማን ‹ሐተታ ዘርአ ያዕቆብ› የሚለውን ከMs. 234 ቢወስድም ነገር ግን ምንጩን አልጠቀሰም፡፡ ‹ፍልስፍና› የሚለውን ቦታ ሰጥቶ
መጻሕፍቱ ‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና› ብሏቸዋል፡፡ ሊትማን መጽሐፉ ከኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ የተለየ ጠባይ እንዳለው ተረድቷል፡፡ ‹የዐረብ
ተጽዕኖ አለበት› እስከማለትም ደርሷል፡፡ በ1916 ደግሞ ‹ዘርአ ያዕቆብ ብቸኛው የአቢሲኒያ አሳቢ›(Zar'a Ya'eqob, ein Denker einsamer in
Abessinien) በሚል ርእስ አንድ ጥናት አሳትሟል፡፡ ሩሲያዊው
ቦሪስ ቱራየቭ ደግሞ በ1905 የ‹ወልደ ሕይወትን ሐተታ› በመተው የዘርአ ያዕቆብን ብቻ Ms. 215ን እንደ ዋና ወስዶ ከ234
ጋር በማነጻጸር ሠራው፡፡ ‹የ17ኛው መክዘ ነጻ አሳቢ ኢትዮጵያዊ› በሚል ርእስ ጥናት አሳትሞ ነበር፡፡ ሁለቱም ሊቃውንት ሐተታዎቹ
የኢትዮጵያውያን ድርሳናት መሆናቸውን ገልጠዋል፡፡
በ1907 ደግሞ ኬ. ቤዞልድ (K. Bezold) ሁለቱን ቅጅዎች በማስተያየት አንድ የጥናት
ሥራ አሳተመ፡፡ በዚህ ጥናቱ የሊትማንን ስሕተቶች ከማሳየቱም በላይ በሁለቱ ቅጅዎች(215 ና 234) መካከል ያለው ልዩነት ከሰዋሰው፣
ከፊደላትና ከሌሎች ቀላል ልዩነቶች የሰፋ መሆኑን አመለከተ[12]፡፡
ታዋቂው የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥነ ጽሑፎች አጥኝ ኮንቲ ሮሲኒ በ1914 የዲ. አባዲን መጻሕፍት ካታሎግ ሲሠራ መጽሐፉ የፍልስፍና ሥራ
መሆኑንን መስክሮ ነበር፡፡ በ1920 ግን ይህንን ሐሳቡን ቀይሮ ሌላ ተች ጥናት አሳተመ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የኢትዮጵያዊው
ካቶሊካዊ የአባ አየለ ተክለ ሃይማኖት ሥራ ነው፡፡ ምን ይሆን? እንቀጥላለን፡፡
[1] Ms. 234, fol.31a
[2] Ms. 234, fol.31a
[3] Ms. 234, fol.31b-32a
[4] EMML
3473,fol.84;
[5] ጄምስ ብሩስ በ1770 ከጎንደር ያመጣው
[6] EMML 8071
[7] EMML
9002
[8] Ms. 200 የተመዘገበው ፍትሐ ነገሥት ላይ ጸሐፊው ደብተራ ገብረ ማርያም ዘቤተ ልሔም
መሆኑን በ1843 ዓም ለአባ ጀስት እንደጻፈለትም ይገልጣል፡፡
[9] Aissatou Mbodj-Pouye et Anais Wion, Hatata Zar’a
Ya’eqob, Episod 1, 2013
[10] Aissatou Mbodj-Pouye et Anais Wion, Hatata Zar’a
Ya’eqob, Episod 1, 2013
[11] Philosophi
abessini. (Corpus Scriptorum
Christianorum Orientalium, 18-19; Scriptores Aetiopici, 1-2)
[12]
Bezold, K., 1907, "[CR of
the critical edition of the text by E. Littmann]," Deutsche Literatur, p.
1242-1244.
i wounder what will hapen next
ReplyDeletegreat job
ReplyDeletebertalin daneil
ReplyDelete