Tuesday, January 16, 2018

የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ (‹ፈላስፋው› ዘርዐ ያዕቆብ ማነው?)

የመጽሐፉ ታሪክ
ከደብረ ታቦር ከተማ የተላኩ ሁለት መጻሕፍት በ1848 ዓ.ም. ፓሪስ ደረሱ፡፡ መጽሐፎቹ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ያልተለመደ ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡ የተላኩለት ሰው አንቶኒዮ ዲ. አባዲ የተባለ ፈረንሳዊ የካቶሊክ ሚሲዮናዊ ነው፡፡ ዲ. አባዲ በዘመነ መሳፍንት እኤአ ከ1836 – 1848 ዓም ኢትዮጵያ ውስጥ ለ12 ዓመታት በሚሲዮናዊነት የቆየ ፈረንሳዊ ነው፡፡ ከሚሲዮናዊነቱ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ጥንታውያን መጻሕፍት በማሰባሰብና በማጥናትም የራሱን አካዳሚያዊ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ የነበረበት ዘመን መንግሥት በተናጋበት በዘመነ መሳፍንት በመሆኑ አያሌ መጻሕፍትን ሰብስቦ ወደ አውሮፓ ለማሻገር ጠቅሞታል፡፡ ከኢትዮጵያ ሲወጣ 192 የብራና መጻሕፍትን ይዞ ወጥቷል[1]፡፡ 

ዲ. አባዲ ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላ የኢትዮጵያን መጻሕፍት መሰብሰቡን አላቆመም፡፡ ለዚህ የጠቀሙት ደግሞ ኢትዮጵያ የነበሩ ካቶሊክ ሚሲዮናውያንና ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረበት ጊዜ የመለመላቸውና ወደ ካቶሊክነት የለወጣቸው ደባትር ናቸው፡፡ እነዚህ ሚሲዮናውያንና ልውጥ ደባትር ከእርሱ ገንዘብና ሞራል እያገኙ አያሌ መጻሕፍትን ሀገሩ ከገባ በኋላ ይልኩለት ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ሚሲዮናውያኑና ልውጥ ደባትሩ ማዕከላቸውን በደብረ ታቦርና በድጓ ማስመስከሪያዋ ቤተልሔም አካባቢ በመትከላቸው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት፣ ለመጻሕፍቱና መጻሕፍቱን ለሚገለብጡት ጸሐፍት ቀረቤታ እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል፡፡ ዛሬ የአንቶኒዮ ዲ. አባዲ ስብስብ መጻሕፍት በፈረንሳይ ዋናው ቤተ መጻሕፍት በስሙ ተመዝግበው ተቀምጠዋል፡፡ ልዩ ልዩ ባለሞያዎችም ካታሎግ አድርገዋቸዋል[2]፡፡   

አነቶኒዮ ዲ. አባዲ ፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ተቀምጦ በነበረ ጊዜ መልእክትና መጽሐፍ ይልኩለት ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዱ እርሱ ከሰበሰባቸው መጻሕፍት ወጣ ያለ መጽሐፍ ማግኘቱን አበሰረው፡፡ የጠለየ ነገር መፈለግና ማግኘት ያስደስተው ለነበረው ለዲ. አባዲ ይህ ዜና እልል በቅምጤ የሚያሰኝ ነበር፡፡ ላኪው ጀስቶ ዲ. ኡርቢኖ (Justo d’ Urbino) ይባላል፡፡ ከ1847- 1855 (እኤአ) ኢትዮጵያ ውስጥ የኖረ በአቡነ ማስያስ (Bishop Massaia) ይመራ የነበረው የካቶሊክ ሚሲዮን አባል ነው፡፡ ኡርቢኖ ምን እንኳን የሚሲዮኑ አባል ቢሆን በወንጌላዊነት ለመሠማራትና ከጎንደር አካባቢም ለመውጣት ፍላጎት አልነበረውም፡፡ በየጊዜው ከዲ. አባዲ ጋር የተጻፋቸውን ደብዳቤዎች ስንመረምር[3] ዲ. አባዲን እንደ መምህሩና የበላይ ጠባቂው ይመለከተው ነበር፡፡ በ1847 ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ አኩስም አካባቢ ከተቀመጠ በኋላ ወደ ተድባበ ማርያም መጣ፡፡ በ1849 የመስቀልን በዓል በተድባበ ማርያም አክብሮ በ1850 ወደ ጎንደር ተሻገረ፡፡ ጎጃም ለመኖር ፍላጎት ነበረው፡፡  ነገር ግን አቡነ ሰላማ ሚሲዮናውያን ሀገር ለቀው እንዲወጡ ባወጁት ዐዋጅ የተነሣ በ1855 ከኢትዮጵያ እስኪወጣ ድረስ የኖረው በደብረ ታቦር አካባቢና በቤተ ልሔም ነው፡፡
ኡርቢኖ ከኢትዮጵያ በስናር በኩል ወደ ሱዳን ተሻገረ፡፡ ከዚያም ካይሮ ሄደ፡፡ ካይሮም ሆኖ ከአንቶኒዮ ዲ. አባዲ ጋር ይጻጻፍ ነበር፡፡ ለአንድ ዓመት ካይሮ ተቀምጦ በ1856 ተመልሶ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ወሰነ፡፡ ከካይሮም ወደ ሱዳን ተመለሰ፡፡ ነገር ግን በሱዳን እያለ በጥቅምት 1856(እኤአ) በኮሌራ በሽታ ሞተ፡፡
በመስከረም 20 ቀን 1852 (እኤአ) ኡርቢኖ ለአንቶኒዮ ዲ. አባዲ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለ አንድ መጽሐፍ ሲገልጥለት ‹እጅግ አስደናቂ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ በአንተ ስብስብ ውስጥ የለም፡፡ የመጽሐፉም ስም ጤፉት ይባላል፡፡ የሚገኘውም በግሼን አምባ ነው፡፡ ቅጅውንም በሌላ ቦታ ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ መጽሐፉ ከታሪከ ነገሥት ለየት ይላል፡፡› ይለዋል፡፡  በጥቅምት 26 ቀን 1853(እኤአ) ኡርቢኖ በጻፈው ሌላ ደብዳቤ ላይ ‹ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ የነገሥታትንና የመሳፍንትን ቤተሰብ ትውልድና ታላቅ ታሪክ የያዘውን ጤፉት የተባለውን መጽሐፍ በካታሎግህ ልታካትተው ትችላለህ፡፡ እርሱም በግሼን አምባ የሚገኝ ነው፡፡ የእርሱ ቅጅም በጎንደርና በተለያዩ ቦታዎች ይገኛል› ብሎት ነበር፡፡ ይህ ኡርቢኖ የገለጠው መጽሐፈ ጤፉት በግሼን አምባ ይገኝ ከነበረው ቅጅ አድያም ሰገድ ኢያሱ አስገልብጠውት ለጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴ የሰጡትና በአሁኑ ጊዜ በብሪቲሽ ሙዝየም በቁጥር 481 ተመዝግቦ የሚገኘው ነው፡፡ ይህ የኡርቢኖ ስለ መጽሐፈ ጤፉት የሰጠው ገለጻ የኢትዮጵያን መጻሕፍትን በተመለከተ የነበረውን መረዳት የሚያመለክተን ነው፡፡ ኡርቢኖ ስለ ኢትዮጵያ መጻሕፍት የማወቅ ብቻ ሳይሆን የመፈለግና የማሰባሰብ ፍላጎትም ነበረው፡፡ በዚህ ጥረቱም ለዲ. አባዲ 24 የብራና መጻሕፍትን ልኮለታል፡፡
ኡርቢኖ በዚሁ በመስከረም 1852 በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‹ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተለመደ ዓይነት መጽሐፍ አግኝቻለሁ፡፡ መጽሐፉ ልቦለድ ወይም የሕይወት ታሪክ ይመስላል፡፡ የጻፈው በፖርቹጋሎች ዘመን የነበረ መርማሪ ፈላስፋ ነው፡፡ ጸሐፊው የአኩስም ደብተራ ነው፡፡ በሃይማኖቱ ምክንያት ተሰድዶ ጫካ ውስጥ ኖሯል፡፡ እዚያም ብቻውን እያለ ሁሉንም የታወቁ እምነቶች መርምሮ አጣጣለ፡፡ በምክንያታዊ ምርመራም ፈጣሪ መኖሩን ዐወቀ› ይላል፡፡ ኡርቢኖ ስለ ጸሐፊውና ስለ መጽሐፉ ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ መጽሐፉን ከአንድ የዋድላ ባለ መድኃኒት እጅ እንዳገኘው፤ የተጠረዘ ነገር ግን የተጎዳ መሆኑን፤ መጠኑ አነስተኛ እንደሆነ፤ በአንድ ብር(ታለር) እንዲሸጥለት ጠይቆት ፈቃደኛ እንዳልሆነ፤ ዐሥር ብር ቢሰጠው እንኳን እንደማይሸጥለት እንደነገረው፤ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በመጽሐፉ ላይ የመድኃኒት ቅመማ ጥበብ ስለተጻፈበት መሆኑን ይገልጣል፡፡ ለመገልበጥ ጊዜና ገንዘብ ስላልነበረው እንደተወው ኡርቢኖ ለዲ. አባዲ ጽፎለታል፡፡ ስለ መጽሐፉ ርእስ ሲገልጥም ‹ሐተታ ያዕቆብ› ወይም መጽሐፈ ያዕቆብ ልንለው እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ባለ ታሪኩ ራሱን ያዕቆብ በማለት ነውና የሚጠራው› በማለት ገልጦ ነበር፡፡
‹ሐተታ ዘርዐ ያዕቆብ› የተሰኘው ድርሰት ከአውሮፓ ጋር የተዋወቀው በዚህ መንገድ ነበር፡፡ ኡርቢኖ በአንድ በኩል ጊዜ የለኝም እያለ በሌላ በኩል እንዴት መጽሐፉን ሊያነበውና አሳጥሮ ሊተርከው እንደቻለ ነገሩ አጠያያቂ ቢሆንም መጽሐፉን ‹መጽሐፈ ያዕቆብ፣ ሐተታ ያዕቆብ› ብሎ መግለጡን፤ ባለ ታሪኩንም ያዕቆብ ብሎ መጥራቱን ስንመለከት በኋላ ዘመን ‹ዘርዐ ያዕቆብ› ወደሚለው ስም ለም እንደተለወጠ እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡
ይቀጥላል…


[1] Aissatou Mbodj-Pouye et Anais Wion, Hatata Zar’a Ya’eqob, 2013
[2] C. Conti Rossini, 1914; Mr. Chain, 1912.
[3] ደብዳቤዎቹ በፈረንሳይ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት በቁጥር Ms. BNF NAF 23852 ይገኛሉ

3 comments:

  1. DANIYE MINALE SHI HUNEH BITIFETER !!! EHES ANDIE HONE ESKEAHUN DIRES EYETEZEREFN AYIDEL YALEN ! MIN YISHALENAL BEFIKRE NIWAY AGELIGAYOCHACHIN TEMETUBN!! ERE AMLAK ALEHU YIBELEN !!!

    ReplyDelete
  2. Dani, let's see and hear such a heartfelt history and recording from professionals like you. Because, you have a responsibility ( professional,identity-ship and citizenship responsibility). I am not historian but I really love to read,hear and see such readings. When I was about 8 and more, I was observing that some Ethiopians were searching for "Birana Books" even early traditional weapons like "Goradie" to buy with a huge birr. Now, I would have wished If I had had been now. It was really a missed opportunity to keep our identity. Still, we need to work on our heritages because now there might be a few Ethiopians as well as foreigners who are changing such historical and precious materials with a dollars.

    ReplyDelete