Thursday, January 25, 2018

የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ (ክፍል አራት)

የፍልስፍናው ይዘታዊ ማስረጃዎች
ኮንቲ ሮሲኒ እንደሚለው የሐተታ ዘርአ ያእቆብን ፍልስፍና ከዳ. ኡርቢኖ ደብዳቤዎች ጋር ለማስተያየት ሞክሮ ነበር፡፡ ዳ. ኡርቢኖ በግንቦት 1854 ለአንቶንዮ ዲ. አባዲ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሰውን የዚህ ዓለም ማዕከል አድርጎ የሚያይበትን አመለካከቱን አንጸባርቆ ነበር፡፡ ይህም አስተሳሰብ በሐተታ ዘርአ ያእቆብ ላይ በዚያው መልኩ ይገኛል፡፡ ኡርቢኖ ‹አንዳች ነገር ባውቅ ያ ከእግዚአብሔር ያገኘሁት ነው፡፡ ማንም አላስተማረኝም.. ስለ ፈጣሪና ሀልዎቱ እውነት የሆነ ሐሳብ እንዳለኝ አምናለሁ፡፡ ይህንንም ከማንም ባለመቀበሌ እኮራለሁ› ሲል በደብዳቤው ላይ ገልጦታል፡፡ በመስከረም 1854 በጻፈው ሌላ ደብዳቤ ደግሞ ብቸኝነቱ ከፈጣሪና ከዓለማት ጋር ለመገናኘትና በደስታ ለመኖር የሚቻልበትን መንገድ ለመመርመር እንደገፋፋው ይገልጣል፡፡ ‹እግዚአብሔር መኖሩን አምናለሁ፤ ሌላው ነገር ግን ሊያረካኝ ስላልቻለ እቃወመዋለሁ› ሲል ገልጦ ነበር፡፡ ይህን መሰሉ ሐሳብ በሐተታ ዘርአ ያእቆብም ውስጥ ይገኛል፡፡ በርግጥ ይህንን ደብዳቤ የጻፈው ሐተታ ዘርአ ያእቆብን ካገኘ ከሁለት ዓመታት በኋላ በመሆኑ ማን ከማን እንደወሰደው ግልጽ አይደለም የሚል ትችት ቀርቦበታል፡፡ ነገር ግን ቀደም ብሎ ከጻፋቸው ብቸኝነቱን ከሚጠቅሱት ደብዳቤዎቹ ጋር ስናነጻጽረው ይህ ሐሳብ የ ዳ. ኡርቢኖ ውስጣዊ ሐሳቡ መሆኑን እንረዳለን፡፡

Monday, January 22, 2018

የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ (ክፍል ሦስት)


አባ አየለ ተክለ ሃይማኖትና ዳ. ኡርቢኖ
አባ አየለ ተክለ ሃይማኖት በዳ. ኡርቢኖ ዘመን የነበረ ካቶሊካዊ ሚሲዮናዊ ነው፡፡ በአቡነ ያዕቆብ ይመራ የነበረው የትግራይ ካቶሊክ ሚሲዮናዊ ልዑክ አባል ነበር፡፡ ከትግራይ ወደ ጎንደር መጣ፡፡ ምንም እንኳን ዳ. ኡርቢኖ የተመላለሰበትን መሥመር በሚገባ ቢያውቀውም የእርሱ ዋናው ትኩረት ግን የሚሲዮን አገልግሎት ላይ ነበር፡፡ ዳ. ኡርቢኖ ግን ሚሲዮናዊ ተልዕኮውን ትቶ በቤተ ልሔም አጠገብ ይኖር ነበር፡፡ ይሠራ የነበረው ሥራ ግን ለሌሎቹ የሥራ ባልደረቦቹ ግልጽ አልነበረም፡፡ 

ኮንቲ ሮሲኒ እኤአ በ1916 የአባ ተክለ ሃይማኖትን ማስታወሻ አሳትሞ ነበር[1]፡፡ በዚህ ማስታወሻቸው ላይ ዳ. ኡርቢኖ ከቤተልሔም ደባትር ከደብተራ አማርከኝ(ምናልባት ደብተራ አሰጋኸኝ ይሆናል) እና ከሊቀ ካህናት ጎሹ ጋር የቀረበ ግንኙነት እንደነበረው ይገልጣሉ፡፡ ከእነርሱም የፍሪ ማሶናውያንንና የመናፍቃንን መጽሐፍ መግዛቱን ይናገራሉ፡፡ በዚህ ማስታወሻ ላይ ዳ. ኡርቢኖ ብዙ መጻሕፍትን እንደሚያስጽፍ፤ የእነዚህ መጻሕፍት ደራሲ ራሱ ቢሆንም ነገር ግን የብእር ስም እንደሚጠቀም፣ ይህም መጽሐፍ ወርቄ እንደሚባል፣ ስምሙ የተሰጠው ደራሲው ነው ተብሎ በታሰበው ሰው ስም መሆኑን ያትታሉ፡፡ አባ ተክለ ሃይማኖት ‹ሐተታ ዘርአ ያዕቆብን› አላነበቡትም የሚነግሩን ግን ስለ እርሱ መሆኑ ርግጥ ነው፡፡ የዘርአ ያዕቆብ ሌላው ስሙ ‹ወርቄ› ነውና፡፡ አባ ተክለ ሃይማኖት ዳ. ኡርቢኖ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በፍልስፍናና በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተሻለ ዕውቀት እንዳለውም ይናገራሉ፡፡ አባ ተክለ ሃይማኖት ዳ. ኡርቢኖን በመልካም አያዩትም፤ የሚያጠራጥር ሕይወትና እምነት እንደነበረው ይገልጣሉ፡፡ 

Thursday, January 18, 2018

ቀውስጦስ - የበረሓ ምንጭ


ሲያምኑ እንደ አብርሃም ነው፣ ሲሠሩ እንደ ላሊበላ፡፡ ሲያስተምሩ እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፣ ሲተጉ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ፤ ከቆረጡ እንደ አቡነ ጴጥሮስ ናቸው፣ ከሞገቱ እንደ ሳዊሮስ፡፡ ከመረቁ የሚጠቅሙትን ያህል ከረገሙም ይጎዳሉ፤ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ከሆነባቸው ክብር፣ ፕሮቶኮል፣ ስምና ዝና አይገድባቸውም፡፡ ከቀበሌ እስከ ቤተ መንግሥት ይሞግታሉ፤ በፍትሕ አደባባይ መፍትሔ ካጡ ‹ይግባኝ ለክርስቶስ‹ ብለው ለሰማያዊው ፍርድ ቤት ያቀርባሉ፡፡
አረጋዊ ናቸው፣ ግን እንደ ወጣት ይሠራሉ፤ ሊቀ ጳጳስ ናቸው ነገር ግን እንደ ሰንበት ተማሪ ይሮጣሉ፣ የአንድ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፣ ግን በሁሉም ይወደዳሉ፤ ትምህርታቸው ከሰው ልብ ዕንባቸው መንበረ ጸባዖት ይደርሳል፡፡ በርሳቸው ዘንድ ትንሽ የለም፣ ትልቅም የለም፡፡
የርሳቸውን ስም የያዘው ቅዱስ የዛሬ 700 ዓመት እንዲሁ እንደርሳቸው ነበር፡፡ ቅዱሱ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሲሆን ያስተምራል፣ ገዳማትን ይተክላል፣ ደቀ መዛሙርትን ያፈራል፣ ነገሥታትን ይገሥጻል፣ ለእምነቱ ጥብቅና ይቆማል፣ ግፍንና በደልን ይጸየፋል፡፡ ቅዱስ ቀውስጦስ ዘመሐግል፡፡ በሰማዕትነትም ያረፈው ንጉሥ ዓምደ ጽዮን ከክርስትናው ወጥቶ ሁለት ሚስት አግብቶ፣ የተቃወሙትን ቅዱሳን በግፍ ባሳደደ ጊዜ ነው፡፡ በንጉሡ ፊት እውነቱን ተናግሮ፣ ስሕተቱን ገልጦ በተናገረ ጊዜ ከቤተ መንግሥቱ አውጥተው በጨለማ ቤት አሠሩት፣ በኋላም ከጨለማው እሥር ቤት አውጥተው ዛሬ በሰሜን ሸዋ እንሣሮ በሚባለው ቦታ ወስደው በግፍ ገደሉት፡፡ እርሳቸውም ስሙን ብቻ ሳይሆን ግብሩንም ወርሰውታል፡፡ 

Wednesday, January 17, 2018

የሌለውን ‹ፈላስፋ› ፍለጋ


የመጽሐፉ ታሪክ
(ክፍል ሁለት)
ከስድስት ወር በኋላ በየካቲት 1853(እኤአ) ኡርቢኖ ለአንቶኒዮ ዲ. አባዲ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‹ሐተታ ዘርዐ ያዕቆብ› በእጁ መግባቱን ገለጠለት፡፡ ‹በመጨረሻ ባለፈው የገለጥኩልህን መጽሐፍ አገኘሁት፡፡ መጽሐፉን ተርጉሜዋለሁ፡፡ ነገር ግን ዋናውን እንጂ ትርጉሙን ላንተ መላክ የለብኝም ብዬ ስላሰብኩ በደብዳቤ መልክ ልልክልህ እንድችል በስስ ወረቀትና በጥቃቅን ፊደላት መገልበጥ ጀምሬያለሁ፡፡ አመቺ ጊዜ ካገኘሁ እልክልሃለሁ› ብሎታል፡፡ በዚህ ደብዳቤው ላይ መጽሐፉን አሳጥሮ ገልጦታል፡፡ የዘርአ ያዕቆብን የሞቱን ታሪክ የጻፈው ተማሪው ወልደ ሕይወት መሆኑንና ወልደ ሕይወት ሌላ መጽሐፍ መጻፉን በዚህ መጽሐፍ ላይ እንደገለጠ፤ ነገር ግን ኡርቢኖ እንዳላገኘው ይናገራል፡፡ ቤተሰቦቹ በጣና ደሴቶች ውስጥ የሚገኙ አንድ የደብረ ታቦር ደብተራ ግን መጽሐፉን ሊያመጣለት ቃል እንደገባለት ኡርቢኖ ይገልጣል፡፡
ይህ ኡርቢኖ አገኘሁት ያለውና በአውሮፓውያን ቀለም በወረቀት የገለበጠው ‹የሐተታ ዘርዐ ያዕቆብ› ቅጅ ዛሬ በፈረንሳይ ቤተ መጻሕፍት የሚገኘውና Ms.234 የተመዘገበው ቅጅ ነው፡፡ ይህ ቅጅ ሐተታ ዘርአ ያዕቆብን ብቻ የያዘ ሲሆን ‹መጽሐፈ ሐተታ ዘዘርዐ ያዕቆብ› ይላል፡፡ የመጽሐፉን መጨረሻ የጨመረለት ወልደ ሕይወት የተሰኘው ደቀ መዝሙሩ መሆኑንም እንዲህ ሲል ይገልጠዋል ‹ወአነ ወልደ ሕይወት ዘተብህልኩ ምትኩ ወሰኩ ዝየ ዘንተ ንስቲተ - እኔ ወልደ ሕይወት የተባልኩት ምትኩ፣ እዚህ ላይ ጥቂት ጨመርኩ› ይላል፡፡ የራሱ መጽሐፍ እንዳለው ሲገልጥም ‹ወበእንተ ጥበብየሰ ዘአለብወኒ እግዚአብሔር ወመሀረኒ ዘርአ ያዕቆብ ፶ወ፱ ዓመተ ናሁ ጸሐፍኩ ወአነሂ ካልእ መጽሐፈ - እግዚአብሔር እንዳውቀው ስላደረገኝ፣ ዘርአ ያዕቆብም 59 ዓመት ስላስተማረኝ ጥበብ እኔም ሌላ መጽሐፍ ጻፍኩ› ብሏል[1]፡፡ መጽሐፉ ወልደ ጊዮርጊስ የተባለ ሰው ወልደ ዮሴፍ በሚባል ጸሐፊ እጅ ያስገለበጠው መሆኑን በመጨረሻው ላይ ይገልጣል[2]፡፡

Tuesday, January 16, 2018

የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ (‹ፈላስፋው› ዘርዐ ያዕቆብ ማነው?)

የመጽሐፉ ታሪክ
ከደብረ ታቦር ከተማ የተላኩ ሁለት መጻሕፍት በ1848 ዓ.ም. ፓሪስ ደረሱ፡፡ መጽሐፎቹ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ያልተለመደ ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡ የተላኩለት ሰው አንቶኒዮ ዲ. አባዲ የተባለ ፈረንሳዊ የካቶሊክ ሚሲዮናዊ ነው፡፡ ዲ. አባዲ በዘመነ መሳፍንት እኤአ ከ1836 – 1848 ዓም ኢትዮጵያ ውስጥ ለ12 ዓመታት በሚሲዮናዊነት የቆየ ፈረንሳዊ ነው፡፡ ከሚሲዮናዊነቱ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ጥንታውያን መጻሕፍት በማሰባሰብና በማጥናትም የራሱን አካዳሚያዊ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ የነበረበት ዘመን መንግሥት በተናጋበት በዘመነ መሳፍንት በመሆኑ አያሌ መጻሕፍትን ሰብስቦ ወደ አውሮፓ ለማሻገር ጠቅሞታል፡፡ ከኢትዮጵያ ሲወጣ 192 የብራና መጻሕፍትን ይዞ ወጥቷል[1]፡፡ 

ዲ. አባዲ ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላ የኢትዮጵያን መጻሕፍት መሰብሰቡን አላቆመም፡፡ ለዚህ የጠቀሙት ደግሞ ኢትዮጵያ የነበሩ ካቶሊክ ሚሲዮናውያንና ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረበት ጊዜ የመለመላቸውና ወደ ካቶሊክነት የለወጣቸው ደባትር ናቸው፡፡ እነዚህ ሚሲዮናውያንና ልውጥ ደባትር ከእርሱ ገንዘብና ሞራል እያገኙ አያሌ መጻሕፍትን ሀገሩ ከገባ በኋላ ይልኩለት ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ሚሲዮናውያኑና ልውጥ ደባትሩ ማዕከላቸውን በደብረ ታቦርና በድጓ ማስመስከሪያዋ ቤተልሔም አካባቢ በመትከላቸው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት፣ ለመጻሕፍቱና መጻሕፍቱን ለሚገለብጡት ጸሐፍት ቀረቤታ እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል፡፡ ዛሬ የአንቶኒዮ ዲ. አባዲ ስብስብ መጻሕፍት በፈረንሳይ ዋናው ቤተ መጻሕፍት በስሙ ተመዝግበው ተቀምጠዋል፡፡ ልዩ ልዩ ባለሞያዎችም ካታሎግ አድርገዋቸዋል[2]፡፡