Thursday, December 7, 2017

ስማዳ በአውስትራልያ


አውስትራልያዊው የጤፍ ገበሬ

የአውስትራልያ ዋናው ዲታ ቸርቻሪ (supermarket giant) ኮልስ (Coles) ነጩንና ጥቁሩን ጤፍ በአውስትራልያ ከተሞች እንደ ጉድ ይቸበችበዋል፡፡ በምድረ አውስትራልያ ዋናው የጤፍ ዱቄት አከፋፋይ የሆነው ኮልስ ጤፍ በአሁኑ ጊዜ የስንዴ ዱቄትን እየተካ መምጣቱንና ለዳቦ፣ ለፓስታ፣ ለፓን ኬክ መሥሪያ ከመዋል አልፎ በሰላጣ ውስጥ ከሚጨመሩ ግብዐቶች አንዱ መሆኑን ያናገራል፡፡ 500 ግራም ጤፍ በ10 ዶላር አካባቢ ይሸጣል፡፡

በአሜሪካ፣ በሆላንድ፣በደቡብ አፍሪካና በእሥራኤል በከፍተኛ ሁኔታ መመረት የጀመረውና በዓለም የምግብ ገበያ የከበረ ሥፍራ እየያዘ የመጣው ጤፍ በአውስትራልያ ምድር ባለፉት ዐሥር ዓመታት ከኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ውጭ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ሲጀመር ከአሜሪካ ምድር እየተጫነ ይመጣ ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ጤፉ መምጣቱ ቀርቶ አድአና ስማዳ ራሳቸው ወደ አውስትራልያ መጥተዋል፡፡ ጥንት ባሕር ዛፍ ከአውስትራልያ ወደ ኢትዮጵያ እንደሄደው ሁሉ ‹ብድር መላሽ ያርገን› የሚለውን ምርቃት ለመፈጸም በምትኩ ጤፍን ወደ አውስትራልያ ልከናል፡፡ ቁጥራቸው ከ20 ሺ የሚበልጡት የሜልበርን ኢትዮጵያውያንም የሕንድ ውቅያኖስን አቋርጦ እንዲመጣላቸው ሲጠብቁት የነበረውን ጤፍ እዚሁ ከጓሯቸው እያገኙት ነው፡፡
በጎልበርን ሸለቆ የተዘናፈለው ጤፍ

በደቡብ እስያና በኦሽንያ ገበሬዎች ዘንድ በታየው የአመራረት ዘዴ እድገትና የአካባቢውን ገበያ የመቆጣጠር ሂደት ምክንያት ገቢያቸው እየቀነሰ ለመጣው የአውስትራልያ ገበሬዎች ጤፍ አዲስ ተሥፋ ይዞ መጥቷል፡፡ ከግሉተን ነጻ ስለመሆኑ ባኘው የባለሞያዎች ምስክርነት የተነሣ በችርቻሮ ገበያዎች ብቻ ሳይሆን በመድኃኒት ቤቶች ጭምር እየተሸጠ የመጣው ጤፍ በአውስትራልያ ምድር መዘናፈል ጀምሯል፡፡ 
 
ጥቁር ጤፍ በአውስትራልያ ገበያ
ረቡዕ ኅዳር 27 ቀን ከሜልበርን ከተማ ተነሥተን፣ እኔ፣ ኃይለ ልዑልና ምንዳየ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ተጓዝን፡፡ የሲድኒን አውራ ጎዳና ይዘን፡፡ የምንገሠግሠው ወደ አውስትራልያዊቷ ስማዳ ነው፡፡ በደቡብ ጎንደር የምትገኘው ስማዳ ከጤፍ ዘሮች ሁሉ ምርጡ ጤፍ የሚባለው የስይት ጤፍ መገኛ ናት፡፡ ዐፄ ምኒልክ ጎንደር እያሉ የወደዱትን የስማዳ ስይት ጤፍ በቅርበት ማግኘት ፈለጉ፡፡ ከስማዳ ድረስ እያስጫኑ ማምጣት አላረካቸውም፡፡ የስማዳን የአየር ንብረት የመሰለ ቦታ ሲያፈላልጉ አድአን አገኙ፡፡ ዘሩን ከስማዳ አስመጡና አደአ ላይ ዘሩት፡፡ ይሄው የአድአ ጤፍ ሲወደድና ሲወደስ ይኖራል፡፡ ዛሬ ጤፍን ከ6.3 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ገበሬዎች በዋናነት ሲያመርቱት ከ20 በመቶ በላይ የእርሻ መሬትንም ይሸፍናል፡፡   

በመኪና የዞርነው የጤፍ ማሳ
አውስትራልያዊቷ ስማዳ የምትገኘው ከሜልበርን ከተማ በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሸፐርተን በሚባል ከተማ አቅራቢያ ነው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ በአውስትራልያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ግንባር ቀደም መሪዎች ከሆኑት አንዱ ኃይለ ገብርኤል ገብረ ሥላሴና የሸፐርተን የግብርና አማካሪ ሌስ ሚቸል የጤፍ እርሻ ጀምረዋል፡፡ ‹ጤፍ አውስትራልያ› የተሰኘውን ኩባንያ የመሠረቱት እነዚህ ሰዎች ናቸው በጎልበርን ሸለቆ(Goulburn Valley) ስማዳን የፈጠሯት፡፡ በጎዳናው ግራና ቀኝ እንደ ሰላሌ ሜዳ በተኛው መሬት ላይ እንደ እነዋሪ ሙዝ የደለቡ ከብቶች ሲምነሸነሹበት ሳይ ምነው የሀገሬ ከብቶች ይህንን መስክ ለአንድ ቀን እንኳን አግኝተው ቦርቀውበት በማግሥቱ በሞቱ ብዬ ተመኘሁ፡፡ በዚያ የእንጭኒን የፈረስ መጋለቢያ ሜዳ በሚያህል መስክ ላይ እፍኝ የማይሞሉ ከብቶች ብቻ የቀን ሌባ የሌሊት አውሬ ሳያስፈራቸው ይንጎማለላሉ፡፡ እዚህስ ኢትዮጵያውያንን ሳይሆን ከብቶቹን ነበር ማምጣት፡፡
 
የስማዳዋ የጤፍ ገበሬና ቤቷ
አሁን ወደ ሸፐርተን የሚገነጠለውን መንገድ ይዘናል፡፡ የአየሩ ሁኔታም ከቅዝቃዜ ወደ ሙቀት እየተቀየረ ነው፡፡ ሸፐርተን ከተማ ላይ ሌስ ሚቸልን ጨመርንና ጉዟችንን ወደ አውስትራልያዋ ‹ስማዳ› ወደ ጎልበርን ሸለቆ ቀጠልን፡፡ ግራና ቀኙ ዓይን እስኪደክም ጤፍ ተኝቶበታል፡፡ የማሳው መጨረሻ ከሰማዩ ጋር ተሳስሟል፡፡ 600 ሄክታር መሬት በጥቁርና በነጭ ጤፍ ገነት መስሏል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ጄምስ ሮቨርስ የተባለ የ28 ዓመት ወጣት አውስትራልያዊ ገበሬ ርስት ነው፡፡ እንዳለች ስማዳን ጠቀለላት አትሉኝም፡፡ ሰሞኑን የዘነበው ዝናብ በላዩ ላይ ተኝቶበት ሲድህ እንደደከመው ሕጻን በያለበት ተኝቷል፡፡ ለጤፍ ጠባይ እንግዳ የሆነው አውስትራልያዊ ገበሬ ‹ጤፍ ሲተኛ ምንድን ነው የሚደረገው?› የሚል ጥያቄ ሰነዘረልኝ፡፡ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረኝም፡፡ እሱ ብዙም አላስጨነቀውም፡፡ ‹አጭጄ ለከብቶች ምግብ ላርገው?› ብሎ ኃይለ ልዑልን ጠየቀው፡፡ አሳብ የለሽ፣ አንተ ምን አለብህ፡፡ ይህንን የመሰለ ማኛ ጤፍ ለከብት ልስጠው ትላለህ?
ማኛውን በልቼ ማኛ ጠጥቻለሁ
አሁን ምን ቀርቶብኝ እድሜ እለምናለሁ
ተብሎ እንደተዘፈነ ማን በነገረህ - አልኩ በልቤ፡፡ የአካባቢው ገበሬዎች እዚህ በመንደራቸው በሚዘናፈለው የጤፍ ማሳ ተገርመዋል፡፡ ስለ ጤፍ አልፎ አልፎ ቢሰሙም እንዲህ በዓይናቸው ሥር ሀገሩን ሞልቶ የሚያዩት መስሎ አይሰማቸውም ነበር፡፡ ሮቨርስ የአካባቢው ገበሬዎች ‹ለመሆኑ ገበያው እንዴት ነው? ከስንዴ የተሻለ ገቢስ ያመጣል ወይ?› የሚለው ነገር የዘወትር ጥያቄያቸው መሆኑን ይናገራል፡፡ እርሱ ግን ተስፋ አድርጓል፡፡ በዚህ በቆሎውን ትቶ በዘራውና ሰማይ ላይ የተበተነ ኮከብ በሚያህለው እህል፣ እኔ ነኝ ያለ ሀብት እንደሚዝቅበት፡፡ ‹ትዕቢተኛ በቆሎ ከጤፍ ሆድ ውስጥ ዱቄት የሚወጣ  አይመስላትም› የተባለውን ብነግረው ደግሞ እርሻው መሐል የሚሰቅለው መፈክር ይሆነው ነበር፡፡ 
የአውስትራልያዊው ገበሬ ቤት

ቢያዩት ቢያዩት ከማይጠገበው የጤፍ እርሻ ስንወጣ ሮቨርስን አንድ ጥያቄ ጠየቅሁት
‹ለመሆኑ እንጀራ በልተህ ታውቃለህ?›
 ‹‹አላውቅም››፡፡
ሜልበርን አውስትራልያ 

4 comments:

 1. የእኛስ ግብርና መቼ ይሆን እንደዚህ የሚዘምነው... ክብር ይስጥልን::

  ReplyDelete
 2. ዲያቆን ዳንኤል
  አሁን የምፈራው እንደ ጤፉ አይጠቅማችሁም ብለው የሌሎቹንም እውቅና እንዳይነጥቁን ሙያተኞቻችን ነቅተው ቢጠብቁ እላለው !!!!
  "ክብረት ይስጥልኝ"

  ReplyDelete
 3. መቼ ይሆን እኛ በግብርና እራሳችንን የምንችለው የምናድገው... አስተማሪ ታሪክ ነው ዳኒ

  ReplyDelete