የኖርዌዩ አባ ቴዎድሮስ የሚተርኳት
አንዲት ገጠመኝ አለቻቸው፡፡ በአንድ ወቅት የቅኔ መምህር ሆነው አንድ ቦታ ይመደባሉ፡፡ በተመደቡበት ቦታ አንድ የታፈሩና የተከበሩ
አፈ ንቡረ እድ ነበሩ፡፡ ሰው ሁሉ ይፈራቸዋል፡፡ አባ ቴዎድሮስ የቅኔውም የመጽሐፉም ዕውቀት አለ፡፡ በዚህ ላይ ከሰው ጋር ተግባቢ
ናቸው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ያኔ ወጣት ናቸው፡፡
አፈ ንቡረ እዱ በእኒህ ወጣት መምህር
መምጣት አልተስማሙም፡፡ ዐውቃለሁ ባይ ወጣት አድርገው ቆጠሯቸው፡፡ ይህንን ያወቁ ሌሎች ሰዎች ለአባ ቴዎድሮስ አንድ ነገር ሹክ
አሏቸው፡፡ ‹እኒህ ሊቅ ከባድ ሰው ናቸው፡፡ ፊት ለፊት አግኝተው እፍ ካሉብዎት ሽባ ሆነው ይቀራሉ› ይሏቸዋል፡፡ አባ ለሀገሩም
ለነገሩም እንግዳ ስለሆኑ ግራ ገባቸው፡፡ እንዴት ከእፍታው እንደሚያመልጡ ሆነ የዘወትሩ ሐሳባቸው፡፡ እንዲህ እያሰቡ ሰሞነ ጽጌ
ደረሰ፡፡ በሌሊቱ ማኅሌት አባ በአንድ መሥመር አፈ ንቡረ እዱ በአንድ መሥመር ለማስረገጥ ተሰለፉ፡፡ ደግሞ ይግረምዎ ብለው አባና
አፈ ንቡረ እዱ ፊት ለፊት ገጠሙ፡፡