Wednesday, October 18, 2017

መርከቧ በባሕሩ ላይ፣ ወይስ ባሕሩ በመርከቧ ላይ?


 
ታዋቂው ሩሲያዊ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ባለሞያ ዶክተር ሰርጌይ ላቭሮቭ ‹Reformation in the Orthodox Perspective> በተሰኘውና እኤአ በ1998 ባወጣው መጽሐፉ ላይ በሕንድ፣ በጆርጅያና በዩክሬይን የተደረገውን የተሐድሶ እንቅስቃሴ ባጠናበት መጽሐፉ ላይ ‹በቤተ ክርስቲያን ጉዞ ውስጥ ዋናው ጥያቄ - መርከቧ በባሕሩ ላይ ትሂድ ወይስ ባሕሩ በመርከቧ ውስጥ ይሂድ የሚለው ነው› ይላል፡፡ ለዚህ ሐሳብ መነሻ ያደረገው በሦስቱ ሲኖፕቲክ ወንጌሎች ላይ በማቴ.8፥23፤ሉቃ. 8፥22 እና በማር. 4፥35 የተጻፈውን ታሪክ ነው፡፡ 
 
በእነዚህ የወንጌል ክፍሎች ላይ ጌታችንና ሐዋርያት በመርከብ ወደ ገሊላ ማዶ ሲሻገሩ ጌታችን ተኝቶ ነበረ፡፡ በመንገዱ መካከል መጀመሪያ ነፋስ፣ በኋላም ማዕበል ተነሣ፤ በመጨረሻም ማዕበሉ የባሕሩን ውኃ ወደ መርከቧ ውስጥ መጨመር ጀመረ፡፡ ማቴዎስ ‹ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ›፣ ማርቆስ ‹ውኃ በታንኳዪቱ እስኪሞላ ድረስ› ሉቃስ ‹ውኃም ታንኳዪቱን ይሞላ ነበር› በማለት የገለጡት አደጋ ተከሠተ፡፡ መርከቧ በውኃው ላይ መሄዷ ቀርቶ ውኃው በመርከቧ ላይ መሄድ ጀመረ፡፡ ያን ጊዜ ሐዋርያቱ ተጨነቁ፡፡ ጌታችንንም ቀሰቀሱት፡፡ እርሱም ‹እናንተ እምነት የጎደላችሁ‹ በማለት መጀመሪያ ሐዋርያትን ቀጥሎም ማዕበሉን ገሠጸው፡፡
መርከቧ ቤተ ክርስቲያን በውኃ ላይ እየተንሳፈፈች፣ እየተላጋችና ከፍ ዝቅ እያለች መሄዷ የተለመደ ነው፡፡ ይህም ምንም ፈታኝ ቢሆን ጤናማ ጉዞ ነው፡፡ ‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ›(ዮሐ.16፥33) የተባለው ይፈጸማልና፡፡ ውኃው ወደ መርከቡ ከገባ ግን አደጋ ይከሰታል፡፤ ወይ መርከቧ ትሰምጣለች ወይም መርከቧ ትሰበራለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን እየተፈተነች በዓለም ላይ መጓዟ ችግር የለውም፡፡ ፈተናውም ቤተ ክርስቲያንን ያጠነክራታል፣ አያሌ ቅዱሳንንም ያስገኝላታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ‹ወደ አግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል› (የሐዋ.14፥23) ያለው ይሄንን ነው፡፡ የዓለም አስተሳሰብ ወደ መርከቧ ቤተ ክርስቲያን መግባት ከጀመረ ግን በመጨረሻ ውኃ በታንኳዪቱ ይሞላል፤ ቅዱስ ማርቆስ እንደገለጠውም ‹እስኪደፍናት ድረስ› ይደርሳል፡፡ በዚህ ውኃ ተደፍነው የቀሩ መርከቦችም አሉ፡፡ እናም የቤተ ክርስቲያን ዋናው የህልውና ጥያቄ - መርከቧ በውኃው ላይ ትሂድ ወይስ ውኃው በመርከቧ ላይ? የሚለው ነው፡፡ 
 
 
የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ቅድስና የሚወሰነው ውኃው ወደ መርከቧ እንዳይገባ በምታደርገው ተጋድሎ ነው፡፡ ውኃው ወደ መርከቧ ውስጥ የሚገባው ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በሚያጋጥማቸው የእምነት ጉድለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ክርስቶስ ማዕበሉን ከመገሠጹ በፊት ሐዋርያትን የገሠጻቸው፡፡ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናትና መምህራን የእምነታቸው ጥንካሬ ሲላላ፣ ማዕበሉ መጀመሪያ እነርሱን ይመታቸዋል፡፡ ቀጥሎም ቤተ ክርስቲያንን ይመታታል፡፡ ምንጊዜም በታሪክ ውስጥ ከውጭ ያሉ ኃይሎች ያለ ውስጥ ኃይሎች ርዳታ ውኃውን ወደ መርከቧ ለማስገባት ችለው አያውቁም፡፡ ሰይጣን ወደ ሔዋን የሄደው ገነት ለመግባት በምትችለው በዕባብ አድሮ ነው፤ ሰይጣን ክርስቶስን ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠው በጉባኤ ሐዋርያት ውስጥ በነበረው በይሁዳ በኩል ነው፤ ግኖስቲኮች የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ከፍልስፍና ጋር ሊቀላቅሉ የሞከሩት ወደ ክርስትና ገብተው መምህራን በሆኑ ሰዎች በኩል ነበር፡፡ እነ አርዮስ፣ ንስጥሮስና ሰባልዮስ የማዕበሉ የውስጥ ወኪሎች ሆነው ነው ቤተ ክርስቲያንን ሊደፍኗት ደርሰው የነበሩት፡፡ መስፍኑ ሶምሶን ‹በጥጃዬ ባላረሳችሁ፣ የዕንቆቅልሼን ትርጓሜ ባላወቃችሁ› ያለው ለዚህ ነበር(መሳ. 14፥18)፡፡ 
‹ተሐድሶ (Reformation) ሌላ ትርጉም የለውም› ይላል ሰርጌይ ላቭሮች ‹ተሐድሶ ማለት ውኃውን ወደ መርከቧ ማስገባት ማለት ነው፡፡ በምዕራቡ ዓለም ያደረገውም ይሄንኑ ነው፡፡ ቀደምት ክርስቲያኖች በየጉባኤያቱ እየወሰኑ የተከላከሉትን፣ ቀኖና ሠርተው ያገዱትን፣ መጻሕፍትን ወስነው የገደቡትን፣ ትውፊታቸውን አጽተው አናስገባም ያሉትን ማዕበል ወደ መርከቧ ውስጥ ማስገባት፡፡ የስሕተት መምህራን በቅዱሳት መጻሕፍት ስም ስሕተትን ማስተማር ሲጀምሩ ነው አበው የቅዱሳት መጻሕፍትን ቁጥር የወሰኑት፡፡ ከዚያም አልፈው በምዕራፍና በቁጥሮች ለክተው ያስቀመጡት፡፡ ዓላማው ማዕበሉን ማገድ ነው፡፡
 
‹ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ አራት ማዕበሎችን ሲከላከሉ ኖረዋል› ይላል ሰርጌይ ላቭሮቭ፡፡ የተሳሳተ ትምህርትን፣ ፍልስፍናን፣ ወገንተኝነትንና ፖለቲካን፡፡ እነዚህ አራቱ ማዕበሎች ለመግባት በቻሉ ጊዜ እንኳን ቶሎ ጠልቀው ያወጧቸው ነበር፡፡
ጌታችን እንዳስተማረን የተሳሳተ ትምህርት ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመግባት የሞከረው ከመጀመሪያው ነው፡፡ የስንዴውና የእንክርዳዱ ምሳሌ ይህንን ነው የሚያሳየን(ማቴ. 13፥24-30)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ገና በሕይወት እያለ ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ የተባሉ መናፍቃን እርሱ ስለ ትንሣኤ ሙታን ያስተማረውን ትምህርት ማጣመም ጀምረው ነበር(2ኛጢሞ. 2፥17)፡፡ ለዚህ ነበር የኤፌሶንን ቀሳውስት ‹እኔ ከሄድኩ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፤ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ ዐውቃለሁ› በማለት ያስጠነቀቃቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ የገለጠውን ‹ሺ ዓመትን› በተመለከተ የተሳሳተውን ትምህርት ለመጀመሪያ ጊዜ ማስተማር የጀመረው ቀሪንጠስ የተባለ መናፍቅ ነው፡፡ ቀሪንጠስ ይህን ትምህርት ማስተማር ሲጀምር ቅዱስ ዮሐንስ በምድር ላይ ነበር፡፡ የቀሪንጠስ የተሳሳተ ትምህርት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠውም ቅዱስ ዮሐንስ በነበረበት በኤፌሶን ከተማ ነው፡፡(1) ቀሪንጠስ ክርስቲያን አልነበረም፤ የግኖስቲኮች ትምህርት አቀንቃኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ፍልስፍናንና ክርስትናን ቀላቅሎ ያስተምር ነበር፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ 1ኛና 2ኛ መልእክቱን የጻፈው ልጆቹ ከዚህ ሰው ትምህርት እንዲቆጠቡ መሆኑን ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ በአንድ ወቅት ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በኤፌሶን የሚገኝ የሕዝብ መታጠቢያ ገንዳን ሲጎበኝ አንድ ሰው መጣና በዚያ ቀሪንጠስ እንደሚገኝ ነገረው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ደቀ መዛሙርቱን ‹ጣሪያው ተንዶ ሁላችንንም ሳይገድለን በፊት ፈጥነን ከዚህ ለቅቀን እንሂድ› አላቸው› ይባላል፡፡
ጌታ ጸራዊ(ጠላት)፣ ሐዋርያት ቢጽ ሐሳውያን፣ ሊቃውንትም መናፍቃን ያሏቸው የስሕተት መምህራን ማዕበሉን ወደ መርከቧ እንዳያስገቡ በትምህርት፣ በመጽሐፍና በዓለም አቀፍ ጉባኤያት አበው ታግለዋቸዋል፡፡ የኒቂያ፣ የቁስጥንጥንያና የኤፌሶን ጉባኤያት ዓላማ ውኃው ወደ መርከቧ እንዳይገባ፣ ገብቶም እንዳይደፍናት ለመከላከል ነበር፡፡ የውግዘታቸውም ምክንያት ወደ መርከቧ የገባው ውኃ ጥፋት ከማድረሱ በፊት ወደ ባሕሩ ለመመለስ ነው፡፡
 
መርከቧ በውኃ እንድትሞላ የሚያደርጋት ዋናው ምክንያት የማዕበሉ ብርታት ሳይሆን የአገልጋዮቹ የእምነት ጉድለት ነው፡፡ የቀደሙት አበው የስሕተት ትምህርቶችን ነቅተው በመጠበቅ ‹የማይተኙ እረኞች› ነበሩ፡፡ ቅዱስ ሄሬኔዎስ ‹በእንተ ኑፋቄ› አቡሊዲስ ዘሮም ‹መድፍነ ኑፋቄ›፣ የተሰኙ መጻሕፍትን የዛሬ 1700 አካባቢ የጻፉት ማዕበሉን ለመከላከል ነው፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረው የሰርምኔሱ ፖሊካርፐስ መርቅያን የተባለውን መናፍቅ ‹የሰይጣን የበኩር ልጅ› ይለው ነበር፡፡ እነ አባ ጊዮርጊስ ‹መጽሐፈ ምሥጢርን›ና ‹ፍካሬ ሃይማኖት›ን፣ በ17ኛው መክዘ የነበሩ አበው ‹መዝገበ ሃይማኖት›ንና ‹ከአፍርንጅ የምንለይበት›ን፣ እነ መልአከ ብርሃናተ አድማሱ ጀንበሬ ‹ኮኩሐ ሃይማኖት›ን፣ እነ አለቃ አያሌው ታምሩ ‹መች ተለመደና ከተኩላ ዝምድና›ን የጻፉት ማዕበሉን ለማቆም ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ይህንን ተጋድሎ ሲገልጠው በፍካሬ ሃይማኖት መጽሐፉ ማጠቃለያ ላይ እንዲህ ብሏል፡-
              ‹‹በዚህ ሃይማኖቴ መናፍቃን እያወገዙኝ እኔም እያወገዝኳቸው ዕድሜ ልኬን በዚህ ዓለም ኖርኩ፡፡
              የእግዚአብሔር ልጆች ከጋኔን ልጆች ጋር አንድነት ስምምነት የላቸውምና፡፡››
 
ሌላው ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመግባት ሲሞክር የሚኖረው ማዕበል ፍልስፍና ነው፡፡ ፍልስፍና ሃማኖትን እንደ አንድ ፍልስፍና ስለሚቆጥረው ከእርሱ ጋር መሳ ለመሳ መጓዝን ይፈልጋል፡፡ በዚህም የተነሣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ከፍልስፍና ጋር መቀላቀል የሚፈልጉ ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን ሲፈትኗት ኖረዋል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ሺ ጥያቄዎችን በማቅረብና የክርስትናን ትምህርት በፍልስፍና መርሖዎች በመተንተን ለማሳፈር ጥረዋል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ግኖስቲኮች ዋና ዓለማ የነበረው የአፍላጦናውያንንና(Platonisem) የሐዲሳን አፍላጦናውያንን (Neo Platonism) አስተምህሮ ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጋር ለመቀላቀል ያደረጉት ጥረት ነው፡፡ እንደ ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያና እንደ አርጌንስ ያሉት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም ፍልስፍናውን ከክርስትና ጋር ለማስማማት በሄዱት ርቀት ውድቀት ገጥሟቸዋል፡፡ ፍልስፍናናን ከቤተ ክርስቲያን የድኅነት ትምህርት ውስጥ ነቅሎ ያወጣው ሐዋርያዊው አትናቴዎስ ነው፡፡  
 
እንዲያውም ምዕራባውያን ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ የሚመጡትን ጥያቄዎች በሃይማኖታዊ መንገድ ከመመለስ ይልቅ ክርስትናውን ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር ማስማማትን መርጠዋል፡፡ እንደ ክርስቲያን ሳይንስ፣ የብልጽግና ወንጌል ያሉ አስተምህሮዎች የመጡትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ዓለምን ለቤተ ክርስቲያን ከማስገዛት ይልቅ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም እንድትገዛ አደረጓት፡፡ ወይም በሰርጌይ ላቭሮቭ አገላለጥ ‹ወንዙ በረሃውን ሊያጠጣ ሲገባው፣ በረሃው ወደ ወንዙ እንዲመጣ፣ በረሃማነትም እንዲስፋፋ ተደረገ፡፡ በረሃማነቱ ሲስፋፋም ወንዙን አደረቀው› ይላል፡፡ እንደ ግብረ ሰዶም ያሉትን ቤተ ክርስቲያን ወደ ውስጧ እንዳይገቡ ለዘመናት ስትከላከላቸው የኖረችውን ማዕበሎች ለማስገባት የተቻለው በዓለምና በቤተ ክርስቲያን መካከል ሊፈጠር የሚገባው አጥር ወደ ድልድይነት በመለወጡ ነው፡፡ ዛሬም ቤተ ክርስቲያን በእኩልነትና በመብት ስም ‹ውርጃን፣ የሴቶች ክህነትን፣ በፈቃድ መሞትን(Euthanasia) የሰው ዘርን ማዳቀልን(cloning)፣ እንድትቀበል እየተሞገተች ነው፡፡
 
‹አብዝኆ ፍኖት› (all roads) የተሰኘው ንቅናቄ ሃይማኖታዊ ሳይሆን ፍልስፍናዊ ነው፡፡ ይህ ‹በጠባቧ በር ግቡ› የተሰኘውን የወንጌል ትምህርት ንዶ ‹መንገዶች ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት ያደርሳሉ - all roads lead to heaven› ወደሚል የመጣው አስተምህሮ የስሕተት ትምህርቶችን ሁሉ ‹የአንድ ግብ ልዩ ልዩ መዳረሻዎች› አድርጎ የመመልከት አባዜ አለው፡፡ ይህ ግን ፍልስፍናዊ ወይም ሳይንሳዊ አስተሳሰብ እንጂ ሃይማኖታዊ አይደለም፡፡ ጌታችን በእርሱ በቀር ሌላ መንገድ መኖሩን አልነገረንም፤ በክርስቶስ አምኖና በእርሱ ሞትና ትንሣኤ በተገኘው ጸጋ ካልሆነ በቀር ሌላ መንገድ የለም፡፡ ክርስትና እምነቱ ይሄ ነው፡፡ በምሥጢረ ሥጋዌ በኩል ከተዘጋጀው መንገድ ውጭ ሌላ መንገድ የለውም፡፡ በክርስትና ውስጥ ያሉ ነገሮች ሁሉ በዚያ መንገድ ውስጥ የምናገኛቸው በረከቶች ናቸው፡፡  
 
መለካዊነት ከቀደምቶቹ የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች ወገን ነው፡፡ መለካዊነት የንጉሥ ፈቃድ ፈጻሚነት ነው፡፡ ወይም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርትና ሕይወት ለዘመኑ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ማስገዛት ማለት ነው፡፡ የሮም ነገሥታት ቤተ ክርስቲያንን ከውጭ ሆነው መርታት ሲያቅታቸው በክርስትና ስም ወደ ውስጥ ገቡ፡፡ ሐሳባቸውንና ርእዮታቸውንም የቤተ ክርስቲያን ለማድረግ ሞከሩ፡፡ አባቶች ግን አልተቀበሏቸውም፡፡ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት አብረው በሠሩባቸው ዘመናት ሁሉ ‹ኅብረት በተዐቅቦ› በተሰኘው መርሕ ነው አበው የተጓዙት፡፡ ተዐቅቦው የመንግሥታቱ አስተሳሰብ ወደ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት፣ ጸሎት፣ ሕይወትና ሥርዓት ውስጥ እንዳይገባ ነው፡፡ እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፣ እነ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣ እነ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ እነ ቅዱስ እጨጌ ፊልጶስ፣ እነ አቡነ አሮን፣ እነ አቡነ አኖሬዎስ፣ እነ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልና እነ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ፣ እነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ እነ አቡነ ተክለ ሐዋርያት፣ እነ አቡነ እንድርያስ ዘደብረ ሊባኖስ፣ እነ እጨጌ ዕንባቆም የመናዊ  መከራ የተቀበሉት ለዚህ ነበር፡፡ ‹ወንጌል ወደ ቤተ መንግሥት እንጂ፣ ቤተ መንግሥት ወደ ወንጌል አይግባ› ብለው፡፡  
 
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ከ13ኛው መክዘ ጀምሮ አገልጋዮቿን ለሁለት የከፈለው ለመለካዊነት የከፈሉት ዋጋ ነው፡፡ በአንድ በኩል ‹ኅብረት በተዐቅቦ› የተሰኘውን የቤተ ክርስቲያን መርሕ የተከተሉ ገዳማውያን አባቶች ሲፈጠሩ በሌላ በኩል ደግሞ ‹እንደ ንጉሡ አጎንብሱ› የሚሉ ካህናተ ደብተራ ተፈጠሩ፡፡ ገዳማውያን አበው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት፣ ሥርዓት፣ ጸሎት፣ አገልግሎትና ቅዱሳት መጻሕፍት ሲጠብቁ፤ ካህናተ ደብተራ ደግሞ የንጉሡን ክብር፣ ሥልጣንና አስተሳሰብ ይጠብቁ ነበር፡፡
የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት የተጻፉትና የተተረጎሙት፣ የጸሎት መጻሕፍት የተዘጋጁትና የተጠበቁት፣ ሥርዓታት የተዘጋጁትና የጸኑት፣ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሲሰጥ የኖረውና ወንጌል የተሰበከው፣ የቅዱሳን ሕይወትና ዜና ሲዘጋጅ የኖረው፣ የዝማሬና የቅዳሴ አገልግሎት የጸናውና የተጠበቀው በገዳማውያን አባቶች ነው፡፡ ለዚህም ነው በኢትዮጵያ ታሪክ ታላላቅ ቦታ ያላቸው እንደነ ዐፄ ይኩኖ አምላክ፣ ዐፄ ዳዊት፣ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ፣ ዐፄ በዕደ ማርያምና ዐፄ ናዖድን የመሳሰሉ ነገሥታት ከዕለት ማስተዋሻ ያላለፈ የቅድስና ማዕረግ ያላገኙት፡፡ በዛግዌ ነገሥታትና ‹ሰሎሞናውያን› በተሰኙት ነገሥታት መካከል የሥልጣን ሽኩቻው እያለ ቤተ ክርስቲያን ግን ከ‹ሰሎሞናውያኑ› ይልቅ ለዛግዌ ነገሥታት የቅድስና ማዕረግ የሰጠችው በእነዚህ ገዳማውያን አበው ምክንያት ነው፡፡        
 
ካህናተ ደብተራ ሥርዓት በመሥራት፣ ገድልና ድርሳን በመጻፍ፣ የጸሎትና የቅዳሴ መጻሕፍት በማዘጋጀት፣ ገዳማዊ ሕይወትን በማጽናትና የቤተ ክርስቲያንን የትምህርት መንገድ በመቅረጽ ቦታ አልነበራቸውም፡፡ እነርሱ ታሪከ ነገሥትና ዜና መዋዕል ሲጽፉ ነው የኖሩት፡፡ ዓላማቸውም ‹ርስት ሽልማት› ማግኘት ነው፡፡ አባ በጸሎተ ሚካኤል እንዲህ ብሎ የገሠጻቸው ለዚህ ነው ‹እናንተ ደብተራ ከምትባሉ በቀር ይህንን ሁሉ ያደረገ ማነው? ታመሰግኑታላችሁ፤ ታወድሱታላችሁ፤ እንዳንተ ያለ ኀያል ማነው ትሉታላችሁ፡፡ እንዳንተ ያለ ድል አድራጊ ማነው፣ እንዳንተስ ያለ ለጋሥ በሁሉ ዘንድ ወዴት አለ፣ እንዳንተ ያለ ምጽዋት ሰጭ የት አለ ትሉታላችሁ፡፡ እንዲህ ስታመሰግኑትም በኃጢአት ላይ ኃጢአት ይጨምራል፡፡›[2] ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ተጋድሎ በሁለቱ መካከል የሚደረግ ነው፡፡ 
 
ሰርጌይ ላቭሮቭ ‹ሁሉም ርእዮተ ዓለማቸው ይዘው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሮጣሉ፤ መድረኳን መዋቅሯንና ሥርዓቷን መጠቀም ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱን ደግፋ ሌላውን እንድትቃወም ይሻሉ፤ ዐውደ ምሕረቱን ዐውደ ፖለቲካ ያደርጉታል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የሰው ልጆች ጉዳይ እንጂ የርዕዮተ ዓለም ጉዳይ አይመለከታትም፡፡ ጸሎቷና አገልግሎቷም ለሰው ልጆች ሁሉ እንጂ ለአንድ ርእዮተ ዓለም ተከታዮች አይደለም፡፡ ይህን በማይረዱ ፖለቲከኞችና ይህን በማይረዱ የራስዋም ልጆች ግን ትፈተናለች፡፡ አንዳንድ ጊዜም ማዕበሉ ወደ መርከቧ ገብቶ እስኪደፍናት ድረስ ታላቅ መናወጥ ያመጣባታል› ይላል፡፡ 
 
አራተኛው ማዕበል ዘረኝነት ነው፡፡ ዘረኝነት ማለት ቤተ ክርስቲያንን ማጥበብ ነው፡፡ ‹ቤተ ክርስቲያን ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች›(ማቴ.13፥47) የተባለውን ትቶ አንድ ዓይነት ዓሣ ብቻ እንድትሰበስብ ማስገደድ ነው፡፡ ከአራቱ የቤተ ክርስቲያን መገለጫዎች አንዱ ኩላዊነት(Catholicity) ነው፡፡ ይህም ክርስቲያኖች የክርስቶስ አካላት በመሆናቸው በክርስቶስ አንድ ናቸው ብሎ ማመን ነው፡፡ አንድ ሰው ክርስቲያን ሲሆን የዚህ አንድነት ሱታፌ ይኖረዋል፡፡ ትውልዱ፣ ሀገሩ፣ ዘሩ፣ ቋንቋውና ቀለሙ ዋጋ አይኖራቸውም፡፡ ኩላዊነት ሁለት መልክ አለው አፍአዊና ውሳጣዊ፡፡ አፍአዊ መልኩ የቤተ ክርስቲያን መልክዐ ምድራዊ መስፋፋት ነው፡፡ እርሱ ግን ሁል ጊዜ አይገኝም፡፡ ለምሳሌ በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት ቤተ ክርስቲያን ያልደረሰችባቸው ቦታዎች ነበሩ፡፡ ያ ግን ኩላዊነቷን አይቀንሰውም፡፡ በመጨረሻው ዘመንም ‹እምነት ያለው ሰው ያንሳል›(ሉቃ. 18፥8)፡፡ ኩላዊነቷ ሁሉም ቦታ ላይ ከመድረስ አንጻር ሳይሆን ለሁሉም ቦታዎች ክፍት ከመሆን አንጻር የሚመጣ ነውና፡፡ ለሐዋርያትም የተሰጠው ትእዛዝ ‹አሕዛብን ሁሉ›(ማቴ. 28፥20) ተብሎ የተሰጣቸው ትእዛዝ በአንድ ጊዜ አልተፈጸመም፤ እስካሁንም ተሟልቶ አልተደረሰም፤ ምንጊዜም ግን ቤተ ክርስቲያን መንገድ ላይ ናት፡፡
 
 ሁለተኛው መልክ ደግሞ ውሳጣዊ ነው፡፡ እምነቷ፣ ሥርዓቷ፣ ሐዋርያዊ ትውፊቷና ትምህርቷ የሰውን ዘር ሁሉ ለማዳን የሚሠራ ማለት ነው፡፡ ለምታውቃቸው ብቻ ሳይሆን ለማታውቃቸውም ትጸልያለች፡፡ ወደ እርሷ ያልተጨመሩ፣ ከእርሷም የተነጠሉ ቢኖሩም እንኳን ኩላዊነቷን አያስቀሩትም፡፡ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ‹ኤቅሌሲያ ካቶሊኬ - Ekklêsia Katholikê - የሚለውን ቃል ሲጠቀሙ ‹በዓለም የተዳረሰች› ማለታቸው አይደለም፡፡ ከዓለም ሁሉ የላቀች ወይም ‹እንተ ላዕለ ኩሉ› ማለታቸው እንጂ፡፡ ከቡድኖችም፣ ከነጠላዎችም፣ ከስብስቦችም ሁሉ የላቀች፣ ከድምራቸውም በላይ የሆነች ማለት ነው፡፡ ሁሉን ለማካተት የምትችል - ቡድናዊነት፣ ንጣሌያዊነትና ግላዊነት (sectarian separatism and particularism) የሌለባት ማለት ነው፡፡ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም ኩላዊነት ማለት ‹የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ ምንም ሳይሸራርፉ ለሁሉም ፍጹም በሆነ መንገድ ማስተማር (katholikôs kai anelleipôs) ማለት ነው› ይላል[3]፡፡ ኩላዊነትን ለመልክዐ ምድራዊ ስፋት በመስጠት ካቶሊክ የሚለውን ‹ዓለም ዐቀፍ› ብለው የተረጎሙት የምዕራብ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ናቸው፡፡ ምክንያታቸውም አካባቢያዊ የሆነውን የዶናታውያንን[4] ትምህርት ለመቃወም ሲሉ ነበር፡፡ 
 
እነዚህ አራቱ ማዕበሎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመግባት ሲጥሩ ኖረዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም ተሳክቶላቸው ለመግባት ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን ‹እያንዳንዱ በሽታ የራሱን ሐኪም ያስነሣል› እንደሚለው የቻይኖች አባባል በየዘመናቱ ዐቃብያነ እምነት እየተነሡ ውኃው መርከቧን ከመድፈኑ በፊት ጌታቸውን ይቀሰቅሱታል፡፡ በተለይ ደግሞ ይህ ዘመን ዩኒቨርሳሊዝም(ሁሉም ትክክል ነው)፣ ሊብራሊዝም(እምነትን፣ ትውፊትንና ባሕልን ሁሉ ለሉላዊነት ሲሉ ማመቻመች)፣ እና ሴኩላሪዝም(ዓለማዊነት) የሠለጠነበት በመሆኑ የመርከቧን ከለላ ሰብሮ ውኃውን ለማስገባት የሚደረገው ዘመቻ ብዙም ከባድም ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ወደ ሮም ሲሄዱበት የነበረው መርከብ በማልታ ደሴት አጠገብ ያጋጠመውን ፈተና ሲነግረን ‹ከማዕበሉ ግፊያ የተነሣ መርከቡ ይሰበር ነበር› እንዳለው (የሐዋ. 27፥41) ማዕበሉ በዝቶና ጠንክሮ ቤተ ክርስቲያንን ሰብሮ እንዳይገባ ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ እነሆ ጥያቄው አንድ ነው - መርከቧ በውኃው ላይ ትሂድ ወይስ ውኃው በመርከቧ ላይ? 
[1] St. Eusebius of Caesarea, Church History, V.4,14,6


[2] አራቱ ኃያላን፣ ገጽ 162


[3] Catech. 18:23 (Migne P.G. XXXIII c. 1044)


[4] በሰሜን አፍሪካ በዛሬዋ አልጄርያና ቱኒዝያ የነበሩ መናፍቃን ናቸው፡፡

9 comments:

 1. Thank you, Dn Daniel.
  Very interesting and timely writing.
  May God bless you more abundantly.

  ReplyDelete
 2. ቃለ-ሕይወትን ያሰማልን! ፅሁፉ በጣም ወቅታዊ እና አስተማሪ ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ሰዎች ሁሉ እንዲያነቡት እናዳርስ!

  ReplyDelete
 3. ነገር ግን ‹እያንዳንዱ በሽታ የራሱን ሐኪም ያስነሣል› እንደሚለው የቻይኖች አባባል በየዘመናቱ ዐቃብያነ እምነት እየተነሡ ውኃው መርከቧን ከመድፈኑ በፊት ጌታቸውን ይቀሰቅሱታል፡፡

  ReplyDelete
 4. you are reily "GOD" of man !!!
  GOD blees you !!!

  ReplyDelete
 5. Very timely.

  This must be a core theme of preaching in every means.

  Please also deliver teaching on this topic at all levels.

  All the church leaders and workers must note of it and they should be awakened.

  ReplyDelete
 6. May God bless you for this reflection of yours. At the same time, I have a question for you and for all the audience on which I need some clarity. The Ethiopian Orthodox Church is getting more and more into money making schemes at the expense of the our last resting space. Recently I read on a newspaper that it is going to join the private financial industry launching a bank with other 22 share holders. I read in the bible how Jesus Christ reacted to the traders in the church. Is our church reforming (mutating)? How does our church define usury? Is interest usury if it is institutional> It is each of us who will stand judgement for our deeds; did you feed me when I was starved, did you clothed me when I was naked, is it not the 10% we have to give with which the chruch has to be administered with? Money corrupt our religious values. Please give me any verse in the bible that allow

  ReplyDelete
 7. እነሆ ጥያቄው አንድ ነው - መርከቧ በውኃው ላይ ትሂድ ወይስ ውኃው በመርከቧ ላይ? kale hiywet yasemalin D/n Daniel K.

  ReplyDelete
 8. Thank you Dn Daniel Kerbert

  i have got good knowledge. It add value on my current mindset

  ReplyDelete