Saturday, October 14, 2017

አብርሃ ወአጽብሐ


ክርስትና በአኩስም በፍሬምናጦስ ስብከት መሠረት ሲይዝ ዋናውን መሠረት የጣለው በቤተ መንግሥቱ ነው፡፡ ይህ በቤተ መንግሥቱ የነበረው ቦታ በአርኬዎሎጂ ቁፋሮዎችም በኢዛና ሳንቲሞች ላይ በተገኙት ስመ እግዚአብሔርና መስቀል ተረጋግጧል፡፡ በምሁራኑ ዘንድ አከራካሪው የመጀመሪያው ክርስቲያን ንጉሥ ማነው? የሚለው ነው፡፡ እስካሁን ያገኘናቸው የአርኬዎሎጂ ምርመራዎችና የድንጋይ ላይ ጽሑፎች የሚነግሩን ኢዛና የተባለ ንጉሥ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ክርስቲያን ንጉሥ መሆኑን ነው፡፡ ሀገራዊ መዛግብት ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያን ነገሥታት አብርሃና አጽብሐ መሆናቸውን ይገልጡልናል፡፡ ለመሆኑ አብርሃና አጽብሐ ማናቸው? የሚለውን በተመለከተ ሁለት ዓይነት መልሶች ተሰጥተዋል፡፡
1.      ‹‹አብርሃና አጽብሐ›› የሚለው ጥምረት በ6ኛው መክዘ አኩስምን የመራው የካሌብ(እለ አጽብሐ) እና የየመኑ የኢትዮጵያ ገዥ የነበረው የአብርሃ ስም በኋላ ዘመን የፈጠሩት የስሕተት ጥምረት ነው የሚለው የመጀመሪያው ነው፡፡ ይህን ለመቀበል የሚያስቸግር ነገር አለው፡፡ ካሌብም ሆነ አብርሃ በሀገራዊ መረጃዎች ላይ በሚገባ የተመዘገበ ታሪክ አላቸው፡፡ በታሪከ ነገሥቶቹና በገድለ ሀገረ ናግራን ዐፄ ካሌብም ሆነ የጦር አዛዡ አብርሃ ይታወቃሉ፡፡ መጀመሪያ በግእዝ በተጻፉት ገድለ ሰማዕታት ውስጥም የሀገረ ናግራን የሰማዕትነት ዜና ተጽፏል፡፡ እነዚህ ገድለ ሰማዕታት መነሻቸው ዘመነ አኩስም ነው፡፡ በመሆኑም ሁለቱን ነገሥታት በሚገባ በሚያውቁት የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊዎች ዘንድ ሁለቱ ስሞች ከመጀመሪያዎቹ ክርስቲያን ነገሥታት ስሞች ጋር ሊምታቱ አይችሉም፡፡

2.     አትናቴዎስን የተመለከተው የቆስጠንጢኖስ 2ኛ ደብዳቤ የተላከላቸው ‹‹ኢዛናና ሳይዛና›› የተባሉ የአኩስም ነገሥታት መሆናቸውን ቅዱስ አትናቴዎስ ለቆስጠንጢኖስ 2ኛ ክሶች ባዘጋጀው መልስ ላይ ገልጦታል[1]፡፡ ከሁለቱ ስሞች መካከል ኢዛና ንጉሥ መሆኑ በአርኬዎሎጂ ግኝቶችና በድንጋይ ላይ ጽሑፎች ተረጋግጧል፡፡ ሁለቱም በደብዳቤው ላይ በእኩል ደረጃ ከተጠሩ በእኩል ሥልጣን ላይ ነበሩ ማለት ነው፡፡ ቆስጠንጢኖስ 2ኛ በደብዳቤው ላይ ‹‹እናንተን የተከበራችሁ ወንድማማቾችን እግዚአብሔር ይጠብቃችሁ›› ይላል፡፡ በዚህም ወንደማማቾች መሆናቸውን ገልጧል፤ በመሆኑም በኋላ በክርስትና ስማቸው አብርሃ(አበራ)ና አጽብሐ(አነጋ) ተብለው የተጠሩት እነዚህ ሁለት ወንድማማቾች ናቸው፡፡
ከሁለቱ ምላሾች ሁለተኛው ከታሪክና ትውፊት ጋር የገጠመ ነው፡፡ አብርሃና አጽብሐ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያን ነገሥታት ናቸው፡፡ በዓላቸውም ጥቅምት 4 ቀን ይከበራል፡፡ የስማቸው ትርጉምም ለክርስትና ሀገራዊ ቦታ ከመስጠታቸው ጋር የተገናኘ ነው፡፡ አብርሃ (አበራ) የሚለው- የወንጌልን ብርሃን ማብራታቸውን፣ አጽብሐ(አነጋ) የሚለው ደግሞ ከጨለማ ወደ ብርሃን ማምጣታቸውን ያሳያል፡፡ በስማቸው የተሰየመ ገዳም አላቸው፤ ገድልም ተጽፎላቸዋል[2]፡፡ እንዲያውም በዘመነ አኩስም ከነበሩ ነገሥታት ገድል የተጻፈላቸው ብቸኛ ነገሥታት ናቸው፡፡ ምናልባትም በስማቸው ቤተ ክርስቲያን የተተከለላቸው ብቸኞቹ የአኩስም ነገሥታት ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ከ15ኛው መክዘ በፊት ጀምሮ ይኼ ታሪካቸው የታወቀ መሆኑን የሚያሳዩ መዛግብትም አሉ፡፡ አቡነ ተክለ ሐዋርያት ወደ አኩስም(ገበዘ አኩስም) በሄዱ ጊዜ የነገሥታተ አኩስም አብርሃ ወአጽብሐ ዐጽም በአኩስም እንደነበር ነግረውናል[3]፡፡ በአኩስም አካባቢ በተገኘው የኢዛና የድንጋይ ላይ ጽሑፍም ኢዛና ሐዴፋ እና ሳይዛና የተባሉ ወንድሞቹን ለጦርነት ልኳቸው እንደነበረ ይናገራል[4]፡፡ በገድለ ተክለ ሃይማኖት አብርሃና አጽብሐን በተመለከተ የተቀመጠው መረጃ በገድለ አብርሃና አጽብሐ የተቀመጠውን የሚመስል ነው፡፡ ምናልባትም የታሪኩ ምንጭ ገድሉ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ገድሉ በመግቢያው ላይ መጻሕፍትን ከዓረብኛ ወደ ግእዝ የተረጎሙ አባ ተክለ ሃይማኖትና አባ …..[5] የተባሉ አባቶች እንደጻፉት ይናገራል፡፡ ይህም ገድሉ የተጻፈው በመካከለኛው ዘመን ምናልባትም በአባ ሰላማ መተርጉም ጊዜ ሊሆን እንደሚችል እንድንገምት ያደርገናል[6]፡፡ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ(1426-1460ዓ.ም.) ለእንዳ አባ ገሪማ በሰጠው የተዝካር ትእዛዝ ላይ የገዳሙ አበው መታሰቢያ እንዲያደርጉላቸው ካዘዛቸው ቀደምት ነገሥታት መካከል ‹አብርሃና አጽብሐ› ይገኙበታል፡፡
በዘ፡ ንዜከር፡ ተዝካሮሙ፡ ለነገሥተ፡ ኢትዮጲያ፡ አመ፡ ፬ለጥቅምት፡ አብር
ሀ፡ ወአጽብሐ። አመ፡ ፴ለኅዳር፡ ገብረ፡ መስቀል። አመ፡ ፲ወ፪፡ ለመጋቢ
ት፡ ዐምደ፡ ጽዮን። አመ፡ ፲ወ፭፡ ለግንቦት፡ {ሰይፈ፡ አርዐደ።} አመ፡ ፳ወ፬
ለሰኔ፡ <> ;እንድርያድስ። አመ፡ ፳ወ፱ለዝ፡ ወርኅ፡ ቴዎድሮስ። አመ፡ ፲ወ፬ለ
መስከረም፡ ሕዝበ፡ ይናኒ። አመ፡ ፱ለጥቅምት፡ ዳዊት። አመ፡ ፳ወ፱፡ ለዝ፡
ወርኅ፡ ይስሐቅ።
ወዘይትገበርሂ፡ በኀበ፡ ፩ሥዩም፡ ፶ኅብስት፡ ወ፳ኮራ፡ ወክልኤሆሙ፡ ከማሁ፡
ዘንተሰ፡ በኀበ፡ ገባር። ወበኀበ፡ ቤቶሙሂ፡ በበ፡ ፬ኮራ፡ ወበበ፡ ፲ኅብስት።
ዘንተሰ፡ ዘሠርዐ፡ ዘርአ፡ ያዕቆብ፡ ንጉሠ፡ ሃይማኖት። ወእለ፡ ኢይገብሩ፡ ዘን
ተ፡ አማን፡ ዐላዊ[]ነ፡ ነገሥት።[7]

ይሄው ንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ በደረሰውና ‹እግዚአብሔር ነግሠ› በተሰኘው ቅዱሳንን ሁሉ ያመሰገነበት ድርስቱ አብርሃንና አጽብሐን በጥቅምት 4 ቀን እንዲህ አመስግኗቸዋል፡፡ 
ሰላም እብል ለአብርሃ ወአጽብሐ(ለአብርሃና አጽብሐ ሰላም እላለሁ)
በወርቅ ሐናጽያኒሃ (በወርቅ ላነጽዋት)
ለገበዘ አኩስም ትኩኖሙ ምክሐ (አኩስም ጽዮንን መመኪያ ትሆናቸው ዘንድ)
ድሙረ ነግሡ ወኢተባረዩ (ሳይለዋወጡ አንድ ሆነው ነገሡ)
በኦሪት አርወዩ በወንጌል አጽገዩ[8] (በኦሪት አጠጡ፣ በወንጌልም እንዲያብ አደረጉ)

አፄ ዘርዐ ያዕቆብ አብርሃና አጽብሐ አንድ ሆነው መንግሠቸውንና አኩስም ጽዮንን (በጥንት መዛግብተ ገበዘ አኩስም ትባል ነበር) ማነጻቸውን ትኩረት ሰጥቶታል፡፡ 

የአባ ጊዮርጊስ ደቀ መዝሙር የነበረው አርከ ሥሉስ ደግሞ ‹ውዳሴ ሰማያውያን ወምድራውያን› በተሰኘው የ15ኛው መክዘ ድርሰቱ ላይ በጥቅምት 4፡-
ሰላም ለአብርሃ ወለአጽብሐ ዘነበሩ (አንድ ሆነው ለነገሡ ለአብርሃና አጽሐ ሰላም አላለሁ)
በመንግሥት አሐቲ እንዘ ይትፋቀሩ(በአንዲት መንግሥት እየተፋቀሩ)
ለእለ ትካት ሰብእ በትእዛዘ ኦሪት ዘሖሩ(በኦሪት ትእዛዝ ለኖሩ ለቀደሙት ሰዎች)
ተሰብከ በአፉሆሙ ለወንጌለ ክርስቶስ ነገሩ( የክርስቶስ ወንጌሉ ነገር በአንደበታቸው ተሰበከላቸው)
ወበዕደዊሆሙ ካዕበ ተሐንጸት ማኅደሩ[9] (ማኅደሩ - አኩስም ጽዮን- በእጃቸው ታነጸች) 

አርከ ሥሉስ ደግሞ በዘመናቸው የተሰበከውን ወንጌል አንሥቶታል፡፡
ይላቸዋል፡፡ 
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ደግሞ በእግዚአብሔር ነግሠ ድርሰቱ 
አብርሃ ወአጽብሐ
ለገበዘ አኩስም ሐናጽያኒሃ (አኩስም ጽዮንን ያነጽዋት)
ለአሚን በክርስቶስ ዘኮኑ መርሐ (በክርስቶስ ለማመን መሪዎች ሆኑ)
ምግበ መንግሥቶሙ በጽድቅ አዕለው (የመንግሥታቸውን ዘመን በጽድቅ ፈጸሙ)
ለንጉሠ ነገሥት ሎቱ አድለው (ለንጉሠ ነገሥቱ (ለክርስቶስ) አስገዝተው)[10]
ይላቸዋል፡፡ 

ሦስቱም ሊቃውንት ክርስትና በዘመናቸው መሰበኩንና አኩስም ጽዮን መሠራቷን መስክረዋል፡፡
በረከታቸው ይደርብን፡፡[1] Saint Athnasius, Apology to The Emperor (Apologia ad Constantinum), Letter of Constantius to the Ethiopians against Frumentius.Chrstian classics Ethereal Library.
[2] ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ ገድሉን በ2008 ዓ.ም. በአማርኛ አሳትመውታል፡፡
[3] Conti Rossini, AGTA SANCTI TAKLA HAWARYAT,98
[4] ‹‹አፅሪሮ ሕዝበ ብጋ ፈኖነ አኀዊነ ሥዓዛና ወሐዴፋሃ ይጽብዕዎሙ›› Deutsche Aksum – Expedition, Band 4, 1913, p .10
[5] ጽሑፉ ግልጥ አይደለም
[6] በርግጥ በገድሉ ውስጥ ገድሉ የተጻፈው በአቡነ ሰላማ መሆኑን ይነግረናል፡፡ ይህ ግን ሊሆን አይችልም፡፡ አንደኛ በዚያ ዘመን የኢትዮጵያውያንን ገድሎች መጻፍ አልተጀመረም፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በአቡነ ሰላማ ዘመን መጻሕፍት ከግሪክ እንጂ ከዐረብኛ አይተረጎሙም ነበር፡፡
[7] የእንዳ አባ ገሪማ ወንጌል ‹Aethiopica 19 (2016)›, Getatchew Haile, The Marginal Notes in the Abba Gärima Gospels.
[8] EMML 3128 (የ15ኛው መክዘ ቅጅ ነው)
[9] በ17ኛው መክዘ የተጻፈ የመራዌ ክርስቶስ ገዳም(ትግራይ፣ ሽሬ) ቅጅ
[10] EMML 204, 98b

4 comments:

 1. egeziyabeher regem edemy endiste emgnalwu gen daniyel aned meteykhe teyaqi alegn bezun gizy mels yalagegnhubten newu set lej yewur abeba seat lay tsebl metmeqe dawit medgm betmeqds gibi wuset megebat techelalche wy

  ReplyDelete
 2. what kind of article.

  ReplyDelete
  Replies
  1. i rely sorry Dani i write it as negative but i found very nice.thanks a lot as usual.

   Delete
 3. Dear Daniel Kale hiywot yasemalin

  ReplyDelete