ሁሉ በሽተኛ ሁሉ ራሴን ባይ
በቤታችን ደኅና መጥፋቱ ነወይ
የሚል የበገና ዘለሰኛ አለ፡፡ አሁን
ያለችውን ሀገራችንን ቀድሞ ያየ ደራሲ መሆን አለበት የገጠመው፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ጤነኛ አካል የጠፋ ይመስላል፡፡ የገዛ ወገኑን
አባርሮ የሚፎክር ወገን፣ ሕዝብ እንዳይሰደድ የሚያደርግ አሠራርና አስተዳደር መዘርጋት ሲገባው ሲያባብስ ኖሮ ሕዝብ ሲሰደድ መጠለያ
ድረስ ሄዶ የሚጎበኝ ባለ ሥልጣን፣ የሀገሩን ሀብትና ንብረት አቃጥሎ በኩራት የሚደነፋ ጎረምሳ፤ ሕዝብን እያዋረደና እየተሳደበ መግለጫ
የሚሰጥ የክልል ሹም፤ ነገሩ ሁሉ እንዳይሆን እንዳይሆን ሲበላሽ እያየ መንገዱን ለመመርመር የማይፈልግ መንግሥት፤ ሀገር እየጠፋ
ግደል ተጋደል የሚል ተቃዋሚ፣ ለሌላው ይተርፋል ሲሉት የራሱ የሚያርበት የእምነት ተቋም፤ ጢሱ እንዳይነካው ተደብቆ ገሞራ ሊያስነሣ
የሚባዝን የማኅበራዊ ሚዲያ ተዋናይ፤ የሀገሪቱን መጻኢ ዕድል ሳይሆን የምእመኖቻቸውን የጫማ ቁጥር የሚተነብዩ ‹ነቢያት›፣ ምኑ ቅጡ
- ሁሉ በሽተኛ ሆኗል፡፡ በቤቱም ደኅና ጠፍቷል፡፡
ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት እየወደቅንም
እየተነሣንም፣ እየተቃቀፍንም እየተቧቀስንም፣ ሆ ብለን እየወጣንም አድፍጠን እየተቀመጥንም፤ እየተከፋፈልንም አንድ ለመሆን እየሞከርንም፤
እያሠርንም እየታሠርንም ለመጓዝ ሞክረናል፡፡ ማንም የአንድ ዓመት የልጅነት ልብሱን በሃያ ስድስት ዓመቱ አይለብስም፡፡ ኢትዮጵያም
እንዲያ ሆናለች፡፡ የዛሬ ሃያ ስድስት ዓመት የተሰፋው ልብሷ ጠቦ፣ ጠቦ፣ ጠቦ - እየተቀዳደደ ነው፡፡ ሊጣፍ፣ ሊሰፋ አይችልም፡፡
አሁን ሌላ ልብስ ያስፈልጋታል፡፡ ‹ሞኝ ማለት በተመሳሳይ መንገድ እየሄደ የተለየ ውጤት የሚጠብቅ ነው› ይባላል፡፡ የሀገሪቱን ችግሮች
ለመፍታት በአንድ ዓይነት መንገድ ብቻ ማላዘናችን አላዋጣንም፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ መንገድ ልንሞክር ግድ ነው፡፡