Thursday, September 28, 2017

አንዳንድ ነገሮች ስለ ግማደ መስቀሉ


ዳጋ የሚገኘው የግማደ መስቀሉ ክፋይ

ስለ ግማደ መስቀሉ አመጣጥ ግሼን በሚገኘው በመጽሐፈ ጤፉት የተጻፈውን ባለፉት ዘመናት ስናነበውና ስንሰማው ኖረናል፡፡ እስኪ ዛሬ ደግሞ ሌሎች ምንጮች ስለ ግማደ መስቀሉ አመጣጥ የሚነግሩንን ተጨማሪ ነገር እንፈትሽ፡፡
በ1394 ዓ.ም በሰኔ ወር ላይ የተለያዩ አስደናቂ ስጦታዎችን የያዙ የኢትዮጵያው ንጉሥ የዐፄ ዳዊት 2ኛ(1374-1406) የልዑካን ቡድን ቬነስ ደረሱ፡፡ ታላቁ የቬነስ ሪፐብሊክ ምክር ቤት መዛግብት በነሐሴ 15 ቀን በ1394 ዓም ከቄሱ ዮሐንስ (ፕሪስተር ጆን)[1] የተላኩ መልዕክተኞች እጅግ አስደሳች የሆኑ ስጦታዎችን ይዘው መምጣታቸውን መዝግቦታል፡፡ ከእነዚህ ስጦታዎችም መካከል አራት ዝንጉርጎር ነብሮችና መዓዛቸው ልዩ የሆኑ የከበሩ ድንጋዮች እንደሚገኙበት ያሳያል፡፡ ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ስጦታ ምላሽ ለመስጠት 1000 የወርቅ ገንዘብ (ዱኬቶች)[2]መድቦ ነበር፡፡ በነሐሴ 4 ቀን 1394 ዓ.ም. የኢትዮጵያዊው ንጉሥ መልእክተኞች ከልዩ ልዩ የቬነስ ባለሞያዎች ጋር ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ይሄው የቬነስ ሪፐብሊክ ምክር ቤት መዝገብ ያመለክታል፡፡
በ1394 ዓ.ም. ከተደረገው የቬነሱ የሳን ማርኮ(ቅዱስ ማርቆስ) መቅደስ ንብረት ቆጠራ መዝገብ ላይ አግኝተውት በ17ኛው መክዘ የገዳሙ አበ ምኔት የነበሩት ፎርቱናቶ አልሞ(Fortunato Olmo,) የገለበጡትን ዝርዝር ስንመለከተው ለኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ከተሰጡት ስጦታዎች መካከል አንድ ጽዋ ይገኝበታል፡፡ ይህ ጽዋ ከመዳብ፣ ብርና እርሳስ የተሠራ ሲሆን ከ12 ካራት የሚበልጡ የከበሩ ድንጋዮች የተጌጠ ነበር፡፡ ቀሪው የንብረት ዝርዝር አይነበብም፡፡ 


ከዚህ የቀረውን ታሪክ ደግሞ በ14ኛው መክዘ የተጻፈው የግብጽ ፓትርያርኮች ታሪክ ይነግረናል፡፡ በ1370 ዓ.ም. ወደ መንበረ ፓትርያርክ የመጣው አባ ማቴዎስ ከኢትዮጵያውያን ጋር ልዩ የሆነ ወዳጅነት አለው፡፡ እርሱ የደብረ ቁስቋም መነኮስ እያለ ከኢትዮጵያ በሰንበት ክርክር ምክንያት የተሰደዱትን አባ ኤዎስጣቴዎስን አግቷቸው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ መነኮሳት ሕይወት የተማረከው አባ ማቴዎስ ከእርሳቸው ጋር ለጥቂት ጊዜ ቆይቷል፡፡ በዚህ የተነሣ ገድለ አባ ኤዎስጣቴዎስ አባ ማቴዎስን ከእርሳቸው ደቀ መዛሙርት እንደ አንዱ ይቆጥረዋል[3]፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ አባ ሰላማ መተርጉም የተባለውንና በ1341 ዓም ወደ ኢትዮጵያ የመጣውን አባት የሾመው ይህ አባ ማቴዎስ ነው፡፡ አባ ማቴዎስ ዐፄ ዳዊት እንደሚነግሥ አስቀድሞ በመንፈስ ማወቁንና ይህንንም በመልዕከተኞቹ በኩል መላኩን  በግሼ ደብረ ከርቤ የሚገኘውና በዐፄ ዳዊት ዘመን የተጻፈው ተአምረ ማርያም ይነግረናል[4]፡፡ ይህም በዐፄ ዳዊትና በአባ ማቴዎስ መካከል የቆየ ግንኙነት መኖሩን ያሳያል[5]፡፡ አባ ማቴዎስ በአካባቢው ከነበሩ የልዩ ልዩ ሀገሮች ነጋዴዎች ጋር መልካም ግንኙነት ነበረው፡፡ በእርሱ ዘመን የነበረው የግብጽ ሡልጣንም በክርስቲያኖች ላይ የነበረውን ችግር አቃልሎ ነበር፡፡
 
ዳጋ የሚገኘው የዐፄ ሰይፈ አርዕድ ሰይፍ ሰገባ
ይህን የአባ ማቴዎስንና የአካባቢው መሪዎችን ግንኙነት የተመለከተው ዐፄ ዳዊት መልእክተኞቹን ወደ እስክንድርያ ልኮ ነበር፡፡ የእስክንድርያ ፓትርያርኮች ታሪክ እንደሚነግረን ‹የኢትዮጵያ ንጉሥ የፈረንጆች ነገሥታት ይህን አባት መውደዳቸውንና ታላላቅ ስጦታዎች እንደሰጡት ሲሰማ ከእነርሱ የሚበልጥ ስጦታ ለፈረንጆቹ ነገሥታት ላከላቸው፡፡ እንዲህም አላቸው ‹ይህንን ስጦታ የምልክላችሁ ተመጣጣኙን ፈልጌ አይደለም፡፡ በእጃችሁ የሚገኘውን የጌታችንን ግማደ መስቀል ፈልጌ ነው እንጂ›፡፡ ይህ መልእክት ወደ ፈረንጆቹ ንጉሥ በደረሰ ጊዜ በተላከለት ስጦታ እጅግ ተደሰተ፡፡ ከእነርሱ ስጦታ የሚበልጠውን ታላቅ ስጦታም ላከለት፡፡ እርሱም በቤተ መዛግብቱ ውስጥ የነበረው ግማደ መስቀሉ ነው፡፡ ያንንም ግማደ መስቀል በወርቅ በተሠራ ሌላ መስቀል ውስጥ ከተተው[6]፡፡ የወርቁም መስቀል በልዩ ልዩ የከበሩ ድንጋዮች ያጌጠ ነበር፡፡ ሄሮድስ ከገደላቸው ሕጻናትም የአንዱን ዐጽምም አብሮ አደረገ፡፡ እነዚህንም ሁሉ በማኅደር ውስጥ አስቀመጠ፡፡ ከእነርሱም ጋር ለነገሥታትና ለካህናት የሚገቡ የወርቅና የብር ንዋያተ ቅድሳትን አደረገ፡፡ ከንዋያተ ቅድሳት በአንዱም የአባ ማቴዎስን መልክ አሳለበት፡፡ ይህንንም ለ(አባ ማቴዎስ ላከለት)፡፡
… የጌታችን ግማደ መስቀል እና በሄሮድስ የተገደለው ሕጻን ዐጽም ኢትዮጵያ ውስጥ በደረሱ ጊዜ ጻድቁ ንጉሥ ስጦታዎቹን ተመልክቶ ተደነቀ፡፡ ዘውዱንም ከራሱ አወረደ፡፡ ለአንድ ሰዓትም ያህል ሰግዶ ቆየ፡፡ ከዚያም ቀና አለና የተላከለትን የቅዳሴውን ልብስ ተመለከተ፡፡ በዚያም ልብስ ላይ የአባ ማቴዎስ ሥዕል ነበረበት፡፡ እጅግም ደስ አለው፡፡ እግዚአብሔርንም አመሰገነው፡፡ ከመሞቱ በፊት የዚህን አባት ሥዕል በሀገሩ አግኝቷልና፡: አስቀድሞ ስለ እርሱ ንግሥና በተናገረለት ትንቢት ምክንያት መልኩን ሊያየው ይወድ ነበርና[7]፡፡
በግሼን በሚገኘውና በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በተጻፈው መጽሐፈ ጤፉት ላይ እንደተጻፈው ግማደ መስቀሉ ከኢየሩሳሌም ወደ ግብጽ፣ ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል፡፡ ዐፄ ዳዊት ከፈረስ ላይ ወድቀው ጥቅምት 9 ቀን 1406 ዓም በማረፋቸው ግማደ መስቀሉን የተቀበሉት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ናቸው፡፡ 
Schatzkammer, Viena የሚገኘው የመስቀሉ ክፋይ

እነዚህን ሁለት መረጃዎች ስንመለከት ሁለት ነገር እንድንጠይቅ እንገደዳለን፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ ይሆን ግማደ መስቀሉ የመጣው? ወይስ ሁለቱም መዛግብት ስለ አንድ ታሪክ በተለያየ አተራረክ ይነግሩናል? እስካሁን ድረስ መስቀሉ ለተለያዩ ዓለም ክርስቲያኖች እየተከፈለ ሲሰጥ እንደነበር እንጂ ለአራት ተከፍሎ ለተለያዩ ነገሥታት ስለመሰጠቱ የሚተርክ መዝገብ የለንም፡፡ የኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ቄርሎስም በ348 ዓም በጻፈው ድርሳኑ ላይ ‹መላው ዓለም በጌታችን መስቀል ክፍልፋዮች ተሞልቷል› ብሎ ጽፎ ነበር[8]፡፡ ዕሌኒ ሮማዊት በመሆኗና በ8ኛው መክዘ ከፋርሶች ጋር ተዋግቶ መስቀሉን ያስመለሰውም የባዛንታይሙ ንጉሥ ሕርቃል በመሆኑ የመስቀሉ ክፍልፋዮች ወደ አውሮፓ ተጉዘዋል፡፡ የቬነሱ ንጉሥም ወደ ኢትዮጵያ በእስክንድርያ በኩል ልኮልናል፡፡ በኢትዮጵያ ጥንታውያን መዛግብት ኢየሩሳሌም ማለት ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኝ የክርስቲያን ሀገር ማለት ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ ፍሬምናጦስን ‹ከኢየሩሳሌም የመጣ› ይለዋል፡፡ በመሆኑም ግማደ መስቀሉ ከኢየሩሳሌም መጣ ሲል ከክርስቲያን ሀገር መጣ ማለቱ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ታሪክ የሚደግፉ ሀገራዊ መዛግብትም ይገኛሉ፡፡ ታላቋ የተድባበ ማርያም ደብር ከግማደ መስቀሉ ጋር አብረው የመጡ ንዋያት ከሚገኙባቸው አድባራት አንዷ ናት፡፡ በተደባበ ማርያም መዝገብ ላይ እንደተጻፈው የ75 ቅዱሳን ተረፈ ዐጽም ወደ ደብሯ መጥቷል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ በሄሮድስ የተሠዉ ሕጻናት ተረፈ ዐጽም ነው[9]፡፡ ተድባበ ማርያም የቀደምት ነገሥታትን ንዋያት ከምናገኝባቸው አድባራት አንዷ ናት፡፡ ከእነዚህ አንዱ የዐፄ ዳዊት ዙፋን ነው፡፡ እስካሁን ግን ጽዋው የት እንዳለ አልታወቀም፡፡ ፍለጋችን ይቀጥላል፡፡ 
 
ስፔይን የሚገኘው የመስቀሉ ክፋይ
ታድያ በግሼን ማርያም ዛሬ የምናገኘው ግማደ መስቀል ታሪኩ እንዴት ነው? ዐፄ ዳዊት ከግሼን ደብረ ከርቤ ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበራቸው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ መጀመሪያ ከዐረብኛ ወደ ግእዝ የተተረጎመው ተአምረ ማርያም የሚገኘው ግሼን አምባ ነው፡፡ በዚያ ተአምረ ማርያም ላይ የዐፄ ዳዊትም ሥዕል ይገኛል፡፡ይህንን አስጽፈው የሰጡት ራሳቸው ንጉሡ ናቸው፡፡ በመሆኑም በእርሳቸው ዘመን የመጣውን ግማደ መስቀል ልጃቸው ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ በተለያዩ የሀገሪቱ ቦታዎች ለማስቀመጥ ከሞከሩ በኋላ በመጨረሻ በግሼ ማርያም ዋናውን ግማደ መስቀል አስቀምጠውታል፡፡ ዐፄ ዳዊት ያመጡትን ግማደ መስቀልና ሌሎች ንዋያት ልጃቸው ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ በአንድ ቦታ ብቻ ያስቀመጡት አይመስልም፡፡ ከአባታቸው ጋር መልካም ግንኙነት ለነበራቸው አድባራት አካፍለውታል፡፡ 

ዐፄ ዳዊት ወንድማቸውን ዐፄ ንዋየ ማርያምን(1364-1374) ገልብጠው ሲነግሡ ሕዝቡ በሁለት መልኩ ነበር የተቀበላቸው፡፡ የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንና የሰሜን ኢትዮጵያ ገዳማት ድርጊቱን ተቀብለውታል፡፡ መንግሥቱ ለዐፄ ዳዊት እንጂ ለንዋየ ማርያም አይገባም ብለው ያምኑ ነበር፡፡ የአባ ማቴዎስ ትንቢትና የላኩት መልእክትም ይህንን ያሳያል፡፡ በደብረ ሊባኖስ የነበሩት አበ ምኔት እጨጌ ቴዎድሮስ ግን ይህን ድርጊት አልተቀበሉትም፡፡ እንዲያውም ዐፄ ዳዊትንና እኅታቸውን ድል ሳፋን አውግዘዋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከንጉሥ ዓምደ ጽዮን የጀመረው የደብረ ሊባኖስና የቤተ መንግሥቱ አለመግባባት ቀጠለ፡፡ ይህ ችግር የተፈታው በእጨጌ ዮሐንስ ከማ ጊዜ በዐፄ ይስሐቅ ዘመን(1406-1421) ነው፡፡ 

በችግሩ ምክንያት ዐፄ ዳዊት ከሸዋ ገዳማት ጋር የነበራቸው ግንኙነት በማቆም ወደ ጣና ገዳማት አዞሩት፡፡ በተለይም ወደ ክብራን ገብርኤልና ዳጋ እስጢፋኖስ፡፡ ዐፄ ዳዊትም የአባታቸው ተዝካር ያወጡ የነበረው በክብራን ገብርኤልና በሌሎች የጣና ገዳማት ነበር፡፡ በክብራን ገብርኤል ወንጌል ላይ በ1404 ዓ.ም. እንዳስጻፉት የአባታቸውን የዐፄ ሰይፈ አርዕድን ተዝካር ግንቦት 15፣ የእናታቸውን የእቴጌ ለዘብ ወርቃን ደግሞ ሰኔ 12 እንዲያደርጉላቸው ክብራኖችን አዘው ነበር[10]፡፡ በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ከግማደ መስቀሉ የተወሰኑትን ክፋዮች ወደ ዳጋ እስጢፋኖስ የላኩት፡፡

እነዚህ ወደ ዳጋ የተላኩት የግማደ መስቀሉ ክፋዮች ልክ ከቬነስ እንደመጣው ግማደ መስቀል ሁሉ በተቦረቦረ መስቀል ውስጥ የገቡ ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ ግማደ መስቀሉን ማስቀመጥ በጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት የታወቀ መሆኑን በስፔን ሌባና ቅዱስ ቶሪቦ[11]፣ በፈረንሳይ ኖትረ ዳሜ እና በቫቲካን የሚገኙ የመስቀሉ ክፍልፋዮች አቀማመጥ ማስረጃ ነው፡፡ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ትልቁን ግማደ መስቀል በግሼን አስቀምጠው ለአንዳንድ አድባራት ግን ለበረከት መስጠታቸውን የዳጋው ምስክር ነው፡፡ አሰጣጣቸውንም ስናይ ልክ ከቬነስ በመጣበት መልክ ነው፡፡ ዳጋ ውስጥ ከግማደ መስቀሉ ክፋዮች በተጨማሪ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ አማካኝነት የተሰጡ ነጋሪት፣ ሰይፍና መስቀሎችም አሉ፡፡ በላያቸውም ላይ በዐረብኛና በቅብጥ የተጻፈ ጽሑፍ አለባቸው[12]፡፡የጌታችንን መስቀል ክፋዮች ንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ዋናውን በግሼን ተራራ ቀብረውታል፡፡ ያን ባያደርጉ ኖሮ ከግራኝ ጥፋት ባልተረፈ ነበር፡፡ የጌታችንን መስቀል በዓይኑ ለማየት የሚወድ የኔ ቢጤ ቢኖር ግን ያለው አማራጭ ዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም መጓዝ ብቻ ነው፡፡ ዳጎችም ይህንን ታላቅ ቅዱስ ንዋይ ሙዝየም ውስጥ ከሚያስቀምጡት ‹መስቀል ቤት› ተሠርቶለት በክብር ተቀምጦ፣ እየታጠነ እንድንሳለመው ቢያደርጉ መልካም ነበር፡፡


[1] በመካከለኛው ዘመን የአውሮፓ ሰዎች የኢትዮጵያን ነገሥታት የሚጠሩበት ስያሜ
[2] 3.545 ግራም ወርቅ የያዘ የቬነስ የጥንት ገንዘብ
[3] Conti Rossini, Il Gadla Filipos e il  Gadla Yohannes, 115
[4] EMML 9002, 285
[5] ኢትዮጵያ ውስጥ በግእዝ ገድል የተጻፈላቸው ብቸኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ አባ ማቴዎስ ናቸው፡፡
[6] በወርቅ የተሠራው መስቀል ውስጡ ክፍት ነው፡፡ ግማደ መስቀሉን የከተተው በዚያ ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳውም በሌሎች ዓለማት እንደምናየው በተመሳቀለ መልኩ ነው የተቀመጠው ማለት ነው፡፡
[7] HISTORY OF THE PATRIARCHS OF THE EGYPTIAN CHURCH KNOWN AS THE HISTORY OF THE HOLY CHURCH BY SAWIRUS IBN AL-MUKAFFA` BISHOP OF AL-ASHMUNIN, VOLUME III., PART III, CYRIL III — CYRIL V (A. D. 1235-1894) , PP. 249-53
[8] Nicene and Post Nicene Fathers, 2-07, Cyril of Jerusalem, Gregory Naizanzen.
[9] Diana Spencer, In Search of St. Luke Ikons in Ethiopia, Journal of Ethiopian studies, Vol. X, No. 2,p.77
[10] EMML 8308,f235a
[12] ትርጉማቸውን እያፈላለግኩ ነው፡፡

10 comments:

 1. በጣም እናመሰግናልን የአገገልግሎት ዘመንህን ያርዝምልን!!

  ReplyDelete
 2. WEDAJE DANI AMLAKE KIDUSAN YITEBIKIH BETAM EWEDIHALEHU!!!

  ReplyDelete
 3. ስለመስቀሉ የጎደለኝን የሞላሁበት ፅሁፍ ነው፡፡ ወንድሜ ቃለ-ሕይወትን ያሰማልን!! በረከትን ያብዛልህ!!

  ReplyDelete
 4. ዳንኤል አምላከ አበው ይጠብቅህ ምሉዕ ሰው ያድርግህ እረጅም እድሜን ከአገልግሎት ጋር ያድልልን፡፡ ከከበሮ ባነሰ እንደ በርሚል ባዶ የሆነውን ነገር ግን መጣም የምናደቁረውን የዕምነታችን ፍሬዎች በአግባቡ አውቀን ሀይማኖታችንን እንድንጠብቅ እግዚአብሄር ይርዳን አሜን፡፡

  ReplyDelete
 5. በጣም ጥሩ መረጃ ነው በአባቶች ተጸልዮ እንዲወጣ አይደረግመም፡፡

  ReplyDelete
 6. በጣም ጥሩ መረጃ ነው በአባቶች ተጸልዮ እንዲወጣ አይደረግመም፡፡

  ReplyDelete
 7. Dani PDF yelem? Betam bizu alefen eko.

  ReplyDelete
 8. የክርንስትያን አምላክ ይባርክM የበለጠ አይነ ልቡናህን ያብራልሕ እኛንም በምናገኘው ነገር ይለውጠን፡፡

  ReplyDelete