ዳጋ የሚገኘው የግማደ መስቀሉ ክፋይ |
ስለ ግማደ መስቀሉ አመጣጥ ግሼን በሚገኘው በመጽሐፈ ጤፉት የተጻፈውን
ባለፉት ዘመናት ስናነበውና ስንሰማው ኖረናል፡፡ እስኪ ዛሬ ደግሞ ሌሎች ምንጮች ስለ ግማደ መስቀሉ አመጣጥ የሚነግሩንን ተጨማሪ
ነገር እንፈትሽ፡፡
በ1394 ዓ.ም በሰኔ ወር ላይ የተለያዩ አስደናቂ ስጦታዎችን የያዙ የኢትዮጵያው
ንጉሥ የዐፄ ዳዊት 2ኛ(1374-1406) የልዑካን ቡድን ቬነስ ደረሱ፡፡ ታላቁ የቬነስ ሪፐብሊክ ምክር ቤት መዛግብት በነሐሴ
15 ቀን በ1394 ዓም ከቄሱ ዮሐንስ (ፕሪስተር ጆን)[1]
የተላኩ መልዕክተኞች እጅግ አስደሳች የሆኑ ስጦታዎችን ይዘው መምጣታቸውን መዝግቦታል፡፡ ከእነዚህ ስጦታዎችም መካከል አራት ዝንጉርጎር
ነብሮችና መዓዛቸው ልዩ የሆኑ የከበሩ ድንጋዮች እንደሚገኙበት ያሳያል፡፡ ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ስጦታ ምላሽ ለመስጠት
1000 የወርቅ ገንዘብ (ዱኬቶች)[2]መድቦ
ነበር፡፡ በነሐሴ 4 ቀን 1394 ዓ.ም. የኢትዮጵያዊው ንጉሥ መልእክተኞች ከልዩ ልዩ የቬነስ ባለሞያዎች ጋር ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን
ይሄው የቬነስ ሪፐብሊክ ምክር ቤት መዝገብ ያመለክታል፡፡
በ1394 ዓ.ም. ከተደረገው የቬነሱ የሳን ማርኮ(ቅዱስ ማርቆስ) መቅደስ
ንብረት ቆጠራ መዝገብ ላይ አግኝተውት በ17ኛው መክዘ የገዳሙ አበ ምኔት የነበሩት ፎርቱናቶ አልሞ(Fortunato
Olmo,) የገለበጡትን ዝርዝር ስንመለከተው ለኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ከተሰጡት ስጦታዎች መካከል አንድ ጽዋ ይገኝበታል፡፡ ይህ ጽዋ
ከመዳብ፣ ብርና እርሳስ የተሠራ ሲሆን ከ12 ካራት የሚበልጡ የከበሩ ድንጋዮች የተጌጠ ነበር፡፡ ቀሪው የንብረት ዝርዝር አይነበብም፡፡