Thursday, July 6, 2017

በዓለ ወልድ የማነው?


አራት ኪሎ ከቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አጠገብ የሚገኘው የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ‹ልማት ላለማ ነው› ብሎ በዚያ ያረፉ ክርስቲያኖችን ዐጽም አንሡልኝ እያለ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የፕሮፌሰር ዐሥራት ወልደየስን፣ ቀጥሎ የመልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬን አሁን ደግሞ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ዐጽም አንሡ ብሏል፡፡ ለመሆኑ በዓለ ወልድ የማን ነው?
 
ለፕሮፌሰር ዐሥራት የማይሆን በዓለ ወልድ የማን ነው? ከልጅነታቸው ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ያደጉ፣ ቤተ መቅደሱን ያገለገሉ፣ በሕክምና ሞያቸው ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ እስከ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ያከሙ፣ አያሌ ጳጳሳትንና መነኮሳትን በየጊዜው እቤታቸው ድረስ እየመጡ ሲረዱ የነበሩትን የሕክምና ሰው እንደ ባዕድ ቆጥሮ ‹አንሥቼ ወደዚያ አደርጋቸዋለሁ› አለ፡፡ ገና ለገና ከዘመኑ ጋር አይስማሙም፣ በእርሳቸው ጉዳይ መንግሥት አይቆጣንም ብለው ካልሆነ በቀር የፕሮፌሰሩ ውለታ ጠፍቷቸው አልነበረም፡፡ ቀድሞውንም አቡነ ጳውሎስ ፖለቲካው ተጭኗቸው እንጂ ለጥላሁን ገሠሠ የሰጡትን የሥላሴ ቦታ ለፕሮፌሰር ዐሥራት መንፈግ አልነበረባቸውም፡፡ በርግጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዋሉባት እንጂ ለዋሉላት መሆን ካቆመች ቆየች፡፡


የፕሮፌሰር ዐሥራትን ጉዳይ ፓርቲዎቹ ጉዳየ ብለው በክብር አስፈጸሙት፡፡ ይመሰገናሉ፡፡ ፓርቲ አልባውን መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬንና ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ግን እንደ ተራ ነገር አንሡልኝ አለ አስተዳደሩ፡፡ ቤተ ክህነቱም አያገባኝም ብሎ ዝም አላቸው፡፡ ለመሆኑ በዓለ ወልድን የሊቀ ሥልጣናቱ ብቻ ያደረገው ማነው? እነዚህ ዛሬ ተነሡ የሚሏቸው ሰዎች እኮ ናቸው በዓለ ወልድን የሠሩት? ምእመኑን በእምነቱ አጽንተው እናንተ የሚከፈላችሁን ደመወዝ እንዳይቋረጥባችሁ ያደረጉት? ለመሆኑ አድማሱ ጀንበሬ የቤተሰቦቻቸው ናቸው? የደብሩ ካህናትና የሊቀ ሥልጣናቱ አይደሉም? ሲያስተምሩና ሲያገለግሉ የኖሩት፣ ሲጽፉና ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ጋር ሲታገሉ የኖሩት ለቤተሰቦቻቸው ርስት ጉልት ለማሰጠት ነው? ኮኩሐ ሃይማኖት የተጻፈው ለቤተሰብ ነው? አድማሱ ጀንበሬ የቤተሰቦቻቸው ከሆኑ ነገ ያሬድም፣ አባ ጊዮርጊስም የቤተሰቦቻቸው ናቸው ልትሉን ነው?   

እኒህ ሰውኮ የቤተክርስቲያን ከዚያም ሲያልፍ የሀገር ሀብት ናቸው፡፡ መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬኮ ሙት ያስነሡ ‹ቅዱስ› ናቸው፡፡ በሙት ዘመን ተፈጥረው ቅድስናቸውን የሚያውቅላቸውና የሚያውጅላቸው ጠፋ እንጂ፡፡ ታዋቂነት እንጂ ዐዋቂነት ክብር የማይሰጥበት ጊዜ ሆነ እንጂ ከአትናቴዎስና ከቄርሎስ የሚስተካከሉ ሊቅ ናቸው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን የሚነሡ አልነበሩም፤ ቤተ ክርስቲያን የሚሠራላቸው ነበሩ እንጂ፡፡ በምን ሂሳብ ነው ‹ቤተሰቦቻቸው መጥተው አጽሙን ያንሡልን› የሚባለው፡፡ ለመሆኑ ለመልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬ ክብርና ፍቅር የሌለው ሰበካ ጉባኤ ሃይማኖቱ ምንድን ነው? ደብሩስ የማነው?

የእኒህ አባት ዐጽም የግድ ይፍለስ ከተባለኮ በቤተ ክርስቲያን የፍልሰተ ዐጽም ሥርዓት አለ፡፡ የነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ የነ አቡነ ፊልጶስ፣ የነ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል፤ ከውጮቹም የነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዐጽም እንዴት እንደ ፈለሰ ከካቴድራሉ ዕቃ ቤት ያሉት መጻሕፍት በዝርዝር ያስረዱናል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ የት ሄዶ ነው የአንድ ደብር አስተዳዳሪ የኒህን ቅዱስ ሰው ዐጽም ‹አንሡ፣ ውሰዱ› የሚለው? ወይስ ዮሴፍን የማያውቅ አዲስ ፈርዖን መጣ?

ቤተ ክህነቱ መጽሐፋቸውን አሳትሞ ከመሸጥ ውጭ አያገባውምን? ዛሬ በመልአከ ብርሃናት አድማሱ ላይ እንዲህ ከተደረገ ነገ የየአንዳንዱ ጳጳስና ካህን ፋንታ ዕጣ ከዚህ የከፋ መሆኑን ረሳው? ዛሬ በበዓለ ወልድ የተጀመረው ነገር ሃይ የሚለው ካጣ ወደ ካቴድራሉ ተዛምቶ የማን ዐጽም እንደሚነሣ መንግሥትስ ጠፋው?

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ የተማሩት በዚህች ቤተ ክርስቲያን፣ የደከሙት ለዚህች ቤተ ክርስቲያን፣ ያገለገሉት ሀገራቸውን ኢትዮጵያን - እንዴት ባለ ሂሳብ ነው አዲስ አበባ ለቴአትሩ ንጉሥ ቦታ የላትም ተብሎ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ዐጽሙ ይሂድ የሚባለው? ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ መቀበርም የሚቻለው በክልላችሁ ነው ልትሉን ነው? ዮፍታሔ ንጉሤ የደብረ ኤልያስ ብቻ ናቸው? ይህቺ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ያበረከትሺውን ሰው ጥቀሽ ስትባል ከምትጠቅሳቸው ተርታ አይደሉምን? ይህ ለትውልዱ እየሰጠነው ያለው ትምህርት የት የሚያደርስ ነው?

መሐል ሠፋሪ ጦር ጃንሜዳ እየተሰበሰበ አንዴ እቴጌ ጣይቱ ከቤተ መንግሥት ይውጡ፣ አንዴ ሚኒስትሮቹ ይነሡ ሲል፣ መኳንንቱም እየተቀበሉ ሲያስፈጽሙ፣ እቴጌ ጣይቱ ‹ለዚህ ጦር ክፉ ትምህርት አታስተምሩት፣ ካልሆነ ሁላችሁንም ያወርዳችኋል› ብለው ነበር፡፤ ሰሚ አልተገኘም፡፡ ያው ጦር ግን በ66 ዓም ንጉሡንም መኳንንቱንም አወረደ፡፡ ያውም እንደ እቴጌ ጣይቱ ወደ እንጦጦ አልላካቸውም ፣ ወደ እንጦሮጦስ እንጂ፡፡ ዛሬም ለዚህ ትውልድ ክፉ ትምህርት ባታስተምሩት መልካም ነው፡፡ ዐጽም እያሽቀነጠሩ ሱቅና አዳራሽ መሥራት ነገ በዐጽመ ቅዱሳን መወጋትን ያመጣል፡፡ ሲሠራና ሲታደስ ገንዘብ ካላመጣችሁ የምትሉን ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲህ ደስ ሲላችሁ ዐጽማችንን የምትወረውሩበት ከሆነ በዓለ ወልድ የማነው? ብለን እንጠይቃለን፡፡

በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቅጽር ውስጥ የሰንበት ትምህርት ቤቱ ሕንጻ እየሠራ ነው፡፡ ከሕንጻው አጠገብ አንድ አምስት መቃብሮች አሉ፡፡ አንዱ የጣልያን ወታደር፣ ሌሎቹ የኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት እነዚህን ዐጽሞች እግር ከሚጠቀጥቃቸው በክብርና በሥርዓት አንሥተን በተገቢው ቦታ እናድርጋቸው፣ ብለው ጠየቁ፡፡ ቤተ ክህነቱ የሰጠው መልስ ግን አስገራሚ ነበር፡፡ ‹ከመቃብሮቹ መካከል የኢትዮጵያውያንን እንደፈለጋችሁ ማንሣት ትችላላችሁ፤ የጣልያኑን መቃብር ግን እኔ መፍቀድ አልችልም› አላቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለጣልያን ወታደር የምትሰጠውን ቦታ ያህል ለአድማሱ ጀንበሬና ለዮፍታሔ ንጉሤ የላትም?

ዛሬ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ
ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ
ይሉ ነበር፡፡  


24 comments:

 1. እግዚያብሔር ያክብርህ ወንድሜ። ሰው በጠፋበት ሰዓት ሰው ሆነው ከተገኙ ከጥቂቶች አንዱ ነህ። ለቅድስት ቤተክርስቲያን ለህጓ ለስርዓቷ፤ ለአገር፤ ለወገን፤ ለፍትህ ትሟገታለህ። ብዙ ታላላቆችህ መምህራን ሊቃውንት ዝም ብለዋል፣ የንተ ብዕር ግን ንቁ ነው ሁሌም ይጮኻል...እሪ.. ኡኡኡ... ይላል። ሳይፈራና ሳያፍር ንግስት አውዶክስያን እንደገሰጻት እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ ያለ ልብ አሁንም አብዝቶ ይስጥህ። እንግዲ ምን እንላለን፣ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ይህን ተግሳጵህን አንብበው ምናልባት ደንገጥ ሊሉ ልባቸው ሊመለስ ይችላልና ጹህፍህን በመጽሔቶች በጋዜች ላይ እንዲወጣ ብታደረግ፤ በኤፍ ኤም ሬዲዮኖች ሽፋን ቢያገኝ፤ ምሁራኑ ሊቃውንቱ ቢወያዩበት፤ ምዕመኑም አባቶች ጋር ቀርቦ ጥያቄውን ቢያነሳ መፍትሔ ሊገኝ ይችላል።

  ReplyDelete
 2. እስጢፎ ዘጣፎJuly 7, 2017 at 10:12 AM

  እውነትም አብዝቶ የሚጮህ ጽሑፍ ነው፡፡ እግዚያብሔር ይስጥህ፡፡ ደግሞ እንደ ዘመነኞቹ ለቤተክርስቲያን የምንቆረቆረው እኛ ነን፤ ከኛ በላይ ላሳር አባ እገሌ መናፍቅ ነው፤ ዲያቆን ማንትስ ተሃድሶ ነው፤ ቄስ እገሌ መናፍቅ ነው እያሉ፤ አንዴ “ግሪሳው” አንዴ መናፍቅ እያሉ፤ አባቶችን፣ ወንድሞችን በአደባባይ የሚያዋርዱ፣ የሚሳደቡ፤ የራሳቸው ጉድፍ ሞልቶ ተረፎ የሌላውን ላጥራልህ የሚሉ፣ ማስተዋል የጎደላቸው፤ ግብዝነት የሞላባቸው፤ ግልብ ጋላቢዎች፤ ማንም በማንም አይፍረድ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል ማሰብ የተሳናቸው፤ ዘመኑ ያበቀላቸው ዘመነኞች እንደሚጽፉት ጽሑፍ በሐሜት በአሉባልታ የታጨቀ ያይደለ ለተግሳጽ ለምክር የሚሆን ነው፤ በትዕቢት ያይደለ በትህትና የተጻፈ ነው፤ በዘፈቀደ ያይደል በዕውቀት የተሞላ ነው፡፡ ለጥላቻ ለመለያየት ያይደል ለፍቅር፣ ለአብሮነት የሚሆን ወደ አንድነት የሚያደርስ ነው፡፡ ተባረክ፤ አንተ ብቻ ጻፍ እኛም እናነባለን፣ እንሰማለን፣ እርስ በእርሳችን እንወያያለን፣ ለችግሩ መፍትሔ ለመፈለግ በጋራ በመሆን እስከ ጥግ እንሄዳለን፡፡ አንተ ብቻ ሁሌም በርታ፤ ችግሮችን ለማሳየት አትስነፍ፤ በያዝከው መንገድ ተጓዝ፤ “እግዚያብሔር እያሃድጋ ለብሔር ዘእንበለ አሐዱ ሔር” የሚባለው እውነት ነው ላካስ፤ እኔ የምለው ለመሆኑ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ግን የት አሉ፤ አይቴ ሀለውክሙ አበዊነ ? ይሄ ወንድማችን ብቻውን ሲለፋ ብቻውን ሲታትር፤ ብቻውን ሲጮኽ ነው የምመለከተው፤ የሊቃውንት አገር ተብላ የተወደሰች አገር ሊቃውንቷን የት ከታ ዝም ጭጭ አለች፤ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት አባቶች የት ነው ያላችሁት ግን፤ ቆይ የት ነው ያላችሁት ግን፤ ድምጻችሁ እንዲህ ጨርሶ እንዴት ጠፋ፤ ወይስ ነብዩ ኢሳይያስ እንደተናገረው ቤታችሁን መዝጊያውን ከኃላችሁ ዘግታችሁ ቆልፋችሁ ተቀመጣችሁ ነው፡፡ ችግር ብሎ የቸገረ፤ ጭንቅ ብሎ የጨነቀ፤ ጥብብ ብሎ የጠበበ ነገር ነው እኮ፡፡ ቆይ የቅርብ ጊዜ አባቶች እንደነ አባ ጉኒና (ግቢ ገብርኤል የነበሩ አባት) ንጉሱን ሳይፈሩ በድፍረት ይገስጹ እንደነበር እኒህን የመሳሰሉ አባቶች ደግሞ በየቦታው እንደነበሩ እየሰማን ነው ያደግነው፤ በኃላም በኔ ዘመን እንኳን ይቅርቦቹ ቆፍጠን ያሉት እንደ ሊቀ ብርሃናት መርቆሪዎስ አረጋ ለቤተክርስቲያን ለአገር እንደተንገበገቡ ኖረው እንደተንገበገቡ ሲያርፉ በቅርብ ተመልክተናል፡፡ አሁን ግን የት ጠፉ እናንተው? ትንቢት ንግርት አለ እንዴ ? ማለቴ በስምንተኛው ሺ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ይጠፋሉ የሚል፤ ሳይኖር አይቀርም፤ እርሱ ግን ጊዜው ገና ይመስለኛል፤ ካህን ከመንበሩ ይጠፋል፤ ምዕመናንም አባቶች መቃብር ላይ ሄደው አባቴ ይፍቱኝ የሚሉበት ዘመን ይመጣል የሚል ጽሑፍ ፍካሬ እየሱስ ላይ ይሁን ሌላ መጽሐፍ ላይ ሳላነብ አልቀርም፤ የዚህ ትንቢት ጊዜው ግን ገና ይመስለኛል፤ ነው ዋዜማው ላይ ስለሆንን ነው ? ወቸው ጉድ እንደ ኖህ ዘመን 120 ዓመት ነው የቀራችሁ ሲባሉ ጊዜው ገና ነው እንዳሉት ሰዎች ሆንኩኝ እኮ፤ “ያን ጊዜ አንባቢው ያስተውል” አለ ወንጌል፤ ለማንኛውም ሁላችንም እንበርታ፡፡

  ReplyDelete
 3. Etege Taitu lik bilewal mechiw zemen yasferal Egziabher Hagerachinin ena Betekristiyanachin yitebik

  ReplyDelete
 4. Thank you Daniel to flag this issue up. I want to ask to our fathers what is development with out developing the human mind and soul. If we do not respect our prevous fathers and leaders who will repect us? The holy synod has to take action.

  ReplyDelete
 5. "...ቤተ ክርስቲያን ለጣልያን ወታደር የምትሰጠውን ቦታ ያህል ለአድማሱ ጀንበሬና ለዮፍታሔ ንጉሤ የላትም?"

  ከሚያዉቁ ሰዎች የማያዉቁ ሰዎች የተረከቧት ይህች ሐገር

  የቀማኞች ምድር
  የህሊና ቢሶች አደር
  ፊተኛ ኋላቀር
  አባክህ በትርህን ሰንዝር
  ቸሩ እግዚአብሕር::


  ReplyDelete
 6. ለመሆኑ ለመልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬ ክብርና ፍቅር የሌለው ሰበካ ጉባኤ ሃይማኖቱ ምንድን ነው? ደብሩስ የማነው?

  ReplyDelete
 7. እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ እንጅ ቤተክህነት ቤተክህደት ከሆነ ቆየ

  ReplyDelete
 8. እንደ ተራ ነገር፡፡

  ReplyDelete
 9. ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ
  የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ

  ReplyDelete
 10. ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ
  የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ

  ReplyDelete
 11. degun zemen fetari yametalen ...............nafeken degu zemen abatu geta hoye endechernethe engi endebedelachen ayehune!!!!

  ReplyDelete
 12. ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ
  የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ

  ReplyDelete
 13. Ere Gude New!! Ezache hager Laye Mejemeriya Sewe Teweldo Madege mejemer Alebet Kaleza....ENDEGENA Meserat Aleben Yemnfelegew Astesaseb Endimeta...

  ReplyDelete
 14. It is so painful to hear this. They thought they live forever. They will get what they are doing right now.

  ReplyDelete
 15. ይህችን አገር ማወቅ ሳይሆን መናቅ፣ ህግ አክባሪ ሳይሆን ሕግ ደፋሪ እየመራት፣ እየኖረባት ነው! የቅዱሳንን አፅም የሚንቅ ትውልድ ከመጣ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ወዴት ነው? ለማንኛውም ሳንከፋፋ ህግ ይከበር!!!

  ReplyDelete
 16. ሁሉም በጊዜዉ ይሆናል ለምን ማለት ፈጣሪን ብቻ ነዉ!
  ችግሮችን ማሳየት ደግሞ ለተሰጣቸዉ ብቻ!

  ReplyDelete
 17. በዓለ ወልድ የማነው?
  አልክ! ቆየኮ የእነሱ ከሆነ

  ReplyDelete
 18. በዘመናችን በቤተክርስቲያናችን ተስፋ እንዳንቆርጥ እግዚአብሔር ያዘጋጀልን ወንድም ዲ/ን ዳንኤል ሲሆን፤ እግዚአብሔር ያዘጋጀልን አባት ደግሞ አቡነ አብርሐም ናቸዉ፡፡ በአሮን ምርቃን መርቄሀለዉ፡-
  እግዚአብሔር ይባርክህ፥ ይጠብቅህም፤
  እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፥ ይራራልህም፤
  እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፥ ሰላምንም ይስጥህ።

  ReplyDelete
 19. ዲያቆን ዳንኤል እጅግ አድናቆትን ያተረፍክ ትልቅ ሰው ፡እወቅ ያለው በ40 ቀኑ ያውቃል ያለታደል ደግሞ እድሜልኩን …… ነው ይባላል ፡፡ ለሁሉም ሰሚ እዝነ ልቦና ያድልን እላለሁ ፡፡ እግዚአብሔር በመልካም ስራ እና ሃሳብ አባቶችንና መሪዎቻችንን እንዲያጎናጽፍልን እመኛለሁ ፡፡

  ReplyDelete
 20. በዓለ ወልድ የማነው?...ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ መቀበርም የሚቻለው በክልላችሁ ነው ልትሉን ነው? ዮፍታሔ ንጉሤ የደብረ ኤልያስ ብቻ ናቸው?

  ReplyDelete
 21. የዳንኤል መነፅር ብዕር ብቻ ሣይሆን እንደ ዳንኤል ረቂቅ በትርም ቢኖረው ምናለበት። ወይ ነዶ!!

  ReplyDelete