Wednesday, July 26, 2017

የደብረ ሊባኖስን ታሪክ ማጥፋት፣ ለምን?
‹በአባታችን በዮሐንስ ከማ ዘመን ሃይማኖቱ የቀና ንጉሥ ይስሐቅ(1406-1421) ታላቅ ቤተ ክርስቲያን በእንጨትና በድንጋይ ያንጹ ዘንድ አዘዘ፡፡ ያቺም ቤተ ክርስቲያን ተሠርታ ስትፈጸም ፈረሰች፡፡ ንጉሡም ይህንን ሰምቶ እጅግ አዘነ፡፡ እንዲህ ሲልም ወደ አባ ዮሐንስ ከማ መልእክት ላከ፤‹‹የዚህን ነገር ምክንያት ታውቅ ዘንድ ጸሎት አድርግ፤ስታውቀውም ወደ እኔ ላክብኝ፡፡›› ያን ጊዜም አባ ዮሐንስ ከማ ቅዱሳን ልጆቹን ሰበሰበ፡፡ ንጉሡ እንዳለው ጸሎትን አጽንተው እንደዲያደርጉ አዘዛቸው፡፡ እነዚህ ንጹሐን በጸሎት ተግተው በጸኑ ጊዜ የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእነዚያ ቅዱሳን ለአንዱ ተገለጠችለት፡፡ እንዲህ ስትልም ተናገረቺው፤ ‹‹ይህንን መሥፈሪያ እንካ፤ ቤተ መቅደሴንም በዚህ መለኪያ ለክተህ ሥራ ብለህ ለአባትህ ለዮሐንስ ከማ ንገረው፡፡ ስትሠሩም ከልጆችህ በቀር ሌሎች አይሥሯት፤ ባስልኤልና ኤልያብ ጥበብን እንደተመሉ(ዘጸ. 31፣1-11) ሁሉ እኔም እነርሱን በጥበብ እመላቸዋለሁ፡፡››
አባታችንም የአምላክ እናት የእመቤታችን የማርያምን የቃል መልእክት በሰማ ጊዜ የሆነውን ሁሉ ለንጉሡ ላከበት፡፡ ንጉሡም የታመነውን የምሥራች ቃል ባገኘ ጊዜ ወደ ደብረ ሊባኖስ መጥቶ[1] መነኮሳቱን፤ ‹‹የአባታችሁ መቃብር ናትና እናንተ ሥሯት፤ ሌሎች ከሠሯት ግን መልካም አይሆንም ብለው ሐሰት የማይገኝባቸው ሰዎች ነገሩኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱ ግን ሊሠሩ አልወደዱም ነበር፡፡ ነገር ግን የንጉሡን ቃል እንዳያስተሐቅሩ ሲሉ ጀመሩ፡፡ እርሱ አስቀድሞ ‹‹በንጉሥ ዜና መዋዕል፣ ንጉሥ ሲለምን፤ ለምኖም እምቢ ሲሉት አልሰማሁም›› አላቸው፡፡ በዚህም የተነሣ ሊሠሩ ጀመሩ፡፡ ሕንጻውም በሰባት ዓመት ተፈጸመ፡፡ እዚህ ላይ ከታሪኩ ጋር የሚሄድ መልካምን ዜና እንንገራችሁ፡፡ በገድል የተጠመደ አንድ መነኮስ ነበረ፡፡ ኅሊና መንፈሳዊ በመጣበትም ጊዜ ቁመትን ከጸሎት ጋር አስተባብሮ ያለ ድካም ዘወትር ይተጋ ዘንድ ገድልን ጀመረ፡፡ እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያንዋን ሕንጻ ፍጻሜ ያሳየው ዘንድ፡፡ በዚህ ሁኔታም ለሰባት ዓመታት ኖረ፡፡ ከዚህም በኋላ የሥራውን ፍጻሜ ሲመለከት የሥጋን ድካም ድል ያደርግ ዘንድ ኃይልን ሰጥቶታልና እግዚአብሔርን አመሰገነው፡፡ የዚህ ጻድቅ ረድኤት ከእኛ ጋር ይሁን፡፡
ይለናል በ1587 ዓም የተጻፈው ‹ዜና ደብረ ሊባኖስ› የተሰኘው መጽሐፍ፡፡ 

ደብረ ሊባኖስ በ1926/27
የደብረ ሊባኖስ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁ ዝም ብሎ እጨጌና መነኮሳት፣ ነገሥታትና መኳንንት፣ መሐንዲሶችና ዶክተሮች ስለፈለጉ ብቻ የሚሠራ አይደለም፡፡ ከደቡብ ኢትዮጵያ እስከ ኢየሩሳሌም ለሐዋርያዊ አገልግሎት የደከሙት፣ ኢትዮጵያን በዮዲት ዘመን ከገባችበት የትምህርት ጨለማ በስብከት ያበሩላት፣ ደቀ መዝሙሮቻቸውን በአራቱ መዓዝን ያሠማሩት፣ ሐዲስ ሐዋርያ ተክለ ሃይማኖት የጸለዩበት፣ ቃል ኪዳን የተቀበሉበትና ያረፉበት የተቀደሰ ሥፍራ ነውና፡፡ አሁን ያለውን ሕንፃ ጨምሮ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ታሪክ ውስጥ 10 አብያተ ክርስቲያናት በተከታታይ ተሠርተዋል፡፡ የመጀመሪያው የገዳሙ ቤተ ክርስቲያን የተሠራው ዔላም በተባለውና ከደብረ አስቦ ወረድ ብሎ በሚገኘው ሜዳማ ሥፍራ ላይ ሲሆን ዘመኑም በ1362 ዓም ነው፡፡ ያሳነጹትም አራተኛው እጨጌ ሕዝቅያስ ናቸው፡፡ አሁን ያለውን ቤተ ክርስቲያን ያሠሩት ደግሞ በ1955 ዓ.ም. በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ አማካኝነት ነው፡፡ ዐሥሩም የደብረ ሊባኖስ አብያተ ክርስቲያናት ከገዳሙ የደስታና የመከራ ታሪክ ጋር የተያያዘ ምክንያት አላቸው፡፡ አንዳቸውም ቢሆኑ ገንዘብ አለን፣ ሞያ አለን፣ ቦታ ጠበበን፣ ተብለው የተሠሩ አይደሉም፡፡ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን የተሠራው አባታችን ቀድመው በተናገሩት መሠረት ዐጽማቸው ከደብረ አስቦ የሚፈልስበት የትንቢት ጊዜው በመድረሱ ነው፡፡ አሁን ያለው ቤተ ክርስቲያን የተሠራው ደግሞ ግንቦት 12 ቀን 1929 ዓም. የአባታችንን የፍልሰተ ዐጽም በዓል ለማክበር የተሰበሰቡትን ካህናትና ምእመናንን የግራዝያኒ ጦር ጨፍጭፎ፣ ቤተ ክርስቲያኑን አቃጥሎ፣ ቅርሱን ዘርፎ በመሄዱ የተነሣ ገዳሙ በመዳከሙ ምክንያት እንደገና እንዲሠራ ጻድቁ የላኳቸው መናንያን ለንጉሡ በመናገራቸው ነው፡፡
የደብረ ሊባኖስ ገዳም ክልል ከ30 በላይ እጨጌዎች የተቀበሩበት፣ የብዙ ቅዱሳን ዐጽም ያረፈበት፣ ታላላቅ ጉባኤያት የተደረጉበት፣ ከዕብራይስጥና በዐረብኛ ሳይቀር ትርጓሜ መጻሕፍት ሲሰጡ የኖሩበት(ዛሬ ተገቢውን ትኩረት የሚሰጣቸው አጥተው ትምህርት ቤቶቹ ቢዳከሙም)፣ አያሌ ቅዱሳት መጻሕፍት ከዐረብኛ ወደ ግእዝ የተተረጎሙበት ቅዱስና ታሪካዊ መካን ነው፡፡ በዚህ ቦታ የሚሠሩ ግባታዎች የጥንቱን ታሪክ እንዳያጠፉ፣ ወደፊት የሚደረገውን የአርኬዎሎጂ ጥናት እንዳያደናቅፉ፣ የገዳሙን ታሪካዊ ክብር እንዳያጎድፉ ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የገዳሙ አስተዳደር ገድል ቤቱ ጠበበ ብሎ በማሰብ ተጨማሪ ሕንጻ (የገድል ማንበቢያ) ለመሥራት በዕቅድ ላይ ነው፡፡ በገዳሙ ቅጽር የለጠፈው የሥራ ማሳወቂያ ሰሌዳም ይህንኑ ያውጃል፡፡ የሥራው ዓላማ መልካም ቢሆንም ሊሠራ የታሰበው ነገርና ሊሠራ የታሰበበት ቦታ ግን ሁላችንም ‹ኡኡ፣ የተክልየ ያለህ› እንድንል የሚያደርገን ነው፡፡
ገዳሙ ሊሠራ የለጠፈው ሰሌደ
ገዳሙ የለጠፈው ሰሌዳ እንደሚገልጠው ሊሠራ የታሰበው ሕንጻ በ1955 ዓም በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ የተሠራውን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ዲዛይን ራሱን የሚደግም ነው፡፡ለምን? ሁለት ተመሳሳይ ሕንጻዎችን በአንድ ግቢ ውስጥ ማቆም ለምን አስፈለገ? በአኩስም ጽዮን ሁለት ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ ዐፄ ፋሲል ያሠሩትና ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ያሠሩት፡፡ ዐፄ ፋሲል የጥንቱን ደብረ ብርሃን ሥላሴና ዳጋ እስጢፋኖስ የተሠሩበትን መንገድ ተከትለው ሲያንጹ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ደግሞ በቁስጥንጥንያ የነበረችውን፣ በ381 ዓም ጉባኤ ቁስጥንጥንያ የተደረገባትን፣ እነ ዮሐንስ አፈወርቅ ያስተማሩባትን፣ በኋላ ቱርክ መስጊድ ያደረጋትን ሐጊያ ሶፍያን የምትመስል ክብ ቤተ ክርስቲያን አሠሩ፡፡ መንታ ቤተ ክርስቲያን ግን አላቆሙም፡፡
ታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ላሊበላ በሮሐ፣ በአንድ አካባቢ ላይ 11 አብያተ ክርስቲያናትን ሲያንጽ መንታ አድርጎ የሠራው ሕንጻ የለም፡፡ እንዲያውም በመጽሐፈ አኩስም የተጻፈላትን የጥንቷን የአኩስም ጽዮን የሕንጻ ዲዛይን አስመጥቶ ቤተ ማርያም ላይ እንዲተገበር በማድረጉ ሲደነቅ ይኖራል፡፡ ደብረ ሊባኖሶች ምንድን ነው የነካብን? እንዲህ ያለውንስ ሥርዓት ከየትኛው ታሪክ ነው የተማሩት? ቤቱ የታሪክ፣ የተውፊትና የሥርዓት ቤት ነበርኮ!
እጅግ የሚደንቀው ደግሞ ይኼው በመልክና በቅርጽ ተመሳሳይ የሆነ ሕንጻ የሚሠራው በጥንቱ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ነው፡፡ ሃምሳ ሜትር በማይርቅ ቦታ ላይ የጥንቱን ቤተ ክርስቲያን ዲዛይን ለዚያውም አሳንሶ መድገም ታሪክ ማጥፋት እንጂ ታሪክ መሥራት ሊሆን አይችልም፡፡ የጥንቱን ቤተ ክርስቲያን የሠሩት ዐቃጆች(አርክቴክቶች) ከሩቅ ከሚታየው ፏፏቴ ጋር ተነጻጽሮ እንዲሠራ ያደረጉበት ምክንያት ነበራቸው፡፡ አላቫሬዝ በመጽሐፉ እንደተረክልን ይኼ ወንዝ የደብረ ሊባኖስ መታወቂያውና መገለጫው ነበር፡፡ እንደነ እጨጌ ዕንባቆም ያሉት ተሻግረውት የመጡት ወንዝ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያታቸው ደግሞ ለ300 ዓመታት ደብረ ሊባኖስ ጠፍ ሆና ስትኖር የአባታችንን መቃብር የሚጠብቁ መናንያን ዐጽሙ ያረፈበትን ቦታ ለመለየት የተጠቀሙበት የመለያ ምልክት ስለነበረ ነው፡፡(ስለዚህ ጉዳይ በቅርቡ በሚታተመው የአቡነ ተክለ ሃይማኖትና የደብረ ሊባኖስ ታሪክ መጽሐፍ ላይ በሰፊው እመለስበታለሁ)
አሁን ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራበትን ቦታ በተመለከት ታሪካዊ መዛግብት እንዲህ ይሉናል ‹በዐፄ ምኒልክ ዘመን በ1895 ዓ.ም. የደብረ ሊባኖስን ቤተ ክርስቲያን ሊሠራ ሕንጻው ሲጀመር እጨጌ ወልደ ጊዮርጊስና ክቡር ራስ አባተ (ቧ ያለው) ለሥራው ተመድበው ነበር፡፡ ሥራው ተጀምሮ አካባቢው ሲቆፈር በዛሬው ቤተ ክርስቲያን መሠረት ላይ በስተ ደቡብ በኩል ‹‹ተ›› የሚል ጽሕፈት ያለበት መቃብር ተገኘ፡፡ እጨጌው ይህ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት መቃብር ሊሆን ስለሚችል ከፍተን እናውጣውና ተአምራት ያድርግ ቢሏቸው ራስ አባተ ቧ ያለው ግን ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ቤተ ክርስቲያኑም በላዩ ላይ ተሠራ[2]፡፡ በ1955 ዓ.ም. የአሁኑ ቤተ ክርስቲያን ሲሠራም በዚያው መሠረት ላይ ነው የታነጸው፡፡›
በመሆኑም አሁን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ በሠራበት አካባቢ የሚደረግ ቁፋሮ ሁሉ ታሪካዊ ምክንያት ሊኖረውና ሊገኙ የሚችሉ ጥንታዊ ቅርሶችን አደጋ ላይ የማይጥል መሆን አለበት፡፡ ቦታው በግሬደር የምንንደው ተራ ቦታ አይደለምና፡፡
ሌላም ጉዳይ አለው? ሁለተኛው ተመሳሳይ ሕንጻ የጥንቱን ሕንጻ ኪነ ጥበባዊ፣ ታሪካዊና መካናዊ(Placement) የሚቀንስና የሚያሳጣ ነው፡፡ ያንን በፎቶ ግራፍ ስናየው፣ በፖስተር ስናትመው ግርማ ሞገስ የሚኖረውን፣ በደን የተከበበውን፣ ከኋላው በበጋ ተራራው፣ በክረምት ፏፏቴው የሚያጅበውን ደብረ ሊባኖስ የሚያጠፋ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ታሪክ ትዝ ይለኛል፡፡ ብጹዕ አቡነ ቀውስጦስ በኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ሆነው ከተመደቡ ከተወሰኑ ወራት በኋላ በኢየሩሳሌም አግኝቻቸው ነበር፡፡ ብጹዕነታቸው አጥብቀው ያዘዙኝ ነገር ቢኖር ከኋላው ጋራውና ፏፏቴው የሚታይበትን የደብረ ሊባኖስን ቤተ ክርስቲያን ፎቶ እንድልክላቸው ነበር፡፡ ዘወትር በዓይነ ኅሊናቸው የሚታያቸው ያ መሆኑን ገልጠውልኛል፡፡ ታድያ ምነው ብጹዕ አባታችን ታሪኩ ሲጠፋ በዝምታ ተመለከቱት? እባክዎን ነገሩን ደግሞው ያስቡበት፡፡
ደግሞስ የቀደሙት አበው በዘመናቸው ሠሩ፡፡ ያ ታሪካችንም ሀብታችንም ነው፡፡ እኛ ደግሞ በዘመናችን የዘመናችንን ለምን አንሠራም? የእነርሱን ታሪክ፣ የገዳሙን ዝናና ታላቅነት፣ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የነበረውን ቦታ (ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት እስከ እጨጌ ወልደ ኪዳን ድረስ ከ52 በላይ እጨጌዎች ነበሩት)፣ ከሌሎች ገዳማት በተለየ ለ300 ዓመታት ያህል ጎንደር ላይ የነበረ ገዳም መሆኑን የሚያሳይ ዲዛይን አሠርተን፣ ያንንም በሃይማኖት፣ በታሪክ፣ በቅርስ፣ በመልክዐ ምድር፣ በአርክቴክቸር፣ ባለሞያዎች አስገምግመን፤ ለቀጣዮቹ 50 ዓመታት የሚያገለግል ሕንጻ መሥራት ነበረብን እንጂ ሌሎች የሠሩትን ማጥፋት ይገባን ነበር?
በደብረ ሊባኖስ ታሪክ ውስጥ ዓይነተኛ ቦታ ያላት፣ ጻድቁም ሲጸልዩባት የኖረችው፣ ራሷን በተመለከተ ‹ዜና ምጽአታ ለታቦተ ማርያም› የሚል መጽሐፍ የተጻፈላት ‹ታቦተ ማርያም› አለች፡፡ የመጀመሪያው የደብረ ሊባኖስ ቤተ ክርስቲያንም የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ሦስተኛዋና በእጨጌ ዮሐንስ ከማ ዘመን(1406-1420) የተሠራችው ቤተ ክርስቲያንም  ቅዳሴ ቤቷ የተከበረው ሰኔ 21 ቀን ከጥንቱ ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያን ጋር በማስተሣሠር ነበር፡፡ ታድያ ምነው ሌላ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ካስፈለገ እንኳን ታሪካዊነቱን ሳይለቅ፣ የአባታችንንም ሥራ በሚያስታውስ መልኩ ለእመቤታችን ታቦት ቤተ ክርስቲያን ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ሊገናኙ በማይችሉበት ቦታ ላይ በገዳሙ ክልል ለምን አይሠራም?
ይህንን ጥያቄ ስናነሣ ሁለት መልሶች ከገዳሙ ይሰጣሉ፡፡ የመጀመሪያው ‹የምንሠራው ገድል ቤት ነው› የሚል ነው፡፡ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ አውጥተን የምንሠራውን ሕንጻ ገድል ቤት ብቻ እናደርገዋለን ማለት የማይመስል ነገር ነው፡፡ ነገ ታቦት እናስገባበታለን፡፡ ያ መሆኑ ካልቀረ ደግሞ ጎን ለጎን ከማድረግ ራቅ አድርጎ በንግሥ ጊዜ የሚመጣውን ሕዝብ ሊያካትት የሚችል ሰፊ ቤተ ክርስቲያን መሥራት ነው፡፡ ሁለተኛው መልስ ደግሞ ‹በገዳሙ ክልል ገደል እንጂ ምቹ ቦታ የለም› የሚል ነው፡፡ ዘመኑ 21ኛው መክዘ መሆኑን የዘነጋ መልስ፡፡ እንኳን በደብረ ሊባኖስ በዜጋመል መሥራት ይቻላል፡፡ መመካከሩና ተረጋግቶ ማቀዱ ካለ፡፡
ደብረ ሊባኖስ የሚታወቀው በምንኩስናና በትምህርት ማዕከልነቱ ነው፡፡ ታላላቆቹ ነገሥታትም በዘመኑ ትልቅ ያሉትን ቤተ ክርስቲያን የሚሠሩት ስብሐት እንዲወርድበት ትምህርት እንዲሰጥበት ነው፡፡ ዐፄ ምኒልክ የደብረ ሊባኖስን ቤተ ክርስቲያን አሠርተው ለንግሡ በወረዱ ጊዜ የሆነውንና ‹ከገድለ ተክለ ሃይማኖት ጋር የተገኘ መዝገብ› የመዘገበልንን ልጥቀሰው ‹ዐፄ ምኒልክ በ1885 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ሠራዊት በዐዋጅ ሰብስበው ደብረ ሊባኖስ ወረዱ፡፡ ከሠራዊቱም ብዛት የተነሣ ደጋውም ቆላውም ለሰፈር ጠቦት ነበር፡፡ በግንቦት 12 ቀን የተክለ ሃይማኖት በዓለ ፍልሰተ ዐጽም በሚከበርበት ቀን ምሳሌ በሌለው አከባበር ታቦቱን አንግሠው ካዲሱ ቤተ ክርስቲያን አግብተው ታላቅ ሥነ በዓል ተደረገ፡፡ መኳንንቱም መሳፍንቱም ባላገሩም አንክሮ ባለው ደስታ እየተደሰቱ ሰነበቱ፡፡ በሁለተኛው ቀን ንጉሡ ቤተ ክርስቲያኑ በጣም ትልቅ ነበርና፤ ‹‹መምህራን ይሰብሰቡ መወድስ ማኅሌት ስብሐተ ነግህ ጾመ ድጓ ይቆምበት፤ የባላገር  ልጅ እየተማረ ደጅ ይጥና፤ እኔ ማደሪያ ቀለብ እሰጣለሁ›› ብለው ዐዋጅ አናገሩ፡፡ መነኮሳቱ ተሰብስበው፤ ‹‹ይኸማ ከሆነ ገዳምነቱ ይቀር የለምን?›› ብለው ቢያመለክቱ፤ ‹‹ይኸን ያህል ቤተ ክርስቲያን ሠርቼ እናንተ ምን ታደርጉበታላችሁ? ለናንተስ ምርፋቅ መስቀል ቤት ሠርቼላችኋለሁ ከዚያው ሳታት ቁሙ፡፡ ዳዊት ድገሙ አሏቸው፡፡›
የጥንቱን ቤተ ክርስቲያን በመንትያው ከማበላሸት ገዳሙን በሚገባ ዐቅድ ሰጥቶ መናንያንና ዓለማውያን እንዳይገናኙ ክልል መከለል፣ ለገዳማውያኑ የሚሆን አነስተኛ ቤተ መቅደስ በመናንያኑ ክልል ውስጥ መሥራት፣ ለሕዝቡ የሚሆን ደግሞ ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ሰፊ ቦታ ፈልጎ መሥራት ይገባል፡፡ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ (አንዳንዶች እንደሚገምቱት 75 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል) ሕንጻ ሠርቶ ገድል ቤት ብቻ ነው የሚለውን ንጉሥ ምኒልክ አለመስማታቸው መልካም ነው፡፡
ስንጠቀልለውም የገዳሙን ክልል በባለሞያ ዕቅድ እንሥራለት፣ የገዳማውያኑን፣ የጠበልተኛውን፣ የመቃብሩን፣ የሱባኤተኛውን፣ የትምህርት ቤቶቹን፣ የቢሮዎቹን ቦታ በአጥር እንለየው፣ አንደኛው ወደ ሌላው አይለፍ፡፡ በተለይ ወደ መናንያኑ፡፡ ለሕዝቡ በመደብነው ቦታ ላይ የዘመኑን አርክቴክቸርና የግንባታ ጥበብ ተጠቅመን አሁን ያለውን ምእመን ቁጥር የሚመጥን ሰፊ ቤተ ክርስቲያን እንሥራ፤ ካስፈለገም ቤተ ክርስቲያኑን ፎቅና ምድር ቤት አድርገን ታቹን ለገድል ቤት እንጠቀምበት፤ እግረ መንገዳችንንም በሚገባቸው ባለሞያዎች አስጠንተን የጥንቱን ቤተ ክርስቲያን የማንበርያ ሥራ (maintenance) እንሥራ፡፡ አዲስ የተመደቡት ጸባቴ እና ብጹዕ አቡነ ቀውስጦስ ጉዳዩን እንዲያዩት አደራ እላለሁ፡፡
በምንም መልኩ ግን የጥንቱን ታሪክ የሚያደበዝዝ፣ ከደብረ ሊባኖስ ታሪክና ክብር ጋር የማይመጥን፣ ቅርሶቻችንን የሚጎዳ ግንባታ መሥራት የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ከሚያጠፉ ጋር መተባበር ነው፡፡ ይህን ጥፋት በዕውቀታችሁና በገንዘባችሁ እየፈጸማችሁ ያላችሁ ካህናት፣ መነኮሳትና ምእመናን የተክልየ ዐጽም ይፋረዳችኋል፡፡11 comments:

 1. እግዚአብሄር አስተዋይ ልቦና ይስጥልን

  ReplyDelete
 2. የእሳት ልጅ አመድ ማለት እኛ ነን የዚህ ትውልድ አባላት፡፡

  ReplyDelete
 3. እግዚአብሔር እንደናንተ ያለውን መምህራን የሰጠን የተመሰገነ ይሁን::እድሜና ጸጋ ይጨምርላችሁ::

  ReplyDelete
 4. በምንም መልኩ ግን የጥንቱን ታሪክ የሚያደበዝዝ፣ ከደብረ ሊባኖስ ታሪክና ክብር ጋር የማይመጥን፣ ቅርሶቻችንን የሚጎዳ ግንባታ መሥራት የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ከሚያጠፉ ጋር መተባበር ነው፡፡

  ReplyDelete
 5. BETAM YASAZNAL LEMIN ......LEMIN....

  ReplyDelete
 6. ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህር፡፡
  ይህንን ጉዳይና ሃሳብ በሚገባ የሚከታተልና ከአባቶቻችን ጋር የሚመክር ህብረት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡
  በተረፈ ግን እንዲህ አይነት የግንባታ እቅዶች በአብዛኛው ሁለት ዓይነት አላማ ያነገቱ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው በአስተዳደር ቦታ ላይ የሚቀመጡ ሰዎች በምክንያት ገንዘብ መዝረፍ ሲፈልጉ ሲሆን በሌላ በኩል ቤተክርስቲያን በመገንባቱ ከበረከት እንሳተፋለን በሚል እሳቤ ይመስለኛል፡፡ በከተማችን በብዙ ደብራት ጥንታዊ ይዘት ያላቸውን ታሪካዊ ህንፃ ቤ/ክ እይታ የሚያደበዝዙ ብዙ ግንባታዎች ተፈፅመዋል ግን ዓላማውና ግቡ ምንድን ነው ሲባል መልስ የለሽ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኑ ለንግስ ጊዜ ለአጿማት ጊዜ ይጠባል ከተባለ ለምን መጠለያና ማረፊያ ቦታዎች እንዲሰሩ አይደረግም?
  አሁን ቀጨኔ መድኃኔዓለምን በሚያክል ትልቅና ታሪካዊ ደብር የተሰራውን አዲስ የቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ እንመልከት፡፡ መቼም የመልአኩ ጠላት መጣብን የሚል አይጠፋም ግን አንደኛ የቅዱስ ገብርኤል ታቦት ድርብ ነው፡፡ እዚያው ከመድኃኔዓለም ታቦት ጋር ሆኖ ቢነግስስ ቦታ እንደሆን አልጠበበ፡፡ ሁለተኛ በቅዱስ ገብርኤል ስም የተሰሩ አብያተ ክርስቲያናት ብዙ ቦታ አሉ ምዕመናን በተለያየ ቦታ በመሄድ ያከብራሉ፡፡ ታዲያ ምንድነው ትርፉ ቦታው እንደሆነ የክርስቶስ ደም የነጠበበት ነው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልን ከመድኃኔዓለም ታቦት መለየቱ ፋይዳው ምንድነው?
  በቅርብ አመታት በኮተቤ ቅድስት ሃና ወኢያቄም ቤ/ክ የተደረገውን ማንሳት ግድ ይላል፡፡ እንደሚታወቀው የቅድትስ ሃና ወኢያቄም ህንፃ ቤ/ክ በጣም ሰፊና በልዩ ዲዛይን የታነፀ ነው፡፡ ህንፃ ቤተክርስቲያኑም ይጠናቀቅ እንጂ ብዙ የሚጎድሉት ነገሮች አሉት፡፡ ቀለም እንኳን በተገቢው መንገድ አልተቀባም፡፡ በዚህ ደብር የአጋዕዝተ ዓለም ቅድስት ሥላሴ፣ የጻድቁ አባታችን የአቡነ አረጋዊ ታቦታት ይከበራሉ፡፡
  ታዲያ በሥላሴ የንግስ በዓል ላይ የደብሩ አስተዳዳሪ ምዕመናን እንዴት የአለም ፈጣሪ ሥላሴ ቤት ያጣሉ? ከቅድስት ሃና ጋር ለምን ይደረባሉ? ቤ/ክ ልንሰራላቸው ይገባል፡፡ በማለት ዶግማንና ቀኖናን በሚያፋልስ መልኩ የአካባቢ ወጣቶች ያሰሩት አዳራሽ ውስጥ እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ ብዙ የልማት ስራዎች የአብነት ት/ቤቶች መገንባት ሲችሉ ከተወሰኑ አጋፋሪዎች /ሆን ብለውም ሳያውቁም ከተሰበሰቡ/ ጋር ታቦቱን ወስደው ሜዳ ላይ የተሰራ አዳራሽ ውስጥ አስቀምጠዋል፡፡
  እስኪ እኚህ አባት አሁን ለሥላሴ ክብር ተቆርቁረው ነው? አጋዕዝተ ዓለም ሥላሴስ ከቅድስት ሃና ጋር እንዴት በድርብ እከበራለሁ? የሚሉ ናቸውን? ለቅድስት ሥላሴስ ክብሩ በሚገባ የተሰራው ህንፃ ቤ/ክ ነው ወይስ ለመሰብሰቢያ የተሰራ አዳራሽ?
  የቤተክርስቲያን አባቶች ምን እየሰሩ እንደሆነ፤ ባለሃብቶችም ገንዘባቸውን ምን ላይ ማዋል እንዳለባቸው ማሰብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እና መምህር ዳንኤል ይህ ጉዳይ በሰፊው የቤተክርስቲያንን ክብር እየነካ ነውና ቅዱስ ሲኖዶሱ በሚገባ እንዲመለከተው ቢደረግ ምዕመናንም ኃላፊነት አለብንና በእግዚአብሔርም ያስጠይቀናልና ቆም ብለን የምንሰራውን ብናስተውል፡፡

  ReplyDelete
 7. እጅግ የመሰጠኝ ፅሁፍ ነው፡፡ እባካችሁ የቤተክርቲያን አባቶች እና የዲዛይን ጥበብ የተሰጣችሁ ሁሉ አስተውላችሁ እንደምትፈፅሙት ባለሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡

  ReplyDelete
 8. E/gr Yakebrhe...Rejem edemae ena tsega yistelen

  ReplyDelete
 9. እኔ ምን እላለሁ ብቻ እንደነዚህ ያሉ አርቆ አስተዋይና ተቆርሪ አያሳጣን!! ጌታ ልቡና ይስጣቸው፡፡

  ReplyDelete
 10. Daniel ebakhi ኦርቶዶክስ መልስ አላት /ከፕሮቴስታንቶች ለሚነሡ አንዳንድ ጥያቄዎች የተሰጡ መልሶች/ methafune keyte engegnwe ke gebya laye teftwale weyme pdf Host arglene

  ReplyDelete
 11. kale heywot yasmlin, egzabher amlikachin melkamun nager yefatsmilin

  ReplyDelete