Friday, July 14, 2017

የዮፍታሔና የአድማሱ ነገር


የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የመልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬንና የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ዐጽም በተመለከተ የሰጠውን ማብራሪያ ተመለከትኩት፡፡ ካቴድራሉ ሐሳቡን ለማስረዳት መትጋቱን አደንቃለሁ፡፡ የካቴድራሉ ሐሳብ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊት የራቀ በመሆኑ ግን ተገርሜያለሁ፡፡
ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤና መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬን በተመለከተ ካቴድራሉ ያየበት መነጽር ነው ስሕተቱን ያመጣው፡፡ ካቴድራሉ አገልጋዮቹን የሚያያቸው በቤተሰብና በጎጥ ደረጃ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን አገልጋዮቿን የምታያቸው በሀገርና ከዚያም ሲያልፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ የወሎ ቦረና፣ ቅዱስ ያሬድ የትግራይ አኩስም፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሸዋ ጽላልሽ፣ አቡነ አረጋዊ የሮም ተወላጆች እንጂ ሀብቶች አይደሉም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ ካቴድራላችን ግን የቤተሰቦቻቸውና የተወላጆቻቸው አድርጎ ያያቸዋል፡፡ ስሕተቱ የመጣው ቤተ ክርስቲያንንና ሀገርን ሲያገለግሉ የኖሩ ሊቃውንትን ዐጽም በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት መሠረት ከማፍለስ ይልቅ ‹ቤተሰቦቻቸው ተገኝተው ያፍልሱ› ብሎ ዐዋጅ ከመንገሩ ላይ ነው፡፡ የካቴድራሉ ካህናትና ዲያቆናት ለመልአከ ብርሃን አድማሱና ለቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ቤተሰቦቻቸው አይደሉምን? በዚህ ዓይነት እጨጌ ዕንባቆም ወደ የመን፣ አቡነ አረጋዊ ወደ ሮም፣ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስም ወደ ግብጽ የሥጋ ቤተሰቦቻቸውን ፍለጋ ይሂዱን? ይህ የካቴድራላችን እንጂ የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት አይደለም፡፡
‹ቅንጣቱ ከምሉዑ ውጭ አይሆንም› የሚል ፍልስፍና አለ፡፡ አንድ ነገር የነገሩ ማኅበረሰብ ከሆነው ውጭ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ የቤተ ዘመድና የተወላጅነት አሠራር የቤተ ክህነት ሰዎችን እየተዋሐደን ስለመጣ ሊቃውንትንና ቅዱሳንንም ከጎጥና ከቤተሰብ ውጭ ልናያቸው አልቻልንም፡፡ 

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ያረፉት ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም. ነው፡፡ የዛሬ 70 ዓመት፡፡ ሊቀ ሥላጣናቱ በመግለጫቸው እንደነገሩን የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ዐጽም ተነሥቶ ሌላ ቦታ የተቀመጠው ‹የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ቤተሰቦች በወቅቱ ባለመምጣታቸው› ነው፡፡ ከሰባ ዓመት በኋላ ትውልድ እንጂ ቤተሰብ እንዴት ይገኛል? በምን ሂሳብ ነው ቤተ ክርስቲያኒቱን አምነው የዛሬ 70 ዓመት የተቀበሩትን ክርስቲያኖች ዐጽም በክብር የማፍለስ ኃላፊነት የልጅ ልጆቻቸው የሚሆነው? አሠራሩ ችግር እንዳለበት የሚያሳየው ካቴድራሉ ባስነገረው ዐዋጅ መሠረት የሚመጣ ጠፍቶ ‹ስምንት ዓመት ዐጽሙ ተነሥቶ ሌላ ቦታ መቆየቱ› ነው፡፡ የዛሬ ስምንት ዓመት ካቴድራሉ የሊቁን ዐጽም ሲያነሣ ምን በዓል አዘጋጅቶ ነበር? ለመሆኑ የእኒህን በቤተ ክርስቲያን በምርግትና ያገለገሉ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም በዓለም ዐቀፍ መድረክ ያስጠሩ፣ ቤተ ክርስቲያን እንኳን ልጄ ሆንክ ብላ የምትኮራባቸውን ሊቅ ዐጽም እያነሣ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር? ለመሆኑ የሀገሪቱ የኪነ ጥበብ ሰዎች ሳይቀር መጋበዝ እንደነበረባቸው ካቴድራሉ ያውቃል? አድባር እኮ ነው እየነቀላችሁ ያላችሁት? ታድያ  እናንተ እኒህን የመሰሉ ሊቅ ዐጽም አንሥታችሁ በማይገባ ቦታ ስታስቀምጡ የሀገሩ ሰዎችማ ምን ያድርጓችሁ? ኃላፊነቱን መውሰድ የነበረባቸው ሀገርና ቤተ ክርስቲያን፣ እንደ ልኳንዳ ቤት ሥጋ ቆጥረው ኃላፊነቱን ለልጅ ልጆቹ ሲሰጡ ምን ያድርጓችሁ? ‹ተወላጆቹ› በ19/10/2009 በጻፉላችሁ ደብዳቤ ዐጽሙን ወደ ደብረ ኤልያስ(ጎጃም) የወሰዱት ሌላ አማራጭ በማጣታቸው መሆኑን ገልጠውታል፡፡ ምን ያድርጉ?
የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ጉዳይ የእኛው የራሳችን የካቴድራሉ አባቶች፣ ከዚያም አልፎ የጠቅላላዋ ቤተ ክርስቲያን፣ ተሻግሮም ሀገራችን የኢትዮጵያ ጉዳይ እንጂ የአጥንትና ጉልጥምት ጉዳይ አይደለም ብላችሁ አትመልሱም ነበር? የዮፍታሔ ታሪክ የዚህች ሀገር ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ታሪክ በሚሰጥበት ትምህርት ቤት ሁሉ ይሰጣል፡፡ የነገው ታሪክ ላይ ግን እንዲህ የሚል ትምህርት ጨምራችሁበታል ‹ካቴድራሉ ዐጽሙን አንሥቶ ለክብሩ በማይመጥን ቦታ ስላስቀመጠው፣ በተቀበሩ በ70 ዓመት እንደገና ዐጽሙ ፈልሶ፣ ዓባይን ተሻገረ›፡፡
ለመሆኑ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የማን ናቸው? የቤተሰቦቻቸው ናቸው? ያስተማሩትና የጻፉት ለቤተሰቦቻቸው ነው? የተጋደሉት ለቤተ ክርስቲያን አይደለም? ካቴድራሉ ምን ቢደፍር ነው ለቤተሰቦቻቸው ኃላፊነቱን ሰጥቶ ማስታወቂያ የሚያወጣው? ለመሆኑ በካቴድራሉ ቤተ መጻሕፍት ያሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ መጻሕፍት ይህንን ነው የሚናገሩት?
በገድለ ተክለ ሃይማኖት መጨረሻ ላይ ‹መጽሐፈ ፍልሰቱ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት› የሚል መጽሐፍ አለ፡፡ የተጻፈው በ1418 ዓ.ም. በሰባተኛው የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት በእጨጌ ዮሐንስ ከማ ነው፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ዐጽም ካረፉ ከ57 ዓመት በኋላ ከደብረ አስቦ ወደ ዔላም ሲፈልስ የነበረውን ሥርዓት ይናገራል፡፡ አራተኛው እጨጌ አቡነ ሕዝቅያስ ለፍልሰተ ዐጽሙ ደቀ መዝሙሮቻቸውን ጠሩ እንጂ በጽላልሽ የሚገኙ ዘመዶቻቸውን አልጠሩም፡፡ ካቴድራሉ ግን የእኒህን ሊቅና ጻድቅ ዐጽም ለማንሣት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊት ውጭ ‹ወንድማቸው መጡ፣ ልጃቸው መጣ› በሚል ጠባብ ምልከታ ጉዳዩን ወደ ዘመድ አዝማድ አወረደው?
የሦስተኛው የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት የአቡነ ፊልጶስ ዐጽም ከደቡብ ጎንደር ደብረ ሐቃሊት ገዳም በ1481 ዓም ፈልሷል፡፡ ይህንን ታሪክም በወቅቱ የዓይን ምስክር የነበረውና ‹መጽሐፈ ፍልሰቱ ለአቡነ ፊልጶስ› የተሰኘውን መጽሐፍ በእጨጌ ጴጥሮስ ዘመን(1489-1516) የጻፈው ፍሬ ቅዱስ በሚገባ ይተርከዋል፡፡ ፍሬ ቅዱስ እንደሚነግረን ዐጽሙን ያፈለሱት ደቀ መዝሙሮቻቸውና መላው ክርስቲያኖች እንጂ ዘመዶቻቸው አይደሉም፡፡ የፈለሰውም ወደ ትውልድ ቦታቸው አይደለም፤ ወደ ገዳማቸው እንጂ፡፡ እንዲያውም በሚያስደንቅ ሁኔታ በንጉሥ ሰይፈ አርእድ ተሰደው በሄዱበት ሀገር ያረፉትን የአቡነ ፊልጶስን ዐጽም ለመጀመሪያ ጊዜ በ1411 ዓ.ም. ለማፍለስ የሞከረው በርናባስ የተባለ ከአገው አውራጃዎች በአንዷ ፍርቃ በምትባለው የሚኖር ክርስቲያን ነው፡፡ ‹ቤተሰባቸው› አይደለም፡፡ ለአባ ፊልጶስ የሥጋ ዘመዱ አይደለም፤ የመንፈስ ልጁ እንጂ፡፡ የመልአከ ብርሃን አድማሱ ጉዳይ የእኛ የመንፈስ ልጆቻቸው፣ የቀለም ልጆቻቸው፣ የሃይማኖት ልጆቻቸው ጉዳይ እንጂ የሥጋ ዘመዶቻቸው ጉዳይ አይደለም፡፡ የሚመለከተው ቅዱስ ሲኖዶስንና ካቴድራሉን ነው፡፡
መጋቢት 27 ቀን 1551 ዓ.ም. ከአዳሎች መሪ ከመሐመድ ኑር ጋር ገጥሞ ንጉሥ ገላውዴዎስ ተሸንፎ ተሠዋ፡፡ አብሮት የነበረው የደብረ ሊባኖሱ አበ ምኔት እጨጌ ዮሐንስም ተሠዋ፡፡ አንድ ምእመንም የእርሱንና የአባ መቃርዮስን ሥጋ ወስዶ በትንሽ መቃብር ቀበራቸው፡፡ በኋላም ሀገር ሲረጋጋ የመንፈስ ልጁ አባ ቴዎሎጎስ ወደሚያስተዳድረው ደብር አመጣው፡፡ የአባ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የሚሆን አባ መብዐ ድንግልም ከዚያ አፍልሶ ወደ ደብረ ሊባኖስ በክብር አመጣው፡፡ በዚህ ሥራ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን እንጂ ቤተ ዘመድ የለበትም፡፡ ለሊቃውንትና ለቅዱሳን ቤተዘመዶቻቸው የመንፈስ ልጆቻቸው፣ ቤታቸውም ቤተ ክርስቲያን ናትና፡፡
ሩቅ ሳንሄድ ሁለት የቅርብ ዘመን ታሪክ ልጥቀስ፡፡
የአሁኑ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስና የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የሠሩትን ተጠቃሽ ሥራ መጥቀሱ ይገባል፡፡ በብጹዕነታቸው መሪነትና በአባ ማርቆስ ተፈራ አስተባባሪነት ትልቁ የዝዋይ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሲታነጽ የነፍስ ኄር ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ (ካልዕ) ዐጽም ከትንሿ ቤተ ክርስቲያን ፈልሶ ወደ ትልቁ ደብር ገብቷል፡፡ ያን ጊዜ ግን ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ(የአሁኑ) የነፍስ ኄር አቡነ ጎርጎርዮስን ዘመዶች ከወሎ አልጠሩም፡፡ ጉዳዩ የዘመድ ጉዳይ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን ነውና፡፡ የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ትምህርት፣ መጻሕፍትና አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠ ነውና፡፡ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ልክ እንደ እጨጌ ሕዝቅያስ የጠሩት በመላው ዓለም የሚገኙ የቀለምና የመንፈስ ልጆቻቸውን ነው፡፡ የሰበሰቡት ጳጳሳትንና ካህናትን ነው፡፡ እንደ ካቴድራሉ ‹ዐጽም አንሡልን› ብለው ዐዋጅ አልነገሩም፡፡ በጸሎትና በቅዳሴ፣ በዝማሬና በማዕጠንት፣ እንደ ጥንቱ ሥርዓት በክብር እንዲፈልስና እንዲያርፍ አደረጉ እንጂ፡፡ ጎርጎርዮስ ጎርጎርዮስን እንዳከበሩ፣ አክባሪ ይላክላቸው፡፡
በደርግ ዘመን በሰማዕትነት አልፎ ዐጽማቸው የትም ተጥሎ የነበሩትን የታላቁን አባት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዐጽም ማፍለስ ቤተ ክርስቲያናችን ‹ቤተሰቦቻቸውን› በዐዋጅ አልጠራችም፡፡ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መሪነት ራስ ቅዱስ ሲኖዶሱ በክብር አፍልሶ ወደ ጎፋ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አፈለሰው እንጂ፡፡ ይህ የሆነው ግን አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመድ ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም፡፡
ካቴድራላችን ይህንን ትውፊት እንዴት ዘንግቶት ነው ጉዳዩን አውርዶ የቤተሰብና የተወላጅ ያደረገው? እንዴው ስንቱን ነገር አውርደንና ወርደን እንችለዋለን? ይህንን በዘመድ መሥራት መቼ ነው የምንተወው?  
<ሆኖም በአሁኑ ወቅት፣ የልጃቸው ባለቤት የሆኑ ግለሰብ ቀርበው በማመልከታቸው፣ ካቴድራሉ፥ የመልአከ ብርሃን አድማሱን ዐፅም ሌላ ቦታ ሰጥቶ ለማፍለስና ለማሳረፍ እየተዘጋጀ እንዳለ አስተዳዳሪው አስታውቀዋል፡፡> ይላል ጋዜጣው፡፡ ባያመለክቱስ ኖሮ ምን ልታደርጓቸው ነበር? እንደ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ አንድ ቦታ ከትታችሁ የተናደደ ወገን ሲመጣ ወንዝ ልታሻግሩ? ለመሆኑስ ከልጃቸው ባለቤት ይልቅ ለመልአከ ብርሃን አድማሱ እናንተ አትቀርቧቸውም? ለመሆኑስ ይህን ከማን ነው የተማራችሁት?
አሁንም ሦስት አካላት እንዲያስቡበት አደራ እላለሁ፡፡ ሲኖዶሱ፣ ካቴድራሉና ምእመናኑ፡፡ ሲኖዶሱ ቢያንስ ቢያንስ ነግ በኔ ብሎ ጉዳዩን በቤተ ክርስቲያኒቱ ደረጃ መመልከት አለበት፡፡ ሊቅ አይውጣላችሁ ተብለን ተረግመን ካልሆነ በቀር፡፡ ካቴድራሉም አሁን እንዳደረገውና እንደሚያደርገው ‹የልጅ ሚስት፣ የልጅ ባል› የሚባለውን ጨዋታ ትቶ ጉዳዩን የቤተ ክርስቲያኒቱ ያድርገው፡፡ ያ ካልሆነ ደግሞ እኛ ምእመናን መንግሥትንም ሆነ ቤተ ክርስቲያንን ጠይቀን ለክብራቸው የሚመጥን ሥራ እንሥራ፡፡ ቢያንስ ከታሪክ ተወቃሽነትና ከርግማን እንድናለን፡፡

16 comments:

 1. amen amen amen kalehiwot yasemalen wondemachin betemertek abatachin.

  ReplyDelete
 2. Thank you Dani ! This is absurd.If you have tribe worshiper goverment /Sinodos then all follow that pipe line.For real.

  ReplyDelete
 3. እግዚሃቤር ይጠብቅህ!!

  ReplyDelete
 4. ፀሁፉ አስገራሚ ማስተዋል የታየበት ነውና እጅግ ተደስቻለሁ፡፡ የበዓለወልድ አጥቢያ ምዕመናን ንቁ! ሌሎቻችንም እንንቃ! ዳንኤል ክብረትን እግዚአብሔር ይጠብቅልን!
  በአንድ ወቅት አንድ አባት ሲያስተምሩ የሰማሁት ቁምነገር ትዝ አለኝ፡፡ በአንድ ገዳም አንድ ወጣት መነኩሴ የተማረ፣ ያወቀ የነቃ እና የቀና ሰው ነው ተባለና አበምኔት ተደርጎ ተሾመ፡፡ እውነትም ወጣቱ አበምኔት በገዳሙ ለውጥ እንዲመጣ ብዙ ዕቅድ አዘጋጀ፡፡በተለይ ከተመሰረተ 100 ዓመት የሞላውን ገዳም የምስረታ በዓል ማክበር አንዱ ዋነኛ ዕቅድ ሆነ፡፡ የገዳሙ ምሥረታ በዓል ሲከበር ደግሞ ከሚሰሩ ሥራዎች አንዱ የምግብና መጠጥ ዝግጅት አንዱ ነው፡፡ ተደገሰ፡፡ የአልኮል መጠጥ ታይቶ በማይታወቅበት ገዳም ጠላ እና ጠጅ ተዘጋጀ፡፡ ሰው በላ ጠጣ፡፡ ከልክ ያለፉ ሁኔታዎች ተፈጥረዋልና በበላና ጠጣ ያልበቁ ጉዳዮች ወደ ስካር እና አእምሮ ወደ መሳት ተገባ፡፡ የ100 ዓመት ግሩም ታሪክ የነበረው ገዳም በቀናት ተግባር ብቻ ስሙ ተቀየረ፡፡ ደግ በሚመስል ወይም በልማት ሰበብ የገዳሙ ሥርዓት ተናደ፡፡ በማያስተውሉ መሪዎች ፈተና እንደሚመጣ የታወቀ ነው፡፡ በሥራ ዕቅዳቸው የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ የማይጠየቅ ከሆነ እና በፀሎትና በምልጃ የማይተጉ ከሆነ የሚታያቸው በልማቱ የሚገኘው ገንዘብ ብቻ ነው፡፡ ማስተዋላቸውን የተነጠቁ መሪዎች ጥፋትን ከማረም ይልቅ በየዕለቱ መረማመድ የቀን ተቀን ግብራቸው ነው፡፡ እባካችሁ መሪዎቻችን ማስተዋላቸው እንዲመለስላቸው ፈጣሪያችንን እንማፀን!!!

  ReplyDelete
 5. ዳኒ እግሂአብሄር ይስጥህ፡፡ ምነው ለእነርሱም እንዳንተ ማስተዋሉን ቢያድላቸው! እኛ ልጆች ማንን እንይ አባቶቻችን አያቶቻችንን አረከሱ ታሪካቸውን ጥላሸት ቀቡ......ምን ይሻላል !!!!!!!! እግዜሩም ዝም አለ .........አባቶቻችንን ጠላናቸው ለምን .....ማንን አየንና .......... ምን እናርግ ታሪኪ ሲያጠፉ እንጂ ሲሰሩ አላየንም፡፡ዳኒ እግሂአብሄር ይስጥህ፡፡ ምነው ለእነርሱም እንዳንተ ማስተዋሉን ቢያድላቸው! እኛ ልጆች ማንን እንይ አባቶቻችን አያቶቻችንን አረከሱ ታሪካቸውን ጥላሸት ቀቡ......ምን ይሻላል !!!!!!!! እግዜሩም ዝም አለ .........አባቶቻችንን ጠላናቸው ለምን .....ማንን አየንና .......... ምን እናርግ ታሪኪ ሲያጠፉ እንጂ ሲሰሩ አላየንም፡፡

  ReplyDelete
 6. ዳኒ እግሂአብሄር ይስጥህ፡፡ ምነው ለእነርሱም እንዳንተ ማስተዋሉን ቢያድላቸው! እኛ ልጆች ማንን እንይ አባቶቻችን አያቶቻችንን አረከሱ ታሪካቸውን ጥላሸት ቀቡ......ምን ይሻላል !!!!!!!! እግዜሩም ዝም አለ .........አባቶቻችንን ጠላናቸው ለምን .....ማንን አየንና .......... ምን እናርግ ታሪኪ ሲያጠፉ እንጂ ሲሰሩ አላየንም፡፡

  ReplyDelete
 7. ዳኒ እግሂአብሄር ይስጥህ፡፡ ምነው ለእነርሱም እንዳንተ ማስተዋሉን ቢያድላቸው! እኛ ልጆች ማንን እንይ አባቶቻችን አያቶቻችንን አረከሱ ታሪካቸውን ጥላሸት ቀቡ......ምን ይሻላል !!!!!!!! እግዜሩም ዝም አለ .........አባቶቻችንን ጠላናቸው ለምን .....ማንን አየንና .......... ምን እናርግ ታሪክ ሲያጠፉ እንጂ ሲሰሩ አላየንም፡፡

  ReplyDelete
 8. ዲያቆን ዳንኤል እጅግ አድናቆትን ያተረፍክ ትልቅ ሰው ፡እወቅ ያለው በ40 ቀኑ ያውቃል ያለታደል ደግሞ እድሜልኩን …… ነው ይባላል ፡፡ ለሁሉም ሰሚ እዝነ ልቦና ያድልን እላለሁ ፡፡ እግዚአብሔር በመልካም ስራ እና ሃሳብ አባቶችንና መሪዎቻችንን እንዲያጎናጽፍልን እመኛለሁ ፡፡

  ReplyDelete
 9. .. ሊቅ አይውጣላችሁ ተብለን ተረግመን ካልሆነ በቀር፡፡ ........ እኛ ምእመናን ........ለክብራቸው የሚመጥን ሥራ እንሥራ...

  ReplyDelete
 10. ይህን ስለጮህክ አንተ ተባረክ ሌሎቹ ግን አንበሳ ሲያረጅ የዝንብ መጫወቻ ይሆናል ነው ነገሩ ልቦና ይስጠን

  ReplyDelete
 11. ቃለህይወት ያሰማልን!!!

  ReplyDelete
 12. በዘመድ መሥራት መቼ ነው የምንተወው?ለመሆኑስ ይህን ከማን ነው የተማራችሁት?...ሲኖዶሱ ቢያንስ ቢያንስ ነግ በኔ ብሎ ጉዳዩን በቤተ ክርስቲያኒቱ ደረጃ መመልከት አለበት፡፡

  ReplyDelete
 13. እኛ ክርሰቲያኖች እንጂ ወሎዬ፣ጎጃሜ ወይም ትግሬ ... አለመሆናችንን እንዴት መረዳ አቃታቸው ሰሲኖዶሱና ካቴድራሉስ የማን ነው የኢትዮጲያ ወይስ ... እንደው በፈጣሪ ወዴት እያመራነ ነው

  ReplyDelete
 14. Dn. Daniel Medihn Alem benefs besiga yitebikilin!

  ReplyDelete
 15. ሲጀመር አለቃ አያሌው ሲያስተምሩ እንደሰማሁት ካቴድራል የሚባል ነገር በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ውስጥ የሌለ እና የካቶሊክ ስርዓት መሆኑን ሲናገሩ ሰምቼ አዘንኩ ስህተቱ የሚጀምረው ከዚህ ነው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አንተም ይህንን እንደምታውቅ እርግጠኛ ነኝ ስለዚህ መጀመሪያ ቤተክርስቲያናችንን ከመጤ ልምዶች እና ከሚሸረሽሩ ክፉ ስራዎች መታደግ አለብን፡፡ ሌላው ይህ ዘረኝነት፣ጎጠኝነት እና ፍቅረ ንዋይ መቼ ይሆን የሚቆመው????

  ReplyDelete