‹በአባታችን በዮሐንስ ከማ ዘመን ሃይማኖቱ የቀና ንጉሥ ይስሐቅ(1406-1421) ታላቅ ቤተ ክርስቲያን
በእንጨትና በድንጋይ ያንጹ ዘንድ አዘዘ፡፡ ያቺም ቤተ ክርስቲያን ተሠርታ ስትፈጸም ፈረሰች፡፡ ንጉሡም ይህንን ሰምቶ እጅግ አዘነ፡፡
እንዲህ ሲልም ወደ አባ ዮሐንስ ከማ መልእክት ላከ፤‹‹የዚህን ነገር ምክንያት ታውቅ ዘንድ ጸሎት አድርግ፤ስታውቀውም ወደ እኔ ላክብኝ፡፡››
ያን ጊዜም አባ ዮሐንስ ከማ ቅዱሳን ልጆቹን ሰበሰበ፡፡ ንጉሡ እንዳለው ጸሎትን አጽንተው እንደዲያደርጉ አዘዛቸው፡፡ እነዚህ ንጹሐን
በጸሎት ተግተው በጸኑ ጊዜ የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእነዚያ ቅዱሳን ለአንዱ ተገለጠችለት፡፡ እንዲህ
ስትልም ተናገረቺው፤ ‹‹ይህንን መሥፈሪያ እንካ፤ ቤተ መቅደሴንም በዚህ መለኪያ ለክተህ ሥራ ብለህ ለአባትህ ለዮሐንስ ከማ ንገረው፡፡
ስትሠሩም ከልጆችህ በቀር ሌሎች አይሥሯት፤ ባስልኤልና ኤልያብ ጥበብን እንደተመሉ(ዘጸ. 31፣1-11) ሁሉ እኔም እነርሱን በጥበብ እመላቸዋለሁ፡፡››
አባታችንም የአምላክ እናት የእመቤታችን የማርያምን የቃል መልእክት በሰማ ጊዜ የሆነውን ሁሉ ለንጉሡ
ላከበት፡፡ ንጉሡም የታመነውን የምሥራች ቃል ባገኘ ጊዜ ወደ ደብረ ሊባኖስ መጥቶ[1]
መነኮሳቱን፤ ‹‹የአባታችሁ መቃብር ናትና እናንተ ሥሯት፤ ሌሎች ከሠሯት ግን መልካም አይሆንም ብለው ሐሰት የማይገኝባቸው ሰዎች
ነገሩኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱ ግን ሊሠሩ አልወደዱም ነበር፡፡ ነገር ግን የንጉሡን ቃል እንዳያስተሐቅሩ ሲሉ ጀመሩ፡፡ እርሱ አስቀድሞ
‹‹በንጉሥ ዜና መዋዕል፣ ንጉሥ ሲለምን፤ ለምኖም እምቢ ሲሉት አልሰማሁም›› አላቸው፡፡ በዚህም የተነሣ ሊሠሩ ጀመሩ፡፡ ሕንጻውም
በሰባት ዓመት ተፈጸመ፡፡ እዚህ ላይ ከታሪኩ ጋር የሚሄድ መልካምን ዜና እንንገራችሁ፡፡ በገድል የተጠመደ አንድ መነኮስ ነበረ፡፡
ኅሊና መንፈሳዊ በመጣበትም ጊዜ ቁመትን ከጸሎት ጋር አስተባብሮ ያለ ድካም ዘወትር ይተጋ ዘንድ ገድልን ጀመረ፡፡ እግዚአብሔር የቤተ
ክርስቲያንዋን ሕንጻ ፍጻሜ ያሳየው ዘንድ፡፡ በዚህ ሁኔታም ለሰባት ዓመታት ኖረ፡፡ ከዚህም በኋላ የሥራውን ፍጻሜ ሲመለከት የሥጋን
ድካም ድል ያደርግ ዘንድ ኃይልን ሰጥቶታልና እግዚአብሔርን አመሰገነው፡፡ የዚህ ጻድቅ ረድኤት ከእኛ ጋር ይሁን፡፡
ይለናል በ1587 ዓም የተጻፈው ‹ዜና ደብረ ሊባኖስ› የተሰኘው መጽሐፍ፡፡