Tuesday, June 20, 2017

ጥበበኛው ግንበኛ

ግንበኛው ድንጋዩን ይጠርብና በድርድሩ ላይ ሰክቶ አንዴ ፈገግ፣ አንዴ ተከዝ፣ አንዴ ቆም አንዴም ጎንበስ ይላል፡፡ ላት አይቶ በግ እንደሚገዛ ሰው በግራ በቀኝ ያገላብጠዋል፡፡ እንደ ገዳም ጸሎት ሲመሰጥ፣ እንደ ጉብታ ዛፍ ሲናወጥ ይታያል፡፡ እንደ ኮከብ ቆጣሪ ሲያፈጥ፣ እንደ ጥሩ ወጥ ቀማሽ ምራቁን ሲወጥ ይታያል፡፡ ድንጋዩን በግራ ቀኝ ሲፈልጠው ልጇን እንደምታጥብ እናት ሲሳሳ፣ ቅባት እንደምትቀባ ፀጉር ሠሪ ሲዳስስ ይታያል፡፡
ይህንን ሁሉ ያየ መንገደኛ ‹ጌታው፣ ሲያዩህ እንደ ግንበኛ ድንጋይ ትጠርባለህ፣ ግንብ ትሰድራለህ፤ ሁኔታህን ላስተዋለው ግን እንደ ሙዚቀኛም፣ እንደ ቲያትረኛም፣ እንደ ቀማሚም እንደ ዘማሚም ትመስላለህ፡፡ ለመሆኑ ምን እያደረግኩ ነው ትላለህ?› ሲል ጠየቀው፡፡ ግንበኛው መዶሻውን ድንጋዩ ላይ አንተራሰና
እኔ! እኔማ እየፈለጥኩም ግንብ እየሠራሁም አይደለም፡፡
እኔ! እኔማ እንደ ያሬድ አዜማለሁ
እንደ ተዋነይ እቀኛለሁ
እንደ ላሊበላ ድንጋዩን አናግረዋለሁ
እንደ ጊዮርጊስ አመሠጥራለሁ
እንደ አፈወርቅ እስላለሁ
እንደ ሐዲስ እደርሳለሁ
እንደ ጸጋዬ እገጥማለሁ
እንደ ወጋየሁ እተርካለሁ
እንደ ሺመልስ እተውናለሁ
እንደ ኤልያስ አቀናብራለሁ
እስኪ ተመልከታቸውማ፤ የበቃ ባለቅኔ የሰባ ቃል እንዲሻ፣ እነዚህ ጥርብ ድንጋዮች ለእኔ ቃላት ናቸው፡፡ እመርጣለሁ፣ እቀርጻለሁ፡፡ የሰላ ባለ ቅኔ ያማረ ቃል እንዲሻ፣ እኔም እኒህን የድንጋይ ቃላት አሣምራቸዋለሁ፡፡ እኔ ድንጋይ አልፈልጥም፡፡ ሕይወትም በድንጋይ አትኖርም፤ ሕይወትም በድንጋይ አትረካም፡፡ ድንጋይማ የጉልበት ሥራ ነው፡፡ እኔ ቃላትን በፈለገው ቅርጽ ከመዝገቡ እንደሚያወጣ እንደ ርቱዕ ደራሲ ነኝ፡፡ አንዳንዱ ድንጋይ ፈሊጥ ነው፤ አንዳንዱ ድንጋይ ምሳሌ፤ አንዳንዱ ድንጋይ ተረት ነው አንዳንዱ ድንጋይ ዘይቤ፡፡ 

እነዚህን የድንጋይ ቃላት በግንቡ ላይ ስደረድር ዜማ ነው የማቀናብር፡፡ እስኪ ተመልከታቸው፣ ድንጋዮቹኮ ምት አላቸው፡፡ አንዱ ከሌላው ጋር ተስማምቶና ተዋሕዶ፣ ላይኛው ከታችኛው ጋር ተናቦና ተገናዝቦ፤ ሥሉጥ አቀናባሪ እንዳገኘው ውብ ዜማ፣ ረቂቅ ነው ሙዚቃው ከግንቡ ላይ የሚሰማ፡፡ እስኪ ቀና በልና ድርደራቸውን እያቸው፤ ድንጋዮችኮ ቃላት ናቸው፡፡ ውብ ባለ ቅኔ ካገኛቸው፣ ምሥጢር ዐዋቂ ካሰናኛቸው፡፡ ይኼ ከላይ የማታየው ከግንቡ ጫፍ እስከ ጫፍ ሠልቶ የተደረደረው፡፡ እርሱ የወል ቤት ግጥም ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በወዲህ ዳር፣ ከግንቡ ጫፍ እስከ መስኮቱ አጥሮ የተገጠገጠው፤ እርሱ ቡሄ በሉ ቤት ነው፡፡
ቡሄ በሉ
ልጆች ሁሉ
ቡሄ መጣ
ያ መላጣ፡፡ እያለ ወደታች ይወርዳል፡፡ እንዲህ አጭር ቤት የሚመታ የቡሄ ቤት ባለ ቅኔ፣ ቃላቱን ሲሰይፍና ሲፎንን እንደሚውለው፡፡ እኔም ድንጋዮቹን ስቀርጽና ስቆራርጥ እውላለሁ፡፡ እይውልህ ወዳጄ፡፡ ቅኔ በቁጥር ይመጠናል፣ ዜማው በቁጥር ይለካል፣ መድፊያው ደግሞ ቤት ይመታል፡፡ እኔም ድንጋይ እቆጥራለሁ፡፡ ባለቅኔው ከላይ ወደ ታች፣ እኔ ግን ከታች ወደ ላይ እገጥማለሁ፡፡ የላይኛው ቤት ሲሠራ ከታችኛው ካልገጠመ፣አንድም ሕንጻው ይፈርሳል፣ አንድም ውበቱ ይጠፋል፡፡ ቆጥሮ ያልተቀኘ ባለ ቅኔ ዜማውን ሲሰብር እንዲገኝ፣ ቆጥሮ ያልሠራ ግንበኛም የግንቡን ዜማ ይሠብራል፣ ያኛው ጆሮን ሲያሳቅቅ ይህኛው ዓይን ያሳቅቃል፡፡
እስኪ ተመልከተው ወዳጄ! አንዳች ሥዕል ይታይሃል? ድንጋዮችኮ ቀለም ናቸው፡፡ መርጠህ የምታፈሳቸው፡፡ ይታዩሃል እነዚያ በድንጋዮቹ መካከል የተሰነቀሩት ቁራጮቹ? እነርሱ ምን ይመስሉሃል? በሥዕሉ መካከል የገቡ ሰረዞች ናቸው፡፡ የቀለም ድርደራህ መልክና ልክ እንዲኖረው፣ በእነርሱ ነው የምትለየው፡፡ የድንጋዮቹ መጠን፣ የአቀማመጣቸው ሁኔታ፣ ቅርጻቸውና መልካቸው ሁሉም አመክንዮ አላቸው፡፡
ደግሞም እፈላሰፋለሁ፡፡ ከላይ ያለው በታቹ ላይ ሲቀመጥበት እያየሁ፡፡ ታቹ ሕዝብ ነው እላለሁ፡፡ ስንቱን ችሎ እንደተሸከመ አሻቅቤ አየዋለሁ፡፡ ደግሞም የዓለምን ነገር አይቼ እገረማለሁ፡፡ ሁሉም ከአንድ ቦታ መጥቶ፣ በአንድ ግንበኛ ተሠርቶ፣ ግን ዕጣ ፈንታው ሆነና አንዱ በሌላው ላይ ተቀመጠ፣ አንዱ ከሌላው በለጠ፡፡  አንዱ መጸዳጃ ሆነ፣ አንደኛው ለሳሎን ተጌጠ፤ አንዱ እልፍኝ ውስጥ ገብቶ የሰው ምሥጢር ላይ አፈጠጠ፣ አንዱ ማዕድ ቤት ተሽጦ ከጢስ ከእሳት ጋር ተጋፈጠ፡፡ አንደኛው ወደ ውጭ ወጥቶ ለዝናብ ለፀሐይ ተጋለጠ፤ አንዱ ወደ ውስጥ ሰምጦ የጥላን ዕንቅልፍ ለጠለጠ፡፡
ታችኞቹ እጅግ ያሳዝኑኛል፡፡ በአንድ በኩል ሌላውን ሁሉ ተሸክመዋል፡፡ይህ አልበቃቸው ብሎ መከራው በእነርሱ ይብሳል፡፡   ቆሻሻ የሚሸከሙት እነርሱ ናቸው፡፡ ዝናብ የሚያገኛቸው እነርሱ ናቸው፤ ሥዕልና ፎቶ እሰቅላለሁ ያለ ሁሉ በሚስማር የሚመታቸው እነርሱ ናቸው፡፡ ወንበር የሚገጫቸው፣ የጠረጲዛ ጠርዝ የሚሠረስራቸው እነርሱ ናቸው፡፡
እይውልህ፤ እኔ እንዲህ ሳደርግ ነው የምውለው፡፡ አንተስ ምንድን ነው የምትሠራው?
‹እኔ የቢሮ ሠራተኛ ነኝ› አለ መንገደኛው፡፡
የቢሮ ሠራተኛ ነኝ ብለህ ካሰብክ ሥራህንም ሕይወትክንም ትጠላዋለህ፡፡ አንድ ዓይነት ይሆንብሃል፤ እየቆየ ይሰለችሃል፤ ሲሰለችህ ጠባይህ ይቀየራል፣ ጠባይህ ሲቀየር አነዋወርህ ይበላሻል፡፡ ይልቅ አዚም፣ ተቀኝ፣ ግጠም፣ ድረስ፣ ሳል፣ አመሥጥር፣ ተፈላሰፍ፣ ተመሰጥ፡፡ በደብዳቤው ተቀኝበት፣ በፋይሉ ተሰላሰፍ፣ ወንበርህን ቡርሽ አድርገው ጠረጲዛህን ሰሌዳ፣ ስክርቢቶህ ብዕር ይሁን፣ ደብዳቤህ ደግሞ ብራና፡፡ ባለ ጉዳይ ስታነጋግር ንግግርህ ዜማ ይሁን፣ የሰውን ችግር ስትሰማ ከባድ ቅኔ ዝረፍ እንደተባለ ደቀ መዝሙር ራስህን ቁጠር፣ ሥራህን በዕለት ካልጨረስክ ቤት የማይመታ ግጥም እንደገጠምክ ቁጠረው፣ ሥራህን ስታበላሸው ዜማ እንደሰበርክ ተረዳው፡፡ ደግሞም ተፈላሰፍበት የኑሮን መንገድ መርምረው፡፡ ዛሬ አንተ ጋር የመጣው ደንበኛ ነገ እርሱ በተራው ሹም ነው፡፡ አንተም ሌሎችን እንዳስተናገድክ፣ ሌላ ቦታ አንተም ተስተናጋጅ ነህ፡፡ ሕይወት ይኼውልህ እንዲህ ናት፡፡ አንተ እዚህ ፋይል ስትከምር ያንተም ፋይል ሌላ ቦታ ይከመራል፤ አንተ እዚህ ነገር ስትቋጭ ያንተም ነገር ሌላ ቦታ ይቋጫል፡፡ ሕይወት ዜማ ከሌላት፣ ሕይወት ምቷን ካልጠበቀች፣ ሕይወት ቅኔ ካልቆጠረች፣ ሰምና ወርቁን ካልሠራች፣ ሕይወት ሥዕል ካልሳለች በቀለማት ካልተዋበች፤ኧረ ትሰለቻለች!
ደስታ ወደ ውስጥ አይገባም፤ ደስታ ከውስጥ ይወጣል እንጂ፡፡ ለዚህች ለአጭር ዘመን እድሜ በድንገት ለምትቀጨው፤ ይህ ሁሉ ጭንቀት ለምን ነው? ባለ ጉዳዮችህን እንደ ችግር አትያቸው፤ እንደ ቅኔ ቁጠራቸው፤ ነገራቸው ሲረዝምብህ መወድስ ቅኔ አድርጋቸው፣ ነገራቸው ሲያጥርልህ ጉባኤ ቃና በላቸው፡፡ እነርሱን ዜማህ አድርጋቸው፡፡ ሮሯቸውን ሲያወሩህ እንጉርጉሮ ነው በላቸው፤ ደስታቸውንም ሲነግሩህ ጉሮ ወሸባዬ ነው በላቸው፡፡ ስብሰባህን ማኅሌት፣ ኮሚቴህን ወረብ አድርገው፡፡ ለምሬት ቦታን አትስጠው፡፡ ሥራህን ሥራ አታድርገው፣ ሥራህን ጥበብ አድርገው፡፡ 

22 comments:

 1. ሕይወት ዜማ ከሌላት፣ ሕይወት ምቷን ካልጠበቀች፣ ሕይወት ቅኔ ካልቆጠረች፣ ሰምና ወርቁን ካልሠራች፣ ሕይወት ሥዕል ካልሳለች በቀለማት ካልተዋበች፤..................ኧረ ትሰለቻለች!

  ReplyDelete
 2. እሽ ምክርህን ተቀብያለሁ፡፡

  ReplyDelete
 3. ደስታ ወደ ውስጥ አይገባም፤ ደስታ ከውስጥ ይወጣል እንጂ፡፡ ለዚህች ለአጭር ዘመን እድሜ በድንገት ለምትቀጨው፤ ይህ ሁሉ ጭንቀት ለምን ነው?

  ReplyDelete
 4. daniye temrebetalehu ameseginalehu!!!

  ReplyDelete
 5. No comment because even if I say wonderful, that will be very small for this article. Thank You Danny

  ReplyDelete
 6. Egziabhir erejm edme ketena gar yadleh.
  Etsub denk mistir new

  ReplyDelete
 7. ......ሥራህን ሥራ አታድርገው፣ ሥራህን ጥበብ አድርገው፡፡

  ReplyDelete
 8. የሁል ግዜ ትልቅ ሰው ነህ...ኣንድ ቀን የትልቅ ትልቅ ሁነህ ስትሸለም ይታየኛል ...ወስብሃት ለእግዚአብሔር

  ReplyDelete
 9. Thank you Dani. A good point, at a time I was needing it.

  ReplyDelete
 10. በጣም ትልቅ ነገር ተምሬአለሁ:: ይገርማል! ለካ ጥበብ ከሌላ ወይም ከየትም አይደለም :: ጥበብ በእጅ ያለ ቅርብ ነው:: እግዚአብሔር ይስጥልን! ወንድሜ ዲያቆን ዳንኤል

  ReplyDelete
 11. Rekik new ytechalegnin lemerdat mekirialem betibeb mastemar yilila yihen !

  ReplyDelete
 12. ሥራህን ሥራ አታድርገው፣ ሥራህን ጥበብ አድርገው፡፡

  ReplyDelete
 13. Great advice. Thank you so much.

  ReplyDelete
 14. Great advice. Thank you so much.

  ReplyDelete
 15. ሥራህን ጥበብ አድርገው፡፡ 

  ReplyDelete
 16. እንደው ምን ቃል ይገልጸዋል ላድናቆት
  እንደው ዝም
  እኔም ላልሰሙ ለማሰማት ማንበብ።

  ReplyDelete
 17. ደስታ ወደ ውስጥ አይገባም፤ ደስታ ከውስጥ ይወጣል እንጂ፡ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡

  ReplyDelete
 18. ጥልቅ ተሐድሶ ተብሎ ይሔ ሁሉ ወጪ ያለ ለውጥ ከሚደረግ ይህን ገጽ ፐሪንት አድርጎ ለህዝብ አገልጋዮች ቢሰጥ መልካም ነበር፡፡ የህዝብ አገልጋይ ነን የምትሉ አንባቢዎች እንደ ልድያ ይህ መልዕክት በልባችሁ ይስረጽ፡፡ መልካሙን ስራ መስራት ለራስ ነው፡፡ ከመንግስት ወይም ከበላይ አካል የተላለፈ መልዕክት ወይም አቅጣጫ ቢኖርም ፈጻሚዎች ተቀኙበት አመስጥሩት ሰዋዊ አድርጉት ጉዳዩን አይሆንም፣ ስብሰባ ላይ ነን፣ መመሪያው አይፈቅድም፣ ቢፈቅድም ደክሞኛል፣… እባካችሁ ከዚህ በላይ ህይወት እንዲከብደን አታድርጉ፡፡ ሌላ ሀገር ሌላ ወገን የለን፡፡
  "ኩሎ አመክሩ ወዘሰናየ አጽንዑ"
  ዲ. ዳንኤል ማስተዋሉን ያብዛልህ

  ReplyDelete
 19. u so exceptional really any thing it comes out from u mind it will not fall down any where but in my mind and heart , I wish those on top get a lesson once in a week at there white house they may improved in there leadership

  ReplyDelete